ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ማነቃቃት ያለባችሁ እንዴት ነው?
“ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ . . . እርስ በርሳችን እንመካከር [“እንበረታታ” የ1980 ትርጉም] እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።”—ዕብራውያን 10:24, 25
1, 2. (ሀ) የጥንት ክርስቲያኖች በአንድነት በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ መጽናኛና ማበረታቻ ማግኘታቸው በጣም አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ላይ የመሰብሰብን አስፈላጊነት የገለጸው የትኛው የጳውሎስ ምክር ነው?
የተገናኙት በምሥጢር ነው፤ በሩ ግጥም ብሎ በተዘጋ ቤት ውስጥ አንድ ላይ ተሰብስበዋል። ከቤቱ ውጭ በየትኛውም ቦታ አደጋ አጥልቷል። መሪያቸው ኢየሱስ በሕዝብ ፊት የተገደለበት ወቅት ነበር። ኢየሱስ ተከታዮቹን ከእሱ የተሻለ ነገር እንደማይገጥማቸው አስጠንቅቋቸዋል። (ዮሐንስ 15:20፤ 20:19) ይሁን እንጂ በጣም የሚወዱትን ኢየሱስን አንስተው እየተንሾካሾኩ ሲነጋገሩ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ላይ በመሆናቸው ሻል ያለ የደህንነት ስሜት ተሰምቷቸው መሆን አለበት።
2 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ክርስቲያኖች ሁሉም ዓይነት ፈተናና ስደት ደርሶባቸዋል። እንደ መጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት እነርሱም አንድ ላይ በመሰብሰብ መጽናኛና ማበረታቻ አግኝተዋል። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር [“እንበረታታ” የ1980 ትርጉም] እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።”
3. ዕብራውያን 10:24, 25 ክርስቲያኖች አንድ ላይ መሰብሰብ እንዳለባቸው የሚገልጽ ትእዛዝ ከመሆንም የበለጠ ትርጉም አለው የምትለው ለምንድን ነው?
3 እነዚህ ቃላት መሰብሰባችንን እንድንቀጥል የሚያሳስብ ትእዛዝ ከመሆንም የበለጠ ትርጉም አላቸው። እነኚህ ቃላት ለሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ሆነ ክርስቲያኖች አንድ ላይ ለሚገናኙበት ማንኛውም አጋጣሚ የሚያገለግል በመንፈስ አነሳሽነት የተነገረ መሥፈርት ያስተላልፋሉ። ዛሬ ከምንጊዜውም በበለጠ የይሖዋ ቀን መቅረቡን በግልጽ ስንመለከት በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ ካሉት ተጽዕኖዎችና አደገኛ ሁኔታዎች አንጻር ስብሰባዎቻችን የግድ ለሁላችንም አስተማማኝ መሸሸጊያ እንዲሁም ጥንካሬና ብርታት የሚሰጡ መሆን መቻል አለባቸው። ስብሰባዎቻችንን እንዲህ ዓይነት ቦታ እንዲሆኑ ምን ማድረግ እንችላለን? እስቲ የሚከተሉትን ሦስት ዋና ዋና ጥያቄዎች በማንሣት የጳውሎስን ቃላት በጥንቃቄ እንመርምራቸው፦ “እርስ በርሳችን እንተያይ” ማለት ምን ማለት ነው? ‘እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራ መነቃቃት’ ማለት ምን ማለት ነው? በመጨረሻም፣ በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ‘እርስ በርስ መበረታታት’ የምንችለው እንዴት ነው?
“እርስ በርሳችን እንተያይ”
4. “እርስ በርሳችን እንተያይ” ማለት ምን ማለት ነው?
