የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 7/15 ገጽ 8-13
  • ክርስቶስ ዓመፅን ጠልቷል—አንተስ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ክርስቶስ ዓመፅን ጠልቷል—አንተስ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሦስት የጥላቻ ዓይነቶች
  • ዓመፅን መጥላት የሚገባን ለምንድን ነው?
  • አመፅን የሚጠሉ
  • ለአመፅ ያለንን ጥላቻ መግለጽ
  • የጾታ ርኩሰትን መጥላት
  • የሐሰት ሃይማኖትንና ክህደትን መጥላት
  • ዓመፅን ትጠላለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ሥርዓት አልበኝነት በዓለም ዙሪያ ጨምሯል—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • ጥላቻን ማስወገድ የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • “ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 7/15 ገጽ 8-13

ክርስቶስ ዓመፅን ጠልቷል—አንተስ?

“ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ።”—ዕብራውያን 1:9

1. የይሖዋ እውነተኛ አገልጋዮች ጽድቅን ከመውደድ በተጨማሪ ምን ሌላ ነገር ይፈለግባቸዋል?

የይሖዋ እውነተኛ አገልጋዮች ይሖዋን በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸው፣ በፍጹም ሐሳባቸውና በፍጹም ኃይላቸው ይወዱታል። (ማርቆስ 12:30) ፍጹም አቋማቸውን ጠብቀው በመኖር የይሖዋን ልብ ደስ ለማሰኘት ይፈልጋሉ። (ምሳሌ 27:11) ይህንንም ለማድረግ ጽድቅን መውደድ ብቻ ሳይሆን ዓመፅንም መጥላት ይኖርባቸዋል። ምሳሌያቸው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲሁ አድርጓል። ስለ እርሱም እንዲህ ተብሏል፦ “ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ።”—ዕብራውያን 1:9

2. ዓመፅ ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?

2 ዓመፅ ምንድን ነው? ዓመፅ ኃጢአት ነው። ይህንንም ሐዋርያው ዮሐንስ ሲገልጽ “ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፣ ኃጢአትም ዓመፅ ነው” ሲል ጽፎአል። (1 ዮሐንስ 3:4) ዓመፀኛ ሰው “ሕግ አይገዛውም ወይም አይቆጣጠረውም።” (ዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሊጅየት ዲክሽነሪ) ዓመፀኝነት መጥፎ የሆኑትን ነገሮች በሙሉ፣ ክፋትን፣ የሥነ ምግባር ጉድለትን፣ ምግባረ ብልሹነትንና አታላይነትን ያጠቃልላል። የዓለምን ሁኔታ ብንመለከት ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን አመፀኝነት እንደተዛመተ እናያለን። ሐዋርያው ጳውሎስ በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ በተናገረለት “የሚያስጨንቅ ዘመን” ውስጥ እንደምንኖር ምንም አያጠያይቅም። ዓመፅ ይህን ያህል የተስፋፋ ከሆነ ክፋትን እንድንጠላ መታዘዛችን ምንኛ ተገቢ ነው! ለምሳሌ “እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] የምትወድዱ፣ ክፋትን ጥሉ” ተብሎ ተነግሮናል። (መዝሙር 97:10) በተመሳሳይም “ክፉውን ጥሉ፣ መልካሙንም ውደዱ” የሚል እናነባለን።—አሞጽ 5:15

ሦስት የጥላቻ ዓይነቶች

3-5. በአምላክ ቃል ውስጥ “መጥላት” የሚለው ቃል በምን ሦስት የተለያዩ መንገዶች ተሠርቶበታል?

