የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ምን ያህል ትክክለኛ ነው?
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ለወጣት ጓደኛው “እውነት፤ እናገራለሁ አልዋሽም” ሲል ገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 2:7) በጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ የሚገኙት እንደዚህ ያሉት አገላለጾች ለመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ተፈታታኝ ይሆናሉ።a የጳውሎስ ደብዳቤዎች ከተጻፉ ከ1,900 ዓመታት በላይ አልፈዋል። ይህ ሁሉ ጊዜ ቢያልፍም በጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ አንድም ነጥብ ስህተት መሆኑን በተሳካ ሁኔታ ያረጋገጠ የለም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስም ስለሚጽፋቸው ነገሮች ትክክለኛነት በጣም እንደሚያስብ ገልጿል። ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚናገረውን ታሪክ ከመዘገበ በኋላ የሐዋርያት ሥራ ተብሎ የሚጠራውን መጽሐፍ ጽፏል። ሉቃስ ‘ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በጥንቃቄ ጻፍሁ’ ሲል አስፍሯል። — ሉቃስ 1:3
የትክክለኝነት ማስረጃዎች
በ19ነኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ሉቃስ እንደ አንድ ታሪክ ጸሐፊ ትክክለኛ ነገር መጻፉን ተቃውመው ነበር። ከዚህም በላይ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ያለው ታሪክ በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ አጋማሽ ላይ የተጻፈ የፈጠራ ታሪክ ነው ብለው ነበር። በቁፋሮ የጥንት ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት እንግሊዛዊው ሰር ዊልያም ሚቼል ራምሴ እንዲህ ብለው ከሚያምኑት አንዱ ነበሩ። ነገር ግን ሉቃስ የጠቀሳቸውን ስሞችና ቦታዎች ከመረመሩ በኋላ “ታሪኩ በተለያዩ ዝርዝር ሁኔታዎች አስደናቂ እውነት እንደያዘ የተገነዘብኩት ቀስ በቀስ ነበር” ሲሉ አምነዋል።
ራምሴ ከላይ ያለውን በጻፉበት ጊዜ የሉቃስን ትክክለኛነት በተመለከተ መፍትሄ ሳያገኝ የቀረ አንድ አከራካሪ ጉዳይ ነበር። ጉዳዩ ኢቆንዮን፣ ልስጥራንና ደርቤ የሚባሉትን ተጠጋግተው የሚገኙትን ከተሞች የሚመለከት ነበር። ሉቃስ ልስጥራንና ደርቤን ‘የሊቃኦንያ ከተማዎች’ በማለት ሲገልጻቸው ኢቆንዮን ግን ከእነሱ የተለየች መሆኗን ጠቅሷል። (ሥራ 14:6) ይሁን እንጂ እዚህ ላይ ያለው ካርታ እንደሚያሳየው ከደርቤ ይልቅ ልስጥራን ለኢቆንዮን ትቀርብ ነበር። አንዳንድ የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች ኢቆንዮን አንዷ የሊቃኦንያ ክፍል እንደነበረች አድርገው ገልጸው ነበር። ስለዚህ ሉቃስ እንደዚህ ብሎ ስላልገለጸ ተቺዎች ተቃወሙት።
ከዚያም በ1910 ራምሴ የኢቆንዮን ከተማ ቋንቋ የሊቃኦንያ ቋንቋ ሳይሆን የፍርግያ ቋንቋ እንደነበረ የሚያሳይ ሐውልት ከከተማዋ ፍርስራሽ ውስጥ አገኙ። ዶክተር ሚሪል ኡንገር አርኪዮሎጂ ኤንድ ዘ ኒው ቴስታመንት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “በኢቆንዮንና በአካባቢው ያሉት ሌሎች ብዙ በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎች ከተማዋ በዘርዋም ፍርግያ ተብላ ልትገለጽ እንደምትችል የሚናገረውን ሐቅ በማስረጃ አረጋግጠውታል” ይላሉ። በእርግጥ በጳውሎስ ዘመን የነበረችው ኢቆንዮን ‘የሊቃኦንያ ቋንቋ’ የሚናገሩ ሰዎች ከሚኖሩባቸው ‘የሊቃኦንያ ከተሞች’ የተለየች ነበረች። የምትከተለውም የፍርግያን ባሕል ነበር። — ሥራ 14:6, 11
በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ሉቃስ በተሰሎንቄ ከተማ የሚገኙትን ገዢዎች ለማመልከት “ፖሊታርክስ” በሚለው ቃል መጠቀሙን ተቃውመው ነበር። (ሥራ 17:6 አዓት የግርጌ ማስታወሻ) ይህ አነጋገር በግሪክኛ ሥነ ጽሑፎች ውስጥ የታወቀ አልነበረም። ከዚያም “ፖሊታርክ” የሚለውን የከተማዋን ገዢዎች ስም የያዘ አንድ ጽላት በጥንቷ ከተማ ተገኘ። ይህም በትክክል ሉቃስ የተጠቀመበት ቃል ነው። ደብልዩ ኢ ቫይን ኤክስፖዚተሪ ድክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “በዚህ ቃል በመጠቀሙ የሉቃስ ትክክለኛነት ተረጋግጧል” በማለት ይገልጻሉ።
የሉቃስ የባሕር ላይ ጉዞ
የባሕር ላይ ጉዞ ባለሙያዎች በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 27 ላይ ስለመርከብ መሰበር የተገለጸውን ዝርዝር ሁኔታ መርምረዋል። ሉቃስ በዘገበው መሠረት እሱና ጳውሎስ ይጓዙባት የነበረችው ትልቅ መርከብ በትንሿ የቄዳ ደሴት አጠገብ በሰሜናዊ ምሥራቅ በኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተያዘች። የመርከቧ ተሳፋሪዎች በአፍሪካ ሰሜናዊ የባሕር ጠረፍ ላይ ወደሚገኘው አደገኛ የአሸዋ ክምር እንወድቃለን ብለው ፈርተው ነበር። (ሥራ 27:14, 17 የግርጌ ማስታወሻ) በጥሩ የመርከበኝነት ችሎታ መርከቧን ከአፍሪካ ወደ ምዕራባዊ ጠረፍ ለማዞር ቻሉ። አውሎ ንፋሱ ጸጥ ሳይል ቀጠለ። በመጨረሻም መርከቧ ወደ 870 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ጨርሳ ማልታ ደሴት ላይ ደረሰች። የባሕር ላይ ጉዞ ባለሙያዎች አንዲት ትልቅ መርከብ በማዕበል ውስጥ ይህን ያህል ርቀት ለመሸፈን ከ13 ቀን በላይ እንደሚፈጅባት አስልተውታል። የእነሱ ስሌት በ14ኛው ቀን መርከቡ እንደተሰበረ ከሚገልጸው ሉቃስ ከዘገበው ታሪክ ጋር ይስማማል። (ሥራ 27:27, 33, 39, 41) መርከበኛው ጀምስ ስሚዝ የሉቃስን የባሕር ላይ ጉዞ ዝርዝር መግለጫዎችን ሁሉ ከመረመሩ በኋላ እንዲህ ሲሉ ደምድመዋል:- “ሉቃስ የመዘገበው ታሪክ ሁኔታዎቹ በራሱ ላይ የደረሱበት አንድ ሰው የጻፈው እውነተኛ ታሪክ ነው። . . . በእርግጥ ሁኔታው በራሱ ላይ ካልደረሰ በስተቀር አንድ መርከበኛ ያልሆነ ሰው የአንድን የባሕር ላይ ጉዞ ሁሉንም ክፍሎች እንዲህ በቅደም ተከተል ሊጽፍ አይችልም።”
እንደዚህ የመሳሰሉት ማስረጃዎች በመገኘታቸው አንዳንድ የሃይማኖት ሊቃውንት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትክክለኛ መሆናቸውን ደግፈው ለመናገር ፈቃደኞች ሆነዋል። ይሁን እንጂ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለሚገኘው ቀደም ስላለው ታሪክስ ምን ሊባል ይቻላል? ብዙ ቄሶች ለዘመናዊ ፍልስፍና በመንበርከክ ይህ ጽሑፍ አፈ ታሪኮችን እንደያዘ ይናገራሉ። ሆኖም በርከት ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ የቀድሞ ታሪክ ዝርዝር መግለጫዎች ትክክለኛነታቸው ተረጋግጧል። ይህም ተቺዎችን አሳፍሯል። ለምሳሌ ተረስቶ የነበረውን የአሦርን መንግሥት መገኘት መርምር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በተጨማሪም ሮሜ 9:1፤ 2 ቆሮንቶስ 11:31፤ ገላትያ 1:20 ተመልከት።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ፍርግያ
ሊቃኦንያ
ኢቆንዮን
ልስጥራ
ደርቤ
የሜድትራንያን ባሕር
ቆጵሮስ