የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ግሪንላንድ ውስጥ ወዳሉት ርቀው የሚገኙ አነስተኛ መንደሮች መድረስ
የይሖዋ ምሥክሮች ለአያሌ አሥርተ ዓመታት ምሥራቹን ሲሰብኩ በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ሲጠቀሙ ቆይተዋል። እነዚህ መጽሔቶች የራሱ ቃል በሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የይሖዋን ጥበብ ያጎላሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር የሚዛመዱ ሁኔታዎችን ነቅተው ይከታተላሉ፤ እንዲሁም በጊዜያችን ለሚገኙ ችግሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክንያታዊ የሆነ ምክር ይለግሳሉ።—ያዕቆብ 3:17 አዓት
በግሪንላንድ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በ1994 በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ለማበርከት ልዩ ጥረት አድርገው ነበር። በበጋው ወቅት ግሪንላንድ ውስጥ ራቅ ብለው ከሚገኙት ትንንሽ መንደሮች መካከል አንዳንዶቹን ለመጎብኘት ዝግጅት አደረጉ። አንድ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቡድን በምድር ሰሜናዊ ጫፍ ከሚኖሩት ማኅበረሰቦች መካከል ወደ አንዳንዶቹ ለመድረስ በምዕራባዊው የባሕር ዳርቻ አድርጎ ወደ ግራናርግ (ቱሌ) ከ4,000 ኪሎ ሜትር በላይ በጀልባ ተጓዘ። ጉዞው ሰባት ሳምንታት ወስዶባቸው ነበር። በሰሜን የባሕር ዳርቻ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ኢዶርግሮርዶርሜት ውስጥ ወደሚገኘው አነስተኛ መንደር ደረሱና ምሥራቹን በዘዴ በመስበክ ክልሉን ሙሉ ለሙሉ ሸፈኑት።
ከአንድ ዓመት በፊት በሚያዝያ ወር ውስጥ 7,513 የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! ቅጂዎች ለግሪንላንድ ነዋሪዎች ተበርክቶ ነበር። ይኸውም 127 የመንግሥቱ አስፋፊዎች እያንዳንዳቸው በአማካይ 59 መጽሔቶች አበርክተዋል ማለት ነው። ለየሰባቱ የግሪንላንድ ነዋሪዎች አንድ መጽሔት ይደርሳቸዋል። በዚያ ወር ንቁ! “የሁሉም ሴቶች ስጋት የሆነው የጡት ካንሰር” በሚል የሽፋን ርዕስ ሥር ተከታታይ ርዕሶች አውጥቶ ነበር። 140 መጽሔቶችን ያበረከተች አንዲት የይሖዋ ምሥክር የዚህን ንቁ! መጽሔት ቅጂ ለአንዲት የቴሌቪዥን ሪፖርተር ሰጠቻት። ከሁለት ቀናት በኋላ አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም የጡት ካንሰርን በተመለከተ የወጡትን ርዕሰ ትምህርቶች አቀረባቸው። ሪፖርተሯ የግሪንላንዲክ ትርጉሙን ጥራት በማድነቅ ብዙዎቹን የመጽሔቱን ገጾች በቴሌቪዥን አሳየች። በተጨማሪም በንቁ! መጽሔት የተሰጡትን ጤንነትን ከበሽታ ለመከላከል የሚያስችሉ ጠቃሚ ምክሮች ጎላ አድርጋ ገልጻ ነበር።
መጽሔቶቹን መጀመሪያ ለሪፖርተሯ ያበረከተችላት የይሖዋ ምሥክር በዚሁ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ቃለ መጠይቅ ተደረገላት። የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ለብዙ ጥያቄዎች መልስ ከመስጠቷም በተጨማሪ በዚያ ወር በሰፊው ስለተሰራጩት መጽሔቶችም ተናገረች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው ተግባራዊ ጥበብ ሐሳብ ከመስጠቷም በላይ እንዲህ ያለው ምክንያታዊ ምክር በጊዜያችን ያሉትን ችግሮች ተቋቁሞ ለማለፍ እንደሚረዳን ግልጽ አድርጋለች።
ፕሮግራሙ የተጠናቀቀው ለግሪንላንዲክ ካንሰር ማኅበር ፕሬዚደንት ቃለ መጠይቅ በማድረግ ነበር። ፕሬዚደንቷ ይህን ርዕስ በተመለከተ በቋንቋዋ እንደዚህ ያለ ግሩምና አዲስ ሐሳብ የሚገኝበት ጽሑፍ ፈጽሞ አይታ እንደማታውቅ ተናገረች። ከዚያም የጡት ካንሰርን በተመለከተ ለማወቅ የሚፈልጉ ሁሉ የንቁ! መጽሔትን ርዕሰ ትምህርቶች እንዲያነቡ ጋበዘች። በራሳቸው አነሳሽነት ላደረጉት ጥረት የይሖዋ ምሥክሮችን ለማመስገን የሚያስችል በቂ ምክንያት እንዳለ ተናገረች።
በግሪንላንድ እንደሚገኙት ሁሉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም ‘ከሰማይ በታች ላለው ፍጥረት ሁሉ’ ምሥራቹን መስበክ ቀጥለዋል። (ቆላስይስ 1:23፤ ሥራ 1:8) መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔትን ጨምሮ በሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በመጠቀም ሁሉም ዓይነት ሰዎች በጊዜያችን ያሉትን ችግሮች ተቋቁመው እንዲወጡ ይረዷቸዋል፤ እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ወደፊት የተሻለ ሕይወት እንደሚያገኙ ተስፋ ይሰጧቸዋል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ግራናርግ (ቱሌ)
ኢዶርግሮርዶርሜት
ኑክ (ጎድዛብ)