3 መጥላት ማለት ምን ማለት ነው? “ጥላቻ” በአምላክ ቃል ውስጥ በሦስት የተለያዩ መንገዶች ተሠርቶበታል። በጠላትነት መንፈስ ተገፋፍቶ የተጠላውን ሰው ለመጉዳት ከማሰብ የሚመጣ ጥላቻ አለ። ክርስቲያኖች ይህን ዓይነቱን ጥላቻ ማስወገድ አለባቸው። ቃየን ጻድቅ የነበረውን ወንድሙን አቤልን እንዲገድል ያነሳሳው ይህ ዓይነቱ ጥላቻ ነበር። (1 ዮሐንስ 3:12) ሃይማኖታዊ መሪዎች ለኢየሱስ የነበራቸውም ጥላቻ ይህን የመሰለ ነበር።—ማቴዎስ 26:3, 4

4 በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች “መጥላት” የሚለውን ቃል ዝቅተኛ በሆነ መጠን መውደድን በሚገልጽ ስሜት ተጠቅመውበታል። ለምሳሌ ኢየሱስ “ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እህቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” ብሎአል። (ሉቃስ 14:26) ኢየሱስ ይህን ሲናገር አባትን፣ እናትን፣ ሚስትን ወይም ልጆችን ከኢየሱስ ያነሰ መውደድ እንደሚገባን መናገሩ እንደነበረ ግልጽ ነው። ያዕቆብ ‘ልያን ይጠላት ነበር።’ ከራሔል ያነሰ ይወዳት ነበር ማለት ነው።—ዘፍጥረት 29:30, 31

5 እንዲሁም በተለይ አሁን የምናተኩርበት “መጥላት” የሚለው ቃል ሌላ ትርጉም አለ። ከአንድ ሰው ወይም ከአንድ ነገር ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖረን የሚያደርግን ከባድ የሆነ የመዘግነን ወይም የመሰቀቅ ስሜት ያመለክታል። ይህ ዓይነቱ ጥላቻ በመዝሙር 139 ላይ “ፍጹም ጥል” ወይም በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መሠረት “ሙሉ ጥላቻ” ተብሎአል። እዚህ ላይ ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “አቤቱ፣ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? ስለ ጠላቶችህም አልተሰቀቅሁምን? [በአንተ ላይ የሚያምፁትንም እጅግ እጸየፋቸዋለሁ (የ1980 ትርጉም)] ፍጹም ጥል [ሙሉ በሙሉ አዓት] ጠላኋቸው፣ ጠላቶችም ሆኑኝ።”—መዝሙር 139:21, 22

ዓመፅን መጥላት የሚገባን ለምንድን ነው?

6, 7. (ሀ) በመሠረቱ ዓመፅን ልንጠላ የሚገባን ለምንድን ነው? (ለ) ዓመፅን የምንጠላበት ሁለተኛ ጠንካራ ምክንያት ምንድን ነው?

6 ዓመፅን መጥላት የሚገባን ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ለራሳችን አክብሮት እንዲኖረንና ጥሩ ኅሊና እንዲኖረን ስለሚረዳን ነው። ጻድቅና አፍቃሪ ከሆነው ሰማያዊ አባታችን ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ሊኖረን የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው። ዳዊት በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ይህንንም መዝሙር 26⁠ን በማንበብ ለመገንዘብ እንችላለን። ለምሳሌ እንዲህ ብሏል፦ “የክፉዎችን ማኅበር ጠላሁ፣ ከዝንጉዎችም ጋር አልቀመጥም።” (መዝሙር 26:5) ለአምላክና ለጽድቁ ያለን ፍቅር ለጽድቅ እንድንቀና፣ በእርሱ አመለካከት ዓመፅ ለሆነ ነገር ሁሉ ልባዊ ጥላቻ እንዲኖረን ሊገፋፋን ይገባል። ይህም ይሖዋን የማይታዘዙና እርሱን የሚጠሉ ሰዎች የሚያደርጉአቸውን የአመፀኝነት ድርጊቶች በሙሉ ያጠቃልላል። በተጨማሪም ዓመፅ በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ የሚያመጣ ስለሆነ ልንጠላው ይገባናል።

7 የይሖዋ ሕዝቦች ዓመፅን የሚጠሉበት ሌላው ምክንያት ዓመፅ በጣም አደገኛና ጎጂ በመሆኑ ነው። በሥጋ መዝራት ማለትም አመፃን መዝራት ምን ውጤት ያስከትላል? ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቆአል፦ “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፣ በመንፈስ ግን የሚዘራ ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።” (ገላትያ 6:7, 8) ስለዚህ ከዓመፅ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዲኖረን አንፈልግም። በእርግጥ ለራሳችን ደኅንነትና የአእምሮ ሰላም ስንል ማንኛውንም ዓይነት ዓመፅ መጥላት ይኖርብናል።

አመፅን የሚጠሉ

8. ዓመፅን በመጥላት ረገድ ዋነኛው አርዓያችን ማን ነው? ይህስ በየትኛው ጥቅስ ላይ ተገልጾአል?

