የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 2/1 ገጽ 4-8
  • ለመዳን ምን ማድረግ አለብን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለመዳን ምን ማድረግ አለብን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኢየሱስን መከተል
  • እምነት ለሥራ ያነሳሳል
  • ኢየሱስ ራሱ የተናገራቸው መልእክቶች
  • ክርስቲያናዊ ቅንዓት
  • ‘የአምላክ ቃል ሕያው ነው’
  • ኢየሱስ ያድናል—እንዴት?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • መጽሐፍ ቅዱስ ‘አንዴ የዳነ ለሁልጊዜው እንደዳነ’ ያስተምራል?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • መዳን በእርግጥ ምን ማለት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • መዳን ምንድን ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 2/1 ገጽ 4-8

ለመዳን ምን ማድረግ አለብን?

በአንድ ወቅት አንድ ሰው ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን?” ሲል ጠይቆት ነበር። ምን ብሎ መለሰ? ‘እኔን እንደ ጌታና አዳኝህ አድርገህ ከተቀበልከኝ ትድናለህ’ አለውን? አላለውም! ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ እላችኋለሁና፣ ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ አይችሉምም።”—ሉቃስ 13:23, 24

ኢየሱስ ለሰውዬው ጥያቄ መልስ አልሰጠምን? ጥያቄውን መልሶለታል። የሰውዬው ጥያቄ መዳን ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ሳይሆን የሚድኑት ሰዎች ጥቂት መሆናቸውንና አለመሆናቸውን ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ይህንን አስደናቂ በረከት ለማግኘት የሚጣጣሩ ሰዎች አንድ ሰው ከሚጠብቀው ያነሰ ቁጥር እንዳላቸው ጠቁሟል።

አንዳንድ አንባብያን ‘እኔ የማውቀው እንደዚህ አይደለም’ በማለት ተቃውሟቸውን ያቀርቡ ይሆናል። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል” በማለት የሚናገረውን ዮሐንስ 3:16ን ሊጠቅሱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ መልሳችን የሚከተለው ነው፦ ‘ለመዳን ማመን ያለብን ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ በእርግጥ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን ነውን? አዎን። የአምላክ ልጅ መሆኑን ነውን? ይህንንም ማመን ያስፈልገናል! መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “መምህር” እና “ጌታ” ብሎ ስለሚጠራው ያስተማረውን ማመን፣ እርሱን መታዘዝና መከተል የለብንምን?’—ዮሐንስ 13:13፤ ማቴዎስ 16:16

ኢየሱስን መከተል

ችግር የሚፈጠረው እዚህ ላይ ነው! “እንደ ዳኑ” የተነገራቸው ብዙዎቹ ሰዎች ኢየሱስን የመከተልም ሆነ የመታዘዝ ዝንባሌ የሌላቸው መሆኑ ነው። እንዲያውም አንድ የፕሮቴስታንት ቄስ “እርግጥ ነው፣ በክርስቶስ ላይ ያለን እምነት መቀጠል አለበት። ነገር ግን እምነታችን በምንም ዓይነት መቋረጥ የለበትም ወይም የግድ የሚቀጥል መሆን ይኖርበታል የሚለው አባባል ፈጽሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የለውም” በማለት ጽፈዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ግን “ድነናል” ብለው በሚያስቡ አንዳንድ ሰዎች ዘንድ የተለመዱ ሥነ ምግባራዊ ውስልትናዎችን ይዘረዝራል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ መንገድ መመላለሱን የሚቀጥለውን ሰው በተለመከተ “ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት” በማለት ክርስቲያኖችን ያዝዛል። አምላክ ንብረቱ የሆነውን የክርስቲያን ጉባኤ መጥፎ ሰዎች እንዲበክሉት አይፈልግም!—1 ቆሮንቶስ 5:11-13

እንግዲያው ኢየሱስን መከተል ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ልንከተለው እንችላለን? ኢየሱስ ያደረገው ምንድን ነበር? ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው ነበርን? ዘማዊ ነበርን? ሰካራም ነበርን? ውሸታም ነበርን? በሥራው እምነት አጉዳይ ነበርን? በፍጹም አልነበረም! ‘ሆኖም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ማስወገድ አለብኝን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ለመልሱ ከኤፌሶን 4:17 እስከ 5:5 ያለውን አንብብ። ይህ ጥቅስ ተግባራችን ምንም ይሁን ምን አምላክ ይቀበለናል አይልም። ከዚህ ይልቅ እንደሚከተሉት ያሉትን ከሚያደርጉ ዓለማዊ ሰዎች የተለየን እንድንሆን ይነግረናል፦ “ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ . . . እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም . . . ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ . . . የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ . . . ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ . . . ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኩስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም።”

