ወጣቶች—የክርስቲያን ታማኝነትን ፈተና ታልፋላችሁን?
“የብልግና ጠባይን ታማኝ ሆኖ እንደመቆም አድርገህ አትመለከተውም። ነገሩ’ኮ እንዲሁ ደስታ ብቻ ነው። እውነት ነው፤ ነገሩን ወላጆችህ ወይም ሽማግሌዎች ቢደርሱበት ኀዘንንና ብዙ ችግሮችን እንደሚያስከትል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ራስህን በምታስደስትበት ጊዜ ይህን ሁሉ ሃሳብ ከአእምሮህ ታወጣለህ።”
እዚህ ላይ የተጠቀሰው ወጣት በድብቅ ዝሙት ይፈጽም ነበር። ወላጆቹንና የክርስቲያን ጉባኤን በማታለል ሁለት ዓይነት ኑሮ ይኖር ነበር። በዚህን ጊዜ ለክርስቲያን እምነቱ ታማኝ ሆኖ መቆምን በሚመለከት በፈተና እየወደቀ እንዳለ አልተገነዘበም ነበር።
በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ክርስትያን ወጣቶች ተመሳሳይ በሆኑ የታማኝነት ፈተናዎች ወድቀዋል። ነገሩ አያስደንቅም ምክንያቱም ሰይጣን ዲያብሎስ ‘ከአምላክ ሕዝብ ጋር በመዋጋት’ በአቋማቸው እንዳይጸኑ የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ነው። (ራእይ 12:17) በተለይም ወጣቶችን ‘የተንኮል ድርጊቶቹ’ ዒላማ አድርጎአቸዋል። (ኤፌሶን 6:11 ኪንግደም ኢንተርሊኒየር) ስለዚህ ታማኝ ሆኖ ለመቆም ከፍተኛ ጥረትንና ቁርጥ ውሳኔን ይጠይቃል።
ሆኖም ታማኝ ሆኖ መቆም ምንድን ነው? በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ታማኝ ሆኖ መቆም” (በእንግሊዝኛ ሎያልቲ) ለተባለው ቃል የገባው የመጀመሪያው ቋንቋ ቃል ከአንድ ዓላማ ጋር በተያያዘ ከአንድ ሰው ጋር የሚኖርን በፍቅር መጣበቅን ያመለክታል። (መዝሙር 18:25 አዓት) ይህ ቃል በቀላሉ ሊበጠስ የሚችልን ደካማ መተሳሰር የሚገልጽ ሳይሆን ከዚያ ሰው ጋር የሚያገናኘው ዓላማ እስኪፈጸም ድረስ ዝንፍ ሳይሉ ተጣብቆ መኖርን የሚገልጽ ነው። በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ታማኝ ሆኖ መቆም” ተብሎ የተተረጐመው የመጀመሪያው ቋንቋ ቃል የቅድስናን፣ የጽድቅን፣ ወይም ልዩ አክብሮት የሚቀሰቅስ ቅድስናን ሐሳብ የሚያስተላልፍ ነው።
ስለዚህ ታማኝ ሆኖ መቆም ከአምላክ ጋር ትክክለኛ የሆነ ዝምድና መኖሩን ያመለክታል። ኤፌሶን 4:24 “በእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ምሳሌ የተፈጠረውን አዲስ ሰው ልበሱ” ሲል ይነግረናል። ለይሖዋ ታማኝ ሆነህ ለመቆም ትፈልጋለህን? ከሆነ ከእርሱ ጋር በታማኝነት መጣበቅን፣ የማይበጠስ መተሳሰርን፣ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ለማስደሰት መቁረጥን ኰትኩት። ይህን ማድረጉ ምንም ያህል ፈታኝ ቢሆንም ከይሖዋ የጽድቅ ብቃቶች ጋር መጣበቅ ይኖርብሃል።
በታማኝነት እንዳትቆም የሚገፋፉ ተጽዕኖዎች
በይሖዋ ምስክሮች መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች ታማኝ ሆነው ለመቆም የሚያደርጉት ጥረት የሚያስመሰግናቸው ነው፤ በዚህም ምክንያት ንጹሕ ሕሊና አግኝተዋል። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ሰዎች በአጠቃላይ በከዳተኝነታቸው የታወቁ እንደሚሆኑ ተንብዮ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) የሚያሳዝነው አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶችም ይህ ከዳተኛ ዓለም ‘በራሱ ምስል እንዲቀርጻቸው’ መፍቀዳቸው ነው። (ሮሜ 12:2 ፊሊፕስ) ሰይጣን ይህንን ማከናወን የቻለው እንዴት ነው?