8 ዓመፅን በመጥላት ረገድ አሳቢ ለሆኑ ፍጥረታት ሁሉ ዋነኛ አርዓያ የሚሆነው አምላክ ነው። ቃሉ “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፣ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ ትዕቢተኛ ዓይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፣ ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፣ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፣ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ” በማለት በዓመፅ ላይ የጽድቅ ቁጣ እንደሚቆጣ ይናገራል። እንዲሁም “እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] መፍራት ክፋትን ይጠላል፤ ትዕቢትንና እብሪትን ክፉንም መንገድ ጠማማውንም አፍ እጠላለሁ” የሚል ቃል እናነባለን። (ምሳሌ 6:16-19፤ 8:13) በተጨማሪም “እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ፍርድን የምወድድ ስርቆትንና በደልን [ዓመፅን የ1980 ትርጉም] የምጠላ ነኝ” ብሎ ነግሮናል።—ኢሳይያስ 61:8

9, 10. ኢየሱስ ዓመፅን ይጠላ እንደነበር ያሳየው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ ክርስቶስም ዓመፅን በመጥላት ረገድ አባቱን መስሎአል። በዚህም ምክንያት “ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ” የሚል ቃል እናነባለን። (ዕብራውያን 1:9) ኢየሱስ ይህን ዓይነቱን ጥላቻ በሚመለከት ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ሆን ብለው ዓመፅ ይሠሩ የነበሩትን ሐሰተኛ የሃይማኖት መሪዎች በማጋለጥ ለዓመፅ ያለውን ጥላቻ አሳይቶአል። በተደጋጋሚም ግብዞች መሆናቸውን በመናገር አውግዟቸዋል። (ማቴዎስ ምዕራፍ 23) በሌላ አጋጣሚም “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ” ብሎአል። (ዮሐንስ 8:44) ኢየሱስ በሁለት አጋጣሚዎች አካላዊ ኃይል ሳይቀር ተጠቅሞ ቤተ መቅደሱን ከስግብግብ ሃይማኖተኛ ግብዞች በማጽዳት ይህን ለዓመፅ ያለውን ጥላቻ አሳይቷል።—ማቴዎስ 21:12, 13፤ ዮሐንስ 2:13-17

10 በተጨማሪም ኢየሱስ ከዓመፅና ከኃጢአት ፈጽሞ በመራቅ ለዓመፅ ያለውን ጥላቻ አሳይቷል። በዚህም ተቃዋሚዎቹን “ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው?” በማለት ሊጠይቃቸው ችሏል። (ዮሐንስ 8:46) ኢየሱስ “ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ” ነበር። (ዕብራውያን 7:26) ጴጥሮስም ይህንን በማረጋገጥ ኢየሱስ “ኃጢአት አላደረገም፣ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም” ሲል ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 2:22

11. ዓመፅን በጠሉ ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ረገድ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች አሉ?

11 ይሁን እንጂ ፍጹም የሆነ ሰው ነበር። ዓመፅን ከልብ በመጥላት ረገድ አርአያ ሊሆኑን የሚችሉ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች አሉን? በእርግጥ አሉ! ለምሳሌ ሙሴና ሌዋውያን ባልንጀሮቹ ጣዖታትን ይጠሉ እንደነበር ለማሳየት 3,000 የሚያክሉ ጣዖት አምላኪዎችን በይሖዋ ትዕዛዝ መሠረት ገድለዋል። (ዘጸአት 32:27, 28) ፊንሐስም ሁለት አመንዝሮችን በጦር በመግደል ትልቅ የዓመፅ ጥላቻ እንዳለው አሳይቷል።—ዘኁልቁ 25:7, 8

ለአመፅ ያለንን ጥላቻ መግለጽ

12. (ሀ) ዓመፅን እንደምንጠላ እንዴት ልናሳይ እንችላለን? (ለ) የዓመፅ ሐሳቦችን ለማስወገድ የሚረዱን አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች ምንድን ናቸው?

