የአምላክን መንግሥት ምንነት አስተውላችኋልን?
“በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው።”—ማቴዎስ 13:23
1. ሰዎች ስለ ‘መንግሥተ ሰማያት’ ያሏቸው አንዳንድ የተለመዱ እምነቶች የትኞቹ ናቸው?
የአምላክን መንግሥት ምንነት ‘አስተውላችኋልን?’ ባለፉት መቶ ዘመናት ሰዎች ‘መንግሥተ ሰማያትን’ በተመለከተ በጣም የተለያዩ አመለካከቶች ነበሯቸው። በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባሎች ዘንድ ያለው የተለመደ እምነት የአምላክ መንግሥት አንድ ግለሰብ ወደ ክርስትና እምነት በሚለወጥበት ጊዜ አምላክ በልቡ ውስጥ የሚያሳድርበት ነገር ነው የሚል ነው። ሌሎች ደግሞ ጥሩ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ዘላለማዊ ተድላና ደስታ ለማግኘት የሚሄዱበት ቦታ እንደሆነ ያምናሉ። ክርስቲያናዊ ትምህርቶችንና ልማዶችን በማኅበራዊና መንግሥታዊ ጉዳዮች ውስጥ በማስገባት ይህን መንግሥት በምድር ላይ የማቋቋሙን ሥራ አምላክ ለሰዎች ትቶላቸዋል የሚሉም አልታጡም።
2. መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን መንግሥት የሚገልጸው እንዴት አድርጎ ነው? የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?
2 ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ የሚገኝ አንድን ተቋም እንደማያመለክት በግልጽ ያሳያል። በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት የአንድ ሰው የልብ ሁኔታ ወይም የሰብዓዊ ኅብረተሰብ ወደ ክርስትና እምነት መለወጥ ማለት አይደለም። እርግጥ በአምላክ መንግሥት የሚያምኑ ሰዎች ስለዚህ መንግሥት ትክክለኛ እውቀት ሲያገኙ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ለውጦችን ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ ይህ መንግሥት የአምላክን ፈቃድ የሚያስፈጽም፣ ኃጢአትና ሞት ያስከተሏቸውን ችግሮች የሚያስወግድና በምድር ላይ የጽድቅ ሁኔታዎች እንዲሰፍኑ የሚያደርግ አምላክ ያቋቋመው ሰማያዊ መስተዳድር ነው። በአሁኑ ወቅት ይህ መንግሥት በሰማይ ሥልጣን የያዘ ሲሆን በቅርቡ ‘እነዚያን [ሰብዓዊ] መንግሥታት ሁሉ ይፈጫቸዋል ያጠፋቸውማል፣ ለዘላለምም ይቆማል።’—ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 11:15፤ 12:10
3. ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲጀምር ለሰው ልጆች ምን አጋጣሚ ተከፍቶላቸው ነበር?
3 ታሪክ ጸሐፊው ኤች ጂ ዌልስ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “የኢየሱስ ዋነኛ ትምህርት የነበረውና በክርስትና እምነት ውስጥ ግን በጣም አነስተኛ ቦታ የተሰጠው የዚህ የመንግሥተ ሰማያት መሠረተ ትምህርት እስካሁን ድረስ የሰውን አስተሳሰብ ከቀሰቀሱትና ከለወጡት ከፍተኛ ለውጥ ካስከተሉ መሠረተ ትምህርቶች አንዱ መሆኑ የተረጋገጠ ነው።” ከጅምሩ አንሥቶ የኢየሱስ አገልግሎት ጭብጥ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” የሚል ነበር። (ማቴዎስ 4:17) በዚያን ወቅት ኢየሱስ የተቀባ ንጉሥ ሆኖ በምድር ላይ ይኖር ነበር። በተጨማሪም የሰው ልጆች ከመንግሥቱ በረከቶች ለመካፈል ብቻ ሳይሆን በዚህ መንግሥት ውስጥ ከኢየሱስ ጋር አብረው ነገሥታትና ካህናት ለመሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ተከፍቶላቸው ነበር። ይህ እጅግ አስደሳች የሆነ ነገር ነው!—ሉቃስ 22:28-30፤ ራእይ 1:6፤ 5:10
4. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብዙ ሰዎች ‘ለመንግሥቱ ምሥራች’ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነበር? ይህስ ምን ፍርድ አስከተለባቸው?
