ድነሃልን?
ጆኒ የአሥር ዓመት ልጅ ሳለ በአንድ የንግድ ትርኢት ላይ አንድ ሰው አስቆመውና “አንተ ወጣት ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ጌታህና አዳኝህ አድርገህ ትቀበለዋለህ?” ብሎ ጠየቀው። ጆኒ ቀድሞም በኢየሱስ ያምን ስለነበር ጥያቄው እንግዳ ሆነበት። ስለዚህ “እቀበላለሁ” ብሎ መለሰ። ሰውዬው ድምፁን ከፍ አድርጎ “ጌታ ይመስገን! ክርስቶስ ሌላ የዳነ ነፍስ አገኘ!” በማለት ተናገረ።
በእርግጥ መዳን እንደዚህ ቀላል ነውን? ጆኒ በተቀረው ሕይወቱ ምንም ዓይነት ነገር ቢፈጽም እነዚያን ቃላት ከተናገረበት ጊዜ ጀምሮ “ድኗልን”? አያሌ ቅን ሰዎች አዎን ብለው ይመልሱ ይሆናል። አንዳንድ ሃይማኖታዊ ትራክቶች “የዳንክበትን” ቀን ለማስታወስ እንድትችል ቀኑን እንድትጽፈው ሐሳብ ያቀርባሉ።
አንድ ቄስ “ማንኛውም ሰው ክርስቶስን ተቀብዬአለሁ ብሎ በተናገረበት ቅጽበት ውስጥ . . . የወደፊት ዕጣ ፈንታው ይወሰናል” በማለት ጽፈዋል። አንድ ሰው ለመዳን “አምናለሁ የሚል ቃል አንድ ጊዜ ብቻ ከተናገረ በቂ ነው፤ የግድ በእምነቱ መጽናት አያስፈልገውም” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል ሲሉ ገልጸዋል። ሌላ ሃይማኖታዊ ጸሐፊ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ይህ ያለቀለት ነገር ነው። አንዴ ከዳንክ ሌላ ምንም የሚያስፈልግ ነገር የለም . . . ‘የምታደርገው ተጋድሎ አብቅቷል።’ ‘ኃጢአትህ ተሰርዮአል።’” ሆኖም ሌላው ቀርቶ ይህ እውነት እንደሆነ ጽኑ እምነት ያላቸው ሰዎች እንኳ እዚህ ላይ ችግር እንዳለ ሊመለከቱ ይችላሉ። “እንደ ዳኑ” የተነገራቸው ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዛቸውን ነገር በተግባር እንደማያውሉ በግልጽ ይታያል። ብዙውን ጊዜ ለዚህ የሚሰጠው ሰበብ ምናልባት ክርስቶስን ከልባቸው “አልተቀበሉት” ይሆናል የሚል ነው።
ታዲያ ኢየሱስን “መቀበል” ማለት ምን ማለት ነው? “ተቀብዬአለሁ” ብሎ መናገር ነው ወይስ የማያቋርጥ የአኗኗር መንገድ? የእምነታችን ጥንካሬ ለተግባር ሊያንቀሳቅሰን የሚችል መሆን አለበትን? ኢየሱስን መከተል የሚጠይቅብንን ኃላፊነት ገሸሽ አድርገን መሥዋዕቱ ያስገኛቸውን ጥቅሞች ብቻ መቀበል እንችላለንን?
ብዙ ሰዎች ኢየሱስን መከተልና መታዘዝ የሚያመጣቸውን ኃላፊነቶች መቀበል አይሹም ነገር ግን በረከቶቹን ማግኘት ይፈልጋሉ። እንዲያውም “መታዘዝ” የሚለው ቃል ይረብሻቸዋል። ሆኖም ኢየሱስ ‘ተከተሉኝ’ ብሏል። (ሉቃስ 18:18-23) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለጌታችን ኢየሱስ . . . ወንጌል የማይታዘዙት በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ’ ይላል።—2 ተሰሎንቄ 1:8-10፤ ማቴዎስ 10:38፤ 16:24
መጽሐፍ ቅዱስ መዳንን በተመለከተ በተሰጡት ትምህርቶች ላይ ከባድ ጥያቄዎች የሚያስነሱ ብዙ ነገሮች ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ርዕስ ምን እንደሚናገር ለማወቅ የምትፈልግ ከሆነ የሚቀጥሉት ገጾች የሚያስደስቱ ሆነው ታገኛቸዋለህ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ይህንን አንገብጋቢ ጉዳይ በተመለከተ ምን እንዳስተማሩ ለማወቅ የተጠቀሱትን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስህ አውጥተህ አንብብ።