የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 6/1 ገጽ 28-31
  • “ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” እንዴትና መቼ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” እንዴትና መቼ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኢየሱስ ክርስቶስ “ጌታ” ተብሎ ሲጠራ
  • የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት ለይቶ ማየት
  • የሁሉም የበላይ የሆነው ይሖዋ
  • የአምላክ ስምና “አዲስ ኪዳን”
    ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም
  • ክርስቶስን መከተል ያለብን ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ቅዱሳን ጽሑፎች “ስለ ክርስቶስ መለኮትነት” ምን ይላሉ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • አምላክን እና ክርስቶስን በተመለከተ እውነቱ ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2020
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 6/1 ገጽ 28-31

“ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” እንዴትና መቼ?

“ጌታ ጌታዬን አለው። በቀኜ ተቀመጥ ጸላቶችኽን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ።” ይህ ጥቅስ መዝሙር 110:1 ሲሆን የተወሰደው ከ1879 ትርጉም ነው። እዚህ ላይ “ጌታ” የተባለው ማን ነው? እርሱ የሚያናግረውስ ማንን ነው?

ዕብራይስጡ ይበልጥ ትክክለኛ በሆነ መንገድ ሲተረጐም ለመጀመሪያው ጥያቄ ወዲያው መልሱን እናገኛለን፦ “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ጌታዬን፦ . . . አለው።” ስለዚህ መጀመሪያ ላይ “ጌታ” ተብሎ የተጠራው ሁሉን ማድረግ የሚችለው አምላክ ይሖዋ ራሱ ነው። ምንም እንኳን የኪንግ ጀምስ ትርጉም “ጌታ” የሚለው ቃል መለኮታዊውን ስም የተካ መሆኑን ለማሳወቅ በትልልቅ ፊደላት (ካፒታል ሌተርስ) የተጠቀመ ቢሆንም (ማለትም “Lord” በማለት ፈንታ “LORD” ቢልም) እነዚህን የማዕረግ ስሞች በማምታታት ረገድ ይህ ትርጉም የመጀመሪያው አይደለም። ምክንያቱም ከዕብራይስጥ ጽሑፍ የተተረጎመው የግሪክኛው የሰፕቱጀንት ትርጉም በኋለኞቹ እትሞች ላይ ይሖዋ በሚለው ስም ፈንታ “ጌታ” (“Lord”) የሚለውን ቃል ተጠቅሟል። ለምን? ምክንያቱም አይሁዶች በአጉል እምነታቸው የተነሣ መለኮታዊውን ስም የሚወክሉትን አራቱን የቴትራግራማተን ፊደላት (יהוה) ደብቀው “ጌታ” በሚለው የማዕረግ ስም ተክተውት ስለነበረ ነው። ኤ ኢ ጋርቪ የተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ እንዲህ ብለዋል፦ “በአይሁዶች ምኩራብ ውስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በሚነበቡበት ጊዜ በቃል ኪዳኑ ስም በያህቬህ [በይሖዋ] በመጠቀም ፈንታ ጌታ [በግሪክኛ ኪሪዮስ] በሚለው የማዕረግ ስም ይጠቀሙ ስለነበረ ይህ የማዕረግ ስም ማንን እንደሚወክል በቀላሉ መግለጽ ሳይቻል አይቀርም።”

መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ‘ልዑል ጌታ’ ወይም “ሉዓላዊ ጌታ” ብሎ በመጥራት ለይቶ ይጠቅሰዋል። (ዘፍጥረት 15:2, 8፤ ሥራ 4:24 አዓት ፤ ራእይ 6:10 አዓት) በተጨማሪም ‘እውነተኛው ጌታ’ እንዲሁም ‘የምድር ሁሉ ጌታ’ ተብሎ ተጠርቷል። (ዘጸአት 23:17፤ ኢያሱ 3:13፤ ራእይ 11:4) በመዝሙር 110:1 ላይ የተጠቀሰው ሌላው “ጌታ” ታዲያ ማን ነው? ይሖዋ “ጌታ” ብሎ ሊጠራው የቻለውስ እንዴት ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ “ጌታ” ተብሎ ሲጠራ

