የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 4/1 ገጽ 16-19
  • የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተግባራዊ ጥቅም ያለው መሣሪያ
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ሊያገለግል ይችላል
  • “አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ ምሥራቹን ማቅረብ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1998
  • ውይይት የሚያስቆሙ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ እንዴት መልስ መስጠት ይቻላል?
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • ትምህርቱ ከምሥራቃውያን ሃይማኖቶች ጋር ተቀላቀለ
    ስንሞት ምን እንሆናለን?
  • ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ አምላክ ይመራሉ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 4/1 ገጽ 16-19

የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ

እኛ የይሖዋ ምስክሮች “ንፁሕ ልሳን” የተሰጠን ለምንድን ነው? ለራሳችን ብቻ እንድንይዘው እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። ከሕዝበ ክርስትና ለስላሳ፣ አቋምን አለሳልሶ የመኖር ጎዳና ጋር በሚመሳሰል የአኗኗር ዘይቤ ለመኖር እንድንችልም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘ሁሉም አንድ ሆነው ይሖዋን ያገለግሉ ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ’ ሲባል ነው። (ሶፎንያስ 3:9) አዎን፣ ንፁሑ ልሳን ከሁሉም ዘሮች፣ ብሔራትና ቋንቋዎች ከተውጣጡትና መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት በታማኝነት ምሥራቹን ከሚሰብኩት በሚልዮን ከሚቆጠሩ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ጎን ለጎን ቆመን በሥራ መሳተፍን ይጨምራል።​—ማርቆስ 13:10፤ ሮሜ 13:11፤ ራእይ 14:6, 7

ዛሬ የምናደርገው ስብከት አንዳንድ ጊዜ ልንወጣቸው የሚገቡ ያልተለመዱ ፈተናዎችን ከፊታችን ያስቀምጥልናል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ውስጥ በጦርነት፣ በጭቆና፣ በኤኮኖሚ ተጽዕኖና በሌሎች ምክንያቶች ሕዝብ በብዛት ፈልሶአል። ከዚህም የተነሳ ብዙ ቋንቋዎችን የሚናገሩና ብዙ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ሰዎች ከራሳቸው የተለየ ባሕላዊ የአኗኗር ዘይቤ ወዳለባቸው ስፍራዎች ሄደዋል። በዚህም ምክንያት ብዙ የሂንዱ፣ የቡድሃና የእስላም ማኅበረሰቦች ወደ ምዕራቡ ዓለም ሄደዋል። ንፁሑን ልሳን ይዘን ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ ከእነዚህ ሰዎች ጋር እንገናኛለን። አንዳንድ ጊዜም ስለ ሃይማኖታቸውና ስላለፈ ታሪካቸው ምንም ስለማናውቅ ግራ እንጋባለን። ስለዚህ ጉዳይ ምን ልናደርግ እንችላለን?​—ከሥራ 2:5-11 ጋር አወዳድር

እውነትን ለአንድ እስላም ወይም አይሁዳዊ እንዴት ለማካፈል እንችላለን? አንዱ ከአንዱ የሚለየውስ እንዴት ነው? አንድ የሂንዱ እምነት ተከታይ ምን ምን ብሎ ያምናል? ሲኮች ሻሽ የሚጠመጥሙት ለምንድን ነው? ቅዱስ መጽሐፋቸውስ ምንድን ነው? አንድ ቡድሂስት ከሂንዱ የሚለየው እንዴት ነው? የጃፓን ሺንቶዎች የሚያምኑት ምንድን ነው? የቻይና ዳውኢስቶች ወይም ኮንፊሺያኒስቶች በአምላክ ያምናሉን?a የጥንቱን የአይሁድ እምነት እከተላለሁ ባይው ከዘመናዊው ወይም ከወግ አጥባቂ የአይሁድ እምነት ተከታይ የሚለየው እንዴት ነው? በከፍተኛ ሁኔታ የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ለማግባባት በመጀመሪያ አመለካከታቸውን መረዳት ከዚያም ደግነትና ዘዴ በተሞላበት መንገድ ወደ እውነተኛው አምላክ ወደ ይሖዋ እንዴት እንደምንመራቸው ማወቅ ይኖርብናል።​—ሥራ 17:22, 23፤ 1 ቆሮንቶስ 9:19-23፤ ቆላስይስ 4:6

