በሮማንያ ይሖዋ ጊዜያትንና ዘመናትን ለወጠ
በ1989 ምሥራቅ አውሮፓን የለውጥ ማዕበል አጥለቀለቃት። የ ማይበገሩ ምሽጎች መስለው የቆሙት መንግሥታት በጥቂት ወራት ውስጥ እንደ እንቧይ ካብ ተናዱ። ከፖለቲካዊው ለውጥ ጋር ተያይዞ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ከሁሉም በላይ ደግሞ ለይሖዋ ምስክሮች ትልቅ ትርጉም ያለው ሃይማኖታዊ ለውጥ መጣ። በየአገሩ የይሖዋ ምስክሮች ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴያቸውን በነፃነት ማካሄድ የሚችሉበት ሕጋዊ እውቅና ተመልሶ ተሰጣቸው።
ይሁን እንጂ በሮማንያ የነበረው ሁኔታ ለየት ያለ ይመስል ነበር። በወቅቱ የነበረው መንግሥት ሕዝቡን ጨምድዶ ይዞት ስለነበረ የለውጡ ማዕበል እምብዛም የሚነካው አይመስልም ነበር። በዚህች አገር የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች በሌሎቹ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች እየተከናወነ ያለውን ነገር ሲሰሙ:- ‘ከአርማጌዶን በፊት የአምልኮ ነፃነት አግኝተን መደሰት እንችል ይሆንን?’ እያሉ ራሳቸውን ይጠይቁ ነበር። ከመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው ጋር በትልልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገናኙበትን፣ የምሥራቹን በይፋ የሚሰብኩበትንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻቸውን መደበቅ ሳያስፈልጋቸው በግልጽ ይዘው የሚያጠኑበትን ጊዜ ልባቸው ይናፍቅ ነበር። እነዚህ ነገሮች ይፈጸማሉ ብሎ ማሰቡ ሕልም ይመስል ነበር።
ከዚህ በኋላ ሕልሙ እውን ሆነ! ይህም በታኅሳስ 1989 ተፈጸመ። ሁሉንም ሰው በሚያስገርም መንገድ የቻዎቼስኮ አገዛዝ በአንድ ጀንበር ወደ ቀ። እነዚህ ክርስቲያኖች ሳያስ ቡት ትልቅ እፎይታ አገኙ። ሚያዝያ 9, 1990 የይሖዋ ምስክሮች እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት ሆነው በሮማንያ ሕጋዊ እውቅና አገኙ። ይሖዋ በዚያ ለሚገኙት 17,000 የይሖዋ ምስክሮች ጊዜያትንና ዘመናትን ለውጦላቸዋል። — ከዳንኤል 2:21 ጋር አወዳድር።
ረዘም ያለ ታሪክ
በ1911 ካሮል ሳቦ እና ጆሲፍ ኪስ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከተማሩበትና ፈቃዱን ለማድረግ ራሳቸውን ለይሖዋ ከወሰኑበት ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሮማንያ ተመለሱ። የተመለሱትም የምሥራቹን ለአገራቸው ሰዎች ለማካፈል ስለፈለጉ ነበር። ሮማንያ እንደደረሱም መስበክ ጀመሩ። አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲጀምር ይሠሩት በነበረው ሥራ ምክንያት ታሰሩ። እነሱ የዘሯቸው የመንግሥቱ ዘሮች ግን ውጤት ማስገኘት ጀምረው ነበር። ሥራው በ1920 እንደገና ሲደራጅ በሮማንያ 1,800 የሚያህሉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ነበሩ።
