የተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን ከተደቀነባት አደጋ ትተርፍ ይሆን?
“የክርስቶስ እውነት እንደሚያድን የሚያምኑ ሁሉ የሚታየው ቤተ ክርስቲያን አባላት ናቸው። ሕዝበ ክርስትና ምሥራቅና ምዕራብ ተብላ ለሁለት መከፈሏ እንዲሁም በሮም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና በፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያኖች መካከል ያለው ልዩነት በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰቱ ልዩነቶች ናቸው።” (ክርስቲያንስ ኢን ኮምዩኒየን) አንድ ጸሐፊ ክርስትናን የተመለከቱት በዚህ መንገድ ነው፤ ሁሉም አባሎቹ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑና በተለያየ አቅጣጫ በስፋት የተበታተኑ ሃይማኖቶችን ያቀፈ ቤተሰብ እንደሆነ አድርገው ተመልክተውታል።
ነገር ግን ክርስትና እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ እምነቶችንና የጠባይ ደረጃዎችን የያዘ የተከፋፈለ ቤተሰብ ነው። “በአሁኑ ጊዜ ያለው ክርስትና . . . ለቤተ ክርስቲያን አባልነት ያወጣቸው የብቃት ደረጃዎች አውቶቡስ ውስጥ ለመሳፈር ከሚፈለጉት የብቃት ደረጃዎች ያነሱ ናቸው” ሲሉ አንድ ታዛቢ ተናግረዋል። እንግዲያው የክርስትና ሃይማኖት ያለበትን መንፈሳዊ ሁኔታ መመርመር የሚኖርብን እንዴት ነው? የካቶሊክ ጳጳስ የሆኑት ባሲል በትለር “የተከፋፈለው ክርስትና በጠና መታመሙ አያጠራጥርም” በማለት ደምድመዋል። (ዘ ቸርች ኤንድ ዩኒቲ) ሕመሙ የጀመረው እንዴት ነው? ማገገም እንደሚቻል የሚጠቁሙ የተስፋ ጭላንጭሎች አሉን?
“የዓመፅ ሰው”
ሐዋርያው ጳውሎስ ወደፊት መከፋፈል እንደሚመጣ አስጠንቅቆ ነበር። የክርስቶስ መገኘት በጣም ቅርብ እንደሆነ አድርገው ያስቡ ለነበሩት የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል፦ “ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፣ [የይሖዋ ቀን] አይደርስምና።”—2 ተሰሎንቄ 2:3
ይህ “የዓመፅ ሰው” ክህደትና ዓመፅ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ አስገብቷል። ይህ ሰው ማን ነው? የትኛውም አንድ የተለየ ግለሰብ ሳይሆን የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በጠቅላላ ናቸው። ይህ ቡድን የኢየሱስ ሐዋርያት ሞተው ብዙም ሳይቆይ ራሱን በከዳተኛው ጉባኤ ላይ ከፍ አደረገ። በመጨረሻም እንደ ሥላሴና የሰው ነፍስ አትሞትም የሚሉትን የመሰሉ የአረማውያን ፍልስፍናዎችን ማስተማር ጀመረ። (ሥራ 20:29, 30፤ 2 ጴጥሮስ 2:1–3) ልክ እንደ አንድ ገዳይ ቫይረስ የክርስትናን ጉባኤ ከአጋንንት በመነጩ ትምህርቶች በከለው። ይህም ወደ መከፋፈል ማድረሱ አይቀሬ ነበር።—ገላትያ 5:7–10
ወረርሽኙ በዚያው ሐዋርያው ጳውሎስ በነበረበት ዘመን ጀምሮ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የዓመፅ ምሥጢር አሁን ይሠራልና፤ ብቻ ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ አሁን የሚከለክል አለ።” (2 ተሰሎንቄ 2:7) ሐዋርያት የክህደት መርዝ እንዳይሰራጭ መከላከያ ሆነው አገልግለዋል። ለአንድነት እንደ ምሰሶ የሆነው የእነርሱ መገኘት ሲቀር ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ክህደት ልክ እንደ ጋንግሪን ወይም ጭንቁር እንደተባለ በሽታ ተሰራጨ።—1 ጢሞቴዎስ 4:1–3፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:16–18
