የጎቲክ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፤ ድንቅ የሥራ ውጤት
የጎት ጎሳዎች በኮንፌዴሬሽን የተደራጁ የጀርመን ጎሳዎች ሲሆኑ፤ ምንጫቸው ምናልባት ከስካንዲኔቪያን አገሮች ሳይሆን አይቀርም። እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት የሮማ ግዛት ድንበር መጨረሻ እስከነበሩት በደቡብ እስከ ጥቁር ባህር እና እስከ ዳንዩብ ወንዝ ድረስ ፈልሰው ነበር።
በጀርመን ጎሳዎች ይነገሩ ከነበሩት ቋንቋዎች ሁሉ በጎት ቋንቋ የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የመጀመሪያው የሥነ ጽሑፍ ሥራ ነበር። ዛሬ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የሚገኘው በቁርጥራጭ መልክ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ልዩና ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሆኖ ቆይቷል። ለምን?
አልፌላስ፤ ሚስዮናዊና የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ
የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ አልፌላስ ወይም በጎቲክ ቋንቋ በሚታወቅበት ስሙ ውልፌላስ ነው። እንደ ታሪክ ጸሐፊው ፊሎስቶሪጊየስ አባባል ከሆነ አልፌላስ የጎት ጎሳዎች ካፓዶቅያን ከወረሩ በኋላ ተማርከው የተወሰዱት ጎሳዎች ዝርያ ነው። (ዛሬ ካፓዶቅያ ምሥራቃዊ የቱርክ ግዛት ነው።) በ311 እዘአ የተወለደው አልፌላስ ከ30 ዓመታት በኋላ በኒቆሜዲያው ዩሴቢየስ ለቤተ ክርስቲያን በአገልጋይነት ተሾሞ በጎት ጎሳዎች መካከል በሚስዮናዊነት እንዲያገለግል ሰልጥኖ ነበር።
“አዲስ አማኞችን ለማስተማርና ቁጥራቸውን ለማብዛት ሲል” ይላሉ ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት “ከነገሥት መጽሐፍ በስተቀር ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከግሪክ ወደ ጎቲክ ቋንቋ በትዕግስት ተርጉሟል።” (ዘ ኤጅ ኦቭ ፌዝ ) ዛሬ ከነህምያ መጽሐፍ ቁርጥራጮች ሌላ በጎቲክ ቋንቋ የሚገኙት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆኑት ጥቂት የብራና ጽሑፎች ብቻ ናቸው።
የጎቲክ ቋንቋ ፊደል ያለው ቋንቋ አልነበረም። ስለሆነም አልፌላስ ይህንን ለመተርጎም ለየት ያለ ጥበብ የሚጠይቅ ፈታኝ የትርጉም ሥራ አጋጥሞት ነበር ማለት ነው። ጥንታዊያን ሃይማኖታዊ ታሪክ ጸሐፊዎች በግሪክና በላቲን ፊደል ላይ የተመሠረቱ የጎቲክ ፊደላት የሆኑት 27 ምልክቶች በመጀመሪያ ያመነጨው እርሱ እንደሆነ ይናገሩለታል። ከዚህም በላይ ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚለው ከሆነ “እስከ አሁንም ድረስ በጀርመን ቋንቋ የሚሠራባቸውን የክርስቲያን ሃይማኖታዊ ቃላት ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጠረው እርሱ ነው።”
የጎቲክ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጥንታዊ ታሪክ
አልፌላስ ትርጉሙን በ381 እዘአ ጨረሰና ከሁለት ወይም ከሦስት ዓመታት በኋላ ሞተ። የትርጉም ሥራው በሕዝብ ዘንድ ያገኘው ተወዳጅነት እንደሚከተለው በማለት በተናገረለት ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካናም ተረጋግጧል፦ “ትርጉሙ ወደ ስፔይንና ጣልያን የፈለሱት የጎት ተወላጆች ሁሉ ይጠቀሙበት ነበር።” እንዲያውም አሁን ከተረፉት በርካታ ቁርጥራጮች አንጻር ሲታይ ብዙ የጎቲክ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ቅጂዎች የነበሩ ይመስላል። የጎት ጎሳዎች መንግሥታቸውን መሥርተው በነበረበት በራቬናና በቬሮና አካባቢዎች ባሉት ስክሪፕቶሪያ ውስጥ ሦስትና አራት ያህል የብራና ጽሑፎች ሳይዘጋጁ አልቀሩም። ስክሪፕቶሪያ በገዳማት ውስጥ የመጻፍና የመገልበጥ ሥራ የሚካሄድባቸው ክፍሎች ነበሩ።
የባይዛንታይን ንጉሠ ነገሥት ጁስቲኒያን ቀዳማዊ እንደገና ጣልያንን ድል ሲያደርግ የጎት ጎሳዎች የራሳቸው አገር ያላቸው ሕዝብ መሆናቸው በ555 እዘአ አበቃ። “ይህ ጥፋት ከደረሰባቸው በኋላ” ይላል ቶነስ ክላበርግ “የጎቲክ ቋንቋና ባሕል ከጣልያን ምድር ጠፉ። በጎቲክ ቋንቋ የተዘጋጁ የብራና ጽሑፎች ከዚያ ወዲያ ተፈላጊነታቸው ቀረ . . . አብዛኛዎቹ ተወስደው ጽሑፉን ለማጥፋት ተፍቀዋል። ከዚያም ውድ የነበረው ብራና እንደገና ሌላ አዲስ ነገር ለመጻፍ ተሠራበት።