12 ወደ ዘመናችን መለስ ስንል ለዓመፅ ያለንን ጥላቻ እንዴት ልናሳይ እንችላለን? አስተሳሰባችንን፣ ንግግራችንንና ድርጊታችንን በመቆጣጠር ነው። አእምሮአችን በሥራ በማይያዝበት ጊዜ ስለሚያንጹ ነገሮች የማሰብን ልማድ ማዳበር አለብን። ምናልባት ሌሊት ስንነቃ ስለሚያሳዝኑ ነገሮች ወይም ስለ ሩካቤ ሥጋና ስለመሳሰሉት አፍራሽ ነገሮች የማሰብ ዝንባሌ ሊኖረን ይችላል። እንደነዚህ ላሉት ሐሳቦች ፈጽሞ ቦታ አትስጡ። ከዚህ ይልቅ ጠቃሚ በሆኑ ሐሳቦች የመጠመድ ልማድ ይኑራችሁ። ለምሳሌ ያህል ጥቅሶችን፣ ዘጠኙን ደስታዎችና ዘጠኙን የመንፈስ ፍሬዎች በቃል ለማስታወስ ሞክሩ። (ማቴዎስ 5:3-12፤ ገላትያ 5:22, 23) የ12ቱን ሐዋርያት ስም መጥራት ትችላላችሁ? አሥርቱን ትዕዛዛት ታውቋቸዋላችሁ? የራዕይ መልዕክት የተላከላቸው ሰባቱ ጉባኤዎች እነማን ናቸው? የመንግሥቱን መዝሙሮች ለማስታወስ መሞከርም አእምሮአችን እውነት በሆኑ፣ ጭምትነትና ጽድቅ ባለባቸው፣ ንጹህ በሆኑ፣ ፍቅር፣ መልካም ወሬ በጎነትና ምስጋና ባለባቸው ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ሊረዳን ይችላል።—ፊልጵስዩስ 4:8

13. ዓመፅን መጥላታችን ምን ዓይነት ንግግሮችን እንድንጠላ ያደርገናል?

13 በተጨማሪም ማንኛውንም ዓይነት ንጹህ ያልሆነ ንግግር በማስወገድ ዓመፅን እንደምንጠላ ልናሳይ እንችላለን። ብዙ ዓለማዊ ሰዎች ፀያፍ ቀልዶችን በመናገርና በመስማት ይደሰታሉ። ክርስቲያኖች ግን እነዚህን የመስማት ዝንባሌ እንኳን ሊኖራቸው አይገባም። ከዚህ ይልቅ ወደዚህ ዓይነቱ ወራዳ ጭውውት ሊስበን ከሚችል ከማንኛውም ዓይነት ንግግር መሸሽና መራቅ ይገባናል። ከአካባቢው ልንርቅ የማንችል ከሆነ ደግሞ በፊታችን ሁኔታ እንኳን ይህን ዓይነቱን ንግግር እንደጠላነው ልናሳይ እንችላለን። “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነፅ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ” የሚለውን መልካም ምክር መከተል ያስፈልገናል። (ኤፌሶን 4:29) ንጹህ ያልሆኑ ንግግሮችን በመናገርም ሆነ በመስማት ራሳችንን ማርከስ አይገባንም።

14. ዓመፅን መጥላት ከምን ዓይነት የንግድ ድርጊቶችና ሥራዎች ይጠብቀናል?