በዚያን ጊዜ በቦልካን አገሮች የተቀጣጠለው የአብዮት መንፈስ በሮማንያም እያደር ተዛመተ፤ ረብሻዎችም እየጨመሩ መጡ። በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ሁሉ መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ሥራቸውን ቀጥለው ነበር። በ1924 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በሮማንያ፣ በሀንጋሪ፣ በቡልጋሪያ፣ በዩጎዝላቪያና በአልባንያ ያለውን ሥራ የሚከታተል በሉጅናፖካ ከተማ 26 ሪጂና ማሪያ ስትሪት አካባቢ ቢሮ ከፈተ።
የፖለቲካው ውጥረት እየጨመረ ሲሄድ ከባለ ሥልጣኖች ከሚመጣው ችግር ሌላ በድርጅቱ ውስጥም ችግር ነበር። የ1930 የዓመት መጽሐፍ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “ማኅበሩ ወደዚያ የላከው ሰው ታማኝ ሳይሆን በመቅረቱ ወዳጆቻችን ተበታትነዋል፤ ትምክህታቸውም ተናግቷል። ማኅበሩ እዚያ ያለው ሥራ እንዲያንሰራራ ለማድረግ እየሞከረ ቢሆንም የአገሩ ባለ ሥልጣኖች ሁሉንም ነገር አግደውታል፤ ስለሆነም ጌታ የተሻለ መንገድ እስከሚከፍት ድረስ መጠበቅ ይኖርብናል።” ከዚያም በ1922 የተጠመቀ ማርቲን ማጄሮሽ የተባለ ሮማንያዊ የይሖዋ ምስክር በ1930 አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ ሆኖ ተሾመ፤ ከጊዜ በኋላ የማኅበሩ ቢሮ ወደ ቡካሬስት ከተማ 33 ክሪሻና ስትሪት ተዛወረ። ከብዙ ትግል በኋላ በ1933 ማኅበሩ ሕጋዊ ድርጅት ሆኖ በሮማንያ ውስጥ ተመዘገበ።
ችግሮቹ ቀጠሉ
በሮማንያ በሚገኙት ምስክሮች ላይ ከባድ መከራዎች መምጣታቸውን ቀጠሉ። የ1936 የዓመት መጽሐፍ እንዲህ ሲል ሪፖርት እድርጓል:- “በሩማንያ ውስጥ ካሉት ወንድሞች የበለጠ ችግሮችን እየተቋቋመ ሥራውን የሚሠራ በምድር ላይ የለም።” ይህ ሁሉ መከራ እየደረሰባቸው የ1937 የአገልግሎት ሪፖርት በሩማንያ ውስጥ 75 ጉባኤዎችና 856 አስፋፊዎች መኖራቸውን ጠቅሶ ነበር። በመታሰቢያው በዓል ላይ ደግሞ 2,608 ሰዎች ተገኝተው ነበር።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ሮማንያን ሳይነካት አላለፈም። በመስከረም 1940 ጄኔራል ዮን አንቶኔስኮ የመንግሥት ሥልጣን ያዘና ከሂትለር ጋር ተመሳሳይ የሆነ አገዛዝ ጀመረ። ሽብር የዕለት ተዕለት ኑሮ ገጽታ ሆኖ ነበር። በመቶ የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን ታሰሩ፣ ተደበደቡ እንዲሁም ተሠቃዩ። ወንድም ማጄሮሽ በመስከረም 1942 ታሰረ፤ ይሁን እንጂ እስር ቤት ውስጥም ሆኖ በትራንሲልቫንያ ያለውን ሥራ ማስተባበር ችሎ ነበር።
