የላቲን አሜሪካ ቤተ ክርስቲያን በጭንቅ ላይ ትገኛለች በሚልዮን የሚቆጠሩት አባሎቿ ትተዋት የሚወጡት ለምንድን ነው?
ከሰሜናዊው የሜክሲኮ ጠረፍ እስከ ደቡባዊው የቺሊ ጫፍ ድረስ ባሉት የላቲን አሜሪካ አገሮች የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በየአደባባዩ ያልተሠራበት ከተማ ወይም መንደር የለም። ይሁን እንጂ የካቶሊክ እንቅስቃሴን የሚያራምድ የአንድ ተቋም ዲሬክተር የሆኑት ጆሴፍ ኢ ዴቪስ “አንድ ታላቅ ለውጥ በላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ ብቅ እያለ ነው” በማለት ተናግረዋል። ጨምረውም ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ በሮማ ካቶሊክ ሃይማኖት ቁጥጥር ስር የነበረችው ላቲን አሜሪካ በአሁኑ ጊዜ ታላቅ ለውጥ ለማድረግ መቃረብዋን ገልጸዋል።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የበላይነት በፍጥነት እየተዳከመ መሄዱ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጠቅላላው የላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል 15 በመቶ የሚያክሉት ካቶሊኮች መሆናቸው ተገምቷል። የ1991 ብሪታኒካ ቡክ ኦቭ ዘ ይር:- “የሮማ ካቶሊክ አቡኖችና ጳጳሱ ራሳቸውም ጭምር ታሪካዊዋ ካቶሊካዊት ላቲን አሜሪካ ከጥንት እምነቷ በአደገኛ ሁኔታ በመለወጥ ላይ በመሆኗ የተሰማቸውን ፍርሃት ገልጸዋል” በማለት ዘግቧል። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? ብዙዎቹ የካቶሊክን ሃይማኖት እየተዉ የሚወጡት ለምንድን ነው? እነዚህ የባዘኑት ሰዎችስ ምን አጋጠማቸው?
ምክንያቱን ለማወቅ የተደረገው ጥረት
የካቶሊክ መሪዎች ለችግሩ መነሻ አድርገው የሚጠቅሱት “መናፍቆቹ” እንደ አሸን መፍላታቸውን ነው። በቦሊቭያ የሚያገለግሉ አንድ አውሮፓዊ ቄስ “ቤተ ክርስቲያኗ ዙሪያውን ባሉ አረም መሰል መናፍቃን ተመጥጦ እንደ ተዳከመ ዛፍ ሆናለች” በማለት አማርረዋል።
በአርጀንቲና ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባላትን ከ90 በመቶ ወደ 60 ወይም 70 በመቶ በቁጥር ዝቅ ሊያደርጉ የሚችሉ በየዓመቱ 140 አዳዲስ ሃይማኖቶች ሪፖርት ተደርገዋል። ቲጁዋና በሚባለው የሜክሲኮ ከተማ ከሁለት ሚልዮን ነዋሪዎች ውስጥ 10 በመቶ የሚያክሉት ወደ 327 ካቶሊክ ያልሆኑ ሃይማኖቶች ውስጥ ገብተዋል። ታይም መጽሔት:- “እሁድ እሁድ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይልቅ በፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ብዙ ብራዚላውያን መታየታቸው በጣም ያስገርማል” ሲል ሪፖርት አድርጓል። ስለዚህ በአንድ ጋዜጣ ዘገባ መሠረት “የላቲን አሜሪካ ካርዲናሎች ቤተ ክርስቲያኗ ዛሬ ስለሚያስፈልጓት ነገሮች ከጳጳሱ ጋር ለመነጋገር በቫቲካን ከተማ ውስጥ ስብሰባ ባደረጉበት ወቅት ከተወያዩባቸው ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች” አንዱ “መናፍቆች ስላስከተሉት ችግር” መሆኑ ሊያስደንቀን አይገባም።
በሜክሲኮ ከሚገኙት አቡኖች ጋር ጳጳሱ ስብሰባ ባደረጉበት ወቅት ብዙዎቹ አዳዲስ ሃይማኖቶች የተሳካላቸው “የወንጌላዊነት ሥራቸውን ባልፈጸሙት በለዘብተኞቹና በቸልተኞቹ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ምክንያት ነው” በማለት ጠቅሰዋል። ብዙዎቹ ላቲን አሜሪካውያን ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እያላቸው “የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች” የእነዚህን ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጐቶች ለማርካት ቸልተኞች የሆኑት ለምንድን ነው? ላ ፓዝ በተባለችው የቦሊቪያ ከተማ እየታተመ የሚወጣ ኡልቲማ ኦራ የተባለ አንድ ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ እንዲህ ሲል አትቷል:- “ቤተ ክርስቲያኗ መስመሯን ለቅቃ በየቀኑ ይበልጥ በዓለም ጉዳዮች ውስጥ እየተዘፈቀች ትሄዳለች። በግልጽ እንደሚታየው ቄሶች ሃይማኖታውያን ከመሆን ይልቅ ሶሺዮሎጂስቶች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ ጋዜጠኞች ወይም ፖለቲከኞች መሆናቸው ሊያስደንቀን አይገባም።”
ሰባኪዎች ከመሆን ይልቅ ፖለቲከኞች?