4 ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “እርስ በርሳችን እንተያይ” በማለት አጥብቆ ሲመክራቸው “መረዳት” የተባለውን የተለመደ ቃል ጠበቅ አድርጎ የሚገልጸውን ካታኖኢኦ የሚለውን የግሪክኛ ግሥ ተጠቅሟል። ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ይህ ቃል “ሙሉ በሙሉ በአንድ ነገር ላይ ማተኮር” ማለት ነው ይላል። ደብሊዩ ኢ ቫይን ባሉት መሠረት “ሙሉ በሙሉ መረዳት፣ ጠለቅ ብሎ መመልከት” ማለትም ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ክርስቲያኖች ‘እርስ በእርስ ሲተያዩ’ የሚመለከቱት ውጫዊ ገጽታን ብቻ ሳይሆን የማሰብ ችሎታቸውን በሙሉ በመጠቀም ይበልጥ ጠለቅ ብለው ለመመልከት ይሞክራሉ።—ከዕብራውያን 3:1 ጋር አወዳድር።
5. አንድ ሰው በግልጽ ላይታዩ ከሚችሉት ባሕርይዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? እነዚህን ግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርብንስ ለምንድን ነው?
5 አንድን ሰው ውጫዊ ገጽታውን፣ ሥራውንና ቁመናውን በመመልከት ብቻ ማንነቱን ሙሉ በሙሉ ማወቅ እንደማይቻል ማስታወስ ይኖርብናል። (1 ሳሙኤል 16:7) ብዙውን ጊዜ ውጫዊ ገጽታ ውስጣዊ ስሜቶችን ወይም የተጫዋችነትን ባሕርይ ሊደብቅ ይችላል። በተጨማሪም የእያንዳንዱ ሰው አስተዳደግ በእጅጉ የተለያየ ነው። አንዳንዶች በሕይወታቸው ውስጥ ከባድ ችግሮች አሳልፈዋል፤ ሌሎች ደግሞ ለመገመት እንኳን የሚያዳግቱንን ችግሮች በመቋቋም ላይ ይገኛሉ። ብዙውን ጊዜ በአንድ ሰው ባሕርይ የተነሣ የሚሰማን ብስጭት ስለዚያ ሰው አስተዳደግ ወይም ስላለበት ሁኔታ ይበልጥ ስናውቅ በአንድ ጊዜ ይከስማል።—ምሳሌ 19:11
6. እርስ በርስ የበለጠ መተዋወቅ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? ምን ጥሩ ውጤትስ ሊገኝ ይችላል?
6 እርግጥ ነው፣ ይህ ማለት ሳንጠየቅ በአንድ ሰው የግል ጉዳዮች ጣልቃ እንገባለን ማለት አይደለም። (1 ተሰሎንቄ 4:11) ያም ሆኖ ግን አንዳችን ለሌላው አሳቢነት ማሳየት እንችላለን። ይህ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ለወጉ ያህል ሰላምታ ከመስጠት የበለጠ ነገርንም ይጨምራል። ይበልጥ ልታውቁት የምትፈልጉትን ሰው መርጣችሁ ከስብሰባ በፊት ወይም በኋላ ለጥቂት ደቂቃዎች ለማነጋገር ለምን ግብ አታወጡም? አንድ ወይም ሁለት ወንድሞችን ሻይ ቡና ለማለት ወደ ቤታችሁ በመጋበዝ ‘እንግዳ ተቀባይ መሆን’ ደግሞ የበለጠ ጠቃሚ ይሆናል። (ሮሜ 12:13) የአሳቢነት ስሜት ይኑራችሁ። አዳምጡ። አንድ ሰው ይሖዋን ሊያውቅና ሊወድ የቻለው እንዴት እንደሆነ መጠየቁ ብቻ እንኳን ብዙ ነገር ለማወቅ ያስችላል። ይሁን እንጂ ከዚህም በተጨማሪ በአንድነት ከቤት ወደ ቤት በማገልገል ብዙ ማወቅ ትችላላችሁ። እነዚህን በመሰሉ መንገዶች እርስ በርስ መተያየት ለሌላው ሰው እውነተኛ ወዳጃዊ ስሜት ወይም ችግሩን በእሱ ቦታ ሆኖ የመረዳት ስሜት ማዳበር እንድንችል ይረዳናል።—ፊልጵስዩስ 2:4፤ 1 ጴጥሮስ 3:8
‘እርስ በርስ ተነቃቁ’
7. (ሀ) የኢየሱስ ትምህርት ሰዎችን የነካው እንዴት ነበር? (ለ) ትምህርቱ እጅግ ቀስቃሽ እንዲሆን ያደረገው ነገር ምን ነበር?