የሂትለር ወታደሮች በ1944 አገሪቱን ከወረሩም በኋላ ስደቱ ቀጠለ። ከቡካሬስት የመጣ ሪፖርት በናዚ አገዛዝ ሥር የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር:- “በዚህ አገር የምንኖር የይሖዋ ምስክሮች አስከፊ ስደት ደርሶብናል። ከኮሙኒስቶች ጋር አብረን ታስረን ነበር፤ በተለይም የሂትለር ደጋፊ የሆኑት ቄሶች ከኮሙኒስቶች የባሱ ናቸው ብለው ይከሱን ስለነበረ ብዙዎቻችን የ25 ዓመት እሥራት፣ የዕድሜ ልክ እሥራት ወይም ሞት ይፈረድብን ነበር።”
በመጨረሻም ጦርነቱ አበቃና ሰኔ 1, 1945 በቡካሬስት የሚገኘው የማኅበሩ ቢሮ ሥራውን እንደገና ጀመረ። ወረቀት የማግኘት ችግር ቢኖርም ወንድሞች ተግተው በመሥራታቸው ከ860,000 በላይ ቡክሌቶችንና ከ85,000 ቅጂዎች የሚበልጡ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችን በሮማንያና በሀንጋሪ ቋንቋዎች አትመው አወጡ። ይሖዋ ጥረታቸውን ባርኮላቸዋል። በ1946 ወደ 1,630 የሚጠጉ አዲሶች ተጠመቁ። የዚያ ዓመት ጐላ ያለ ገጽታ መስከረም 28 እና 29 በቡካሬስት የተደረገው ትልቅ ስብሰባ ነበር። ቄሶች ይህንን ስብሰባ ለማደናቀፍና ለማስቆም የሚችሉትን ያህል ሞክረው ነበር፤ ነገር ግን ሳይሳካላቸው ቀርቶ 15,000 የሚያክሉ ሰዎች የሕዝብ ንግግሩን አዳመጡ። የሮማንያ ወንድሞች እንደዚህ ያለ ትልቅ ስብሰባ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነበር።
ማኅበሩ ወንድም አልፍረድ ሩቲማንን ከስዊዘርላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ወደ ሮማንያ ላከው። እሱም በነሐሴ ወር 1947 በ16 የተለያዩ ቦታዎች ከ4,500 ለሚበልጡ ወንድሞች ወደፊት ስለሚጠብቃቸው ጊዜ የሚያንጽ ንግግር ለማድረግ ቻለ። ብዙም ሳይቆይ በምስክሮቹ ላይ እንደገና ተጽእኖ መምጣት ጀመረ። በዚህ ጊዜ ተጽእኖው የመጣው ከኮሙኒስቱ አገዛዝ ነበር። በየካቲት 1948 ባለ ሥልጣኖች የሕትመትና የስብከት እንቅስቃሴያችንን አገዱት። ከዚያም ነሐሴ 1949 በ38 አሊዮን ስትሪት የሚገኘው የማኅበሩ ቢሮ በድንገት ተከበበ። የኋላ ኋላ ወንድም ማጄሮሽን ጨምሮ ብዙ ወንድሞች ታሰሩ። በዚህ ጊዜ የተከሰሱት ኢምፔሪያሊስቶች ናችሁ ተብለው ስለነበረ ከባድ ሥራ እየሠሩ ወደሚቀጡባቸው ቦታዎች ወይም እሥር ቤቶች ተወሰዱ። በተከታዮቹ 40 ዓመታት ሥራው እንደ ታገደ ቆየ፤ የይሖዋ ምስክሮችም ከባድ መከራ ደረሰባቸው። ጠላት በድርጅቱ ውስጥ እንዲፈጠሩ ያደረጋቸው ችግሮች ጭንቀቱን አባባሱት። በመጨረሻም የቻዎቼስኮ አገዛዝ በ1989 ተገለበጠ፤ እነርሱም ነፃ ወጡ! ታዲያ አሁን ባገኙት ነፃነት ምን ያደርጉበት ይሆን?