4 ብዙ ሰዎች ይህን አስደሳች ‘የመንግሥት ምሥራች’ ቢሰሙም ያመኑት ግን ጥቂቶች ናቸው። ለዚህ ሁኔታ በከፊል አስተዋጽኦ ያደረገው ሃይማኖታዊ መሪዎች ‘መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት መዝጋታቸው’ ነበር። በሐሰት ትምህርቶቻቸው አማካኝነት “የእውቀትን መክፈቻ” ወሰዱ። አብዛኞቹ ሰዎች ኢየሱስን እንደ መሲሕና የአምላክ መንግሥት የተቀባ ንጉሥ አድርገው ስላልተቀበሉት ኢየሱስ “የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች” አላቸው።—ማቴዎስ 4:23፤ 21:43፤ 23:13፤ ሉቃስ 11:52
5. የኢየሱስን ምሳሌዎች ይሰሙ ከነበሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በማስተዋል እንዳላዳመጡት ያሳዩት እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ በአንድ ወቅት ተሰብስቦ ለነበረ ብዙ ሕዝብ ትምህርት ሲሰጥ እንደ ልማዱ በዚያ የነበሩትን ሰዎች የሚፈትኑና ለመንግሥቱ የይስሙላ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ማንነት የሚያጋልጡ ተከታታይ ምሳሌዎችን ተጠቀመ። የመጀመሪያው ምሳሌ በአራት ዓይነት መሬቶች ላይ ዘር ስለ ዘራ ሰው የሚገልጽ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓይነት መሬቶች ለተክሎች እድገት የማያመቹ ሲሆኑ የመጨረሻው መሬት ግን መልካም ፍሬ የሚያፈራ “መልካም መሬት” ነበር። ኢየሱስ ይህን አጭር ምሳሌ ያጠቃለለው “ጆሮ ያለው ያዳምጥ” የሚል ጥብቅ ማሳሰቢያ በመስጠት ነበር። (ማቴዎስ 13:1-9 አዓት) በዚያ ተገኝተው የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች እሱ ሲናገር ቢሰሙም ‘አላዳመጡትም’ ነበር። በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር የተዘራው ዘር ከመንግሥተ ሰማያት ጋር እንዴት እንደሚመሳሰል ለማወቅ ልባዊ ፍላጎትም ሆነ ግፊት አልነበራቸውም። የኢየሱስ ምሳሌዎች ሥነ ምግባር የሚመለከቱ ቁም ነገሮችን ያዘሉ ጥሩ ታሪኮች ከመሆን አያልፉም ብለው በማሰብ ወደ ቤታቸው ተመልሰው የተለመደውን የዕለት ተለት ኑሯቸውን ቀጠሉ። ልባቸው ደንዳና ስለ ነበረ ጥልቅ የሆነ ማስተዋልን እንዲሁም ታላላቅ መብቶችንና አጋጣሚዎችን ሳያገኙ ቀሩ!
6. ‘የመንግሥቱን ምሥጢር’ ማስተዋል ለኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ብቻ የተሰጣቸው ለምንድን ነው?
6 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፣ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም” ብሏቸዋል። በተጨማሪም የኢሳይያስን ትንቢት ጠቅሶ እንዲህ አለ፦ “በዓይናቸው እንዳያዩ፣ በጀሮአቸውም እንዳይሰሙ፣ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፣ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፣ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጀሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል። . . . የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን [“ደስተኞች” አዓት] ናቸው።”—ማቴዎስ 13:10-16 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን፤ ማርቆስ 4:11-13
የመንግሥቱን “ምንነት ማስተዋል”
7. የመንግሥቱን ‘ምንነት ማስተዋል’ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
7 ኢየሱስ ችግራቸው ምን እንደሆነ ጠቁሟል። ችግራቸው የመንግሥቱን መልእክት “ትርጉም ከማስተዋል” ጋር ግንኙነት ያለው ነገር ነው። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ሲነግራቸው እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፣ ክፉው ይመጣል፣ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው።” ከዚያም “የመንግሥት ቃል” የሚዘራባቸውን የተለያዩ የልብ ሁኔታዎች ስለሚያመለክቱ አራት የመሬት ዓይነቶች ማብራራቱን ቀጠለ።—ማቴዎስ 13:18-23፤ ሉቃስ 8:9-15
8. በመጀመሪዎቹ ሦስት መሬቶች ላይ የተዘራውን “ዘር” እንዳያድግ የከለከለው ምንድን ነው?