7 እርስ በእርሳችን ስንተያይ አንዳችን ሌላውን ለማነቃቃትና ለሥራ ለመገፋፋት ይበልጥ ዝግጁዎች እንሆናለን። በተለይ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። ኢየሱስ በአንድ ወቅት በሕዝብ ፊት በተናገረበት ጊዜ ስለሆነው ሁኔታ እንዲህ እናነባለን፦ “ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ።” (ማቴዎስ 7:28) በሌላ ጊዜ እርሱን እንዲይዙ የተላኩት ወታደሮች እንኳ “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም” በማለት ትተውት ተመልሰዋል። (ዮሐንስ 7:46) የኢየሱስን ትምህርት እጅግ ቀስቃሽ እንዲሆን ያደረገው ነገር ምን ነበር? ከልክ በላይ የሆነ ስሜታዊ አነጋገር ነበርን? አልነበረም። ኢየሱስ ይናገር የነበረው ሥርዓት ባለው ሁኔታ ነበር። ሆኖም ሁልጊዜ የአድማጮቹን ልብ የመንካት ግብ ነበረው። የሰዎችን ሁኔታ ልብ ብሎ ይመለከት ስለነበረ እንዴት ልባቸውን ሊቀሰቅስ እንደሚችል ያውቅ ነበር። የዕለት ተዕለት የሕይወት እውነታዎችን የሚያንጸባርቁ ግልጽና ቀላል ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 13:34) በተመሳሳይም በስብሰባዎቻችን ላይ የተሰጧቸውን ክፍሎች የሚያቀርቡ ሰዎች ቀስቃሽ የሆኑ ወዳጃዊና የጋለ ስሜት የሚንጸባረቅባቸው አቀራረቦች በመጠቀም ኢየሱስን መምሰል አለባቸው። ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም ከአድማጮቻችን ሁኔታ ጋር የሚስማሙና ልባቸውን የሚነኩ ምሳሌዎችን ፈልገን በማግኘት ረገድ ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ እንችላለን።
8. ኢየሱስ ምሳሌ በመሆን ያነቃቃ የነበረው እንዴት ነበር? በዚህ ረገድ እርሱን ልንመስለው የምንችለውስ እንዴት ነው?
8 አምላክን በማገልገል ረገድ ሁላችንም ምሳሌ በመሆን እርስ በርስ መነቃቃት እንችላለን። ኢየሱስ አድማጮቹን አነቃቅቷል። ክርስቲያናዊ አገልግሎትን ይወድ ነበር፤ አገልግሎቱንም ከፍ አድርጎ ተመልክቶታል። አገልግሎቱ ለእርሱ ልክ እንደ መብል እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:34፤ ሮሜ 11:13) እንዲህ ዓይነቱ የጋለ ስሜት ከአንዱ ወደ ሌላው ሊጋባ የሚችል ነው። አንተም በተመሳሳይ በአገልግሎቱ የምታገኘው ደስታ ለሌሎች እንዲታይ ልታደርግ ትችላለህን? በአነጋገርህ ላይ የጉራ መንፈስ እንዳይንጸባረቅ እየተጠነቀቅህ ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎችህን በጉባኤው ውስጥ ለሚገኙት ለሌሎች አካፍላቸው። ሌሎች ከአንተ ጋር እንዲያገለግሉ ስትጋብዛቸው ስለ ታላቁ ፈጣሪያችን ስለ ይሖዋ ለሌሎች በመናገር ረገድ እውነተኛ ደስታ እንዲያገኙ ለመርዳት ሞክር።—ምሳሌ 25:25
9. (ሀ) ሌሎችን በማነቃቃት ረገድ ልናስወግዳቸው የምንፈልጋቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? ለምንስ? (ለ) ለይሖዋ አገልግሎት ራሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ሊገፋፋን የሚገባው ነገር ምን መሆን አለበት?