የተረፉት የብራና ጽሑፎች
በአንዳንዶቹ ብራናዎች ላይ የሰፈረውን ጽሑፍ ለማጥፋት የተደረገው ሙከራ የተሳካ ስላልነበረ የመጀመሪያው ጽሑፍ ፈዘዝ ብሎ ይታይ ነበር። በድጋሚ ከተጻፈባቸው ከእንደዚህ ዓይነት ጽሑፎች መካከል ሦስትና አራት የሚያክሉት ተገኝተው የመጀመሪያውን ጽሑፍ ለማወቅ ጥረት ተደርጓል። አራቱን ወንጌሎች ማለትም ማቴዎስ፣ ዮሐንስ፣ ሉቃስና ማርቆስ በሚል ቅደም ተከተል ያስቀመጠውና የታወቀው የአርጀንተስ ጥንታዊ ጽሑፍ በሚያስገርም ሁኔታ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ተገኝቷል።
ይህ በጣም ግሩም የሆነ ጥንታዊ ጽሑፍ በ6ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከራቬና ስክሪፕቶሪየም የተገኘ እንደሆነ ይገመታል። ይህ የአርጀንተስ ኮዴክስ በመባል ይታወቃል። ኮዴክስ አርጀንተስ ማለት “የብር መጽሐፍ” ማለት ሲሆን፤ ይህን ስያሜ ያገኘውም በብር ቀለም ስለተጻፈ ነው። የብራናው ገጾች በሐምራዊ ቀለም የቀለሙ ነበሩ። ይህም ለንጉሣዊ ቤተሰቦች ታስበው የተዘጋጁ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ይጠቁማል። የእያንዳንዱን ወንጌል የመጀመሪያ ሦስት መሥመሮች እንዲሁም የተለያዩት ክፍሎች መጀመሪያዎች የተጻፉት በወርቅ ቀለም ነው። የወንጌል ጸሐፊዎቹ ስም በጽሑፉ እያንዳንዱ ረድፍ ስር ካሉት ትይዩ የቅስት በር ቅርጽ ካላቸው ዓረፍተ ነገሮች በላይ በወርቅ ተጽፎ ይገኛል። እነዚህም በወንጌል ውስጥ ተመሳሳይ ሐሳብ የሚገኝባቸውን ቦታዎች ይጠቅሳሉ።
የጎቲክ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምን ጠግኖ ወደቀድሞ ሁኔታው መመለስ
የጎት ሕዝብ ከተበታተነ በኋላ ከፍተኛ ዋጋ የነበረው የአርጀንተስ ኮዴክስ ጠፋ። ጀርመን ውስጥ በኰሎኝ አጠገብ ቬርደን በሚገኘው የመነኮሳት ገዳም ለሕዝብ ይፋ እስከሆነበት እስከ 16ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ድረስ እንደገና አልታየም ነበር።
በ1569 የጌታ ጸሎት በጎቲክ ትርጉም ላይ በሚገኝበት መልኩ ታትሞ ወጣ። ይህም ጸሎቱ የተወሰደበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የሚያስተዋውቅ ነበር። አርጀንተስ ኮዴክስ የሚለው ስም ለመጀመሪያ ጊዜ በ1597 ታትሞ ወጣ። ይህ የብራና ጽሑፍ ከዌርደን ተወስዶ ፕራግ ወደሚገኘው የንጉሡ ቅርሳ ቅርስ ማከማቻ ተቀመጠ። በ1648 የሠላሳው ዓመት ጦርነት ካበቃ በኋላ ግን አሸናፊዎቹ ስዊዲናውያን ከሌሎች ውድ ንብረቶች ጋር ይዘውት ሄዱ። ከ1669 ጀምሮ ይህ ጥንታዊ ጽሑፍ በስዊዲን የአፕሳላ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ በቋሚነት ተቀምጧል።
የአርጀንተስ ኮዴክስ በመጀመሪያ 336 ቅጠሎች የነበሩት ሲሆን ከእነዚህ መካከል 187ቱ በአፕሳላ ይገኛሉ። የመጽሐፉ ክፍል የሆነች ሌላ ቅጠል ወረቀት ይኸውም የማርቆስ መጽሐፍ መጨረሻ በጀርመን ውስጥ በስፔየር በ1970 ተገኝታለች።
ይህ ጥንታዊ ጽሑፍ እንደገና ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎች የሞተውን የጎቲክ ቋንቋ ትርጉም ለማወቅ ጽሑፉን ማጥናት ጀመሩ። በወቅቱ የሚገኙትን ሁሉንም የብራና ጽሑፎችና ጽሑፉን መልሶ ለማግኘት ሲባል ቀደም ሲል የተደረጉትን ሙከራዎች በማቀናጀት ዊልሄልም ሽትሪትበርግ በ1908 የግሪክኛውን በአንዱ ገጽ የጎቲኩን በሌላው በኩል እያደረጉ “ዴ ጎትሼ ቤበል” (የጎት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) ብለው አወጡት።
ዛሬ ይህ የጎቲክ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የሚስበው የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎችን ትኩረት ብቻ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ በተጀመረባቸው በእነዚያ የመጀመሪያ ዓመታት መዘጋጀቱና እስከ ዛሬ ተጠብቆ መቆየቱ አልፌላስ በወቅቱ ዘመናዊ በነበረው ቋንቋ የአምላክ ቃል ተተርጉሞ ለማየት የነበረውን ምኞትና ቁርጠኝነት ያረጋግጣል። የጎት ሕዝብ የክርስትናን እውነት ለመረዳት ተስፋ ሊኖራቸው የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ እንደሆነ በትክክል ተገንዝቦ ነበር።
[ምንጭ]
Courtesy of the Uppsala University Library. Sweden