እርሱ ከተወልን ምሳሌ ጋር ተስማምተን ለመኖር ትንሽ እንኳ ሙከራ የማናደርግ ከሆነ እርሱን እየተከተልን ነው ማለት እንችላለንን? የክርስቶስ ዓይነት ሕይወት እንዲኖረን ጥረት ማድረግ የለብንምን? “ምንም ለውጥ ሳታደርጉ አሁኑኑ ወደ ክርስቶስ ኑ” ብሎ እንደተናገረው አንድ ሃይማኖታዊ ትራክት ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ይህንን አንገብጋቢ ጥያቄ ችላ ብለውታል።

ከኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ እነዚህ ከአምላክ የራቁ ሰዎች “የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ” በማለት አስጠንቅቋል። (ይሁዳ 4) እኛስ የአምላክን ምሕረት ‘በሴሰኝነት ልንለውጥ’ የምንችለው እንዴት ነው? የኢየሱስ መሥዋዕት ልናስወግዳቸው የምንጥረውን ፍጹም ባለመሆናችን የተነሳ የምንሠራቸውን ኃጢአቶች ብቻ ሳይሆን ሆን ብለን የምንሠራቸውን ኃጢአቶች እንደሚሸፍንልን አድርገን በማሰብ የአምላክን ምሕረት በሴሰኝነት ልንለውጥ እንችላለን። “ሕይወታችንን መለወጥ፣ መጥፎ ልማዶቻችንን መተው ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ጋር መስማማት አያስፈልገንም” ብለው ከተናገሩት በአሜሪካ ውስጥ በጣም ታዋቂ ከሆኑት ወንጌላውያን መካከል አንዱ ከሆኑት ሰው ጋር መስማማት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው።—ከሥራ 17:30፤ ከሮሜ 3:25​ና ከያዕቆብ 5:19, 20 ጋር አነጻጽር።

እምነት ለሥራ ያነሳሳል

ብዙ ሰዎች “በኢየሱስ ማመን” ብቻ ስለሚበቃ እምነታችን ለመታዘዝ እስከሚገፋፋን ድረስ ጠንካራ መሆን አያስፈልገውም ብለው ያምናሉ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ አባባል አይስማማም። ኢየሱስ በክርስትና መንገድ መመላለስ የጀመሩ ሰዎች ድነዋል አላለም። ከዚህ ይልቅ “እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል” ብሏል። (ማቴዎስ 10:22) መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን በመጨረሻ የመዳን ሽልማት ከሚያስገኝ የሩጫ ውድድር ጋር ያመሳስለዋል። በተጨማሪም ይህን ሽልማት “ታገኙ ዘንድ ሩጡ” በማለት ይመክራል።—1 ቆሮንቶስ 9:24

ስለዚህ “ኢየሱስን መቀበል” ማለት የኢየሱስ መሥዋዕት ያስገኛቸውን ወደር የሌላቸው በረከቶች መቀበል ብቻ አይደለም። ታዛዥነት ያስፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ፍርድ ‘ከእግዚአብሔር ቤት’ እንደሚጀምር ከተናገረ በኋላ “አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን?” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 4:17 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ስለዚህ እንዲሁ ከመስማትና ከማመን የበለጠ ነገር ማድረግ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ራሳችንን እያሳትን የምንሰማ ብቻ ሳንሆን ቃሉን የምናደርግ’ መሆን እንዳለብን ይናገራል።—ያዕቆብ 1:22

ኢየሱስ ራሱ የተናገራቸው መልእክቶች

የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው የራእይ መጽሐፍ በዮሐንስ አማካኝነት ለሰባት የጥንት ክርስቲያን ጉባኤዎች የተላለፉ የኢየሱስ መልእክቶችን ይዟል። (ራእይ 1:1, 4) የእነዚህ ጉባኤዎች አባላት ኢየሱስን “ተቀብለውት” ስለነበር እኔን “ስለተቀበላችሁ” ሌላ የሚያስፈልግ ነገር የለም አላቸውን? አላላቸውም። ሥራዎቻቸውን፣ ጥረታቸውንና ጽናታቸውን በተመለከተ ምስጋና ካቀረበ በኋላ ስለ ፍቅራቸው፣ ስለ እምነታቸውና ስለ አገልግሎታቸው ተናግሯል። ቢሆንም ዲያብሎስ እንደሚፈትናቸውና ‘እያንዳንዳቸው እንደ ሥራቸው በመቀበል’ እንደሚካሱ ነግሯቸዋል።—ራእይ 2:2, 10, 19, 23

