መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይጋጫልን?
አንድ ጊዜ ሄንሪ ቫንዳይክ የተባሉት ደራሲ እንዲህ ሲሉ ጽፈው ነበር፦ “በምሥራቅ አገሮች የተወለደውና የምሥራቃውያንን አነጋገርና አገላለጽ የተጎናጸፈው መጽሐፍ ቅዱስ የዓለምን ጎዳናዎች በሙሉ በተለመደው እግሩ አዳርሶአል፣ በየአገሩም እየገባ ሊላመድ ችሎአል። በብዙ መቶ በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ለሰው ልጅ ልብ መናገርን ተምሯል። ልጆች የመጽሐፉን ታሪክ በደስታና በአድናቆት ያዳምጣሉ፣ ጠቢባን ደግሞ ለሕይወታቸው መመሪያ እንዲሆናቸው ያሰላስሉታል። ክፉዎችና ትዕቢተኞች በሚሰጣቸው ማስጠንቀቂያዎች ሲንቀጠቀጡ የተጎዱና የሚተክዙ ግን እናታዊ በሆነ ቃናው ይጽናናሉ። . . . ይህን ውድ ኃብት የራሱ ያደረገ ማንኛውም ሰው ድሃ ወይም መድረሻ ያጣ ሊሆን አይችልም።”
በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “በብዙ ቋንቋዎች መናገርን ተምሯል።” እጅግ ቢያንስ ከ66ቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንዱ በ1,970 ቋንቋዎች ተተርጉሞአል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ከአምላክ እንደተሰጣቸው ስጦታ ቆጥረው በደስታ በማንበብ ብዙ ጥቅም አግኝተውበታል። ሆኖም አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ስለሚጋጭ አስተማማኝ ሊሆን አይችልም ይላሉ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተደረጉ ምርምሮች ምን ያሳያሉ?
በዚህ መጽሔት ሽፋን ላይ እንደሚታየው አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ በታማኝ ሰዎች ተጠቅሟል። እርግጥ ነው በጥንቃቄ የተደረጉ ምርምሮች እንደሚያሳዩት መጽሐፍ ቅዱስ 40 በሚያክሉ ሰዎች እንደተጻፈና 16 መቶ ዓመታት ያህል እንደፈጀ ተረጋግጧል። እነዚህ ሰዎች በጸሐፊነት ሥራ የሚተዳደሩ ነበሩን? አልነበሩም። ከመካከላቸው እረኛ፣ አሣ አጥማጅ፣ ቀራጭ፣ ሐኪም፣ ድንኳን ሰፊ፣ ካህን፣ ነቢይ፣ እና ንጉሥ ይገኙበታል። ጽሑፎቻቸው እኛ በ20ኛው መቶ ዘመን የምንኖረው ሰዎች በሚገባ የማናውቃቸውን ሕዝቦችና ልማዶች ይጠቅሳል። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ራሳቸው እንኳን የሚጽፉትን ነገር ትርጉም ሁልጊዜ አያውቁም ነበር። (ዳንኤል 12:8-10) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ ለመረዳት አዳጋች የሆነ ነገር ቢያጋጥመን ሊደንቀን አይገባም።
ይሁን እንጂ እነዚህን የመሳሰሉት ችግሮች ሊፈቱ ይችላሉን? መጽሐፍ ቅዱስ እርስበርሱ ይጋጫልን? መልሱን ለማግኘት እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
እውነት ለመረዳት የማይቻሉ ችግሮች ናቸውን?