9 ይሁን እንጂ ሌሎችን በተሳሳተ መንገድ እንዳታነቃቃ ተጠንቀቅ። ለምሳሌ ያህል ሳናስበው ይበልጥ መሥራት ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው ልናደርግ እንችላለን። ሳናውቀው በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ጎላ ብለው ከሚታዩት ከሌሎች ጋር እነርሱን በማነጻጸር ልናሸማቅቃቸው እንችላለን፤ ወይም ደግሞ ጥብቅ የአቋም ደረጃዎች እናወጣና ያንን የአቋም ደረጃ ሳያሟሉ ሲቀሩ ልንተቻቸው እንችላለን። እነዚህ መንገዶች አንዳንዶችን ለተወሰነ ጊዜ ሊያነቃቋቸው ይችሉ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ጳውሎስ ‘የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ ለመልካም ሥራ አነቃቁ’ በማለት አልጻፈም። እንዲህ ማድረግ የለብንም፤ በፍቅር እንዲነሳሱ አድርገን ማነቃቃት አለብን። ከዚያ በኋላ በጥሩ ውስጣዊ ስሜት ተነሳስተው ይሠራሉ። ማንኛውም ሰው የሚጠበቅበትን ያህል ሳያከናውን ቢቀር አንድ ነገር ለማድረግ የሚገፋፋው ሌሎች በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሰዎች ስለ እርሱ በሚሰማቸው ስሜት ተነሳስቶ መሆን የለበትም።—ከ2 ቆሮንቶስ 9:6, 7 ጋር አወዳድር።
10. በሌሎች እምነት ላይ የምንገዛ እንዳልሆንን ማስታወስ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
10 እርስ በእርስ መነቃቃት ማለት አንዳችን ሌላውን መቆጣጠር ማለት አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ምንም እንኳ ከአምላክ የተሰጠው ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ቢሆንም የቆሮንቶስ ጉባኤን “በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም” በማለት በትህትና አሳስቧቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:24) እኛም እንደ ጳውሎስ ሌሎች በይሖዋ አገልግሎት ምን ያህል መሥራት እንዳለባቸው የመወሰኑ ሥራ ወይም በሌሎች የግል ውሳኔዎች ውስጥ ገብቶ ሕሊናቸውን መምራት የእኛ ሥራ አለመሆኑን በትህትና አምነን ከተቀበልን “እጅግ ጻድቅ፣” ደስታ የሌለን፣ ግትሮች፣ መጥፎ ጎን ብቻ የሚታየን ወይም የሆነ ደንብ ይዘን ችክ የምንል አንሆንም። (መክብብ 7:16) እንዲህ ዓይነቶቹ ባሕርያት ያስጨንቃሉ እንጂ አያነቃቁም።
11. በእስራኤላውያን ዘመን ለማደሪያው ድንኳን ግንባታ መዋጮ እንዲካሄድ ይገፋፋ የነበረው ነገር ምን ነበር? ይህስ በእኛ ዘመን እውን ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