14 ለዓመፅ ያለን ጥላቻ ማንኛውንም ዓይነት የኃጢአት ድርጊት እንድንጠላ ሊያደርገን ይገባል። ዓመፅን መጥላታችን በዚህ ረገድ ያለንን አቋም እንዳናላላና በኃጢአት ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ ይረዳናል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ኃጢአትን ልማድ አያደርጉም። (ከ1 ዮሐንስ 5:18 ጋር አወዳድር።) ለምሳሌ ማንኛውንም ዓይነት ሐቀኝነት የጎደለው የንግድ ሥራ መጥላት ይኖርብናል። በዛሬው ጊዜ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ለአሠሪዎቻቸው ሐቀኝነት የጎደለው ነገር እንዲፈጽሙ ተፅዕኖ ቢደረግባቸውም ይህን ዓይነቱን ድርጊት ለመፈጸም እምቢተኞች ሆነዋል። ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነውን ሕሊናቸውን የሚያስጥስ ነገር ከመፈጸም ይልቅ ሥራቸውን ለማጣት ፈቃደኞች ሆነዋል። ከዚህም በላይ የትራፊክ ሕግጋትን ባለመጣስ ወይም ግብርና ቀረጥ መክፈል በሚኖርብን ጊዜ ባለማጭበርበርና ባለማታለል ለዓመፅ ያለንን ጥላቻ ለማሳየት እንፈልጋለን።—ሥራ 23:1፤ ዕብራውያን 13:18

የጾታ ርኩሰትን መጥላት

15. ሰዎች ጠንካራ የሆነ የሩካቤ ፍላጎት ኖሮአቸው መፈጠራቸው ለምን መልካም ዓላማዎች አገልግሏል?

15 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከጾታ ጋር ግንኙነት ላለው ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት የተለየ ጥላቻ ሊኖረን ይገባል። አምላክ ሰውን ጠንካራ የሆነ የሩካቤ ፍላጎት እንዲኖረው አድርጎ በመፍጠሩ ሁለት ግሩም ዓላማዎችን ለማከናወን ችሎአል። የሰው ዘር ፈጽሞ እንዳይጠፋ ከማስቻሉም በተጨማሪም ደስታ የሚገኝበት ፍቅራዊ ዝግጅት ነው። ድሆች፣ መሃይሞች ወይም በተለያዩ መንገዶች የተጎዱ ሰዎችም እንኳን ከጋብቻ ዝምድና ደስታ ሊያገኙ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከዚህ ዓይነቱ ግንኙነት ለሚገኘው ደስታ ገደብ አበጅቶአል። እነዚህ መለኮታዊ ገደቦች መከበር ይገባቸዋል።—ዘፍጥረት 2:24፤ ዕብራውያን 13:4

16. የጾታ ሥነ ምግባር ስለጎደላቸው መዝናኛዎችና ድርጊቶች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

16 ዓመፅን የምንጠላ ከሆነ ማንኛውንም ዓይነት የጾታ ርኩሰት ከመፈጸምና ሥነ ምግባር በጎደላቸው መዝናኛዎች ከመደሰት በጥንቃቄ እንርቃለን። ስለዚህ አጠያያቂ ሥነ ምግባር ያላቸውን መጽሐፎች፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች እናስወግዳለን። እንደዚሁም ዓመፅን የምንጠላ ከሆንን በቴሌቪዥንም ይሁን በተንቀሳቃሽ ሥዕሎች ወይም በመድረክ ላይ የሚቀርቡትን ንጽህና የጎደላቸው ትርዒቶች አንመለከትም። አንድን ፕሮግራም ሥነ ምግባር የጎደለው ሆኖ ካገኘነው ወዲያውኑ ቴሌቪዥኑን ለማጥፋት ልንገፋፋ ወይም ቲያትር ቤቱን ለቅቀን ለመውጣት ድፍረት ሊኖረን ይገባል። በተመሳሳይም ዓመፅን መጥላት በቅኝቱም ሆነ በግጥሙ የሴሰኝነትን ስሜት ከሚቀሰቅስ ሙዚቃ እንድንርቅ ያደርገናል። ከሥነ ምግባር ውጭ ስለሆኑ ነገሮች ለማወቅ አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ ‘ለክፋት ነገር ሕፃናት ሆነን በማስተዋል ረገድ ግን የበሰልን’ እንሆናለን።—1 ቆሮንቶስ 14:20

17. ቆላስይስ 3:5 በሥነ ምግባር ንጹህ ሆነን እንድንቆይ ሊረዳን የሚችል ምን ምክር ይሰጠናል?