▪ ቃየን ሚስቱን ከየት አገኘ? (ዘፍጥረት 4:17)
አንድ ሰው አቤል ከተገደለ በኋላ በምድር ላይ የቀሩት ሰዎች አዳም፣ ሔዋንና ወንጀለኛው ቃየን ብቻ ናችው ብሎ ሊያስብ ይችላል። ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን ሰፊ ቤተሰብ ነበራቸው። ዘፍጥረት 5:3, 4 እንደሚናገረው አዳም ሴት የሚባል ወንድ ልጅ ነበረው። ታሪኩ በመቀጠል “የአዳም ዘመን ሴትን ከወለደ በኋላ ስምንት መቶ ዓመት ሆነ። በዚህም ጊዜ የወንዶችና የሴቶች ልጆች አባት ሆነ።” (አዓት) ስለዚህ ቃየን ከእህቶቹ አንዷን ወይም ደግሞ ከወንድሞቹ ወይም ከእህቶቹ ልጆች አንዷን አግብቶ ሊሆን ይችላል። በዚያ ዘመን የሰው ልጆች ለፍጽምና በጣም ቅርብ ስለነበሩ በዛሬው ጊዜ የቅርብ ዘመዳሞች ሲጋቡ የሚያጋጥመው ዓይነት የጤና ችግር አያጋጥማቸውም ነበር።
▪ ዮሴፍን ወደ ግብፅ የሸጠው ማን ነው?
ዘፍጥረት 37:27 የዮሴፍ ወንድሞች ዮሴፍን ለእስማኤላውያን ለመሸጥ ወሰኑ ይላል። ይሁን እንጂ ቀጥሎ ባለው ቁጥር ላይ “የምድያም ነጋዶችም አለፉ እነርሱም ዮሴፍን አንስተው ከጉድጓድ አወጡት ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሃያ ብር ሸጡት እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት” ይላል። ዮሴፍ የተሸጠው ለእስማኤላውያን ነው ወይስ ለምድያማውያን? ምድያማውያን እና እስማኤላውያን ነጋዴዎች በቅድመ አያታቸው በአብርሃም በኩል ይዛመዱ ስለነበር ምድያማውያን እስማኤላውያን ተብለው ሊጠሩ ይችሉ ይሆናል። ወይም ምድያማውያን ነጋዴዎች ከእስማኤላውያን ነጋዴዎች ጋር በአንድ ላይ እየተጓዙ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ የዮሴፍ ወንድሞች ዮሴፍን ሽጠውታል። በኋላም “ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ” ሊላቸው ችሎአል።—ዘፍጥረት 45:4
▪ ከሞዓባውያን ሴቶች ጋር በመርከሳቸውና በብዔል ፌጎር የበዓል አምልኮ በመካፈላቸው ምክንያት የሞቱት እስራኤላውያን ቁጥር ምን ያህል ነው?
ዘኁልቁ 25:9 ላይ “በመቅሰፍቱም [በክፉ ሥራቸው ምክንያት አምላክ ያጠፋቸው] ሃያ አራት ሺህ ነበሩ” ይላል። ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ “ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሃያ ሦስት ሺህ እንደወደቁ አንሴስን” ብሎአል። (1 ቆሮንቶስ 10:8) ምናልባት የተገደሉት እስራኤላውያን ቁጥር በ23,000 እና በ24,000 መካከል ሆኖ ሁለቱም ቁጥሮች ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የዘኁልቁ መጽሐፍ በዚህ ኃጢአት የተባበሩት “የሕዝብ አለቆች” የተገደሉት በሕዝቡ ፈራጆች እንደሆነ ያመለክታል። (ዘኁልቁ 25:4, 5) በደለኞቹ የሕዝብ አለቆች 1,000 ከሆኑ ጳውሎስ በጠቀሳቸው 23,000 ሰዎች ላይ ሲደመር ጠቅላላ ቁጥራቸው 24,000 ይሆናል። ይሖዋ ባወረደው መቅሰፍት በቀጥታ የተገደሉት 23,000 ሲሆኑ ሁሉም የተገደሉት ይሖዋ ባወረደባቸው የቅጣት ፍርድ ስለሆነ በይሖዋ የተቀሰፉት 24,000 ናቸው ሊባል ይችላል።—ዘዳግም 4:3
▪ አጋግ የእሥራኤላውያን ንጉሥ በነበረው በንጉሥ ሳኦል ዘመን ይኖር የነበረ ሰው መሆኑ ተገልጾአል። ይሁን እንጂ ከንጉሥ ሳኦል ዘመን በፊት ይኖር የነበረው በለዓም አጋግ ስለሚባል አማሌቃዊ ገዥ መናገሩ ትክክል ሊሆን ይችላልን?