ስለ ሌሎች ሃይማኖቶች፣ ስለ ትምህርታቸውና ስለ ታሪካዊ አመጣጣቸው ግልጽ ግንዛቤ እንድናገኝ እኛን ለመርዳት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በ1990 በመላው ዓለም በተደረጉት “ንፁሕ ልሳን“ የወረዳ ስብሰባዎች ላይ የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የተባለ አዲስ መጽሐፍ አውጥቷል። ይህን መሣሪያ በመታጠቅ ክርስቲያን ባልሆነው ዓለም ውስጥም ሆነ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ላሉት ሰዎች ለመስበክ የተሻለ ዝግጅት ይኖረናል።

ተግባራዊ ጥቅም ያለው መሣሪያ

ይህ 384 ገጽ ያለው መጽሐፍ ባለፉት ስድስት ሺህ ዓመታት ሰው አምላክን ለማግኘት ያደረገውን ፍለጋ ታሪክ የሚገልጹ 16 ምዕራፎችን ይዟል። መጽሐፉ ስለ ዓለም ሃይማኖቶች ለሚነሱ በብዙ መቶ ለሚቆጠሩ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል፦ ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው የአንዱ ሃይማኖት ተከታይ ለመሆን የሚያበቁት ነገሮች ምንድን ናቸው? ሌሎች እምነቶችን መመርመሩ ስሕተት የማይሆነው ለምንድን ነው? በሮማ ካቶሊክ እምነትና በቡድሂዝም መካከል ምን ምን ተመሳሳይነት አለ? በብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ አፈታሪኮች ምን ሚና ይጫወታሉ? ብዙ ሰዎች በአስማት፣ በመናፍስትነት ድርጊትና በኮከብ ቆጠራ የሚያምኑት ለምንድን ነው? ሂንዱዎች ብዙ የወንድና የሴት አማልክት ያሏቸው ለምንድን ነው? ሲኮች ከሂንዱዎች የሚለዩት እንዴት ነው? ቡድሃ ማን ነበር? ምንስ አስተምሯል? ሺንቶ በተለይ የጃፓናውያን ብቻ ሃይማኖት የሆነው ለምንድን ነው? አይሁዶች በቃል የተላለፈና የተጻፈ ሕግ የኖራቸው ለምንድን ነው? ክርስቶስ የአፈ ታሪክ ሰው እንዳልነበረ እንዴት እናውቃለን? ቁርዓን ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚለየው እንዴት ነው? ካቶሊኮች ጴጥሮስ የመጀመሪያው ጳጳስ ነበር ብለው የሚናገሩት ለምንድን ነው? የካቶሊክ ቄስ የነበረው ሉተር ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተገነጠለው ለምንድን ነው?

ጥያቄዎቹ ከመብዛታቸው የተነሣ የሚያልቁ አይመስሉም፤ ይህ ጽሑፍ የተለያየ ሃይማኖትና ታሪክ ላላቸው ሰዎች ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመስበክ እንድንችል ለጥያቄዎቹ መልሶችን ይዞልናል። መጽሐፉ ብዙ ሰዎች የራሳቸው ሃይማኖት ያላቸው መሆኑንና ሃይማኖት የግል ጉዳይ እንደሆነ ያምናል። ሆኖም በገጽ 8 ላይ እንዲህ ይላል፦ “በመሠረቱ ወላጆቻችንና ዘመዶቻችን ከተወለድንበት ጊዜ ጀምሮ የሃይማኖት ወይም የግብረ ገብ አሳቦችን በአእምሮአችን ቀርጸዋል። በዚህም ምክንያት በአብዛኛው የወላጆቻችንንና የአያቶቻችንን ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች እንከተላለን።” ይህም “በብዙ መንገዶች ሃይማኖታችንን የመረጡልን ሌሎች ናቸው። በአጭሩ የተወለድንበት ቦታና የተወለድንበት ጊዜ የሚወስነው ጉዳይ ነው” ማለት ነው።​—ከፊልጵስዩስ 3:4-6 ጋር አወዳድር

መጽሐፉ ቀጥሎ ምክንያታዊ የሆነ ጥያቄ ያነሣል። “አንድ ሰው ሲወለድ የተላለፈለትን ሃይማኖት የግድ እውነት ነው ብሎ ማመኑ ምክንያታዊ ነውን?” በዚህ ምክንያት እያንዳንዱ ሰው አእምሮውን ለአዲስ ሐሳብ ክፍት በማድረግ ሌሎች ሃይማኖቶችን እንዲመረምር ተበረታቷል። በገጽ 10 ላይ እንደተገለጸው፦ “አንዱ የሌላውን አመለካከት መረዳቱ የተለያየ እምነት ባላቸው ሰዎች መካከል ይበልጥ ትርጉም ወዳለው ግንኙነትና ውይይት ሊመራ ይችላል።” ቀጥሎም እንዲህ አለ፦ “እውነት ነው፣ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ሃይማኖታዊ እምነት ጋር ፈጽሞ ላይስማሙ ይችሉ ይሆናል፤ ሆኖም አንድ ሰው የተለየ አመለካከት ስላለው ወይም ስላላት የሚጠሉበት ምንም መሠረት የለም።”​—ማቴዎስ 5:43, 44