8 በእያንዳንዱ መሬት ላይ የተዘራው “ዘር” መልካም ቢሆንም ፍሬው በመሬቱ ሁኔታ ላይ የተመካ ነበር። በመሬት የተመሰለው ልብ ተላላፊዎች እንደሚበዙበት የተጨናነቀ መንገድ ከሆነ ማለትም መንፈሳዊ ባልሆኑ ብዙ እንቅስቃሴዎች ከደነደነ የመንግሥቱን መልእክት የሚሰማው ግለሰብ ለመንግሥቱ ጊዜ የለኝም የሚል ሰበብ ለመፍጠር ቀላል ይሆንለታል። ችላ የተባለው ዘር ሥር ከመስደዱ በፊት በቀላሉ ሊወሰድ ይችላል። ሆኖም ዘሩ ጭንጫ በሚመስለው ልብ ውስጥ ቢዘራስ? ዘሩ ሊበቅል ቢችልም ምግብ ለማግኘትና ጠንክሮ ለመቆም እንዲችል ሥሩን ወደ ተፈለገው ቦታ ለመስደድ ያዳግተዋል። በተለይ ከባድ ስደት በሚያጋጥምበት ወቅት የአምላክ አገልጋይ መሆን በጣም አስቸጋሪ ስለሚሆን ግለሰቡ ሊደናቀፍ ይችላል። በተጨማሪም በመሬት የተመሰለው ልብ እንደ እሾኽ በሆኑት የኑሮ ጭንቀቶች ወይም በቁሳዊ ሀብት ምኞት ከተዋጠ የቀጨጨው የመንግሥቱ ዘር ሊታነቅ ይችላል። በእነዚህ በሕይወት ውስጥ የተለመዱ ሦስት ሁኔታዎች ሥር የመንግሥቱ መልእክት ፍሬ አያፈራም።
9. በመልካም መሬት ላይ የተዘራው ዘር መልካም ፍሬ ሊያፈራ የቻለው ለምንድን ነው?
9 ይሁንና በመልካም መሬት ላይ የተዘራው የመንግሥቱ ዘር ሁኔታ ምንድን ነው? ኢየሱስ “በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል” በማለት መልስ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 13:23 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) የመንግሥቱን ‘ምንነት ስለሚያስተውሉ’ እንደየግለሰቦቹ ሁኔታ ጥሩ ፍሬ ያፈራሉ።
ከእውቀት ጋር ኃላፊነት ይመጣል
10. (ሀ) የመንግሥቱን ‘ምንነት ማስተዋል’ በረከትንና ኃላፊነትን እንደሚያመጣ ኢየሱስ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ሄዳችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጉ በማለት የሰጠው ተልእኮ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ደቀ መዛሙርት ብቻ የሚመለከት ነውን?
10 ኢየሱስ የመንግሥቱን ልዩ ልዩ ገጽታዎች የሚገልጹ ሌሎች ስድስት ምሳሌዎችን ከሰጠ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” በማለት ጠየቃቸው። “አዎን” ብለው ሲመልሱለት “ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀ መዝሙር የሆነ ጻፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል” አላቸው። ኢየሱስ የሰጣቸው ትምህርትና ማሠልጠኛ ደቀ መዛሙርቱን ‘ከመዝገባቸው’ ወሰን የሌለው ጥሩ መንፈሳዊ ምግብ የሚያወጡ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ያደርጋቸዋል። ከዚህ መንፈሳዊ ምግብ ውስጥ አብዛኛው ከአምላክ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው ነው። ኢየሱስ የመንግሥቱን ‘ምንነት ማስተዋል’ በረከቶችን ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትንም ጭምር እንደሚያመጣ ግልጽ አድርጓል። “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል።—ማቴዎስ 13:51, 52፤ 28:19, 20
11. በ1914 ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ምን ሁኔታዎች ተከስተዋል?