በ1473 ከዘአበ በለዓም የእሥራኤል ንጉሥ ከአጋግ ከፍ ያለ እንደሚሆን ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ዘኁልቁ 24:7) ሆኖም ንጉሥ ሳኦል እስከነገሠበት ዘመን ድረስ (ከ1117-1078 ከዘአበ) ስለ አጋግ የተነገረ አንዳችም ነገር የለም። (1 ሳሙኤል 15:8) ይሁን እንጂ “አጋግ” የሚለው ስም ፈርኦን እንደሚለው የግብፃውያን ነገሥታት ስም ለነገሥታት የሚሰጥ የማዕረግ ስም ሊሆን ስለሚችል የሐሳብ ግጭት አያስከትልም። በተጨማሪም ይህ ስም አማሌቃውያን መሪዎች በተደጋጋሚ የሚጠቀሙበት የመጠሪያ ወይም የተፀውኦ ስም ሊሆን ይችላል።
▪ ዳዊት እሥራኤላውያንን እንዲቆጥር ያነሳሳው ማን ነው?
በሁለተኛ ሳሙኤል 24:1 “ደግሞም ዳዊትን አነሳስቶ [ወይም “ዳዊት ተነሳስቶ” የግርጌ ማስታወሻ] ‘ሂዱና እስራኤልንና ይሁዳን ቁጠሩ’ ባለ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በእሥራኤል ላይ ነደደ።” (አዓት) ይሁን እንጂ ንጉሥ ዳዊት ኃጢአት እንዲያደርግ የገፋፋው ይሖዋ አልነበረም። በ1 ዜና 21:1 ላይ “ሰይጣንም [“ተቃዋሚውም” የግርጌ ማስታወሻ] በእሥራኤል ላይ ተነሣ እሥራኤልንም ይቆጥር ዘንድ ዳዊትን አንቀሳቀሰው” ይላል። አምላክ በእሥራኤላውያን ላይ እጅግ ተቆጥቶ ስለነበር ሰይጣን ይህን የመሰለ ኃጢአት እንዲያሠራቸው ፈቀደለት። 2 ሳሙኤል 24:1 አምላክ ራሱ ድርጊቱን እንደፈፀመ የሚገልጸው በዚህ ምክንያት ነው። የጆሴፍ ቢ. ሮተርሃም ትርጉም እንዲህ ይላል፦ “የያህዌህም ቁጣ በዳዊት ላይ ነደደ ስለዚህም ዳዊት እሥራኤልንና ይሁዳን ለመቁጠር እንዲሳሳት አደረገ።”
▪ ዳዊት ቆጥሮ ስላገኘው የእሥራኤላውያንና የአይሁዳውያን ብዛት ሁለት የተለያዩ ቁጥሮች ተሰጥተዋል። ይህንንስ እንዴት ማስማማት ይቻላል?