በአንድ ሃይማኖታዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የነበሩ ሰዎች ኢየሱስን “ተቀብለናል” ብለው ሲናገሩ ወዲያውኑ መዳናችሁ “ተረጋግጧል” የሚል ማስተማመኛ ተሰጥቷቸው ነበር። በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች የተገነዘቡት ነገርና ኢየሱስ ከላይ የገለጸው ሐሳብ ፈጽሞ አይገናኝም። ኢየሱስ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ [“ሳያቋርጥ ይከተለኝ” አዓት]። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል” ብሏል።—ማቴዎስ 16:24, 25

ራስን መካድ? ኢየሱስን ሳያቋርጡ መከተል? ይህ ጥረት ይጠይቃል። እንዲህ ማድረጉ ሕይወታችንን ይለውጠዋል። ሆኖም ኢየሱስ ሌላው ቀርቶ አንዳንዶቻችን ‘ነፍሳችንን እንደምናጣ’ ይኸውም ለእርሱ ስንል ልንሞት እንደምንችል እየተናገረ ነውን? አዎን፣ እንዲህ ዓይነቱ እምነት የሚገኘው የአምላክን ቃል በማጥናት ልናውቃቸው ከምንችላቸው ታላላቅ ነገሮች ብቻ ነው። ይህም ‘ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ መቃወም ያቃታቸው’ ሃይማኖታዊ አክራሪዎች እስጢፋኖስን በድንጋይ በወገሩት ጊዜ ታይቷል። (ሥራ 6:8-12፤ 7:57-60) በጊዜያችንም በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ኅሊናቸውን ከማቆሸሽ ይልቅ በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ መሞት የመረጡ በመቶ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ እምነት አሳይተዋል።a

ክርስቲያናዊ ቅንዓት

ክርስቲያናዊ እምነታችን እንዳይጠፋ አጥብቀን መጠበቅ አለብን፤ ምክንያቱም በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያኖች ወይም ሃይማኖታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ከምትሰማው በተለየ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ልንወድቅ እንደምንችል ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ቅን ከሆነው መንገድ’ ስለወጡ ክርስቲያኖች ይናገራል። (2 ጴጥሮስ 2:1, 15) በዚህ የተነሳ ‘የራሳችንን መዳን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ መፈጸም’ ያስፈልገናል።—ፊልጵስዩስ 2:12፤ 2 ጴጥሮስ 2:20

የኢየሱስንና የደቀ መዛሙርቱን ትምህርት ያዳመጡት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ይህንን ጉዳይ የተመለከቱት በዚህ መንገድ ነውን? አዎን። ማድረግ ያለባቸው ነገር እንዳለ ያውቁ ነበር። ኢየሱስ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሎ ነበር።—ማቴዎስ 28:19, 20

ኢየሱስ ይህንን ከተናገረ ከሁለት ወር በኋላ በአንድ ቀን ብቻ 3,000 ሰዎች ተጠመቁ። ከዚያም የአማኞች ቁጥር በፍጥነት ወደ 5,000 ከፍ አለ። ያመኑት ሰዎች ሌሎችን ያስተምሩ ነበር። በስደት ምክንያት መበታተናቸው መልእክቱን ከማሰራጨት ሌላ ያስከተለው ነገር የለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይህንን ያደረጉት ጥቂት መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ‘የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞረዋል።’ በዚህ የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹ ‘ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ እንደተሰበከ’ 30 ከሚያህሉ ዓመታት በኋላ ለመጻፍ ችሏል።—ሥራ 2:41፤ 4:4፤ 8:4፤ ቆላስይስ 1:23

ጳውሎስ አንዳንድ የቴሌቪዥን ወንጌላውያን እንደሚያደርጉት ‘ኢየሱስን አሁኑኑ ተቀበልና ለዘላለም ዳን’ በማለት ሃይማኖት እንዲቀይሩ የሚያደርግ አልነበረም። ወይም ደግሞ “ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ ነው የዳንኩት” ብለው እንደጻፉት አሜሪካዊ ቄስ ያለ ትምክህት አልነበረውም። ጠንካራ ሠራተኛ የነበረው ጳውሎስ የክርስትናን መልእክት ለሰዎች ሁሉ እንዲያደርስ ኢየሱስ በቀጥታ ከመረጠው ከ20 ዓመታት በኋላ “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ” በማለት ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 9:27፤ ሥራ 9:5, 6, 15