11 ኢየሱስ በገባው ቃል መሠረት ካለፉት በርካታ መቶ ዘመናት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከእውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ ጋር መሆኑን ቀጥሏል። በእነዚህ መጨረሻ ቀናት ደረጃ በደረጃ እውቀት ሰጥቷቸዋል። በተጨማሪም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደውን እውነት በመጠቀም ረገድ በኃላፊነት እንዲጠየቁ አድርጓል። (ሉቃስ 19:11-15, 26) በ1914 መንግሥቱ ያከናወናቸው ነገሮች በፍጥነትና በአስደናቂ ሁኔታ ግልጽ መሆን ጀመሩ። በዚያ ዓመት ለረጅም ጊዜ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው መንግሥት ‘ከመወለዱም’ በተጨማሪ “የሥርዓቱ መደምደሚያ” ጀምሯል። (ራእይ 11:15፤ 12:5, 10፤ ዳንኤል 7:13, 14, 27) በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ሁኔታዎች ትርጉም ያስተዋሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች በታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የመንግሥት ስብከትና የማስተማር ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ይህን ሁኔታ አስቀድሞ ተናግሯል።—ማቴዎስ 24:14
12. (ሀ) በዘመናችን የተሰጠው ሰፊ የመንግሥት ምሥክርነት ምን ውጤት አስገኝቷል? (ለ) በዚህ ተጠራጣሪ ዓለም ውስጥ ክርስቲያኖች ምን አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል?
12 ይህ ሰፊ የመንግሥት ምሥክርነት ከ230 በሚበልጡ አገሮች ተዳርሷል። በአሁኑ ጊዜ በዚህ ሥራ ከአምስት ሚልዮን የሚበልጡ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት በመካፈል ላይ ሲሆኑ ሌሎችም በመሰብሰብ ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ የደቀ መዛሙርቱን ቁጥር ከ5.6 ቢልዮን የምድር ነዋሪዎች ጋር ስናወዳድረው እንደ ኢየሱስ ዘመን ሁሉ በዛሬው ጊዜም አብዛኞቹ ሰዎች የመንግሥቱን ‘ምንነት እንዳላስተዋሉ’ ለመረዳት እንችላለን። አስቀድሞ እንደ ተነገረው ብዙዎች እያሾፉ “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው?” በማለት ላይ ናቸው። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) የዚህ ዓለም ሕዝቦች ያላቸው የራስ ወዳድነት፣ የጥርጣሬና ቁሳዊ ሀብትን የማሳደድ ዝንባሌ ቀስ በቀስ እኛ ክርስቲያኖች የመንግሥቱን ተስፋዎች የምንመለከትበትን ሁኔታ ሊነካ ይችላል። የምንኖረው በዚህ ዓለም ሕዝቦች መካከል ስለ ሆነ በቀላሉ አንዳንድ ዝንባሌዎቻቸውንና ልማዶቻቸውን መቀበል ልንጀምር እንችላለን። የአምላክን መንግሥት ‘ምንነት ማስተዋላችን’ እና አጥብቀን መያዛችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ራሳችንን መመርመር
13. የመንግሥቱን ምሥራች እንድንሰብክ በተሰጠን ተልእኮ ረገድ በማስተዋል ‘እያዳመጥን’ መሆናችንን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ ስለምንኖርበት የመከር ዘመን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፣ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ። . . . በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።” (ማቴዎስ 13:41, 43) ስለ መንግሥቱ በመስበክና ደቀ መዛሙርት በማድረግ ረገድ የተሰጠውን ትእዛዝ በፈቃደኝነት በመቀበል ‘መስማትህን’ እየቀጠልክ ነውን? “በመልካም መሬት ላይ የተዘራው” ‘ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውለውና’ መልካም ፍሬ የሚያፈራው እንደሆነ አስታውስ።—ማቴዎስ 13:23