ሰይጣን የሚጠቀምበት አንዱ ኃይለኛ መሣሪያ በዕድሜ እኩዮች ከሆኑ የሚመጣ ግፊት ነው። አብዛኞቹ ሰዎች ሌሎች በጥሩ እንዲገምቷቸው ይፈልጋሉ፤ ሰይጣንም በዚህ ተፈጥሮአዊ ምኞት እንዴት መጫወት እንደሚችል ያውቃል። አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች እንዳይሾፍባቸው ስለሚፈልጉ ጤናማ ባልሆነ ንግግር፣ በብልግና ጠባይ፣ ሲጋራ በማጨስ፣ በስካር፣ ዕፅ በመውሰድ ድርጊትም ጭምር ተካፍለዋል። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት በዕኩዮቻቸው ተቀባይነትን ለማግኘት ሲሉ ነው።
ሰይጣን ‘የሥጋችንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፣ በሥጋችን ምኞት እንድንኖር’ ይፈልጋል። (ኤፌሶን 2:3) ‘በወጣትነት አበባነት’ ወቅት የፆታ ምኞት ግፊት ምን ያህል ኃይለኛ እንደሚሆን በደንብ ያውቃል። (1 ቆሮንቶስ 7:36) በእነዚህ ምኞቶች እንድትሸነፍም ይፈልጋል። አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች የብልግና ስዕሎችን፣ ሲኒማዎችን፣ ቪዲዮዎችን በመመልከት ወይም የራሳቸውን ብልት በማሻሸት የጾታ ስሜታቸውን በማርካት ሳያውቁት በሰይጣን እጅ ወድቀዋል። እነዚህ ነገሮች በአጸፋው ብዙውን ጊዜ ወደ ከባድ ታማኝነትን የማፍረስ ድርጊቶች ይመራሉ። የሰይጣን ዓለም በአንዳንድ ሁኔታዎች ‘በራሱ መልክ እየቀረጸህ ነውን?’
ሁለት ዓይነት ኑሮ መኖር
እንደ ምንዝር ያለ አንድ ትልቅ ኃጢአት መፈጸም ራሱ በጣም ከባድ ጉዳይ ሆኖ እያለ አንዳንድ ወጣቶች ችግሮቻቸውን ያባብሳሉ። እነርሱ በመዝሙር 26:4 ላይ ‘ማንነታቸውን የሚደብቁ’ ተብለው እንደተገለጹ ‘ሐሰተኛ ሰዎች’ ናቸው። እንደነዚህ ያሉት ወጣቶች በወላጆቻቸው ወይም በጎለመሱ ሌሎች ክርስቲያኖች ፊት አንድ ዓይነት መልክ በእኩዮቻቸው ፊት ደግሞ ሌላ ዓይነት መልክ በማሳየት ሁለት ዓይነት ሕይወት ይኖራሉ።
ይሁን እንጂ ሁለት ዓይነት ኑሮ መኖር ሽንፈትና አደገኛ ነው። መጥፎ ድርጊቶች ቁጥጥር ካልተደረገባቸው ወደ ሌላ መጥፎ ድርጊት የሚመሩ ናቸው። የአንድ ሰው ሕሊና በመጀመሪያው ላይ ቢረበሽም እንኳ ኃጢአት በመሥራት እየቀጠለ በሄደ መጠን ሕሊናው የኃጢአት ድርጊትን የመቃወም ችሎታው እየቀነሰ ይሄዳል። አንድ ሰው ስህተት ሲሠራ የሚሰማው ‘የሥቃይ ስሜት ቃል በቃል ያቆማል።’—ኤፌሶን 4:19 ኪንግደም ኢንተርሊኒየር
በዚህም ነጥብ ላይ ሲደርስ አንድ ሰው ኃጢአቱን ለመናዘዝና እርዳታ ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ ይሆንበታል። በተለይ በኃጢአት ድርጊቱ ሌሎች ክርስቲያን ወጣቶችም ካሉበት መናዘዝ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ የተሳሳተ የታማኝነት ስሜት ያይላል። በመግቢያው ላይ የተገለጸው ወጣት እንዲህ ሲል ገለጸ፦ “የምታደርገው ነገር ምን እንደሆነ ትገነዘባለህ፤ ስህተት መሆኑንም ታውቀዋለህ። በነገሩ ተሳታፊ የሆነ ሌላ ግለሰብ በችግር ውስጥ እንዳይወድቅ ለማንም ላለመንገር ትስማማለህ።”
አንድ ሰው ከወላጆቹ ወይም ከጉባኤው ‘ማንነቱን መደበቅ’ ቢችልም ከይሖዋ ግን ለመደበቅ አይችልም። “እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፣ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።” (ዕብራውያን 4:13) መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም” ሲል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ምሳሌ 28:13) ውሎ አድሮ ስህተቱ ይገለጣል። አንድ ሰው በብልጠት ይሖዋን ሊያታልለው አይችልም። ምሳሌ 3:7 “በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ [ይሖዋን (አዓት)] ፍራ፣ ከክፋትም ራቅ” ይላል። ‘የይሖዋ ዓይኖች በስፍራ ሁሉ መሆናቸውንና ክፉዎችንና ደጎችን እንደሚመለከቱ’ አስታውስ።—ምሳሌ 15:3
ቀደም ሲል ተጠቅሶ የነበረው ወጣትና በምስጢራዊ የኃጢአት ድርጊት ተባባሪ የነበሩ ሌሎች ተጋልጠዋል። እርሱና ጓደኞቹም ከክርስቲያን ጉባኤ መወገድ ነበረባቸው። ከጊዜ በኋላ ከመንፈሳዊ ውድቀታቸው ተነስተው እንደገና ተመልሰዋል። ሆኖም በታማኝነት የመቆምን ትርጉም እንዴት አስቸጋሪ በሆነ መንገድ ተማሩት!