17 “እንግዲህ በምድር ያሉትን ብልቶቻችሁን ግደሉ፣ እነዚህም ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጐምጀት ነው” የሚል ጥሩ ምክር ተሰጥቶናል። (ቆላስይስ 3:5) በሥነ ምግባር ረገድ ንጹሐን ሆነን ለመኖር ከፈለግን ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልገን ምንም አያጠያይቅም። “ግደሉ” ተብሎ የተተረጎመውን የግሪክኛ ቃል በተመለከተ ኤክዝፖዚተርስ ባይብል ኮሜንታሪ እንዲህ በማለት ያትታል፦ “ይህ የሚያመለክተው ክፉ ድርጊቶችንና አመለካከቶችን አምቀን እንድንይዝ ወይም እንድንቆጣጠር ብቻ አይደለም። አሮጌውን ዓይነት አኗኗር ፈጽመን ማጥፋትና ማስወገድ ይኖርብናል። ምናልባት ‘ፈጽሞ መግደል’ የሚለው ትርጉም ኃይለ ቃሉን ይገልጽ ይሆናል። . . . የግሡ ትርጉምም ሆነ የግሡ የጊዜ አገባብ የሚያመለክተው ብርቱ የሆነና የግል ቆራጥነት የሚጠይቀውን ኃይለኛ ድርጊት ነው።” ስለዚህ የጾታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ጽሑፎችንና ሥዕሎችን አደገኛና ቀሳፊ እንደሆኑ ተላላፊ በሽታዎች መመልከት ይኖርብናል። በእርግጥም ጥሩ ሥነ ምግባርንና መንፈሳዊነትን የሚገድሉ አደገኛ በሽታዎች ናቸው። ክርስቶስም እጃችን ወይም እግራችን ወይም ዓይናችን የሚያደናቅፈን ከሆነ ቆርጠን እንድንጥል በመንገር ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሐሳብ ገልጾአል።—ማርቆስ 9:43-48

የሐሰት ሃይማኖትንና ክህደትን መጥላት

18. ለሃይማኖታዊ ዓመፅ ያለንን ጥላቻ እንዴት መግለጽ እንችላለን?

18 ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ግብዞቹን የሃይማኖት መሪዎች በማውገዝ ለዓመፅ ያለውን ጥላቻ እንዳሳየ ሁሉ ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች ለማንኛውም ዓይነት የሃይማኖታዊ ግብዝነት ዓመፅ ያላቸውን ጥላቻ ያሳያሉ። እንዴት? ታላቂቱ ባቢሎንን ራቁቷን ያስቀሯትንና በእርግጥ ሃይማኖታዊ አመንዝራ መሆኗን ያጋለጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች በማሰራጨት ነው። የሃይማኖታዊ ግብዝነትን ዓመፅ ከልብ የምንጠላ ከሆነ የዓለም የሐሰት ሐይማኖት ግዛት የሆነችውን ታላቂቱን ባቢሎን በማጋለጥ ሥራ በግንባር ቀደምትነት እንሰለፋለን። ይህንንም የምናደርገው እሷ ላሳወረቻቸውና በመንፈሳዊ እስር ውስጥ ላስገባቻቸው ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ስንል ነው። የታላቂቱ ባቢሎንን አመፀኝነት በምንጠላበት መጠን ልክ በሁሉም የመንግሥቱ አገልግሎት መስኮች በቅንዓት እንካፈላለን።—ማቴዎስ 15:1-3, 7-9፤ ቲቶ 2:13, 14፤ ራዕይ 18:1-5

19. ከሃዲዎችን እንዴት ልንመለከታቸው ይገባናል? ለምንስ?