14. ትምህርት በሚሰጥበት ወቅት ምክሩን ‘ማስተዋላችንን’ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
14 የግል ጥናት ስናደርግና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ‘ልባችን ወደ ማስተዋል እንዲያዘነብል’ ማድረግ ይኖርብናል። (ምሳሌ 2:1-4) ጠባይን፣ አለባበስን፣ ሙዚቃንና መዝናኛን በተመለከተ ምክር በሚሰጥበት ወቅት ምክሩ ወደ ልባችን ጠልቆ እንዲገባ መፍቀድና አስፈላጊዎቹን ማስተካከያዎች ለማድረግ መገፋፋት አለብን። ላለመቀበል ሰበብ አስባብ መፍጠር ወይም አዎንታዊ ምላሽ ከመስጠት መቆጠብ የለብንም። መንግሥቱ በሕይወታችን ውስጥ እውን ከሆነልን ከአቋም ደረጃዎቹ ጋር ተስማምተን ከመኖራችንም በተጨማሪ ስለ እርሱ ለሌሎች ሰዎች በቅንዓት እንናገራለን። ኢየሱስ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” ብሏል።—ማቴዎስ 7:21-23
15. ‘መንግሥቱንና የአምላክን ጽድቅ አስቀድመን መፈለጋችን’ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ሰዎች ስለሚያስፈልጋቸው ምግብ፣ ልብስና መጠለያ የመጨነቅ ዝንባሌ ቢኖራቸውም ኢየሱስ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” ብሏል። (ማቴዎስ 6:33, 34) በሕይወታችሁ ውስጥ ቅድሚያ ስለምትሰጧቸው ነገሮች ውሳኔ ስታደርጉ መንግሥቱን አስቀድሙ። በሚያስፈልጓችሁ ነገሮች ብቻ በመርካት አኗኗራችሁን ቀላል አድርጉት። እነዚህ ነገሮች እንዲሁ ሲታዩ መጥፎ ስላልሆኑ ተቀባይነት አላቸው በሚል የግድ የማያስፈልጉንን ነገሮች ብናደርግ ወይም ብናግበሰብስ ቂልነት ይሆንብናል። ይህ እውነት ሊሆን ቢችልም እነዚህን የግድ የማያስፈልጉ ነገሮች ማግበስበሳችንና መጠቀማችን ለግል ጥናት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና በስብከቱ ሥራ ለመሳተፍ ያለንን ፕሮግራም የሚነካው እንዴት ነው? ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ‘ዋጋዋ እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ አግኝቶ ያለውን ሁሉ ሸጦ የገዛ’ ነጋዴን ይመስላል ብሏል። (ማቴዎስ 13:45, 46) ስለ አምላክ መንግሥት እንደዚህ ሊሰማን ይገባል። “የአሁኑን ዓለም ወዶ” አገልግሎቱን የተወውን ዴማስን ሳይሆን ጳውሎስን መምሰል ይኖርብናል።—2 ጢሞቴዎስ 4:10, 18፤ ማቴዎስ 19:23, 24፤ ፊልጵስዩስ 3:7, 8, 13, 14፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10, 17-19
‘ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም’
16. የአምላክን መንግሥት ‘ምንነት ማስተዋላችን’ ከመጥፎ ጠባይ እንድንርቅ የሚረዳን እንዴት ነው?
16 የቆሮንቶስ ጉባኤ አባላት የጾታ ብልግናን በቸልታ ሲመለከቱ ጳውሎስ በግልጽ እንዲህ አላቸው፦ “ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) የአምላክን መንግሥት ‘ምንነት ካስተዋልን’ በክርስቲያናዊ አገልግሎት እስከ ተጠመድኩኝ ድረስ አንዳንድ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶች ብፈጽምም ይሖዋ ምንም አይለኝም ብለን በማሰብ ራሳችንን አናታልልም። በመካከላችን ንጹሕ ያልሆነ ነገር መሰማት እንኳ የለበትም። (ኤፌሶን 5:3-5) ከዚህ ዓለም መጥፎ አስተሳሰቦችና ልማዶች መካከል አንዳንዶቹ ሳይታወቅህ በሕይወትህ ውስጥ ቀስ በቀስ ጣልቃ መግባት እንደ ጀመሩ ተመልክተሃልን? እነዚህን ነገሮች ከሕይወትህ ውስጥ በቶሎ አስወግዳቸው! ለእነዚህ ነገሮች ስትል በጣም ውድ የሆነውን የአምላክ መንግሥት ማጣት አይኖርብህም።—ማርቆስ 9:47
17. ለአምላክ መንግሥት ያለን አድናቆት ትሑቶች እንድንሆንና ሌሎችን እንዳናሰናክል የሚረዳን በምን መንገዶች ነው?
17 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?” ብለው ጠይቀው ነበር። ኢየሱስ በመካከላቸው አንድ ትንሽ ልጅ ካቆመ በኋላ እንዲህ በማለት መለሰላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፣ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፣ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው።” (ማቴዎስ 18:1-6) ትዕቢተኞች፣ በቃኝ የማይሉ፣ አሳቢነት የሌላቸውና ዓመፀኞች ወደ አምላክ መንግሥት አይገቡም፤ በተጨማሪም የመንግሥቱ ዜጎች አይሆኑም። ለወንድሞችህ ያለህ ፍቅር፣ ትሕትናህና አምላካዊ ፍርሃትህ በጠባይህ ሌሎችን ከማደናቀፍ እንድትቆጠብ ይገፋፋሃልን? ወይስ ዝንባሌህና ጠባይህ የቱንም ያህል ሌሎች ሰዎችን የሚጎዳ ቢሆንም “መብቴ” ነው ብለህ ትገፋበታለህ?—ሮሜ 14:13, 17
18. የአምላክ መንግሥት የአምላክ ፈቃድ ‘በሰማይ እንደ ሆነ እንዲሁ በምድር እንዲሆን’ በሚያደርግበት ወቅት ታዛዥ ሰዎች ምን በረከቶችን ያገኛሉ?
18 ሰማያዊ አባታቸን የሆነው ይሖዋ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት ለምናቀርበው ልባዊ ጸሎት በቅርቡ ሙሉ በሙሉ መልስ ይሰጠናል። አሁን በመግዛት ላይ የሚገኘው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በቅርቡ “በጎችን” እና “ፍየሎችን” ለመለየት በፍርድ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ንጉሡ “በቀኙ ያሉትን ይላቸዋል፦ እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።” ፍየሎቹ “ወደ ዘላለም ቅጣት፣ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።” (ማቴዎስ 6:10፤ 25:31-34, 46) “ታላቁ መከራ” ይህን አሮጌ ሥርዓትና የመንግሥቱን ‘ምንነት ለማስተዋል’ ፈቃደኛ ያልሆኑትን ሰዎች ጠራርጎ ያስወግዳቸዋል። ይሁን እንጂ በሚልዮን የሚቆጠሩ “ከታላቁ መከራ” በሕይወት የሚተርፉ ሰዎችና በቢልዮን የሚቆጠሩ ከሞት የሚነሡ ሰዎች ተመልሳ በምትቋቋመው ምድራዊ ገነት ውስጥ ፍጻሜ የሌላቸውን የመንግሥቱን በረከቶች ይወርሳሉ። (ራእይ 7:14) ይህ መንግሥት ከሰማይ የሚገዛ የምድር አዲስ መስተዳድር ነው። የአምላክ መንግሥት ይሖዋ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ በማስፈጸም ከሁሉ የላቀ ቅዱስ ስሙን ያስቀድሳል። ይህ ሊደከምለት፣ መሥዋዕት ሊከፈልለትና በጉጉት ሊጠበቅ የሚገባው ውርሻ አይደለምን? የአምላክን መንግሥት ‘ምንነት ማስተዋላችን’ በእኛ ላይ ይህን የመሰለ ውጤት ማምጣት ይኖርበታል!
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
◻ አብዛኞቹ የኢየሱስ አድማጮች የመንግሥቱን ‘ምንነት ያላስተዋሉት’ ለምንድን ነው?
◻ የአምላክ መንግሥትን ‘ምንነት ማስተዋል’ በረከትንና ኃላፊነትን የሚያመጣው እንዴት ነው?
◻ በስብከት ረገድ የመንግሥቱን ‘ምንነት እንዳስተዋልን’ የሚያሳየው ምንድን ነው?
◻ በጠባያችን የሚሰጠንን ምክር ‘እንዳስተዋልን’ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የመንግሥቱን ‘ምንነት አስተውለው’ መልካም ፍሬ አፍርተዋል