11 በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ የሚከናወነው ማንኛውም ሥራ የጥንት እስራኤላውያን ለማደሪያው ድንኳን ግንባታ መዋጮ ሲያደርጉ በነበረው ዓይነት መንፈስ እንዲከናወን እንፈልጋለን። ዘጸአት 35:21 እንዲህ ይነበባል፦ ‘ከእነርሱም ሰው ሁሉ ልቡ እንዳነሣሣው መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለሥራው ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ።’ በሌሎች ተገፋፍተው ያደረጉት ሳይሆን ልባቸው ገፋፍቷቸው ያደረጉት ነበር። የዕብራይስጡም ቃል ቢሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “ልቡ ያነሣሣው ሰው ሁሉ” እነዚህን ስጦታዎች እንዳበረከተ ይናገራል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) አንድ ላይ በምንሆንበት ጊዜ ሁሉ አንዳችን የሌላውን ልብ ለማነሳሳት ይበልጥ ጥረት እናድርግ። የተቀረውን የይሖዋ መንፈስ ሊሠራው ይችላል።
“እርስ በርሳችን እንበረታታ”
12. (ሀ) “ማበረታታት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንዳንድ ፍቺዎች ምንድን ናቸው? (ለ) የኢዮብ ጓደኞች ኢዮብን ሳያበረታቱ የቀሩት እንዴት ነው? (ሐ) አንዳችን በሌላው ላይ ከመፍረድ መታቀብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
12 ጳውሎስ “እርስ በእርሳችን እንበረታታ” ብሎ በጻፈ ጊዜ ‘ማጠንከር፣ ማጽናናት’ የሚል ትርጉምም ያለውን ፓራካሌኦ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። በግሪክ ሰፕቱጀንት ትርጉም ላይ ይኸው ቃል ኢዮብ በኀዘን የተደቆሱ ሰዎችን እንደሚያጽናና ሆኖ በተገለጸበት በኢዮብ 29:25 ላይ ተጠቅሷል። ኢዮብ ራሱ በከባድ ፈተና ውስጥ በነበረበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ማበረታቻ እንዳላገኘ የሚጠቁም ምጸታዊ አነጋገር ነበር። ሦስቱ “አጽናኞቹ” ጊዜያቸው በሙሉ በእሱ ላይ በመፍረድና ዲስኩር በመስጠት ተይዞ ስለነበር ችግሩን በእርሱ ቦታ ሆነው ለመረዳትም ሆነ ለእርሱ አዘኔታ ለማሳየት ሳይችሉ ቀርተዋል። እንዲያውም ያን ሁሉ ነገር ሲናገሩ አንድ ጊዜም እንኳ ኢዮብን በስሙ አልጠሩትም። (ከኢዮብ 33:1, 31 ጋር አነጻጽር።) ኢዮብን እንደ ሰው ሳይሆን እንደ አንድ ችግር አድርገው እንደተመለከቱት ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ኢዮብ “ነፍሳችሁ በነፍሴ ቦታ ቢሆን ኖሮ”! በማለት እነዚህን ሰዎች በብስጭት መናገሩ ምንም አያስደንቅም። (ኢዮብ 16:4) በተመሳሳይም ዛሬ አንድን ሰው ለማበረታታት ስትፈልጉ ችግሩን ተረዱለት! በሰውየው ላይ አትፍረዱ። ሮሜ 14:4 እንደሚለው “አንተ በሌላው ሎሌ ላይ የምትፈርድ ማን ነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል።”
13, 14 . (ሀ) ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለማጽናናት የትኛውን መሠረታዊ እውነት ልናሳምናቸው ይገባል? (ለ) ዳንኤል በአንድ መልአክ አማካኝነት ብርታት ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?