19 ዓመፅን እንድንጠላ የተጣለብን ግዴታ ከሃዲዎች የሚያደርጉአቸውን ነገሮች በሙሉ ያጠቃልላል። ለከሃዲዎች ያለን ዝንባሌ የሚከተለውን የተናገረውን የንጉሥ ዳዊትን የመሰለ መሆን ይኖርበታል፦ “አቤቱ፣ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? ስለ ጠላቶችህም አልተሰቀቅሁምን? “አቤቱ፣ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? ስለ ጠላቶችህም አልተሰቀቅሁምን? [በአንተ ላይ የሚያምፁትንም እጅግ እጸየፋቸዋለሁ (የ1980 ትርጉም)] ፍጹም ጥል [ሙሉ በሙሉ አዓት] ጠላኋቸው፣ ጠላቶችም ሆኑኝ።” (መዝሙር 139:21, 22) ዘመናዊዎቹ ከሃዲዎች ከ“ዓመፅ ሰው” ማለትም ከሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ጋር በዓላማ ተባብረዋል። (2 ተሰሎንቄ 2:3) ስለዚህ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ከነዚህ ከሃዲዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሊኖረን አይገባም። ፍጹም ባለመሆናችን ምክንያት ልባችን ወንድሞቻችንን ወደ መተቸትና ስህተት ወደመፈለግ ሊያዘነብል ይችላል። በግለሰብ ደረጃ ስንመለከታቸው የ“ታማኝና ልባም ባሪያ” አባሎች ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። (ማቴዎስ 24:45-47) ይሁን እንጂ በቡድን ደረጃ ታማኝና ልባም ባሪያ ነው። ከሃዲዎች በአመራር ቦታ ላይ የሚገኙትን ወንድሞች ግድፈቶች ወይም ስህተት የሚመስሉ ድርጊቶችን ያጎላሉ። ከዚህ አደጋ ልንጠበቅ የምንችለው የከሃዲዎችን ፕሮፓጋንዳ እንደ ቀሳፊ መርዝ በመሸሽ ነው። በእርግጥም ቀሳፊ መርዝ ነው።—ሮሜ 16:17, 18

20, 21. ዓመፅን የምንጠላባቸውን ምክንያቶች እንዴት ልናጠቃልል እንችላለን?

20 ዓለም በዓመፅ እንደተሞላ ተመልክተናል። ዓመፅ ደግሞ ኃጢአት ነው። ጽድቅን መውደዳችን ብቻውን በቂ አይደለም። ዓመፅንም መጥላት ያስፈልገናል። ከክርስቲያን ጉባኤ ከተወገዱት ሰዎች አንዳንዶቹ ጽድቅን እንወዳለን ብለው ያስቡ ነበር። ይሁን እንጂ በሚፈለገው መጠን ዓመፅን ሳይጠሉ ቀርተዋል። በተጨማሪም ዓመፅን መጥላት የሚገባን ለምን እንደሆነ ተመልክተናል። ዓመፅን ካልጠላን ጥሩ ኅሊናም ሆነ ለራሳችን አክብሮት ሊኖረን አይችልም። በተጨማሪም ዓመፅ ለይሖዋ አምላክ ታማኝ አለመሆን ማለት ነው። እንዲሁም ዓመፅ በጣም መራራ የሆኑ ውጤቶችን ማለትም መከራን፣ ውድቀትንና ሞትን እንድናጭድ ያደርገናል።

21 ዓመፅን እንደምንጠላ እንዴት ማሳየት እንደምንችልም ተገንዝበናል። ዓመፅን የምንጠላ መሆናችንን ልናሳይ የምንችለው እምነት ከማጉደል፣ ከጾታ ብልግና ወይም ከክህደት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ባለማድረግ ነው። ይሖዋን ለመቀደስ የምንፈልግና ልቡን ደስ ለማሰኘት የምንመኝ ከሆንን ጽድቅን መውደድና በአገልግሎቱ በትጋት መካፈል ብቻ ሳይሆን መሪያችንና አዛዣችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገው ዓመፅንም መጥላት ይገባናል።

እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ቅዱሳን ጽሑፎች “መጥላት” የሚለውን ቃል የተጠቀሙበት እንዴት ነው?

◻ ዓመፅን እንድንጠላ የሚያደርጉን አንዳንድ ጥሩ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

◻ ዓመፅን በመጥላት ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑን እነማን ናቸው?

◻ ዓመፅን እንደምንጠላ እንዴት ልናሳይ እንችላለን?

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ አመፅን ይጠላ ስለነበር ቤተ መቅደሱን አፀዳ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አመፅን ከጠላን በጾታ ሥነ ምግባር የረከሱ መዝናኛዎችን እናስወግዳለን

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