በ2 ሳሙኤል 24:9 ላይ 800,000 እሥራኤላውያንና 500,000 አይሁዳውያን እንደተቆጠሩ ሲገልጽ በ1 ዜና 21:5 ላይ ግን የእሥራኤል ተዋጊዎች 1,100,000 የይሁዳ ደግሞ 470,000 ያህል እንደሆኑ ይናገራል። በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ተመዝግበው እያንዳንዱ ክፍል 24,000 ወታደር በሚይዝ 12 ክፍሎች ተከፍለው በየዓመቱ ውስጥ አንድ ወር ንጉሡን የሚያገለግሉ 288,000 ወታደሮች ነበሩ። በተጨማሪም የ12ቱን ነገዶች 12 መሣፍንት የሚያገለግሉ 12,000 ወታደሮች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ ሲደመሩ 300,000 ይሆናሉ። በ2 ሳሙኤል ላይ ግን እነዚህ ቁጥሮች አልተደመሩም። (ዘኁልቁ 1:16፤ ዘዳግም 1:15 1 ዜና 27:1-22) ስለ አይሁዳውያን በተሰጠው ቁጥር ረገድ ደግሞ በ2 ሳሙኤል 24:9 ላይ የተገለጸው ቁጥር የፍልስጥኤማውያንን ድንበር ይጠብቁ የነበሩትን 30,000 የሚያህሉ አይሁዳውያን እንደሚጨምር ግልጽ ነው። በ1 ዜና 21:5 ላይ ግን አልተጨመሩም። (2 ሳሙኤል 6:1) 2 ሳሙኤል እና 1 ዜና የተለያየ አመለካከትና አስተሳሰብ ባላቸው ሁለት ሰዎች መጻፉን ካስታወስን ቁጥሮቹን ልናስማማ እንችላለን።
▪ የሰላትያል አባት ማን ነበር?
አንዳንድ ጽሑፎች የሰላትያን ሥጋዊ አባት ንጉሥ ኢዮአቂን እንደሆነ ያመለክታሉ። (1 ዜና 3:16-18፤ ማቴዎስ 1:12) ዳሩ ግን ወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ ሰላትያልን “የኔሪ ልጅ” በማለት ይጠራዋል። (ሉቃስ 3:27) በመሠረቱ ኔሪ ልጁን ሚስት እንድትሆነው ለሰላትያን ሰጥቶታል። ዕብራውያን የልጃቸውን ባል እንደ ልጅ አድርገው ስለሚቆጥሩ በዘር ሐረግ ዝርዝር ውስጥ ሉቃስ ሰላትያል የኔሪ ልጅ እንደሆነ ይገልጻል። በተመሳሳይም ሉቃስ ዮሴፍ የማርያም አባት የሆነው የኤሊ ልጅ እንደሆነ ገልጾአል።—ሉቃስ 3:23
ስለ ኢየሱስ የሚናገሩ ጥቅሶችን ማስማማት
▪ ኢየሱስ ወደ እርያ መንጋ እንዲገቡ ያደረጋቸው አጋንንት ከስንት ሰዎች የወጡ ናቸው?
ወንጌል ጸሐፊ የነበረው ማቴዎስ ከሁለት ሰዎች የወጡ ናቸው ብሎ ሲጽፍ ማርቆስና ሉቃስ ግን ከአንድ ሰው የወጡ እንደሆኑ መዝግበዋል። (ማቴዎስ 8:28፤ ማርቆስ 5:2፤ ሉቃስ 8:27) ማርቆስና ሉቃስ ትኩረት ያደረጉት ወደ አንድ አጋንንት ያደረበት ሰው ነበር። ምክንያቱም የእርሱ ሁኔታ ጎላ ብሎ የሚታይና ኢየሱስም ያነጋገረው ይህን ሰው ብቻ ስለነበረ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ይህ ሰው ይበልጥ ኃይለኛ ወይም አጋንንት ለረዥም ጊዜ ሲያሰቃዩት የቆየ ሊሆን ይችላል። ከተፈወሰም በኋላ ኢየሱስን ለመከተል የፈለገው ይህ ሰው ብቻ ይሆናል። (ማርቆስ 5:18-20) ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሌላም ሁኔታ አለ። ኢየሱስ ሁለት ዕውሮችን እንደፈወሰ ማቴዎስ ሲጽፍ ማርቆስና ሉቃስ ግን አንድ ዓይነ ሥውር ብቻ እንደተፈወሰ ገልጸዋል። (ማቴዎስ 20:29-34፤ ማርቆስ 10:46፤ ሉቃስ 18:35) ይህ ደግሞ እርስ በርሱ የሚጋጭ መግለጫ አይደለም። ምክንያቱም ቢያንስ አንድ ሰው መፈወሱ ተገልጾአል።
▪ ኢየሱስ ሲሞት የለበሰው ልብስ ቀለሙ ምን ዓይነት ነበር?
ማርቆስ (15:17) እና ዮሐንስ (19:2) በገለጹት መሠረት ወታደሮቹ ኢየሱስን ያለበሱት የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ልብስ ነበር። ማቴዎስ (27:28) ግን ደማቅ ቀይ ጥምጥም አደረጉበት በማለት የቅላቱን ድምቀት ጭምር ገልጾአል። የወይን ጠጅ በሰማያዊና በቀይ መካከል የሚገኝ ቀለም በመሆኑ ማርቆስና ዮሐንስ ቀላ ያለ ጥምጥም መሆኑን ተስማምተውበታል። የብርሃን ነፀብራቅና ከጀርባ በኩል ያለው ሁኔታ ለጥምጥሙ የተለየ መልክ ሊሰጠው ይችላል። በዚህ ምክንያት የወንጌል ጸሐፊዎቹ የጻፉት ለራሳቸው ወይም ታሪኩን ላስተላለፉላቸው ሰዎች ዓይን ደመቅ ብሎ የታያቸውን ነው። እነዚህን የመሳሰሉ ጥቃቅን ልዩነቶች መኖራቸው የሚያመለክተው ጸሐፊዎቹ የተለያዩ መሆናቸውን እንጂ የሐሳብ ግጭት መኖሩን አይደለም።
▪ ኢየሱስ የተሰቀለበትን እንጨት የተሸከመው ማን ነበር?
ዮሐንስ (19:17) እንደሚለው “ኢየሱስንም ይዘው ወሰዱት መስቀሉንም [የመሰቀያውንም እንጨት አዓት] ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደተባለው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ” ይላል። ሆኖም ማቴዎስ (27:32)፣ ማርቆስ (15:21)፣ እና ሉቃስ (23:26) “በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ ይዘው ከኢየሱስ በኋላ መስቀሉን [የመከራውን እንጨት አዓት] እንዲሸከም ጫኑበት።” ዮሐንስ የጻፈው ኢየሱስ ራሱ የመከራውን እንጨት እንደተሸከመ አድርጎ ነው። ዮሐንስ አጠር አድርጎ በጻፈው ታሪክ ውስጥ ስምዖን እንጨቱን እንዲሸከም መገደዱን አልገለጸም። ስለዚህ የወንጌል ታሪኮች በዚህ ረገድም ስምምነት ያላቸው ናቸው።
▪ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሞተው እንዴት ነበር?
