የተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን ውዝግቡ ምን ያህል የከፋ ነው?
“በፊት ለፊት በኩል ያለው ግድግዳ በድንገት በወደቀበት ያዘመመ አሮጌ ቤት ውስጥ እንደሚኖር ብዙ አባላት ያሉትና ግራ የገባው ቤተሰብ የኢየሱስ ልጆችም ቃል በቃል በየክፍላቸው ታምቡር እየደለቁ የሚንጫጩ ይመስላል፤ እንግሊዛውያን ካቶሊኮች በሆኑ ከጥቁር ሐር የተሠራ ልብስ ለብሰው በሚንጎራደዱ መልከ መልካም ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች ላይ ይጮኻሉ።”—ዘ ሳንደይ ታይምስ፣ ለንደን፣ ሚያዝያ 11, 1993
ይህ ቤተሰብ የእንግሊዝ የኤፒስኮፓል ቤተ ክርስቲያን ነው። ጫጫታው ሴቶች የቅስና ማዕረግ ይሰጣቸው ወይስ አይሰጣቸው በሚል የተደረገ ሙግት ነው። ሥር ስለሰደደው መከፋፈል የሚገልጸው ጉልህ መግለጫ ለሁሉም የሕዝበ ክርስትና ክፍሎች የሚሠራ ነው። ሴቶች ቄሶች መሆን እንዲችሉ የተደረሰውን ውሳኔ የሮምን ጳጳስ ጨምሮ የኦርቶዶክስ ፓትሪያርኮች የተቃወሙት ሲሆን የተገኘውን አጠቃላይ ውጤት ሲገልጽ አንድ ሪፖርት የሚከተለውን መደምደሚያ ሰጥቷል፦ “ከሌሎቹ የሕዝበ ክርስትና ክፍሎች ጋር አንድነት ለመፍጠር የታለመው ሕልም ከምን ጊዜውም ይበልጥ የማይጨበጥ ሆኗል።”
ቤተ ክርስቲያን የቱን ያህል የተከፋፈለች ናት?
በማቴዎስ 7:21 ላይ እንደምናነበው ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙዎች እሱን እንደ ጌታ አድርገን እናምንበታለን ብለው እንደሚናገሩ፤ ያም ሆኖ ግን ‘የአባቱን ፈቃድ እንደማያደርጉ’ ተናግሯል። ማክሌያንስ የተባለው መጽሔት “መዳንን የሚሹ የማቴዎስ አንባቢዎች ክርስቲያኖችና ቤተ ክርስቲያኖቻቸው በጥያቄው ላይ ያላቸው አመለካከት በእጅጉ የተራራቀ ከሆነ ትክክለኛው የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ግራ ቢገባቸው ይቅርታ ሊደረግላቸው ይችላል” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። ከአንዳንድ ካናዳውያን ጋር ቃለ ምልልስ ካደረገ በኋላ መጽሔቱ “በካናዳውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ የእምነትና የልማድ ልዩነት” አለ፤ “እንዲያውም በራሳቸው በእምነት ክፍሎቹ መካከል ካለው ልዩነት ይልቅ በአንድ የእምነት ክፍል ውስጥ ባሉ አባላት መካከል ያለው ልዩነት ይበልጣል” ሲል ደምድሟል።
መጽሔቱ ባደረገው ጥናት መሠረት ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያናቸው የሚቃወመው ቢሆንም 91 በመቶ የሚሆኑ ካቶሊኮች ተፈጥሮአዊ ያልሆነ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴ መጠቀምን ይደግፋሉ፤ 78 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ቄሶች እንዲሆኑ ሊፈቀድላቸው ይገባል ብለው ያስባሉ፤ 41 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ “አንዳንድ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ” ጽንስ ማስወረድን ይደግፋሉ። የተለያዩ የእምነት ክፍሎች “ሥፍር ቁጥር በሌላቸው ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች” ላይ ስምምነት ማጣታቸው ይላል ማክሌያንስ፣ “ለዋና ዋናዎቹ ቤተ ክርስቲያኖች መፈረካከስ ምክንያት የሆኑትን ልዩነቶች ጎላ አድርጎ ያሳያል።”
ሁለት ዓይነት የአቋም ደረጃዎች
በሥነ ምግባር ረገድ ሁለት ዓይነት የአቋም ደረጃዎች እንዲሁም እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ የአቋም ደረጃዎች አሉ። አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንደግፋለን ይላሉ፤ ሌሎቹ ግን ከምንም ባለመቁጠር ያፈርሷቸዋል። ለምሳሌ ያህል ቶሮንቶ በሚገኝ አንድ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሁለት ሴቶች መካከል የተከናወነው “የጋብቻ” ሥነ ሥርዓት እውን ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ነውን? ተጋቢዎቹ እንደዚያ እንደተሰማቸው ግልጽ ነው። “ፍቅራችንን በሕዝብና በአምላክ ፊት ማክበር እንፈልጋለን” ብለዋል።
አንድ የጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ አዘጋጅ “የግል ፋይላቸው በክስ የተሞላ አንድ ሊቀ ጳጳስ ልጆችን የሚያስነውሩ ቄሶችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉ ሌሎች ልጆችን ሊያገኙ ወደሚችሉበት ቦታ ሊያዛውሩ” እንዴት ይችላሉ? ሲሉ ጠይቀዋል። አንድሩ ግሪሌይ የተባሉ ቄስ ከ2,000 እስከ 4,000 የሚደርሱ ቄሶች ለአቅመ አዳም ያልደረሱ 100,000 ወጣቶችን የዚህ ድርጊት ሰለባ አድርገዋቸው ሊሆን ይችላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች ብዙውን ጊዜ በቸልታ ታልፈዋል።
የተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን የተከፋፈሉ ሰዎችን ታፈራለች። በባልካን ግዛቶች የሚገኙት ሁለቱም የሰርቢያና የክሮአት “ክርስቲያኖች” በሚያካሄዱት “ፍትሐዊ” ጦርነት ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር እንዳለ ሆኖ ይሰማቸዋል። ብዙዎች በውጊያ ላይ መስቀል በአንገታቸው ያንጠለጥላሉ፤ አንድ ሰው “ጦርነቱ ሲፋፋም ሁልጊዜ መስቀሉን በአፉ እንደሚይዝ” ታውቋል።
“መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን”
እውነት ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጉዳዮችን ለሕሊና ይተዋል፤ ነገር ግን ይህ ለእንዲህ ዓይነቱ መከፋፈል ቦታ መስጠት አይኖርበትም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ . . . መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን” ሲል በግልጽ ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 1:10፤ ኤፌሶን 4:15, 16
ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን ቃላት ከጻፈ ወደ ሁለት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ “ክርስትናን” በሐቅ ስንመለከተው አንዳንድ ከባድ ጥያቄዎችን የግድ ማንሳታችን አይቀርም። “ክርስቲያኖች” በእጅጉ የተከፋፈሉት ለምንድን ነው? እንዲህ ዓይነቷ የተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን ከተደቀነባት አደጋ ትተርፍ ይሆን? ወደፊት አንድነት ያላት ሕዝበ ክርስትና ትፈጠር ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ያብራራል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቄሶች ፅንስ ማስወረድን በመቃወም ያደረጉት ሰልፍ
[ምንጭ]
በሽፋኑ ላይና ከላይ ያለው ፎቶ፦ Eleftherios/Sipa Press