13 ፓራካሌኦ የሚለው ቃል በ2 ተሰሎንቄ 2:16, 17 ላይ ‘መጽናኛ’ ተብሎም ተተርጉሟል፦ “ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የወደደን በጸጋም የዘላለምን መጽናናት በጎንም ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን ልባችሁን ያጽናኑት በበጎም ሥራና በቃል ሁሉ ያጽኑአችሁ።” ጳውሎስ የልባችንን መጽናናት ይሖዋ እንደሚወደን ከሚገልጸው መሠረታዊ እውነት ጋር እንዳያያዘው ልብ በሉ። ስለዚህ አስፈላጊውን እውነት አስረግጠን በመንገር አንዳችን ሌላውን ልናበረታታና ልናጽናና እንችላለን።
14 አንድ ጊዜ ነቢዩ ዳንኤል አንድ አስፈሪ ራእይ ካየ በኋላ በጣም በመረበሹ እንዲህ ብሏል፦ “ደም ግባቴም ወደ ማሸብሸብ ተለወጠብኝ፣ ኃይልም አጣሁ።” ይሖዋ አንድ መልአክ በመላክ ዳንኤል በአምላክ ፊት ‘እጅግ የተወደደ’ መሆኑን በተደጋጋሚ እንዲያሳስበው አድርጓል። ውጤቱስ ምን ሆነ? ዳንኤል መልአኩን “አበርትተኸኛል” ብሎታል።—ዳንኤል 10:8, 11, 19
15. ሽማግሌዎችና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ምስጋናንና እርማትን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መስጠት የሚኖርባቸው እንዴት ነው?
15 ስለዚህ ሌሎችን ለማበረታታት የምንችልበት ሌላው መንገድ ይህ ነው። አመስግኗቸው! ሰዎችን መንቀፍና በክፉ ዓይን ማየት በጣም ቀላል ነው። እርግጥ ነው፣ በተለይ ሽማግሌዎችና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እርማት መስጠታቸው አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ይሁን እንጂ ስህተት ፈላጊ ነው ከመባል ይልቅ ወዳጃዊ ማበረታቻ በመስጠት የሚታወቁ ቢሆን ጥሩ ይሆናል።
16. (ሀ) የመንፈስ ጭንቀት ያደረባቸውን ሰዎች ስናበረ ታታ ብዙውን ጊዜ በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ እንዲሳተፉ አጥብቆ መምከሩ ብቻ በቂ የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኤልያስ የመንፈስ ጭንቀት አድሮበት በነበረበት ጊዜ ይሖዋ የረዳው እንዴት ነው?
16 በተለይ የመንፈስ ጭንቀት ያደረባቸው ሰዎች ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ይሖዋ ደግሞ መሰል ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን በተለይ ሽማግሌዎች ከሆንን የእርዳታ ምንጭ እንድንሆን ይፈልጋል። (ምሳሌ 21:13) ምን ልናደርግ እንችላለን? መልሱ በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ እንዲያከናውኑ እንደ መንገር ያለ ቀላል ነገር ላይሆን ይችላል። ለምን? እንዲህ ብሎ መናገሩ፣ የመንፈስ ጭንቀት ያደረባቸው በበቂ ሁኔታ ባለማገልገላቸው የተነሣ ሆኖ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ስለሚችል ነው። ብዙውን ጊዜ ግን ምክንያቱ ይህ አይደለም። ነቢዩ ኤልያስ በአንድ ወቅት እጅግ ከመጨነቁ የተነሣ ሞትን ተመኝቶ ነበር፤ ይሁን እንጂ ይህ ስሜት ያደረበት በይሖዋ አገልግሎት በጣም ይዋከብ በነበረበት ጊዜ ነበር። ይሖዋ በዚህ ጊዜ ያደረገው ነገር ምን ነበር? ተግባራዊ እርዳታ ለመስጠት አንድ መልአክ ላከ። ኤልያስ የሞቱ አባቶቹን ያህል ምንም ዋጋ እንደሌለው ሆኖ እንደተሰማው፣ ሥራውን ሁሉ ውኃ እንደበላውና ሙሉ በሙሉ ብቻውን እንደቀረ በመግለጽ የልቡን ግልጥልጥ አድርጎ ለይሖዋ ነገረው። ይሖዋ ሰማው፤ እንዲሁም ኃይሉን በሚያሳዩ አስፈሪ መግለጫዎችና ኤልያስ ብቻውን እንዳልሆነና የጀመረው ሥራ ፍጻሜው ላይ እንደሚደርስ በሚጠቁሙ ማረጋገጫዎች አጽናናው። በተጨማሪም ይሖዋ ለኤልያስ የምታሠለጥነውና በመጨረሻም አንተን የሚተካህ ጓደኛ እሰጥሃለሁ ብሎ ቃል ገባለት።—1 ነገሥት 19:1–21
17. አንድ ሽማግሌ ራሱን ከመጠን በላይ የሚኮንንን ሰው ማበረታታት የሚችለው እንዴት ነው?