ከአምላክ ጋር ‘ያለህን ጉዳይ ማስተካከል’
አንድ ሰው በአንድ መንገድ ምናልባት መጥፎ ድርጊት በመፈጸም ታማኝ ሳይሆን ቀርቶ ቢሆንስ? ራስን አሞኝቶ ነገሮችን የማስተካከልን አስፈላጊነት ችላ ማለቱ ቀላል ነው። በምሥጢር ዝሙት የፈጸመ አንድ ወጣት “ይህ ምናልባት ስህተቴን ይሸፍንልኝ ይሆናል ብዬ በማሰብ የመስክ አገልግሎት ተሳትፎየን ከፍ አደረግሁ” ብሏል። ከዳተኞቹ የእስራኤል ሕዝብም በተመሳሳይ በመስዋዕት ይሖዋን ለማባበል ሞክረው ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንደዚህ ያለውን የግብዝነት አምልኮ አልተቀበለውም። “ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁንም ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተው” በማለት አጠንክሮ አሳሰባቸው። ይሖዋ መስዋዕታቸውን የሚቀበለው ‘ከእርሱ ጋር የነበራቸውን ጉዳይ ካስተካከሉ’ በኋላ ብቻ ነበር። ዛሬም ኃጢአት ለሚፈጽሙ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።—ኢሳይያስ 1:11, 15-18
አንድ ሰው ችግሩን በምስጢር ለጓደኛው በመንገር ከይሖዋ ጋር ያለውን ጉዳይ ማስተካከል አይችልም። ለዚህ አንዱ ምክንያት ብዙውን ጊዜ ጓደኞች በሕይወት ውስጥ ያላቸው ተሞክሮ ልክ እንዳንተው የተወሰነ ስለሆነ ሁልጊዜ የተሻለውን እርዳታ ሊሰጡ አይችሉም። ከዚህም ሁሉ በላይ ኃጢአትህን ይቅር ሊሉ አይችሉም። ይህን ማድረግ የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። ስለዚህ ኃጢአትህን በመናዘዝ ‘ልብህን ለእርሱ አፍስስ።’ (መዝሙር 62:8) አድራጎትህ በጥልቅ ቢያሳፍርህም እንኳ ይሖዋ ‘በብዙ ይቅር ባይ እንደሆነ’ እርግጠኛ ሁን።—ኢሳይያስ 55:7
ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልግሃል። እንደዚህ ካለው እርዳታ ጥቅም ያገኘ አንድ ወጣት “ወዲያውኑ ከመጀመሪያው ለወላጆችህ አሳውቃቸው፤ ለሽማግሌዎችም አሳውቃቸው” በማለት ያሳስባል። አዎን፣ ምናልባት ወላጆችህ አንተን ለመርዳት የተሻለ ሁኔታ ሳይኖራቸው አይቀርም። የችግሮችህን መጠን ሙሉ በሙሉ በመግለጽ ‘ልብህን ስጣቸው።’ (ምሳሌ 23:26) አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ከጉባኤው ሽማግሌዎች ተጨማሪ እርዳታ እንድታገኝ ዝግጅት ሊያደርጉልህ ይችላሉ።—ያዕቆብ 5:14, 15
እውነተኛ ታማኝነትን ማሳየት—እንዴት?