መዳን ከአምላክ የሚገኝ ስጦታ ነው። የሥራችን ዋጋ ሆኖ የሚከፈል ነገር አይደለም። ቢሆንም የበኩላችንን ጥረት እንድናደርግ ይጠይቅብናል። አንድ ሰው ውድ ዋጋ ያለው ስጦታ ቢሰጥህና አንተ ግን ከአድናቆት ጉድለት የተነሳ ስጦታውን ተቀብለህ ባትወስደው አመስጋኝ አለመሆንህ ሰውዬው ስጦታውን ወስዶ ለሌላ ሰው እንዲሰጥ ሊገፋፋው ይችላል። የኢየሱስ ክርስቶስ ደመ ሕይወት ምን ያህል ውድ ነው? የማይከፈልበት ስጦታ ቢሆንም ለዚህ ስጦታ ጥልቅ አድናቆት ማሳየት አለብን።

እውነተኛ ክርስቲያኖች በአምላክ ፊት ተቀባይነት ስላላቸው መዳን በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ናቸው። በቡድን ደረጃ ሲታዩ መዳናቸው የተረጋገጠ ነው። በግለሰብ ደረጃ አምላክ የሚፈልግባቸውን ነገሮች ማሟላት አለባቸው። ቢሆንም ኢየሱስ “በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል” በማለት ስለተናገረ ልንወድቅ እንችላለን።—ዮሐንስ 15:6

‘የአምላክ ቃል ሕያው ነው’

ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ሁለት ሰዎች የተነጋገሩት 60 ከሚያክሉ ዓመታት በፊት ነው። ጆኒ መዳን ሊገኝ የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ብቻ እንደሆነ አሁንም ያምናል፤ ሆኖም ይህንን መዳን ለማግኘት መጣጣር እንዳለብን ተገንዝቧል። መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛውን እውነተኛ ተስፋ ለሰው ልጅ የሚሰጠው ማን እንደሆነ የሚጠቁም መጽሐፍ እንደሆነ ያምናል። ከዚህም በላይ ይህንን አስደናቂ መጽሐፍ ማጥናት፣ መጽሐፉ የሚለውን ተግባራዊ ማድረግ፤ እንዲሁም አፍቃሪ፣ እምነት ያለን፣ ደግ፣ ታዛዥና ጽኑ እንድንሆን እንዲገፋፋን ማድረግ እንዳለብን ያምናል። ልጆቹን በዚህ መጽሐፍ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ አድርጎ ያሳደጋቸው ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እነርሱም ልጆቻቸውን በተመሳሳይ ሁኔታ ሲያሳድጉ ማየቱ ያስደስተዋል። ሁሉም ሰው እንዲህ ያለ እምነት እንዲኖረው ከመመኘቱም በላይ ይህንን በሌሎች ሰዎች ልብና አእምሮ ውስጥ ለመትከል የቻለውን ያህል ይጥራል።

ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተነሳስቶ ‘የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው’ በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 4:12) ሕይወትን ሊለውጥ ይችላል። ከልብህ የመነጨ የፍቅር፣ የእምነትና የታዛዥነት ተግባር እንድታከናውን ሊያነሳሳህ ይችላል። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን “መቀበል” ብቻ አይበቃም። አጥናው እንዲሁም ያጠናኸውን በተግባር ላይ ለማዋል እንዲያንቀሳቅስህ ፍቀድለት። በውስጡ ያለው ጥበብ እንዲመራህ ፍቀድለት። 5,000,000 የሚያክሉ በፈቃደኝነት የሚያገለግሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ያለ ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናሉ። ከዚህ ጥናት ምን ልትማር እንደምትችል ለማወቅ ከፈለግህ ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች ጻፍ። የምታገኘው እምነትና መንፈሳዊ ጥንካሬ ያስደስትሃል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዶክተር ክርስቲን ኢ ኪንግ ዘ ናዚ ስቴት ኤንድ ዘ ኒው ሪሊጅንስ፤ ፋይቭ ኬዝ ስተዲስ ኢን ነን ኮንፎርሚቲ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “በጀርመን ከሚገኙ ሁለት [የይሖዋ] ምሥክሮች አንዱ የታሰረ ሲሆን ከአራቱ አንዱ ተገድሏል” ብለዋል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘ስለ እምነት በብርቱ መጋደል’ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው ይሁዳ የተጻፈው ‘ለኢየሱስ ክርስቶስ ተጠብቀው ለተጠሩ’ ነው። ‘ኢየሱስን ስለ ተቀበሉ’ መዳናቸው ተረጋግጧል ማለቱ ነውን? አይደለም፣ ይሁዳ እነዚህን ክርስቲያኖች ‘ስለ እምነት በብርቱ ተጋደሉ’ ብሏቸዋል። እንደዚህ ማድረግ ያስፈለገበትን ሦስት ምክንያቶች አቅርቦላቸዋል። በመጀመሪያ ደረጃ አምላክ ‘ሕዝቡን ከግብጽ አገር ቢያድንም’ ብዙዎቹ ከጊዜ በኋላ ወድቀዋል። በሁለተኛ ደረጃ መላእክት እንኳ ዓምፀው አጋንንት ሆነዋል። በሦስተኛ ደረጃ አምላክ ሰዶምና ገሞራ ውስጥ ይፈጸም በነበረው የከፋ የጾታ ብልግና የተነሳ እነዚህን ከተሞች አጥፍቷቸዋል። ይሁዳ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች “[የማስጠንቀቂያ አዓት] ምሳሌ” አድርጎ አቅርቧቸዋል። አዎን፣ ሌላው ቀርቶ ‘ለኢየሱስ ክርስቶስ የተጠበቁት’ እንኳ ከእውነተኛው እምነት እንዳይወድቁ መጠንቀቅ አለባቸው።—ይሁዳ 1-7 የ1980 ትርጉም