17 ምንኛ የሚያበረታታ ነው! እኛም እንደዚሁ የስሜት መረበሽ ያጋጠማቸውን በመካከላችን የሚገኙትን ሰዎች እናበረታታቸው። በጥሞና በማዳመጥ ችግራቸውን ለመረዳት ጥረት አድርጉ! (ያዕቆብ 1:19) በግል ከሚያስፈልጓቸው ነገሮች ጋር የሚጣጣም ቅዱስ ጽሑፋዊ ማጽናኛ ስጧቸው። (ምሳሌ 25:11፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14) ሽማግሌዎች ራሳቸውን ከሚገባው በላይ የሚኮንኑ ሰዎችን ለማበረታታት በደግነት መንፈስ ይሖዋ እንደሚወዳቸውና ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጣቸው የሚያሳይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ሊያቀርቡላቸው ይችላሉ።a ስለ ቤዛው አንስቶ መወያየቱ ምንም ዋጋ እንደሌላቸው የሚሰማቸውን ሰዎች ለማበረታታት የሚያስችል ጥሩ ውጤት ያለው መንገድ ሊሆን ይችላል። ቀደም ሲል በሠራው ኃጢአት ምክንያት በኀዘን ተደቁሶ የሚገኝ ሰው ከልቡ ንስሐ ገብቶና ከእንዲህ ዓይነቱ ልማድ ተመልሶ ከሆነ ቤዛው ከኃጢአቱ እንዳነጻው እንዲገነዘብ ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል።—ኢሳይያስ 1:18
18. አስገድዶ መድፈርን በመሰለ ድርጊት በሌላ ሰው ጥቃት የደረሰበትን ግለሰብ ለማበረታታት የቤዛውን ትምህርት በምን መንገድ መጠቀም ይገባል?
18 እርግጥ ነው፣ አንድ ሽማግሌ የሚሰጠውን ትምህርት በሚገባ ሊጠቀምበት እንዲችል ስለ ጉዳዩ በጥሞና ማሰብ አለበት። እስቲ አንድ ምሳሌ ተመልከት፦ ከማንኛውም ኃጢአት ለመንጻት እንዲቻል መቅረብ የነበረባቸው የእንስሳ መሥዋዕቶች ለኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥላ ሆነው አገልግለዋል። (ዘሌዋውያን 4:27, 28) ይሁን እንጂ ተገዳ የተደፈረች ሴት እንዲህ ዓይነት የኃጢአት መሥዋዕት ታቅርብ የሚል ደንብ አልነበረም። ሕጉ ሴቲቱን ለመቅጣት ‘ምንም ማድረግ እንደሌለባቸው’ ይናገራል። (ዘዳግም 22:25–27) ስለዚህ በዛሬው ጊዜ አንዲት እህት ጥቃት ደርሶባት ተገዳ ብትደፈርና በዚህም ሳቢያ እንደረከሰችና ምንም ዋጋ እንደሌላት ሆኖ ቢሰማት ከዚህ ኃጢአት ለመንጻት እንድትችል ቤዛው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ መግለጹ ተገቢ ነውን? በፍጹም አይደለም። ወንጀል ስለተፈጸመባት ኃጢአተኛ ልትሆን አትችልም። ኃጢአት የሠራውና መንጻት የሚያስፈልገው አስገድዶ የደፈራት ሰው ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋና ክርስቶስ ቤዛውን በማቅረብ ያሳዩት ፍቅር ሌላ ሰው በፈጸመው ኃጢአት በአምላክ ፊት እንዳልረከሰች ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ ውድ እንደሆነችና በፍቅሩ ውስጥ ታቅፋ እንደምትቀጥል ለማስገንዘብ እንደ ማስረጃ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።—ከማርቆስ 7:18–23ና ከ1 ዮሐንስ 4:16 ጋር አወዳድር።
19. ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር የምናደርገው ግንኙነት በሙሉ አበረታች ይሆናል ብለን መጠበቅ የሌለብን ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ ምን ቁርጥ ውሳኔ መውሰድ ይኖርብናል?
