‘አንዷ ቅጠል ወረቀት ጨለማውን የኮከብ ብርሃን ልትፈነጥቅበት ትችላለች’
ዛሬ የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በሁሉም ዘንድ ይገኛል ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተደረገው ትግል የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነበር።
ፊፍቲንዝ ሴንቸሪ ባይብልስ በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ዌንደል ፕራይም እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል፦ “የማተሚያ ቴክኖሎጂ ከተፈለሰፈ ከ30 ዓመታት በኋላ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መናፍቃን ብላ የምትጠራቸውን ለመደምሰስ የተጀመረው ኢንኩዚሽን የተባለው እርምጃ በስፔይን ውስጥ ሙሉ በሙሉ በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ ነበር። በዚያች አገር በዚህ መንገድ ከተቀጡት 342,000 ሰዎች መካከል 32,000 ሰዎች በቁማቸው በእሳት ተቃጥለዋል። ወደ ሰማዕትነት ነበልባል ያመጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ መያዛቸውና ማንበባቸው ነበር። ይህ የጥፋት ተልዕኮ በኢጣልያ ሰሜናዊም ሆነ ደቡባዊ ክፍል ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ ይካሄድ ነበር። ሊቃነ ጳጳሳት በዚህ ደምሳሽ እርምጃ በመታገዝ ለመጽሐፍ ቅዱስና ለአንባቢዎቹ የሚባላ እሳት ሆነው ነበር። ኔሮ አንዳንድ ክርስቲያኖችን በጆንያ ጠቅልሎ በሙጫ በማጣበቅ የብልሹ ድርጊቱን ትዕይንት ለዓለም እንደ ብርሃን አብርተው እንዲያሳዩ በእሳት ለኩሶ እንደ ሻማ አብርቷቸዋል። በአውሮፓ ከተማዎች ውስጥ በየጎዳናው የመጽሐፍ ቅዱስ ደመራዎች ተንቦገቦጉ። መጽሐፍ ቅዱሶች ለድህነት ሊዳረጉ፣ ልብሳቸውን ሊገፈፉ፣ ሊገረፉ፣ አካላቸውን ሊቆረጡና ሊገለሉ እንደሚችሉት አንባቢዎቻቸው አልነበሩም። ከእሳት ልትተርፍ የቻለችው አንዷ ቅጠል ወረቀት እንኳን ይህን ጨለማ እንደ ኮከብ ብርሃኗን ልትፈነጥቅበት ትችላለች።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን)
የመጽሐፍ ደራሲ ፕራይም ከላይ የገለጹት ነገር እዚህ በምታዩት የመጽሐፍ ቅዱስ ገጽ ላይ ተፈጽሟል። ይህ የተርጓሚው ማንነት የተገለጸበት የመጽሐፉ የመደምደሚያ ገጽ ነው። ከላይ የሚታዩት ሁለት ትይዩ ዓምዶች የአፖካሊፕስ ወይም የራእይ መጽሐፍ የመደምደሚያ ቁጥሮች ናቸው።
ይህንን መጽሐፍ በተመለከት ዘ ካምብሪጅ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በስፔይን በ1478 በካታላን ቋንቋ የቦኒፋሲዮ ፌሬር የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ታተመ። ከ1500 በፊት በቋንቋው ይገኙ የነበሩት ቅጂዎች በሙሉ በአሳሽ ቡድኑ ታድነው ተቃጠሉ። ሆኖም አንድ ገጽ ተርፋ በሂስፓኒክ ሶሳይቲ ኦቭ አሜሪካስ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ትገኛለች። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን)
ዌንደል ፕራይም ያስተዋሉትን ሌላም ነገር ሲጠቅሱ፦ “በፍርሃት የተዋጡት ካህናት ማየት የሚፈልጉት የተቃጠሉ መጽሐፍ ቅዱሶችን እንጂ በደህና ሁኔታ የሚገኝ መጽሐፍ ቅዱስ አልነበረም። ይህ ቅዱስ እሳት የሚቃጠል ጠፍቶ እንጂ ከዚህም በበለጠ ድምቀትና ድግግሞሽ በነደደ ነበር። በብዙ ቦታዎች ዘንድ ባለ ሥልጣኖች ገና ከመጀመሪያው ምንም መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይዘጋጅ በንቃት ይከታተሉ ስለነበር ለቃጠሎ የበቃ መጽሐፍ ቅዱስ አልተገኘም ስለሆነም እነዚህ ቦታዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዳመራ አልታየባቸውም” ብለዋል። ለተራው ሕዝብ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶችን ለማጥፋት ይህንን የመሰለ የተጠናከረ ጥረት ቢደረግም ብዙ ቅጂዎች ከመቃጠል ተርፈዋል። ፕራይም በመቀጠል እንዲህ ይላሉ፦ “በጭንቀትና በአደጋ ወቅት መጽሐፍ ቅዱሶች ከመቃጠል ሊተርፉ የቻሉት ስደተኞች ይዘዋቸው ወደሌላ አገር በመሄዳቸው ወይም ልክ እንደ ክቡር ድንጋይና ማዕድን መሬት ውስጥ ቆፍረው ስለደበቋቸው ነው።”
የአምላክ ነቢይ የነበረው ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፣ . . . ሣሩ ይደርቃል አበባው ይረግፋል፣ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።” (ኢሳይያስ 40:6, 8) ባለፉት መቶ ዘመናት ብዙ መጽሐፍ ቅዱስ ወዳዶችና ደፋር ተርጓሚዎች ለአምላክ ቃል ሲሉ ሕይወታቸውን በከፍተኛ አደጋ ላይ ጥለዋል እንዲሁም ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል። ይሁንና የሰዎች ጥረት ብቻውን ለመጽሐፍ ቅዱስ መትረፍ አስተማመኛ አይሆንም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ለመትረፍ በመቻሉ የመጽሐፉ ጸሐፊ የሆነውን ይሖዋን እናመሰግናለን።
[ምንጭ]
Courtesy of The Hispanic Society of America, New York