የዚህ “የዓመፅ ሰው” እንቅስቃሴዎች ምንም ሳያባሩ ቀጠሉ። “በጾታ ጉዳይና በሃይማኖታዊ ትምህርቶች መዘዝ የምትሠቃይ ቤተ ክርስቲያንን” በሚል አስመልክቶ በቅርቡ በወጣ ሪፖርት ላይ አንድ የእንግሊዝ ኤፒስኮፓል ቤተ ክርስቲያን አቡን እንዲህ በማለት ያሰሙትን ቅሬታ ጠቅሶ ዘግቧል፦ “ቤተ ክህነት ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸሙ የጾታ ድርጊቶች እንድታግድ የቀረቡት ሐሳቦች ውድቅ ሆነዋል። ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ሰዎች የቤተ ክህነት አባሎች እንዲሆኑ ይፈቀድላቸዋል። መልካሙን ክፉ፣ ክፉውን መልካም አድርገዋል።”—ዘ ሳንደይ ታይምስ ማጋዚን፣ ለንደን፣ ኅዳር 22, 1992
ስንዴና እንክርዳዶች
ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እውነተኛ ክርስትና ለጥቂት ጊዜ ከእይታ እንደሚሰወር አስተምሮ ነበር። የክርስቲያን ጉባኤ አመሠራረት በእርሻው ላይ መልካም ዘርን የሚዘራ ሰውን እንደሚመስል ተናግሯል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ” አለ። ባሪያዎቹ እንክርዳዶቹን ለመንቀል እንሞክርን? ብለው በጠየቁት ጊዜ የእርሻው ባለቤት “እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም” አላቸው። ስንዴውና እንክርዳዶቹ ተቀላቅለው አንድ ላይ የሚቆዩት እስከ መቼ ድረስ ይሆን? የእርሻው ባለቤት “እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ” ብሏል።—ማቴዎስ 13:25, 29, 30
እስከ “መከር” ጊዜ ድረስ ወይም በ“ነገሮች ሥርዓት” መጨረሻ ቀኖች ውስጥ እስከሚከናወነው የመለያየት ሥራ ጊዜ ድረስ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ጎን ለጎን አስመሳይ ክርስቲያኖችም አብረው አደጉ። (ማቴዎስ 28:20 አዓት) ሰይጣን ዲያብሎስ የክህደት አራማጆችን የተበከለና የተከፋፈለ የአስመሳይ ክርስቲያኖች ጉባኤን ለመፍጠር ተጠቅሞባቸዋል። (ማቴዎስ 13:36–39) አሳፋሪ የሆነ አስመሳይ የክርስትና እምነት ፈጥረዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:3, 13–15፤ ቆላስይስ 2:8) ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት እየተገነጣጠለች በመምጣቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይቶ ማወቁ አስቸጋሪ እየሆነ ሄዶ ነበር።
አዳዲስ ቡድኖች
በዘመናችን ይላል ዘ ቴስቲንግ ኦቭ ዘ ቸርችስ 1932–1982 ከበፊቱ በላቀ ሁኔታ “የተገነጠሉ ቡድኖች ብቅ ብቅ ብለዋል፤ በተለይም ለግል እምነትና ተሞክሮዎች ጎላ ያለ ቦታ የሚሰጡት በተአምራዊ ድንቆች የሚያምኑ ቤተ ክርስቲያኖች መገነጣጠል ታይቶባቸዋል።” የሚገርመው ነገር አንዳንዶች አዲሶቹን በተአምራዊ ድንቆች የሚያምኑ ቤተ ክርስቲያኖች እንደ አዲስ ቡድኖች ከማየት ይልቅ እንደ መንፈሳዊ ተሐድሶ ምልክቶች አድርገው ማየታቸው ነው። ለምሳሌ ያህል ሰሜናዊው የአየርላንድ ክፍል እንዲህ ዓይነቱ የማንሰራራት ክስተት በ1850ዎቹ አጋጥሞት ነበር። ክስተቱ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። አንድ ሪፖርት “በፕሪስቢቴሪያን፣ በዌስሌያንና ገለልተኛ አገልጋዮች በሚባሉት መካከል . . . ስለተፈጠረው ወንድማዊ ውህደት” ከተናገረ በኋላ “እያንዳንዱ ቀን በሰመመንና በእንቅልፍ ልብ ስለተፈጸሙ ነገሮች፣ ስለ ሕልሞችና ስለ ተአምራት የሚገልጹ አዳዲስ ሪፖርቶችን ይዞ ከተፍ ይላል” ብሏል።—ሪሊጅየስ ሪቫይቫልስ