በመጽሐፉ ውስጥ በየቦታው የተነሣ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ሰው ሲሞት በሕይወት የምትቆይና ወደ ሌላ ሕይወት የምትሄድ የማትሞት ነፍስ አለችውን? የሚል ነው። በአንዱ መልኩም ይሁን በሌላው አብዛኛው ሃይማኖት ይህንን ጽንሰ ሐሳብ ያስተምራል። የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የተባለው መጽሐፍ (በገጽ 52) እንደገለጸው “ሰው አምላክን ለማግኘት ባደረገው ፍለጋ በአለመሞት የሐሰት አስተሳሰብ ተሞኝቶ የሚሆነውንም የማይሆነውንም ለመጨበጥ ሞክሯል። . . . በነፍስ አለመሞት ወይም በሌላ መልክ የቀረቡ ተመሳሳይ እምነቶች ባለፉት ሺህ ዓመታት ወደ እኛ እየተላለፉ የመጡ ውርሻ ናቸው።” ሌሎች ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፦ ነፍሳት የሚሰቃዩበት ሲኦል ተብሎ የሚጠራ ቦታ አለን? የሞቱ ሰዎች ያላቸው እውነተኛ ተስፋ ምንድን ነው? ያለው አንድ አምላክ ብቻ ነው፣ ወይስ ሌሎች አማልክትም አሉ?​—ዘፍጥረት 2:7፤ ሕዝቅኤል 18:4

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ሊያገለግል ይችላል

መጽሐፉ ዋና ዋናዎቹ የሰው ዘር ሃይማኖቶች የተመሠረቱበትን ጊዜ መሠረት በማድረግ ከሞላ ጎደል በቅደም ተከተል ይገልጻቸዋል። እነዚህ ማብራሪያ የተሰጠባቸው ሃይማኖቶች የሚከተሉት ናቸው፦ ሒንዱይዝም፣ ቡድሂዝም፣ ዳውኢዝም፣ ኮንፊሽያኒዝም፣ ሺንቶ፣ የአይሁድ እምነት፣ ክርስትና፣ የሕዝበ ክርስትና እምነትና እስልምና ናቸው። ቅን ልብ ያለው ማንኛውም አማኝ ጥቅሶቹን ራሱ ለማስተያየት እንዲችል በእነዚህ ሃይማኖቶች ቅዱስ መጻሕፍት ምዕራፎች ውስጥ የሚያገኙ አንዳንድ ጥቅሶች ቀርበዋል። ስለ እስልምና በሚያብራራው ምዕራፍ ውስጥ ሦስት የተለያዩ የእንግሊዝኛ የቁርዓን ትርጉሞች ተጠቅሰዋል። ስለ አይሁድ እምነት በሚገልጸው ምዕራፍ ውስጥ ደግሞ የዘመናዊው የአይሁድ የጽሑፍ ማኅበር ትርጉም የሆነው ታናክ​—አዲስ የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ተጠቅሶአል።​—ከሥራ 17:28፤ ከቲቶ 1:12 ጋር አወዳድር

አምላክ የለም ለሚለው ኤቲስትና አምላክ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል ለሚለው አግኖስቲክ ምን የተዘጋጀ ነገር አለ? ምዕራፍ 14 ዘመናዊ ፈሊጥ ስለሆነው በአምላክ አለማመን ሁኔታና የይሖዋ ምስክሮች አምላክ እንዳለ የሚያውቁበትን ምክንያት ያብራራል። በሁሉም ምዕራፍ ላይ አንባቢው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያተኩር ተደርጓል። ስለዚህ የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ በተባለው መጽሐፍ በመጠቀም ማንኛውም ዓይነት እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር ወይም ምንም እምነት የለንም ከሚሉት ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር በተሻለ ሁኔታ የተዘጋጀን ለመሆን እንችላለን። መጽሐፉ እያንዳንዱን ሃይማኖት በአክብሮትና በዘዴ ይይዛል፣ ነገር ግን ወደ ይሖዋና ወደ እውነት ሊመሩ የሚችሉ ጥያቄዎችን ያነሣል። አምላክን ለማግኘት ከልባቸው ለሚፈልጉ ሰዎች ይህ መጽሐፍ እውነተኛ በረከት ይሆንላቸዋል።​—መዝሙር 83:18፤ ዮሐንስ 8:31, 32፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