ኢየሱስ በአራቱ ወንጌሎች ውስጥ፣ በተለይም በሉቃስና በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ በተደጋጋሚ “ጌታ” ተብሎ ተጠርቷል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይህ የማዕረግ ስም “ጌቶች” እንደሚለው አጠራር ያለ የአክብሮትና የትሕትና መግለጫ ነበር። (ዮሐንስ 12:21፤ 20:15) በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ይበልጥ ተደጋግሞ የተጠራው “መምህር” ወይም ረቡኒ ተብሎ ነው። (ማርቆስ 10:51ን ከሉቃስ 18:41 ጋር አወዳድር።) ሳውል ወደ ደማስቆ እየሄደ ሳለ “ጌታ ሆይ፣ ማን ነህ?” ብሎ መጠየቁም የተለመደ የትሕትና አጠያየቅ ነው። (ሥራ 9:5) የኢየሱስ ተከታዮች ግን የጌታቸውን ማንነት ባወቁ ጊዜ እርሱን “ጌታ ሆይ” እያሉ መጥራታቸው ለአክብሮት ያህል ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

ኢየሱስ ሞቶ ከተነሣ በኋላ፣ ግን ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ ታይቶ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” በማለት ለጊዜውም ቢሆን የሚያስገርም ነገር ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 28:18) ከዚያም በጰንጠቆስጤ ዕለት በፈሰሰላቸው መንፈስ ቅዱስ ተነሣስቶ ጴጥሮስ መዝሙር 110:1ን ጠቀሰና “እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ” አለ። (ሥራ 2:34–36) ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ በአሳፋሪ መንገድ እስከመሞት ድረስ ታማኝ ስለሆነ ከሞት እንዲነሣና ለማንም ያልተሰጠ ከፍተኛ ሽልማት እንዲሰጠው ተደርጓል። ከዚያም ወደ ሰማይ ሄደና ጌትነት ተሰጠው።

ሐዋርያው ጳውሎስ “ክርስቶስንም . . . ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና ከዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ” እንዳስቀመጠው በጻፈ ጊዜ ጴጥሮስ የተናገረው ነገር ትክክል መሆኑን አረጋግጧል። (ኤፌሶን 1:20, 21) የኢየሱስ ክርስቶስ ጌትነት ከማንኛውም ጌትነት በላይ የሆነና እስከ አዲሱ ዓለም ድረስ የሚዘልቅ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:15) “ከሁሉ በላይ” ከፍ ተደረገ፤ እንዲሁም “ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ” ሰው ሁሉ ይመሰክር ዘንድ ‘ከስም ሁሉ በላይ ያለው ስም’ ተሰጠው። (ፊልጵስዩስ 2:9–11) በዚህ መንገድ የመዝሙር 110:1 የመጀመሪያው ክፍል ፍጻሜውን አገኘና “መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም” ለኢየሱስ ጌትነት ተገዙ።—1 ጴጥሮስ 3:22፤ ዕብራውያን 8:1

በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “የጌቶች ጌታ” ይባል የነበረው ይሖዋ ብቻ ነበር። (ዘዳግም 10:17፤ መዝሙር 136:2, 3) ጴጥሮስ ግን በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት ክርስቶስ ኢየሱስ “የሁሉ ጌታ” [ወይም እንደ ጉድስፒድ የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “የሁላችን ጌታ”] መሆኑን ተናግሯል። (ሥራ 10:36) በርግጥም እርሱ “የሕያዋንና የሙታን ጌታ” ነው። (ሮሜ 14:8, 9 የ1980 ትርጉም) ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታቸው መሆኑንና የሱ ንብረት መሆናቸውን ይቀበላሉ፤ እጅግ ውድ በሆነ ደሙ የዋጃቸው ተገዢዎቹ በመሆንም በፈቃደኝነት ይታዘዙለታል። ኢየሱስ ክርስቶስ በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ በመሆን ጉባኤውን ሲገዛ ቆይቷል። አሁን ግን ከ1914 ጀምሮ ጠላቶቹ ‘የእግሩ መቀመጫ’ ተደርገውለት ንጉሥ ሆኖ የመግዛት ሥልጣን ተሰጥቶታል። ከዚያ በኋላ ‘በነሱ መካከል የሚገዛበት’ ጊዜ ደረሰ። ይህ ሁሉ የመዝሙር 110:1, 2 ፍጻሜ ነው።—ዕብራውያን 2:5–8፤ ራእይ 17:14፤ 19:16