ማቴዎስ 27:5 ራሱን ሰቀለ ሲል ሥራ 1:18 ደግሞ “ይህም ሰው በአመጽ ዋጋ መሬት ገዛ፣ በግንባሩም ተደፍቶ ከመካከሉ ተሰነጠቀ፣ አንጀቱም ሁሉ ተዘረገፈ” ይላል። ማቴዎስ የገለጸው ራሱን በራሱ የገደለበትን ሁኔታ ሲሆን የሐዋርያት ሥራ ደግሞ በመጨረሻ ላይ የደረሰበትን ሁኔታ ነው። ይሁዳ ገመዱን በግንድ ቅርንጫፍ ላይ ያሰረ ይመስላል። በኋላም ሸምቀቆ አበጅቶ አንገቱ ውስጥ በማስገባት ከገደል ጫፍ ላይ ተንጠልጥሎ ይሆናል። የዛፉ ቅርንጫፍ ተሰብሮ ወይም ገመዱ ተበጥሶ ከታች ባሉት ድንጋዮች ላይ በመውደቁ ሆዱ ተሰንጥቆ አንጀቱ ተዘርግፎ ይሆናል። የኢየሩሳሌምን የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ስንመለከት ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ምክንያታዊ መሆኑን እንገነዘባለን።
ነገሮችን እንዴት ትመለከታለህ?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እርስበርሳቸው የሚጋጩ መስለው የሚታዩ ታሪኮች ሲያጋጥሙን ብዙ ጊዜ ሰዎች እርስበርሳቸው የሚጋጩ የሚመስሉ ነገር ግን በቀላሉ ለመረዳት የሚቻሉ ነገሮችን እንደሚናገሩ ብንገነዘብ ጥሩ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ የመስሪያ ቤት አለቃ ለጸሐፊው በቃሉ እያነበበ ደብዳቤ እንድትጽፍለት ሊያደርግ ይችላል። ከተጠየቀም ደብዳቤውን የላክሁት እኔ ነኝ ለማለት ይችላል። ሆኖም ጸሐፊዋ ደብዳቤውን በታይፕ መትታ ስለላከችው ደብዳቤውን የላክሁት እኔ ነኝ ልትል ትችላለች። በተመሳሳይም ማቴዎስ (8:5) የመቶ አለቃው ወደ ኢየሱስ መጣ ብሎ መጻፉና ሉቃስ (7:2, 3) ደግሞ መቶ አለቃው መልዕክተኞችን ወደ ኢየሱስ ላከ ብሎ መጻፉ እርስ በርሱ አይጋጭም።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ የሚመስሉትን ሐሳቦች ማስማማት እንደሚቻል ያየናቸው ምሳሌዎች ያመለክታሉ። ስለዚህ ለቅዱሳን ጽሑፎች አዎንታዊና ብሩሕ አመለካከት እንዲኖረን የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለን። በ1876 ታትሞ በወጣ አንድ የቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲኖረን ተመክረናል፦
“በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመረዳት የሚያዳግቱ ነገሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛ ዝንባሌ ሁሉንም አጠራጣሪ ሁኔታ በሙሉ ለማስወገድ ባይቻልም በተቻለ መጠን አስቸጋሪውን ነገር ከአእምሮ ውስጥ አውጥቶ ከእውነቱ ጋር መጣበቅና ለእውነቱ መገዛት ነው። የሐዋርያትን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። አንዳንድ ደቀ መዛሙርት “ይህ ንግግር ከባድ ነው” ብለው ክርስቶስ በተናገረው ቅር ተሰኝተው ክርስቶስን መከተል ቢተውም ሐዋርያት ግን “ጌታ ሆይ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም” ብለዋል። . . . አንድ እውነት ከሌላ እውነት ጋር የሚጋጭ በሚመስልበት ጊዜ እርስበርሱ ለማስማማት ጥረት ማድረግና የተስማሙትን ሃሳቦች መስማማታቸውን ለሰዎች ሁሉ መግለጽ ይኖርብናል”—ዮሐንስ 6:60-69 የ1980 ትርጉም
አንተስ እንደዚህ ታደርጋለህን? ቅዱሳን ጽሑፎች እርስበርሳቸው የሚስማሙ መሆናቸውን የሚያሳዩትን ጥቂት ምሳሌዎች ከመረመርህ በኋላ “ቃልህ እውነት ነው” ካለው መዝሙራዊ ጋር እንደምትስማማ ተስፋ እናደርጋለን። (መዝሙር 119:160) የይሖዋ ምሥክሮች መላው መጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንደሆነ ያምናሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑበትንም ምክንያት በደስታ ለሰዎች ያስረዳሉ። ተወዳዳሪ ስለሌለው ስለዚህ መጽሐፍ ለምን ከእነርሱ ጋር አትወያይም? የሚያጽናናው መልዕክቱ ደስታና ተስፋ እንዲሞላብህ ያደርጋል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ለምን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት እንዳላቸው ጠይቃችኋቸው ታውቃላችሁን?