ብዙዎቹ የላቲን አሜሪካ አገር ሰዎች ለካቶሊክ ሃይማኖት ጥላቻ እንዲያሳድሩ አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች መካከል አንዱ ቤተ ክርስቲያኗ በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ ዓመታት በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግቧቷ መሆኑ አያጠራጥርም። ሜሪኖል የተባለ የአሜሪካ ካቶሊኮች የውጭ አገር ሚስዮን ማኅበር በላቲን አሜሪካ ያደረጋቸውን ብዙ ተልዕኮዎች በተመለከተ ስለተደረገው ጥናት የሚገልጽ በ1985 የታተመ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ሜሪኖል ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀኝ እጅ ሆኖ ያገለገለ ድርጅት በመሆኑ የማርክሲስት ሌኒኒስት ደም አፋሳሽ የአብዮት መልእክት በሕዝብ ዘንድ በተሳካ ሁኔታ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጓል። መልእክቱ እያንዳንዱን ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚ ብቻ ሳይሆን ዋነኞቹን የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎችንም ጭምር ነክቷቸው ነበር።”
በ1970ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ከ10,000 እስከ 30,000 ለሚደርሱት አርጀንቲናውያን ታፍኖ መወሰድና ያለፍርድ መገደል ምክንያት የሆነውን ቆሻሻ ጦርነት እየተባለ የሚጠራውንም ጦርነት እንመልከት። ናሽናል ካቶሊክ ሪፖርተር የተባለው ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ ላይ “በደም የተበከለች ቤተ ክርስቲያን በአርጀንቲና” በሚል ርዕስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በአርጀንቲና የደረሰው ሁኔታ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በናዚ ጀርመን ካደረገችው ነገር ጋር በጣም ይመሳሰላል፤ ይህም የሚከተለውን ጥያቄ በድጋሚ ያስነሳል:- ቤተ ክርስቲያኗ በሥልጣን መጠቀምን ነው የምታስበልጠው ወይስ ለእውነት ምስክር ሁኑ የሚለውን የወንጌል ኃይል?”
ቤተ ክርስቲያኗ በዓለም መንግሥታት መካከል ሥልጣን ለማግኘት ያላት ጥማት የአምላክ ወዳጅ አለመሆኗን በግልጽ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል” ይላል። (ያዕቆብ 4:4) እንግዲያው ብዙዎች ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አመራር ለማግኘት ተስፋ ማድረጋቸውን ማቆማቸው አያስደንቅም። ይሁን እንጂ የካቶሊክን ሃይማኖት ጥለው የወጡትስ ምን አጋጠማቸው?