እንደገና በይፋ መስበክ
ምስክሮቹ ምንም ጊዜ አላባከኑም። ወዲያውኑ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክ ጀመሩ። ይሁን እንጂ ለብዙ ዓመታት ተደብቀው መደበኛ ባልሆነ መንገድ በድፍረት ሲሰብኩ ለቆዩት ለብዙዎቹ ይህ ሥራ ቀላል አልነበረም። በይፋ መስበክ እንደሚችሉ ሲያውቁ ፍርሃት ተሰማቸው። አብዛኛዎቹ ይህን ሥራ ከዚህ በፊት ሠርተውት አያውቁም። ለመጨረሻ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የሰበኩ ቢኖሩም ይህን ያደረጉት በ1940ዎቹ መጨረሻ ላይ ነበር። ምን ዓይነት ውጤት እያገኙ ይሆን? እስቲ እንመልከት።
ጥሩ መነሻ ልትሆነን የምትችለው 2.5 ሚልዮን ነዋሪዎች ያሉባት ዋና ከተማዋ ቡካሬስት ናት። ከሁለት ዓመታት በፊት በከተማይቱ ውስጥ አራት ጉባኤዎች ብቻ ነበሩ። አሁን ግን አሥር ጉባኤዎች ሲኖሩ በ1992 በተከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ ከ2,100 በላይ ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። ዕድገት የሚያሳዩ ብዙ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እየተመሩ ስለሆነ በቅርቡ ብዙ አዳዲስ ጉባኤዎች ሊመሠረቱ ይችላሉ።
በአገሪቱ ደቡባዊ ምዕራብ የምትገኘው የክሬዮቭ ከተማ 300,000 የሚያክሉ ነዋሪዎች አሏት። እስከ 1990 ድረስ በከተማዋ ውስጥ ይገኙ የነበሩት 80 የሚያክሉ ምስክሮች ብቻ ነበሩ። ከዚያም የአቅኚነት መንፈስ ተቀጣጠለና ሥራው በጣም ተስፋፋ። በ1992 ብቻ 74 ሰዎች ሲጠመቁ ከ150 በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም ተመርተዋል። ከ200 በላይ የሆኑት አስፋፊዎች በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት አዳራሽ መሥሪያ የሚሆን ተስማሚ ቦታ ለማግኘት እየፈለጉ ነው።
በቲርጉ ሙረስ አንዲት እኅትና ሁለት ወንድሞች የእኅት ስም ከቤተ ክርስቲያኑ መዝገብ ላይ እንዲሰረዝ ለመጠየቅ ወደ አንድ የኦርቶዶክስ ቄስ ሄዱ። ቄሱ የመጡበትን ጉዳይ ከተረዱ በኋላ ወደ ቤት ውስጥ እንዲገቡ ጋበዟቸውና ጥሩ ውይይት አደረጉ። ከዚያም ቄሱ እንዲህ አሉ:- “ታስቀኑኛላችሁ፣ በመጥፎ መንገድ ግን አይደለም። እናንተ የምትሠሩትን ሥራ መሥራት የነበረብን እኛ ነን። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መተኛቷ ያሳዝናል!” በሥላሴ ማመን ይኖርብሃልን? የተባለውን ብሮሹርና አንድ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂ ተቀበሉ። እህት ከእንግዲህ ወዲያ የተኛችው ቤተ ክርስቲያን አባል ባለመሆኗ ደስተኛ ናት። — ራእይ 18:4
በአሁኑ ጊዜ እውነትን ከሚያጠኑት መካከል የሚበልጡት ወጣቶች መሆናቸው አያስገርምም። ለምን? ምክንያቱም የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ ብዙ ነገር ተስፋ አድርገው የነበረ ይመስላል፤ ነገር ግን እንዳሰቡት ሳይሆን ቀረ። ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ የምታመጣው የይሖዋ መንግሥት ብቻ መሆኗን በማወቃቸው ተደስተዋል። — መዝሙር 146:3–5
በትንንሽ ቦታዎች እየተከናወኑ ያሉ ትልልቅ ነገሮች
ኦኮሌሽ በሰሜናዊ ሮማንያ የምትገኝ ትንሽ መንደር ነች። በ1920 ፒንታ ሞይዝ የተባለ ሰው የጦር ምርኮኛ ሆኖ ተወስዶ ከነበረበት ከሩስያ የጦር ግንባር ተመልሶ መጣ። ቀደም ሲል ካቶሊክ ነበረ፤ ወደ አገሩ ከመመለሱ በፊት ግን ባብቲስት ሆነ። ከሦስት ሳምንታት በኋላ በዚያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል ይታወቁ የነበሩት የይሖዋ ምስክሮች አነጋገሩት። ከውይይቱ በኋላ “አሁን ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውነት አግኝቻለሁ!” ብሎ ተናገረ። በ1924 በኦኮሌሽ 35 ሰዎች ያሉበት አንድ ቡድን ነበረ።