ከመጀመሪያው ታማኝነትን በሚያስጥስ ድርጊት ፈጽሞ አለመውደቁ የተሻለ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም። መዝሙር 18:25 “ታማኝ ሆኖ ከሚቆምልህ ጋር ታማኝ ሆነህ ትቆማለህ፤ ያለ ነቀፋ ከሚሄደውም ጐበዝ ጋር ያለ ነቀፋ ትሄዳለህ” በማለት ይነግረናል። (አዓት) ይሖዋ በታማኝነት ከፍተኛ የጠባይ ደረጃ የሚጠብቁትን በከፍተኛ ሁኔታ ይባርካል።
ሆኖም ታማኝነትህ የሚፈተንባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ለምሳሌ አንድ ጓደኛህ መጥፎ መንገድ መከተል ጀምሯል እንበል። ለዚህ ጓደኛህ ያለህ የተሳሳተ ታማኝነት ለይሖዋ ሊኖርህ የሚገባውን ታማኝነት ይሸፍነው ይሆንን? ልታደርገው የሚገባው ፍቅራዊ ነገር ወደ ጓደኛህ ቀርበህ ጉዳዩን ለወላጆቹ ወይም ለሽማግሌዎች እንዲገልጽ ማሳሰብ ነው። በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ይህንን ባያደርግ አንተ እንደምትነግር ለጓደኛህ አስታውቀው። ምሳሌ 27:5 “የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል” ይላል። ጓደኛህን በዚህ መንገድ በመርዳት የጓደኝነትህን እውነተኝነት ብቻ ሳይሆን ለይሖዋ ያለህን የታማኝነት ጥልቀትም ታሳያለህ።
ፈተናው ምንም ዓይነት ይሁን ታማኝነትን የማሳየቱ ጥንካሬ የሚመጣው ከይሖዋ አምላክ ጋር ጠንካራ የግል ዝምድና ከመያዝ ነው። እንደዚህ ያለውን ዝምድና ለማግኘት ትርጉም ያለው ጸሎትና ትጋት የተሞላበት የግል ጥናት አስፈላጊ ነው። ቀደም ብሎ የተጠቀሱት መጥፎ ድርጊት የፈጸሙ ወጣቶች ጸሎትና ትጋት የተሞላበት የግል ጥናት አስፈላጊ ነው። ቀደም ብሎ የተጠቀሱት መጥፎ ድርጊት የፈጸሙ ወጣቶች ጸሎታቸውና የግል ጥናታቸው እንዲሁ ለይስሙላ የሚደረግ እንደነበረና አንዳንድ ጊዜም እንደሚረሱት አምነዋል። ይሖዋ ለእነርሱ እውን ሆኖ መታየቱ አቆመ፤ ከዚያም የረከሰ ድርጊት ተከተለ። አንተስ ታማኝ ሆነህ ለመቀጠል ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና በጸሎትና በግል ጥናት ታጠናክረዋለህን?
እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ደስታ እንዳመለጠህ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። አንዲት ወጣት “አንዳንድ ጊዜ ዓለማውያን ብዙ ደስታ ያገኙ መስሎ ይታያል” ካለች በኋላ “ነገር ግን በነገሩ ስትያዙ ምንም ደስታ እንዳልነበረ ልትመለከቱ ትችላላችሁ” ብላለች። ይህን የተናገረችው ከራስዋ ተሞክሮ ነው፤ በፆታ ብልግና ድርጊት ምክንያት አርግዛ አስወርዳለች። አሁን በከባዱ መንገድ ትምህርት ካገኘች በኋላ “በእውነት ውስጥ መሆኑ መከላከያ ነው” ትላለች። መዝሙር 119:165 “ሕግህን [የአምላክን] ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው” በማለት ያሳስበናል።
ስለዚህ ታማኝ ሆነህ ለመቀጠል የምትችለውን ሁሉ አድርግ። ከይሖዋ ጋር ጽኑ የሆነ ዝምድና ለመገንባት ጥረት አድርግ። መጥፎ የሆነውን ጥላ፤ ጥሩ ከሆነው ጋር ተጣበቅ። (ሮሜ 12:9) መዝሙር 97:10 “[ይሖዋን (አዓት)] የምትወድዱ፣ ክፋትን ጥሉ፤ [እርሱ (አዓት)] [የታማኞችን (አዓት)] ነፍሶች ይጠብቃል ከኃጥኣንም እጅ ያድናቸዋል” በማለት ይነግረናል። አዎን ክርስቲያን ወጣት እንደመሆንህ የክርስቲያን ታማኝነትን ፈተና ካለፍክ ከይሖዋ ጥበቃና ለዘላለም ሕይወት ለማግኘት ትችላለህ።