19 አዎን፣ አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ያለበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ያለፈውን ሕይወቱን ምንም ዓይነት መጥፎ ሁኔታዎች ቢያጨልሙትም በይሖዋ ሕዝብ ጉባኤ ውስጥ ማበረታቻ ማግኘት መቻል አለበት። እያንዳንዳችን በአንድነት በምንገናኝበት በማንኛውም ጊዜ እርስ በርስ ለመተያየት፣ እርስ በርስ ለመነቃቃትና እርስ በርስ ለመበረታታት የምንጥር ከሆነ ይህ ሰው መበረታታቱ አይቀርም። ይሁን እንጂ ፍጽምና የሌለን ሰዎች በመሆናችን ሁላችንም አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ሳናደርግ እንቀራለን። አልፎ አልፎ አንዳችን ሌላውን ቅር እንደምናሰኝና አልፎ ተርፎም አንዳችን ሌላውን እንደምንጎዳ የታወቀ ነው። ሌሎች በዚህ ረገድ ባላቸው ድክመት ላይ ላለማተኮር ጥረት አድርጉ። በድክመቶች ላይ የምታተኩሩ ከሆነ ጉባኤውን ከሚገባው በላይ የመተቸት አደጋ ሊጋረጥባችሁና አልፎ ተርፎም ጳውሎስ እንድንርቀው ብሎ በጠቀሰው ወጥመድ ውስጥ በመውደቅ አንድ ላይ የመሰብሰብን ልማድ ልትተዉ ትችላላችሁ። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በፍጹም አይድረስብን! ይህ አሮጌ ሥርዓት ከምንጊዜውም በበለጠ አደገኛና አስቸጋሪ እየሆነ ሲሄድ በስብሰባዎቻችን ላይ የምናደርገው ግንኙነት ገንቢ እንዲሆን የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ ይልቁንም የይሖዋ ቀን ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንድ ሽማግሌ “ከማይገባህ ደግነት ጥቅም ታገኛለህን?” እንዲሁም “የመንፈስ ጭንቀትን ለማስወገድ በሚደረገው ውጊያ አሸናፊ መሆን” የሚሉትን 4–111 እና 5–111 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኙትን ርዕሶች የመሰሉ የሚያበረታቱ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! ርዕሶችን ከእንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ ጋር ለማጥናት ይመርጥ ይሆናል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች ስብሰባዎቻችንና አንድ ላይ ሆነን የምናሳልፋቸው ጊዜያት አበረታች መሆናቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ እርስ በርስ መተያየት ማለት ምን ማለት ነው?
◻ እርስ በርስ መነቃቃት ማለት ምን ማለት ነው?
◻ እርስ በርስ መበረታታት ምን ነገርንም ይጨምራል?
◻ የመንፈስ ጭንቀት ያደረባቸውንና ቅስማቸው የተሰበረ ሰዎችን ማበረታታት የሚቻለው እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንግዳ ተቀባይነት እርስ በርሳችን ይበልጥ መተዋወቅ እንድንችል ይረዳናል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤልያስ የመንፈስ ጭንቀት አድሮበት በነበረበት ወቅት ይሖዋ በደግነት መንፈስ አጽናንቶታል