ታዲያ ኢየሱስ ሞቶ ከመነሣቱ በፊት “ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል” ሲል የተናገረውን ቃል እንዴት ልንረዳው ይገባናል? (ማቴዎስ 11:25–27፤ ሉቃስ 10:21, 22) ይህ አባባል ከላይ ስንመለከታቸው እንደነበሩት አጠቃላይ መግለጫ አይደለም። ማቴዎስም ሆነ ሉቃስ ላይ ኢየሱስ ‘አባቱን በደንብ ስለሚያውቀው’ በዓለም ዘንድ ጠቢባን ከሆኑ ሰዎች ተሰውሮ በእርሱ በኩል ስለተገለጠው እውቀት እየተናገረ እንደነበረ ከጥቅሱ ላይና ታች ያሉ ሐሳቦች ያሳያሉ። ኢየሱስ በውኃ በተጠመቀና የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ሆኖ ከተወለደ በኋላ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት በሰማይ የነበረውን ሕይወትና እዚያ ያገኘውን እውቀት ሁሉ ለማስታወስ ችሎ ነበር። ሆኖም ይህ በኋላ ካገኘው ጌትነት የተለየ ነበር።—ዮሐንስ 3:34, 35

የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት ለይቶ ማየት

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች አንዳንድ ትርጉሞች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተወስደው የተጠቀሱ “ጌታ” በማለት ይሖዋ አምላክን በግልጽ ለማመልከት የገቡ ጥቅሶችን ሲተረጉሙ ችግር ይፈጥራሉ። ለምሳሌ ኪንግ ጀምስ ቨርሽን ወይም ዘ ኒው ጀሩሳሌም ባይብል በተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሉቃስ 4:19ን ከኢሳይያስ 61:2 ጋር አወዳድር። አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ “ጌታ” የሚለውን የማዕረግ ስም ከይሖዋ ወስዷል፤ ሥጋ የለበሰው ኢየሱስም ይሖዋ ራሱ ነው ብለው ይከራከራሉ። ሆኖም እንዲህ ብሎ መከራከር ምንም ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የተለያዩ መሆናቸውን ለመግለጽ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። ኢየሱስ የአባቱን ስም አሳውቋል፤ እንዲሁም አባቱን ይወክል ነበር።—ዮሐንስ 5:36, 37

በሚቀጥሉት ምሳሌዎች ላይ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተወስደው የተጠቀሱ ጥቅሶች በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ እንዴት እንደሰፈሩ ልብ በል። መዝሙር 2:1, 2ን በሚጠቅሰው በሥራ 4:24–27 ላይ ይሖዋ አምላክና እርሱ የቀባው ወይም መሲሑ ተጠቅሰዋል። ሮሜ 11:33, 34 ከኢሳይያስ 40:13, 14 ላይ የተጠቀሰ ሲሆን የሚናገረው የጥበብና የእውቀት ሁሉ ምንጭ ስለሆነው አምላክ መሆኑ ግልጽ ነው። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ ሲጽፍላቸው ጥቅሱን በመድገም “የጌታን [የይሖዋን አዓት] ልብ ማን አውቆት ነው?” ካለ በኋላ “እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን” ሲል አክሏል። ጌታ ኢየሱስ ስለ በርካታ አስፈላጊ ጉዳዮች ይሖዋ ያለውን ሐሳብ ለተከታዮቹ ገልጦላቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 2:16

አንዳንድ ጊዜ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ ይሖዋ የሚናገሩ ጥቅሶች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ተፈጻሚነታቸውን አግኝተዋል። ምክንያቱም እርሱ ለኢየሱስ ኃይልና ሥልጣን በውክልና ሰጥቶታል። ለምሳሌ መዝሙር 34:8 “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ቸር እንደሆነ ቅመሱ እዩም” በማለት ይጋብዘናል። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ “ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደሆነ” በማለት ይህ ጥቅስ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደሚሠራ ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 2:3) ጴጥሮስ መሠረታዊውን ሐሳብ በመውሰድ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንዴት እንደሚሠራ ገልጿል። ክርስቲያኖች ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በማወቅና ያወቁትን ተግባራዊ በማድረግ ከአብና ከልጁ ብዙ በረከት አግኝተው ሊደሰቱ ይችላሉ። (ዮሐንስ 17:3) ጴጥሮስ ጥቅሱን የተጠቀመበት መንገድ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋን ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ አካል አያደርገውም።—በባለማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ላይ የ1 ጴጥሮስ 2:3ን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ሐዋርያው ጳውሎስ “ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፣ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን” በማለት ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸውን የተለያየ ቦታ በሚገባ ግልጽ አድርጎታል። (1 ቆሮንቶስ 8:6፤ 12:5, 6) ጳውሎስ በኤፌሶን ይገኝ ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ሲጽፍ “አንድ ጌታ” የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን “አንድ አምላክ የሁሉም አባት” ከሆነው ከይሖዋ በሚገባ ለይቶ ገልጾታል።—ኤፌሶን 4:5, 6