ብዙዎች እነዚህን ልዩ ክስተቶች የአምላክ መንፈስ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲያንሰራራ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ አድርገው ተመልክተዋቸው ነበር። “የአምላክ ቤተ ክርስቲያን” አሉ አንድ ታዛቢ “በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ አንሠራርቷል።” ይሁን እንጂ ይህ የተወሰነ የማንሠራራት ሂደት “በአልስተር ሃይማኖታዊ ታሪክ ውስጥ አንድ ታላቅና ታይቶ የማይታውቅ ክስተት የተከናወነበት ዘመን” እንደ ሆነ ተደርጎ ቢነገርለትም እንኳን እርሱም ሆነ እንደ እርሱ ያሉ ሌሎች ሂደቶች የመንፈሳዊነት ዳግም ልደት አግኝተናል ብለው በሚናገሩት መካከል ሃይማኖታዊ አንድነትን አላፈሩም።
እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች አንድ ነን በማለት ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ ይህ “እስከ አሁንም ድረስ የሚለያዩአቸው ጉዳዮች በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያኖችን አንድ ከሚያደርጓቸው ነገሮች ጋር ሲነጻጸሩ ከቁብ የማይቆጠሩ” እንደሆኑ አድርገው የሚያስቡት የተቀሩት የሕዝበ ክርስትና ክፍሎች ከሚያቀርቡት የመከራከሪያ ሐሳብ ጋር አንድ ነው። (ዘ ቸርች ኤንድ ዩኒቲ) ሕዝበ ክርስትና “እርስ በእርሳችንና መሰሎቻችን ከሆኑት ከሁሉም ክርስቲያኖች ጋር ያለን መሠረታዊ አንድነት በክርስቶስ ስም በምናደርገው ጥምቀታችን ላይ የተመሠረተ ነው” በማለት ትናገራለች። (ክርስቲያንስ ኢን ኮሚዩኒየን) ይሁን እንጂ በኢየሱስ ላይ የጋራ እምነት እስካለን ድረስ ልዩነቶቹ ይህን ያህል የሚያሳስቡ ነገሮች አይደሉም ብሎ መናገር ልብህ ደህና እስከሆነ ድረስ ካንሰር ይህን ያህል ከባድ ነገር አይደለም እንደ ማለት ነው።
እንዲህ ዓይነቶቹ ዘመናዊ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ሰዎች ይበልጥ ግራ እንዲጋቡ ከማድረጋቸውም በላይ ሰዎችን ለማሳመን የሚጥሩ አስተማሪዎች ለራሳቸው ተከታዮችን የሚያሰባስቡ በመሆኑ መንፈሳዊ ሥርዓት አልበኝነትን ማፍራታቸው የማይታበል ሐቅ ነው። ጂም ጆንስና ዴቪድ ኮሬሽ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያሳቱ የቅርብ ጊዜ ምሳሌዎች የሆኑ መንፈሳዊ መሪዎች ናቸው። (ማቴዎስ 15:14) አንድ መጥምቃዊ (ባፕቲስት) ቄስ በኩ ክላክስ ክላን (በ20ኛው መቶ ዘመን የተቋቋመ ነጮች የሆኑ የአሜሪካ ተወላጅ ክርስቲያኖችን ብቻ በአባልነት የሚቀበል ቡድን) ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያያዙ አባል ናቸው። ለነጮች የበላይነት የሚያካሂደውን ዘመቻ ከሃይማኖታዊ የማንሠራራት ሂደት ጋር አያይዞታል። በዚህ ዘመቻ የሚሳተፉ ሰዎች “መለኮታዊ ብርታትን ያገኛሉ፤ በጎልጎታ የሞተው የኢየሱስ ድፍረት ይሰጣቸዋል” ብለዋል።