ትምህርት ሰጪ የሆኑ የማስተማሪያ ሳጥኖችም በእያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ ተጨምረዋል። ለምሳሌ ያህል በገጽ 226 እና 227 ላይ “የአይሁድ እምነት​—የብዙ ድምፆች ሃይማኖት” የሚል በአይሁድ እምነት ውስጥ ስላሉት ዋና ዋና ክፍፍሎች የሚያብራራ ሳጥን አለ። “ሒንዱይዝም​—ነፃነት ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ” በሚለው ርዕስ ስር በገጽ 116 እና 117 ላይ “ሒንዱይዝም—​አንዳንድ የወንድና የሴት አማልክቶቻቸው” የሚል ሳጥን ይገኛል። ይህም ሒንዱዎች ከሚያመልኳቸው ከ330 ሚልዮን በላይ ከሆኑት አማልክት ውስጥ ጥቂቶቹን ብቻ ይዘረዝራል። ቡድሂስቶች የምዕራቡ ዓለም አምላክ የሚለውን ቃል በሚረዳው መንገድ በአምላክ ያምናሉን? በገጽ 145 ላይ “ቡድሂዝምና አምላክ” የሚለው ሳጥን ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል። በተጨማሪም መጽሐፉ ዋና ዋና ለሆኑ ርዕሶች ጠቃሚ የሆነ ማውጫም አለው። ለምርምር የረዱት የዋና ዋናዎቹ መጻሕፍት ስምም አንድ ሰው የበለጠ ዝርዝር ሐሳብ ለማግኘት ከፈለገ በማለት ተዘርዝረዋል።

መጽሐፉ ከ200 የሚበልጡ ፎቶግራፎችና ሥዕሎች አሉት፤ ሆኖም እዚያ የቀረቡት ለጌጥ ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ ሥዕል የማስተማሪያ ነጥብ አለው፤ ማብራሪያ ስለተሰጠበት ሃይማኖት ተጨማሪ መግለጫ ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል በገጽ 238 ላይ ኢየሱስ ያስተማራቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች የሚያሳዩ ፎቶግራፎች አሉ። በሌላም ቦታ የክርስቶስን አገልግሎት የተለያዩ ገጽታዎች ማለትም ተዓምራቶቹን፣ በደቀመዛሙርቱ ፊት በተአምር መለወጡን፣ መስዋዕታዊ ሞቱንና ደቀ መዛሙርቱ በመላው ዓለም እንዲሰብኩ ስልጣን ሲሰጣቸው የሚያሳዩ አምስት ተከታታይ ሥዕሎች አሉ።

በገጽ 289 ላይ የእስላሞችን ፍላጎት የሚስቡ በቅደም ተከተል የቀረቡ ፎቶግራፎች አሉ። ተመልካቹን ወደ መካ፣ ካባ ወደሚገኝበት ታላቅ መስጊድ ከዚያም እስላሞች ቅዱስ አድርገው ወደሚመለከቱት ጥቁር ድንጋይ ይወስደዋል። የቡድሂዝም የተለያየ አምልኮ በገጽ 157 ላይ በስዕል ተገልጾአል። ሒንዱዎችም ጋኔሳና ክሪሽና የሚባሉትን ተወዳጅ አማልክቶቻቸው ሥዕል በገጽ 96 እና 117 ላይ ሲመለከቱ ፍላጎታቸው ይቀሰቀሳል።

በዓለም ላይ የሚገኙ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ክርስቲያን አገልጋዮች ስለ እያንዳንዱ ታላቅ ሃይማኖት ልዩ ማብራሪያ ለማግኘት ምክር ተጠይቀዋል። ለምሳሌ ያህል ስለ አይሁድ እምነትና ስለ ባሐይ እምነት ለሚገልጹት ምዕራፎች ጠቃሚ ሐሳብ ከእስራኤል ተገኝቷል። በእስላም አገሮች ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች ስለ እስልምና የሚገልጸው ምዕራፍ የያዛቸውን ሐሳቦች በጥንቃቄ መርምረውታል። ስለ ሒንዱዎች፣ ስለ ሲኮችና ስለ ጄይንስ እምነቶች ከሕንድ ጠቃሚ ማብራሪያ ተገኝቷል። በምሥራቅ የሚገኙት አገልጋዮች ስለ ሺንቶ የሚናገረው ምዕራፍ የተሟላ መሆኑን አረጋግጠዋል፤ እንዲሁም ስለ ቡድሂዝም፣ ዳዊኢዝምና ኮንፊሺያኒዝም ምክር ለግሰዋል።