የሁሉም የበላይ የሆነው ይሖዋ

“የዓለም መንግሥት ለጌታችን [ለይሖዋ አምላክና] እርሱ [ለሾመው] ክርስቶስ ሆነች፣ ለዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል” የሚሉት የራእይ 11:15 ቃላት ከ1914 ጀምሮ ተፈጽመዋል። ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ የተባለው መዝገበ ቃላት (በጥራዝ 2፣ ገጽ 514) እንዲህ ይላል፦ “ክርስቶስ ሥልጣን የነበራቸውን ሁሉ ካሸነፈ በኋላ (1 ቆሮ. 15:25) እርሱ ራሱ ለእግዚአብሔር አብ ይገዛል። በዚህ መንገድ የኢየሱስ ጌትነት ግቡን ስለሚመታ አምላክ ሁሉ በሁሉ ይሆናል። (1 ቆሮ. 15:28)” ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛቱ ሲያበቃ በፊት አባቱ በውክልና ሰጥቶት የነበረውን ኃይሉንና ሥልጣኑን ለአባቱ ማለትም ሁሉን ማድረግ ለሚችለው አምላክ ያስረክባል። በመሆኑም ክብርና አምልኮ ሁሉ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ” ለሆነው ለይሖዋ ይሰጣል፤ ይህም ተገቢ ነው።—ኤፌሶን 1:17

ምንም እንኳን ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ የጌቶች ጌታ ቢሆንም የአማልክት አምላክ ተብሎ በፍጹም አልተጠራም። ይሖዋ ለዘላለም የሁሉም የበላይ እንደሆነ ይኖራል። በዚህ መንገድ ይሖዋ ‘ለሁሉም ሁሉን ይሆናል።’ (1 ቆሮንቶስ 15:28 አዓት) ኢየሱስ ጌታ በመሆኑ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የመሆን ትክክለኛ ሥልጣን ይኖረዋል። ምንም እንኳን በዚህ ዓለም ውስጥ በከፍተኛ ቦታ ላይ ያሉ ኃያላን የሆኑ ብዙ “ጌቶች” ቢኖሩም ትምክህታችንን የምንጥለው በጌቶች ጌታ ላይ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍ ያለና የላቀ ሥልጣን ቢኖረውም “እግዚአብሔር . . . በሁሉ ላይ ሥልጣን እንዲኖረው” ለአባቱ መገዛቱን ይቀጥላል። (1 ቆሮንቶስ 15:28 የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ጌታችን ቢሉትም እንዴት ያለ የትሕትና ምሳሌ ትቶላቸዋል!

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ስለ አምላክ ሲናገሩ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት መናገራቸው ነው። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚናገሩበት ጊዜ እርሱ እግዚአብሔር ነው አላሉም፤ ወይም እንደ አምላክ አድርገው አላሰቡትም። እርሱ አምላክ የቀባው ክርስቶስ፣ የአምላክ ልጅ፣ የአምላክ ጥበብ፣ የአምላክ ቃል ነው። ወደ ኒቅያ ጉባኤ ቀረብ የሚለው በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል መክፈቻ ላይ ያለው ሐሳብ እንኳን ወንጌሉ በጠቅላላው በግልጽ በሚያስተምረው ክርስቶስ የአባቱ የበታች እንደሆነ በሚገልጸው ሐሳብ መሠረት መታየት አለበት። የወንጌሉ የመክፈቻ ሐሳብ በግሪክኛው የተጠቀሰው ከአመልካች ቃል [ቴኦስ] ጋር አይደለም። ስለዚህ ከግሪክኛው ይልቅ የእንግሊዝኛው ትርጉም ይበልጥ ግልጽ ነው።” —“ የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮትነት” (“ ዘ ዲቪኒቲ ኦቭ ጂሰስ ክራይስት”)፤ በጆን ማርቲን ክሪድ የተጻፈ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