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ትክክለኛው የትኛው ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት ይጸድቃል’ ይላል። በተጨማሪም ‘ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ ይጸድቃል’ በማለት ይናገራል። ትክክለኛው የትኛው ነው? የምንጸድቀው በእምነት ነው ወይስ በሥራ?—ሮሜ 3:28፤ ያዕቆብ 2:24

ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው እርስ በርሱ የሚስማማ መልስ ሁለቱም አባባል ትክክል እንደሆኑ ያሳያል።

አምላክ በሙሴ በኩል የሰጠው ሕግ አይሁዳውያን አምላኪዎች ተለይተው የታዘዙ መሥዋዕቶችንና መባዎችን እንዲያቀርቡ፣ በዓላትን እንዲያከብሩ እንዲሁም ከአመጋገብና ከሌሎች ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ለብዙ መቶ ዓመታት ጠይቆባቸው ነበር። እንደነዚህ ያሉ ‘የሕግ ሥራዎች’ ወይም ‘ሥራዎች’ ኢየሱስ ፍጹም መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ አስፈላጊነታቸው አክትሟል።—ሮሜ 10:4

ሆኖም በሙሴ ሕግ ሥር ይፈጸሙ የነበሩ እነዚህ ሥራዎች ተወዳዳሪ በሌለው የኢየሱስ መሥዋዕት መተካታቸው የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ችላ ማለት እንችላለን ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ . . . ለሕያው አምላክ ቅዱስ አገልግሎት ታቀርቡ ዘንድ ከሞቱ [ከአሮጌ] ሥራዎች ሕሊችሁን ያነጻ ይሆን?” ይላል።—ዕብራውያን 9:14

‘ለሕያው አምላክ ቅዱስ አገልግሎት የምናቀርበው’ እንዴት ነው? የሥጋ ሥራዎችን መዋጋት፣ የዓለም የሥነ ምግባር ውስልትና እንዳይጋባብን መከላከልና ከወጥመዶቹ መራቅ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠን ምክሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። “መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፣” “ቶሎ የሚከበንን ኃጢአት” አስወግድ እንዲሁም ‘ኢየሱስን ተመልክተህ፣ በፊትህ ያለውን ሩጫ በትዕግሥት ሩጥ’ ይለናል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘በነፍሳችን ዝለን እንዳንወድቅ’ ይመክረናል።—1 ጢሞቴዎስ 6:12፤ ዕብራውያን 12:1-3፤ ገላትያ 5:19-21

አንድ ሰው ማድረግ የሚፈለግበትን በማሟላት ይህንን አስገራሚ በረከት ማግኘት ስለማይችል መዳን የምናገኘው እነዚህን ነገሮች በመፈጸማችን አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጹትን አምላክና ክርስቶስ እንድናደርጋቸው የሚፈልጉብንን ነገሮች በማድረግ ፍቅራችንንና ታዛዥነታችንን ካላሳየን ይህንን ታላቅ ስጦታ አናገኝም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው” በማለት ስለሚናገር እምነታችንን በሥራ ሳናሳይ ኢየሱስን እንደምንከተል ብንናገር ዋጋ የለውም።—ያዕቆብ 2:17

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን አጥና፤ የተማርከውን በተግባር ላይ ለማዋል እንዲያንቀሳቅስህም ፍቀድለት

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