ዛሬ 473 ከሆኑት የመንደሩ ነዋሪዎች ውስጥ 170ዎቹ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ናቸው። እያንዳንዱ አስፋፊ እንደ አገልግሎት ክልሉ ተደርገው የተመደቡለት ሁለት ሁለት ቤቶች ይደርሱታል፤ በተጨማሪም በአካባቢው ባሉ መንደሮች ያገለግላሉ። አሁንም ቢሆን ወንድሞች ብሩህ አመለካከት አላቸው። 400 ሰዎችን ማስቀመጥ የሚችል ደስ የሚል አንድ የመንግሥት አዳራሽ ሠርተዋል። አዳራሹ የተሠራው በአካባቢው ባሉት የይሖዋ ምስክሮች ነው።
ቫሌያ ላርጋ የተባለችው ከተማ ወንድም ሳቦ እና ወንድም ኪስ በ1914 የነበሩባት ቦታ ነች። በ1991 በ3,700 ነዋሪዎቿ መካከል የሚገኙ ስምንት ጉባኤዎችና 582 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ነበሩ። በ1992 የመታሰቢያው በዓል ላይ 1,082 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። ይህም በዚህ ሸለቋማ ቦታ ከሚኖሩት ከ 3 ሰዎች መካከል አንዱ ተገኝቶ ነበር ማለት ነው።
ልዩ አቅኚዎች መንገዱን ጠረጉ
ልዩ አቅኚዎች ምሥራቹን ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች በማድረስ በኩል ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታሉ። የመስበኩ ነፃነት እንደተገኘ ዮኔል አልባን የተባለ ወንድም በሁለት ከተማዎች መሥራት ጀመረ። ከሳምንቱ ውስጥ ሁለቱን ቀን ኦርሾቫ አምስቱን ቀን ደግሞ ቱርኑ ሰቨርን ውስጥ ያገለግላል።
ዮኔል ወደ ኦርሾቫ ሲሄድ በከተማው ውስጥ አንድም የይሖዋ ምስክር አልነበረም። በመጀመሪያው ሳምንት ከአንድ የ14 ዓመት ልጅ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረ። ልጁ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ስላደረገ ጓደኛውና አንድ ሌላ ጐረቤቱ ማጥናት ጀመሩ። ካቶሊክ የነበረው ጐረቤቱ ሮላንድ የሚያስገርም ዕድገት አሳየ። በአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ከዮኔል ጋር በስብከቱ ሥራ ተሰማራ፤ በአምስተኛው ወር ተጠመቀ። ወዲያውኑ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረ። እናቱም ማጥናት ጀምረችና በ1992 በተደረገው የ“ብርሃን አብሪዎች” የወረዳ ስብሰባ ላይ ተጠመቀች። አሁን በኦርሾቫ ውስጥ አሥር አስፋፊዎች ሲኖሩ 30 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመራሉ።
በቱርኑ ሰቨርን እውነትን ለመቀበል የመጀመሪያ የሆነው ዮኔል ባረፈበት ሆቴል ውስጥ በእንግዳ ተቀባይነት ተቀጥሮ የሚሠራ ሰው ነው። ከሁለት ወር በኋላ ሰውየው ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆነ። በሦስት ወር ጊዜ ውስጥም ተጠመቀ። ዛሬ 84 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ከሚመሩት 32 አስፋፊዎች መካከል አንዱ ነው።