እረኛ የሌላቸው በጎች
እነዚህ ሰዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የአይሁድ ሃይማኖት መንፈሳዊ መሪዎች ሳይንከባከቧቸው ከቀሩት ሰዎች ጋር ይመሳሰላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው” ይላል። (ማቴዎስ 9:36) አባሎቿ የነበሩ ብዙ ሰዎች ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እየኮበለሉ ወንጌላውያን ተብለው ወደሚጠሩት ሃይማኖቶች ገብተዋል። እነዚህስ ቢሆኑ ለባዘኑት በጎች የተሻለ እንክብካቤ አድርገውላቸዋልን? ፕሮቴስታንቶችስ ኢየሱስ “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” ብሎ እንደተናገረላቸው እውነተኛ ተከታዮቹ ናቸውን? — ዮሐንስ 17:14
ካቶሊክ ያልሆኑ ብዙ ሃይማኖቶች ከሃይማኖታዊ ወግ ይልቅ ለመጽሐፍ ቅዱስ የሚታዘዙ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ። ብዙውን ጊዜ ግን ይህ ሽፋን ብቻ ነው። የፕሮቴስታንት ድርጅቶች የሚያስተምሯቸው መሠረታዊ ትምህርቶች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከምታስተምራቸው ትምህርቶች ጋር ተመሳሳይ ስለሆኑ ብዙ ተመልካቾች “ኢስ ላ ሚስማ ኮሊታ ኮኖ ትራ ፖሌራ ” (ቀሚሷን ቀየረች እንጂ ያቺው ትንሿ ሕንዳዊት ሴት ናት) የሚለውን የአንዲያን አባባል ሊጠቅሱ ይችላሉ።
ለምሳሌ ሁሉም የፕሮቴስታንት ቡድኖች አምላክ ሥላሴ ነው ብለው ያስተምራሉ ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ይህን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም። ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ሪሊጅን “ኢክዘጀትስ እና ቲኦሎጂያንስ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት እንዳልያዘ ተስማምተዋል። . . . አዲስ ኪዳንም ቢሆን ግልጽ የሆነ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት የለውም” በማለት አምኗል።a
ፕሮቴስታንቶችም የካቶሊኮችን ያህል በዚህ ዓለምና በፖለቲካ ጉዳዮችዋ የተጠላለፉ ናቸው። ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ላቲን አሜሪካ እንዲህ ይላል:- “በላቲን አሜሪካ የሚገኘው የፕሮቴስታንት ሃይማኖት . . . በሕዝባዊ ምርጫዎች በሚደረገው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ይሳተፋል። የአገሩ ተወላጆች የሆኑ ፓስተሮች ብዙ ጊዜ ለጥቅም ወደ ፖለቲካ ሰዎች ይጠጉና መንግሥት ለቤተ ክርስቲያኗ ለሚሰጣት ድጋፍ አጸፋ እንዲሆን በምርጫ ጊዜ እነሱን በመደገፍ ድምፅ ይሰጣሉ።” ላቲን አሜሪካን ሪሰርች ሪቪው የተባለው መጽሔት ሲናገር “የፕሮቴስታንት ሃይማኖት በጓቴማላ ውስጥ መሰበክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከፖለቲካው ጋር ተሳስሯል” ካለ በኋላ “ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ልማዶችን ሃይማኖታዊ መልክ ሰጥቶ በማስተላለፍ ረገድ እንደ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል” ብሏል።
ፕሮቴስታንት በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ማድረጓ ብዙውን ጊዜ በጦርነት እንድትካፈል አድርጓታል። በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ተደማጭነት አላቸው ከሚባሉት የፕሮቴስታንት ቄሶች አንዱ ሟቹ ሃሪ ኢመርሰን ፎስዲክ እንዲህ በማለት ሳይሸሽጉ ተናግረዋል:- “የምዕራቡ ዓለማችን ታሪክ በተደጋጋሚ ጦርነቶች የታወቀ ነው። ሰዎችን ለጦርነት ቀስቅሰናል፤ አሠልጥነናል፤ ጦርነትን አወድሰናል፤ የጦርነት አርበኞቻችንን አድንቀናል፤ ሌላው ቀርቶ የጦርነት ባንዲራዎችን በቤተ ክርስቲያኖቻችን ላይ አውለብልበናል። . . . በአንደኛው የአፋችን ክፍል የሰላሙን መስፍን እያሞገስን በሌላው በኩል ጦርነትን አወድሰናል።”
ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው የራእይ መጽሐፍ የሐሰት ሃይማኖትን ከምድር መንግሥታት ጋር የምታመነዝር ምሳሌያዊ ጋለሞታ አድርጎ ከገለጻት በኋላ እንዲህ ይላል:- “ሕዝቤ ሆይ፣ በወንጀሏ እንዳትካፈሉ፣ መቅሰፍቷም እንዳይደርስባችሁ ከእርሷ ዘንድ ውጡ።” — ራእይ 18:4 (ዘ ጀሩሳሌም ባይብል)
ብዙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ብዙ የተበለሻሸ ነገር እንዳለ ቢያውቁም የሮማ ካቶሊክ ጥንታዊ ታሪክ ያላት በመሆኗ ትተዋት ለመውጣት ያመነታሉ። ሆኖም የአይሁዶች የአምልኮ ሥርዓት በጣም ጥንታዊ እንደነበረ አስታውስ። ይሁን እንጂ አምላክ እውነተኛ ትምህርቱን ክደው ባመፁ ጊዜ አይሁዶችን የእርሱ ምርጥ ሕዝብ አድርጎ መመልከቱን አቆመ። አምላክ በአይሁድ ሃይማኖት ምትክ የክርስቲያን ጉባኤን እየተጠቀመበት እንዳለ ሲገነዘቡ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የአይሁድን ሃይማኖት ትተው ወጡ። በዛሬው ጊዜ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ የትኛው እንደሆነ እንዴት ለማወቅ ትችላለህ?
ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ ላቲን አሜሪካውያን የይሖዋ ምስክሮች ሆነዋል። ይህንን ለውጥ ያደረጉት ለምንድን ነው? በሜክሲኮ ውስጥ በማርቴኔዝ ዴ ላ ቶሬ ቬራክሩዝ የሚታተም አንድ ጋዜጣ ይህን ጥያቄ መርምሮ ነበር። “እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሃይማኖት ወደ ፖለቲካ ማመዘኑንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ልማዶችን ይኸውም ሃይማኖትን እንደ መቀላቀል፣ የሥነ ምግባር ብልሹነትንና ዓመፅን መቀበሉንና መደገፉን የታዘቡ 100 በመቶ ከሌሎች ሃይማኖቶች በይበልጥም ከካቶሊክ የመጡ ሰዎች ናቸው ለማለት ይቻላል። ምንነቱ ካልታወቀ ምንጭ የመጣውን ጣዖት አምልኮ ወይም ባሕል ከመቀበል ይልቅ ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራቱ እርካታን አስገኝቶላቸዋል። እንዲህ ያለው አቋማቸው በየትኛውም ቦታ ቢኖሩ ተለይተው እንዲታወቁ የሚያደርጋቸውን የሚያስመሰግን የእምነት አንድነት ሰጥቷቸዋል” ብሏል።
ሌላው የላቲን አሜሪካ ጋዜጣ ሁኔታውን በዚህ መልኩ ገልጾታል:- “የይሖዋ ምስክሮች ታታሪ፣ ሐቀኛና አምላክን የሚፈሩ ሕዝቦች ናቸው። ወግ አጥባቂና ባሕል ወዳድ ሰዎች ናቸው፤ ሃይማኖታቸውም የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ ነው።” በምትኖርበት በማንኛውም ቦታ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና እንጋብዝሃለን። ተስፋቸውና አኗኗራቸው ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ትረዳለህ። አዎን፣ አምላክን “በመንፈስና በእውነት” እንዴት ልታመልከው እንደምትችል ትማራለህ። — ዮሐንስ 4:23, 24
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በሥላሴ ማመን ይኖርብሃልን? የተባለውን በኒው ዮርኩ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር የታተመውን ቡክሌት ተመልከት።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ግራፍ]
በአንዳንድ የላቲን አሜሪካ አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች ብዛት
1971 1992
አገር የአስፋፊዎች ብዛት የአስፋፊዎች ብዛት
አርጀንቲና 20,750 96,780
ቦሊቪያ 1,276 8,868
ብራዚል 72,269 335,039
ቺሊ 8,231 44,067
ኮሎምቢያ 8,275 55,215
ኮስታ ሪካ 3,271 14,018
ዶሜኒካን ሪፑብሊክ 4,106 15,418
ኢኳዶር 3,323 22,763
ኤል ሳልቫዶር 2,181 20,374
ጓዴሎፕ 1,705 6,830
ጓቴማላ 2,604 13,479
ሆንዱራስ 1,432 6,583
ሜክሲኮ 54,384 354,023
ፓናማ 2,013 7,732
ፓራጓይ 901 4,115
ፔሩ 5,384 43,429
ፖርቶ ሪኮ 8,511 25,315
ኡራጓይ 3,370 8,683
ቬኔዙዌላ 8,170 60,444
ጠቅላላ ድምር 212,156 1,143,175