መጽሐፉ እያንዳንዱን ሃይማኖት በጥንቃቄ የሚሸፍን በመሆኑ መጽሐፉን በቋንቋቸው ያገኙት አስፋፊዎች ለእያንዳንዱ ሰው ሃይማኖት በሚስማማው ምዕራፍ አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ሊጀምሩ ይችላሉ። ከዚያም ስለ ጥንቱ ክርስትና አጀማመር ወደሚገልጸውና ክርስቶስ የሰውን ዘር ወደ አምላክ ለማቅረብ የሚያገለግል የአምላክ እውነተኛ ወኪል መሆኑን ለማመን የሚያስችሉ ምክንያቶች ወደሚገልጸው ምዕራፍ ሊሄዱ ይፈልጉ ይሆናል። ክሕደት እንዴት እንደጀመረና የሕዝበ ክርስትናን ክፍልፍሎችንና ኑፋቄዎችን እንዴት እንዳስከተለ የሚያብራሩ ምዕራፎች አሉ። የመጨረሻዎቹ ሁለት ምዕራፎች በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች ውስጥ እውነተኛው አምልኮ እንዴት እንደገና እንደተቋቋመና በፊታችን ያለው ጊዜ የሰይጣን ዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ለሆነችው ለታላቂቱ ባቢሎን ምን እንደሚያመጣባት ያሳያሉ። ከዚያ በኋላ አዲሱ ዓለምና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ የሰጠው ተስፋ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል።​—ዮሐንስ 5:28, 29፤ 12:44-46፤ 14:6፤ ራእይ 21:1-4

ይህ በእርግጥም ያዕቆብ በጻፈው ደብዳቤ በምዕራፍ 4 ቁጥር 8 ላይ እንደሚከተለው በማለት እንደገለጸው በዓለም የሚገኙ ብዙ ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ሊረዳቸው ይገባል፦ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፣ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፣ ልባችሁን አጥሩ።” ኢሳይያስም “[ይሖዋ (አዓት)] በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት” ብሏል።​—ኢሳይያስ 55:6፤ ዮሐንስ 6:44, 65

ሁላችንም ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ይኸውም የጽንፈ ዓለም የበላይ ጌታ ወደ ሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ ዘወር እንበል። በዚህ የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ በተባለው መጽሐፍም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋን “በመንፈስና በእውነት” እንዲያመልኩት እንርዳ። (ዮሐንስ 4:23, 24) እውነት ፈላጊዎችን ለማግኘትና የእውነት ባለቤት ስለሆነው አምላክ ለመንገር በምናደርገው ጥረት እንግፋበት። አምላክ በእርግጥ ሊገኝ ይችላል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “Taoist” የሚለው የእንግሊዝኛ አጻጻፍ ዳውኢስት ተብሎ ይነበባል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሰው አምላክን ለማግኘት በልዩ ልዩ መንገድ ፍለጋ አድርጓል

[ሥዕል]

ቅን ካቶሊኮች ወደ ማርያም ይመለከታሉ

[ሥዕል]

ሂንዱዎች የጋንጀስን ወንዝ እንደ ቅዱስ አድርገው ያከብሩታል

[የሥዕል ምንጭ]

Harry Burdich, Transglobe Agency, Hamburg

[ሥዕል]

አንዳንድ ሃይማኖተኛ አይሁዶች ጥቅስ የተጻፈባቸው ክታቦችን ያደርጋሉ

[የሥዕል ምንጭ]

GPO, Jerusalem

[ሥዕል]

እስላም የሆኑ ወንዶች ወደ መካ ሃይማኖታዊ ጉዞ ያደርጋሉ

[የሥዕል ምንጭ]

Camerapix

[ሥዕል]

ብዙዎች ቡድሃን እንደ ቅዱስ አድርገው ይመለከቱታል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሰዎች እውነተኛውን አምላክ እንዲያገኙት ለመርዳት ኢየሱስ በምሳሌዎች ተጠቅሟል

[የሥዕል ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[የሥዕል ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[የሥዕል ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