ገብርኤላ ጃካ የተባለች ሌላ ልዩ አቅኚ ሥራችን ታግዶ በነበረበት ጊዜም የዘወትር አቅኚ ሆና ታገለግል ነበር። የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውራ ለማገልገል ትመኝ ነበር። ሰፊ የአገልግሎት ክልል ተመደበላት። አንዳንድ ጊዜ ከ100 እስከ 160 የሚደርስ ኪሎ ሜትር እየተጓዘች ፍላጐት ያሳዩ ሰዎችን ታነጋግራለች። ካገለገለችባቸው ቦታዎች አንዱ አራት ምስክሮች ብቻ የነበሩበት ሞትሩ የሚባል ከተማ ነው። ያጋጠማትን ነገር ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “በሞትሩ ከተማ የምናደርገው እንቅስቃሴ እየጨመረ ስለሄደ ቄሶችና ሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች እኛን መቃወም ጀመሩ። ቤቱን ባከራዩኝ ቤተሰቦች ላይ ተጽእኖ እንዲያሳድሩ የከተማውን ከንቲባና ፖሊሶች አግባቧቸው። ከዚያም ስላስወጡኝ በየወሩ የማርፍበት ቤት መፈለግ ነበረብኝ።”
ገብርኤላ በኦርሾቫ ውስጥ በአምላክ መኖር ለማታምን አንዲት ሴት ጥናት ጀመረችላት። ሴትየዋ ስለ ሃይማኖትም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ፍላጎት አልነበራትም። ይሁን እንጂ ከአራት ወር ጥናት በኋላ ሴትየዋ መጽሐፍ ቅዱስን ደግፋ መናገር ጀመረች። ምንም እንኳ ባልዋ በሌሊት አስወጥቶ ቢዘጋባትምና እፈታሻለሁ ወይም እገድልሻለሁ እያለ ቢያስፈራራትም ፍጹም አቋሟን ጠብቃለች። ከመጠመቋ በፊትም እንኳ አሥር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ትመራ ነበር።
ግሩም ተስፋዎች ይጠብቋቸዋል
በነሐሴ 1992 ሮማንያ 286 ጉባኤዎችና 24,752 የደረሰ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ላይ ደርሳለች። የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ደግሞ ከ66,000 በላይ ነበሩ። በቡካሬስት በሚገኘው አነስተኛ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ያሉት 17 ሠራተኞች የወንድሞቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጐት ለማሟላት የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው። በቅርቡ ትልቅ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ መሥራት የሚጀምሩበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቁ ነው።
በሮማንያ የሚገኙት የይሖዋ ምስክሮች ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በተገኙት ፈጣን ለውጦችና ዕድገቶች በጣም ተገርመዋል። በስሙ የተጠራውና ስለ እርሱና ስለማይለወጠው ዓላማው ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ሰዎችን የሚመራው ዓለም አቀፍ ጉባኤ አካል እንዲሆኑ ለሰጣቸው መብት ይሖዋ አምላክን ያመሰግኑታል። በእርግጥም ከብዙ ዓመታት መከራና ስደት በኋላ በሮማንያ ውስጥ ጊዜያትንና ዘመናትን ስለ ለወጠላቸው ይሖዋን ምን ያህል ያመሰግኑታል!
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሀንጋሪ
ሮማንያ
ቡካሬስት
ሉጅ ናፖካ
ክሬዮቭ
ቲርጉ ሙረስ
ኦርሾቫ
ቱርኑ ስቨርን
ሞትሩ
ቱርዳ
ቡልጋሪያ
[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኙ ፎቶዎች]
1. በ1947 በጫካ ውስጥ 700 የሚያህሉ ምስክሮች ተሰብስበው ነበር
2. በ1946 ለተሰጠው የሕዝብ ንግግር የተዘጋጀ የመጋበዣ ወረቀት
3. በቅርቡ በሮማንያ የተደረገ ትልቅ ስብሰባ]
4. በዛሬው ጊዜ በሉጅ ናፖካ ውስጥ ምስክርነቱ ሲሰጥ
5. በቱርዳ አጠገብ የሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ
6. በቡካሬስት የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