በኢየሱስ ስም ይፈጸማሉ ስለሚባሉት ተዓምራት፣ ታላላቅ ሥራዎችና ምልክቶች ምን ሊባል ይቻላል? በእርሱ ፊት ተቀባይነት የሚኖራቸው እንዲሁ “ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ” የሚሉት ሳይሆኑ ‘የአባቱን ፈቃድ የሚያደርጉት ሰዎች’ እንደሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን ኃይለኛ ማስጠንቀቂያ ያስታውሱ። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ይሖዋ የሚለውን የአባቱን ስም እንኳን አያውቁም። ኢየሱስ ‘በስሙ አጋንንትን የሚያወጡና በዚህ ስም ተዓምራት የሚፈጽሙ’ ሰዎች እንደሚመጡ አስጠንቅቋል፤ እነዚህ ሰዎች “ዓመፀኞች” እንደሆኑ ተናግሯል።—ማቴዎስ 7:21–23
“ሕዝቤ ሆይ . . . ከእርስዋ ዘንድ ውጡ”
በሽታ ላይ የወደቀችው ሕዝበ ክርስትና የመዳን ተስፋዋ ምን ይመስላል? እጅግ የመነመነ ነው። ታዲያ የካቶሊኩ ጳጳስ ባትለር “ምንም ጊዜ ሳናጠፋ ከጎኗ [ከቤተ ክርስቲያን] እንድንቆምና ካለችበት ሁኔታ ለመላቀቅ በምታደርገው የማያቋርጥ ‘የመንጻት’ ሂደት የእርዳታ እጃችንን እንድንዘረጋ” ያቀረቡትን ምክር መቀበል ይኖርብናልን? አይኖርብንም! የተከፋፈለችውና የተበታተነችው ሕዝበ ክርስትና ከተደቀነባት አደጋ አታመልጥም። (ማርቆስ 3:24, 25) ታላቂቱ ባቢሎን ተብላ የምትጠራው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ክፍል ነች። (ራእይ 18:2, 3) በደም አፍሳሽነት ተጠያቂ የሆነው ይህ ሃይማኖታዊ ሥርዓት በቅርቡ በአምላክ እጅ ይጠፋል።
መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህች ብልሹ በሆነች ሃይማኖታዊ ድርጅት ውስጥ እንዲቆዩና ከውስጥ ሆነው እርሷን ለማደስ እንዲሞክሩ አይመክራቸውም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ሲል ያሳስባል፦ “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፣ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ።”—ራእይ 18:4, 5
‘ወጥተው’ የሚሄዱት ወዴት ነው? ኢየሱስ በመከሩ ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደገና ወደ ዓለም አቀፋዊ አንድነት አንድ ላይ ይሰባሰባሉ የሚል ተስፋ እንደሰጠ ያስታውሱ። ነቢዩ ሚክያስም እንዲህ ዓይነቱ እንደገና መሰባሰብ እንደሚኖር “እንደ መንጋ በማሰማሪያቸው ውስጥ በአንድነት አኖራቸዋለሁ” በሚሉት ቃላት ተንብዮ ነበር። (ሚክያስ 2:12) ይህ ተፈጽሟልን?
አዎን! እውነተኛ ክርስቲያኖች በአሁኑ ጊዜ በምድር ዙሪያ አንድነት ወዳለው የወንድማማች ማኅበር እየተሰባሰቡ ነው። የወንድማማች ማኅበር የተባሉት እነማን ናቸው? ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች በ231 አገሮች እንደ አንድ አካል ሆነው እያወጁ ያሉትና የክርስቲያን ጉባኤ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። የሕዝበ ክርስትናን የሚከፋፍሉ ትምህርቶች እርግፍ አድርገው ትተዋል፤ የቃሉ እውነት በሚለውም መሠረት አምላክን ለማምለክ ይጥራሉ።—ዮሐንስ 8:31, 32፤ 17:17
ከእነርሱ ጋር እንዲነጋገሩ የሞቀ ግብዣ ቀርቦልዎታል። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ይበልጥ ለማወቅ ከፈለጉ በአካባቢዎ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች ቀርበው ያነጋግሯቸው፤ ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 2 ላይ ካሉት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው ይጻፉ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ”