በመላው ዓለም ደስተኛ አወዳሽ ለመሆን የተለዩ ሰዎች
“እናንተ ሕዝቦች፣ ያህን አወድሱ! እናንተ የይሖዋ አገልጋዮች ሆይ፣ ምስጋናን አቅርቡ፣ የይሖዋን ስም አወድሱ።”— መዝሙር 113:1 NW
1, 2. (ሀ) በመዝሙር 113:1-3 መሠረት ከልባችን ልናወድሰው የሚገባው ማን ነው? (ለ) የትኛውን ጥያቄ ማንሳታችን ተገቢ ነው?
ይሖዋ አምላክ ታላቁ የሰማይና የምድር ፈጣሪ እንዲሁም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ የአጽናፈ ዓለማችን ሉዓላዊ ገዥ ነው። ከልባችን ልናወድሰው የሚገባው አምላክ ነው። ከዚህ የተነሣ መዝሙር 113:1-3 (NW) እንዲህ ይላል:- “እናንተ ሕዝቦች፣ ያህን አወድሱ! እናንተ የይሖዋ አገልጋዮች ሆይ፣ ምስጋናን አቅርቡ፣ የይሖዋን ስም አወድሱ። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ የይሖዋ ስም ብሩክ ይሁን። ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያው ድረስ የይሖዋ ስም ይመስገን።”
2 የአምላክ ምሥክሮች እንደመሆናችን ይህንን ማድረግ ያስደስተናል። ይሖዋ አምላክ ዛሬ እየዘመርነው ያለነው ይህ አስደሳች የውዳሴ መዝሙር በቅርቡ መላዋን ምድር እንዲሞላ ሲያደርግ ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! (መዝሙር 22:27) ምድር አቀፍ በሆነው በዚህ ታላቅ የዘማሪዎች ጓድ መካከል የአንተም ድምፅ ይሰማልን? ከሆነ ከዚህ አንድነት ከሌለውና ደስታ ካጣው ዓለም የተለየህ በመሆንህ ምንኛ ደስተኛ ልትሆን ይገባሃል!
3. (ሀ) የይሖዋን ሕዝቦች ልዩ የሚያደርጋቸው ነገር ምንድን ነው? (ለ) የተለየን የሆነውስ በምን መንገዶች ነው?
3 ይሖዋን በአንድነት ማወደሳችን ልዩ ሆነን እንድንታይ እንደሚያደርገን አይካድም። የምንናገረውና የምናስተምረው ነገር የሚጣጣም ነው፤ ስለ ይሖዋ ‘ጥሩነት ብዛት’ የምናውጅበትም መንገድ ተመሳሳይ ነው። (መዝሙር 145:7) አዎን፣ ራሳችንን የወሰንን የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ለአምላካችን ለይሖዋ አገልግሎት ተለይተናል። አምላክ ራሳቸውን ለእርሱ ወስነው የነበሩትን የጥንቶቹን ሕዝቦቹን ማለትም እስራኤላውያንን በዙሪያቸው ካሉት ብሔራት የተለዩ እንዲሆኑና በልማዶቻቸውም እንዳይበከሉ ነግሯቸው ነበር። (ዘጸአት 34:12-16) ይህንን ማድረግ እንዲችሉ የሚረዳቸውም ሕግ ሰጥቷቸዋል። በተመሳሳይም ዛሬ ይሖዋ ቅዱስ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። በቃሉ ውስጥ ያለው መመሪያ ከዚህ ዓለም ተለይተን መኖር የምንችልበትን መንገድ ይጠቁመናል። (2 ቆሮንቶስ 6:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) የተለየን ሆነን የምንታየው የታላቂቱ ባቢሎን መነኮሳትና ደናግል እንደሚያደርጉት በገዳማትና በአድባራት ተገልለን በመኖር አይደለም። የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ይሖዋን በሕዝብ ፊት እናወድሰዋለን።
ይሖዋን በማወደስ ረገድ ግንባር ቀደም የሆነውን ምሰሉ
4. ኢየሱስ ይሖዋን በማወደስ በኩል ምሳሌ የተወልን እንዴት ነው?
4 ኢየሱስ ይሖዋን ከማወደስ ዓላማው ውልፍት ብሎ አያውቅም። ይህም ከዓለም የተለየ እንዲሆን አድርጎታል። በየምኩራቦቹና ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ የአምላክን ቅዱስ ስም አወድሷል። ኢየሱስ በተራራ ላይም ሆነ በባሕር ዳርቻ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ሁሉ የይሖዋን እውነት በግልጽ አውጆአል። “አባት ሆይ፣ የሰማይና የምድር ጌታ፣ . . . አመሰግንሃለሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 11:25) ኢየሱስ በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት ለፍርድ በቀረበ ጊዜ እንኳ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:37) ኢየሱስ የሥራውን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር። በሄደበት ቦታ ሁሉ ስለ ይሖዋ መስክሯል፤ በሕዝብ ሁሉ ፊት አወድሶታል።
5. መዝሙር 22:22 የሚናገረው ስለ ማን ነው? የእኛስ ዝንባሌ ምን መሆን ይገባዋል?
5 በመዝሙር 22:22 ላይ ይሖዋን በማወደስ ረገድ ግንባር ቀደም የሆነውን ሰው በሚመለከት የተነገረውን የሚከተለውን የትንቢት ቃል እናገኛለን:- “ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፣ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ።” ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን 2:11-13 ላይ ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ጌታ ኢየሱስ እና ይሖዋ አምላክ ለሰማያዊ ክብር ስለቀደሳቸው ሰዎች እንደሆነ ገልጿል። እነርሱም ልክ እንደ ኢየሱስ ስሙን በጉባኤ መካከል ለማወደስ አያፍሩም። እኛስ በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ ስንገኝ እንደዚህ ይሰማናልን? በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በትኩረት በመከታተልም ሆነ ድምፃችንን አውጥተን ሞቅ ባለ መንፈስ ተሳትፎ በማድረግ ይሖዋን እናወድሳለን። ይሁን እንጂ ይሖዋን በደስታ የምናወድስበት መንገድ ይህ ብቻ ነውን?
6. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ተልእኮ ሰጥቷቸዋል? ብርሃንን የሚያፈቅሩ ሰዎች አምላክን የሚያስከብሩት እንዴት ነው?
6 በማቴዎስ 5:14-16 ላይ በተገለጸው መሠረት ጌታ ኢየሱስ ሌሎች ሰዎች ይሖዋን ማወደስ ይችሉ ዘንድ ተከታዮቹ ብርሃናቸውን እንዲያበሩ አዝዟል። “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። . . . መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሏል። ብርሃንን የሚያፈቅሩ ሰዎች አምላክን ያስከብራሉ። ይህንን የሚያደርጉት እንዲሁ ደስ የሚያሰኝና ሰብዓዊነት የተላበሰ ነገር በመናገርና በማድረግ ነውን? አይደለም፤ ይልቁንም አንድ ሆነው ይሖዋን በማክበር ነው። አዎን፣ ብርሃንን የሚያፈቅሩ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው የእርሱ ደስተኛ አወዳሾች ይሆናሉ። አንተስ ይህንን አስደሳች እርምጃ ወስደሃልን?
ይሖዋን በማወደስ የሚገኝ ደስታ
7. ይሖዋን የሚያወድሱ ሰዎች በጣም ደስተኛ የሆኑት ለምንድን ነው? በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለትስ ምን ደስታ አግኝተዋል?
7 ይሖዋን የሚያወድሱ ሰዎች ይህን ያህል ደስተኛ የሆኑት ለምንድን ነው? ደስታ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ ስለሆነ ነው። በገላትያ 5:22 ላይ ከፍቅር ቀጥሎ የተጠቀሰው ደስታ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን የይሖዋ መንፈስ ፍሬ አሳይተዋል። በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት አምላክ በ120ዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈሱን ባፈሰሰ ጊዜ ሁሉም በተለያዩ ቋንቋዎች ይሖዋን ማወደስ ጀመሩ። ከተለያዩ ብሔራት ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው የነበሩት ሃይማኖተኛ አይሁዶች ‘ተገርመውና ተደንቀው’ ነበር። “የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን” ሲሉ ተናግረዋል! (ሥራ 2:1-11) በተለያዩ ቋንቋዎች ለይሖዋ የቀረበው ይህ ድንቅ ውዳሴ ምን ውጤት አስገኘ? ወደ 3,000 የሚያክሉ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ገብተው የነበሩ ሰዎች ስለ መሲሑ የሚናገረውን የመንግሥቱን ምሥራች ተቀበሉ። ተጠመቁ፣ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፣ የይሖዋ ደስተኛ አወዳሾች በመሆን በጉጉት ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጋር ተባበሩ። (ሥራ 2:37-42) ይህ እንዴት ያለ በረከት ነበር!
8. ከጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ ክርስቲያኖች ደስታቸውን ለመጨመር ምን አድርገዋል?
8 ዘገባው በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፣ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።” (ሥራ 2:46, 47) በጣም ያስደሰታቸው ነገር አንድ ላይ ተሰብስበው መብላታቸው ብቻ ነውን? አይደለም፤ ዋነኛው የደስታቸው ምክንያት ይሖዋን በየዕለቱ ማወደሳቸው ነበር። የሰበኩትን የመዳን መልእክት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተቀበሉ ማየታቸው ደስታቸውን እጥፍ ድርብ አድርጎታል። ዛሬም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም።
በሁሉም ብሔራት የሚገኙ ደስተኛ አወዳሾች
9. (ሀ) አምላክ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች የእርሱን ምሥራች መስማት የሚችሉበትን አጋጣሚ እንዲያገኙ ማድረግ የጀመረው መቼና እንዴት ነው? (ለ) ቆርኔሌዎስና አብረውት የነበሩት ሰዎች ከመጠመቃቸው በፊት መንፈስ ቅዱስ የወረደባቸው ለምን ነበር?
9 ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያካሂዱት ብርሃን ሰጭ እንቅስቃሴ በአንድ ብሔር ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ዓላማ አልነበረውም። ስለዚህም ከ36 እዘአ አንስቶ በሁሉም ብሔራት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የእርሱን የምሥራች የሚሰሙበትን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ጴጥሮስ ከአምላክ ባገኘው መመሪያ በቂሣርያ ወደሚገኝ ከአሕዛብ ወገን ወደሆነ አንድ የጦር መኮንን ቤት ይሄዳል። በዚያም ቆርኔሌዎስ ከቅርብ ወዳጆቹና ቤተሰቦቹ ጋር ተሰብስቦ አገኘው። እነርሱም ጴጥሮስ የተናገራቸውን በተመስጦ ያዳምጡ ስለነበር በልባቸው በኢየሱስ አመኑ። ይህንን እንዴት ለማወቅ እንችላለን? ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ከአሕዛብ ወገን በሆኑት በእነዚህ አማኞች ላይ ወረደ። እንደወትሮው ቢሆን ኖሮ የአምላክን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የሚቀበሉት ከተጠመቁ በኋላ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ግን ይሖዋ እነዚህን ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች ከመጠመቃቸው በፊት እንደተቀበላቸው አሳይቷል። ይሖዋ እንደዚህ ባያደርግ ኖሮ አምላክ አሕዛብን እንደ አገልጋዮቹ አድርጎ እንደተቀበላቸውና ለጥምቀት ብቁዎች እንደሆኑ ጴጥሮስ በእርግጠኛነት ማወቅ አይችልም ነበር።— ሥራ 10:34, 35, 47, 48
10. ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ይሖዋን እንደሚያወድሱት ከብዙ ዘመናት አስቀድሞ የተነገረው እንዴት ነው?
10 ይሖዋ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች እንደሚያወድሱት ከረጅም ዘመን በፊት ተናግሯል። በየአገሩ ደስተኛ አወዳሾች ይኖሩታል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንንም ለማረጋገጥ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትንቢቶችን ጠቅሶ ጽፏል። ከብዙ ብሔራት የተውጣጡ ክርስቲያኖች ለነበሩበት የሮም ጉባኤ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ። ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ፣ ደግሞም [በመዝሙር 18:49 ላይ]:- ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ ለስምህም እዘምራለሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ አሕዛብ ስለ ምሕረቱ እግዚአብሔርን ያከብሩ ዘንድ፣ ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር እውነት የመገረዝ አገልጋይ ሆነ እላለሁ። ደግሞም [ዘዳግም 32:43 ላይ]:- አሕዛብ ሆይ፣ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላል። ደግሞም [መዝሙር 117:1 ላይ]:- እናንተ አሕዛብ ሁላችሁ፣ ጌታን አመስግኑ ሕዝቦቹም ሁሉ ይወድሱት ይላል።”— ሮሜ 15:7-11 ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።
11. አምላክ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች እውነቱን እንዲማሩ የረዳቸው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
11 ሰዎች ተስፋቸውን አምላክ በአሕዛብ ሁሉ ላይ እንዲገዛ በሾመው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እስካልጣሉ ድረስ አንድ ሆነው ይሖዋን ማወደስ አይችሉም። አምላክ እነዚህ ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውነት እንዲያስተውሉ ለመርዳት ዓለም አቀፍ የትምህርት መርኃ ግብር ዘርግቷል። በታማኙ ባሪያው አማካኝነት መመሪያ እየሰጠ ነው። (ማቴዎስ 24:45-47) ምንስ ውጤት ተገኝቷል? ከአምስት ሚልዮን የሚበልጡ ደስተኛ ሰዎች ከ230 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ የይሖዋን ውዳሴ በደስታ እየዘመሩ ነው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ደግሞ ተመሳሳይ ሥራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል። በ1996 በተከበረው የመታሰቢያው በዓል ላይ ምን ያህል ሰዎች ተገኝተው እንደነበር ተመልከት:- 12,921,933 ሰዎች ተገኝተው ነበር፤ እንዴት ድንቅ ነው!
እጅግ ብዙ ደስተኛ አወዳሾች እንደሚመጡ አስቀድሞ ተነግሯል
12. ሐዋርያው ዮሐንስ ያየው ስሜት ቀስቃሽ ራእይ ምንድን ነው? የዚህስ ራእይ እውን ፍጻሜ ምንድን ነው?
12 ሐዋርያው ዮሐንስ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሰዎች” በራእይ ተመልክቷል። (ራእይ 7:9) እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ከአምላክ ቅቡዓን ቀሪዎች ጋር ሆነው የሚዘምሩት ውዳሴ ጭብጥ ምንድን ነው? ዮሐንስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጣል:- “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው።” (ራእይ 7:10) ይህ መልእክት በሁሉም የምድር ማዕዘናት በልበ ሙሉነት እየታወጀ ነው። የዘንባባ ዝንጣፊዎችን እንደምናወዛውዝ ያህል በኅብረትና በአንድነት ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ መሆኑን አናሳውቃለን፤ መዳን የምናገኘው ከይሖዋና ከበጉ ማለትም ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በሰማይና በምድር ፊት በደስታ እንመሰክራለን። ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ እጅግ ብዙ ሰዎች ያየው ስሜት ቀስቃሽ ራእይ እንዴት አስደስቶት ይሆን! ዛሬ ደግሞ ዮሐንስ በራእይ የተመለከተው ነገር በእውን ሲፈጸም ስናይና በአፈጻጸሙ ስንካፈል ደስታችን ምንኛ እጥፍ ድርብ ይሆናል!
13. የይሖዋን ሕዝቦች ከዓለም የሚለያቸው ምንድን ነው?
13 የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ስሙን ለመሸከም በመቻላችን ኩራት ይሰማናል። (ኢሳይያስ 43:10, 12) የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችን ከዚህ ዓለም ልዩ ያደርገናል። የአምላክን ልዩ ስም መሸከምና መለኮታዊ ሥራውን የሕይወታችን ዓላማ ማድረጋችን እንዴት ያስደስታል! ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት ስሙን ለመቀደስና አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ ያለው ታላቅ ዓላማ ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርጎታል። ይሖዋ ከስሙና ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘው መለኮታዊ ዓላማ ውስጥ ቦታ እንዲኖረን ረድቶናል። ይህንን ያደረገባቸው ሦስት መንገዶች አሉ።
እውነት በአደራ ተሰጥቶናል
14, 15. (ሀ) አምላክ ከስሙና ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘው መለኮታዊ ዓላማው ውስጥ ቦታ እንዲኖረን እኛን የሚረዳበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? (ለ) በ1914 የተቋቋመው መንግሥት በ607 ከዘአበ ከተገለበጠው መንግሥት የተለየ የሆነው እንዴት ነው?
14 አንደኛ ይሖዋ ለሕዝቡ እውነትን በአደራ ሰጥቷቸዋል። አምላክ ከገለጠላቸው ነገር ሁሉ ይበልጥ አስደሳች የሆነው መንግሥቱ በ1914 መግዛት እንደጀመረ የሚገልጸው እውነት ነው። (ራእይ 12:10) ይህ ሰማያዊ መስተዳድር በዳዊት የዘር መሥመር የሚመጡ ነገሥታት ይቀመጡበት ከነበረውና በጥላነት ካገለገለው የኢየሩሳሌም መንግሥት የተለየ ነው። ይህ ምድራዊ መንግሥት የተገለበጠ ሲሆን ኢየሩሳሌምም ከ607 ከዘአበ አንስቶ ሙሉ በሙሉ በአሕዛብ የዓለም ኃያል መንግሥታት አገዛዝ ሥር ወድቃ ቆይታለች። ይሖዋ በ1914 ያቋቋመው መንግሥት ግን ለማንም የማይንበረከክና ለዘላለም የማይፈርስ ሰማያዊ ኃይል ነው። (ዳንኤል 2:44) በተጨማሪም የመግዛት ሥልጣኑም የተለየ ነው። እንዴት? ራእይ 11:15 እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ [“እርሱ ለሾመው ለክርስቶስ፣” NW] ሆነች፣ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ።”— ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።
15 ‘የጌታችንና እርሱ የሾመው የክርስቶስ መንግሥት’ በጠቅላላው የሰው ዘር ዓለም ላይ ሥልጣን አለው። የይሖዋ ሉዓላዊነት በአዲስ መልክ የተገለጠበት ይህ መንግሥት መሲሐዊውን ልጁንና ዛሬ በአብዛኛው ትንሣኤ አግኝተው በሰማያዊ ግርማ የተቀመጡትን የኢየሱስን 144,000 ወንድሞች ያቀፈ ሲሆን የማይጨበጥ እንዲሁ በቲዎሪ ደረጃ ብቻ ምሁራን የሚያጠኑት ምናባዊ መስተዳድር አይደለም። የለም፣ ይህ ሰማያዊ መንግሥት እውን መስተዳድር ነው። በዚህ መንግሥት አገዛዝ አማካኝነት ያገኘነው በፍጽምና ለዘላለም የመኖር አስደሳች ተስፋ ሐሴት እያደረግን ለመቀጠል በቂ ምክንያት ይሆነናል። በይሖዋ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እንዲህ ያለውን እውነት በአደራ መቀበላችን ዘወትር ስለዚህ መንግሥት እንድንናገር ያነሳሳናል። (መዝሙር 56:10 NW) የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት በሰማይ ላይ መግዛት መጀመሩን ለሰው ሁሉ በመናገር ይህንን ሥራ በቋሚነት በመፈጸም ላይ ነህን?
የመንፈስ ቅዱስንና የዓለም አቀፉን ወንድማማች ማኅበር እርዳታ አግኝተናል
16, 17. አምላክ በመለኮታዊ ዓላማው ውስጥ ቦታ እንዲኖረን እኛን የሚረዳባቸው ሁለተኛውና ሦስተኛው መንገዶች ምንድን ናቸው?
16 አምላክ በመለኮታዊ ዓላማው ውስጥ ቦታ እንዲኖረን እኛን የሚረዳበት ሁለተኛው መንገድ ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ነው፤ ይህ መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ መልካም ፍሬዎቹን እንድናፈራና የአምላክን ሞገስ እንድናገኝ ያስችለናል። (ገላትያ 5:22, 23) ከዚህም በላይ ጳውሎስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች “እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ” ተቀብለናል ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 2:12) ሁላችንም ለይሖዋ መንፈስ በጎ ምላሽ ከሰጠን ዛሬ በደግነት ስለሰጠን መልካም ነገሮች ማለትም ስለ ተስፋው፣ ስለ ሕጎቹ፣ ስለ መሠረታዊ ሥርዓቶቹና እነዚህን ስለ መሳሰሉት ነገሮች ለማወቅና ለመረዳት እንችላለን።— ከማቴዎስ 13:11 ጋር አወዳድር።
17 አምላክ እኛን የሚረዳበት ሦስተኛው መንገድ ዓለም አቀፋዊው ወንድማማችነትና እጅግ አስደሳች የሆነው የይሖዋ የአምልኮ ድርጅታዊ ዝግጅት ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ’ በማለት አጥብቆ ምክር በሰጠ ጊዜ ስለዚሁ መናገሩ ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:17 NW) ወንድሞችና እህቶች የሚገኙበት አፍቃሪ የሆነው ዓለም አቀፉ ቤተሰባችን መዝሙር 100:2 በሚያዝዘው መሠረት ይሖዋን ከልብ በመነጨ ከፍተኛ ደስታ እንድናገለግለው ይረዳናል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “በደስታ ለእግዚአብሔር ተገዙ። በሐሴትም ወደ ፊቱ ግቡ።” ቁጥር 4 በመቀጠል “ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፤ አመስግኑት፣ ስሙንም ባርኩ” ይላል። በመሆኑም ለሕዝብ ስንሰብክም ይሁን በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ ስንካፈል ደስታ ልናገኝ እንችላለን። ውብ በሆነው የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አደባባይ ውስጥ ያገኘነው ሰላምና መረጋጋት እንዴት ታላቅ ነው!
ይሖዋን በደስታ አወድሱት!
18. ስደት ወይም ሌሎች ችግሮች ቢገጥሙንም ይሖዋን በማወደሳችን ደስተኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
18 ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች፣ ስደት ወይም ሌሎች ችግሮች ቢገጥሙን በይሖዋ የአምልኮ ቤት ውስጥ በመሆናችን ደስ ይበለን። (ኢሳይያስ 2:2, 3) ደስታ ከልብ የሚመነጭ ነገር እንደሆነ አስታውሱ። የጥንቶቹ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ብዙ መከራዎችና እጦት ቢያጋጥማቸውም ይሖዋን በደስታ አወድሰዋል። (ዕብራውያን 10:34) ዛሬም ያሉት መሰል አማኞቻችን ልክ እንደ እነርሱ ናቸው።— ማቴዎስ 5:10-12
19. (ሀ) ይሖዋን እንድናወድሰው የሚያነሳሳን የትኛው ተደጋጋሚ ትእዛዝ ነው? (ለ) የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው በምን ላይ ነው? ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምንድን ነው?
19 ይሖዋን የምናገለግል ሁላችን መጽሐፍ ቅዱስ እርሱን እንድናወድስ የሚሰጠውን ትእዛዝ መፈጸም ያስደስተናል። የራእይ መጽሐፍ “ያህን አወድሱ” የሚሉትን ቃላት ደጋግሞ በመጥቀስ የአምላክን መወደስ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ራእይ 19:1-6) በመዝሙር 150 ውስጥ በሚገኙት ስድስት ቁጥሮች ውስጥ 13 ጊዜ ይሖዋን እንድናወድሰው ተነግሮናል። ይህ ፍጥረታት ሁሉ ይሖዋን ለማወደስ ድምፃቸውን እንዲያነሱ የሚጋብዝ አጽናፈ ዓለማዊ ጥሪ ነው። የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው በዚህ ታላቅ የሆነ የሃሌ ሉያ ዝማሬ በመተባበራችን ላይ ነው! አዎን፣ ለዘላለም የሚኖሩት ለይሖዋ ያላሰለሰ ውዳሴ የሚያቀርቡ ሰዎች ብቻ ናቸው። እንግዲያው መጨረሻው እየቀረበ ሲመጣ ከታማኙ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ጋር ለመጣበቅ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ ይሖዋን ያወድስ። እናንተ ሕዝቦች ያህን አወድሱት” (NW) የሚሉት የመዝሙር 150 የመደምደሚያ ቃላት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ለማየት ተስፋ ማድረግ እንችላለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የይሖዋን ሕዝቦች ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
◻ የይሖዋ አገልጋዮች በጣም ደስተኛ የሆኑት ለምንድን ነው?
◻ ከዓለም የተለየን የሚያደርገን ምንድን ነው?
◻ አምላክ በመለኮታዊ ዓላማው ውስጥ ቦታ እንዲኖረን እኛን የሚረዳባቸው ሦስት መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በሄደበት ቦታ ሁሉ ስለ ይሖዋ መስክሯል፤ በተጨማሪም በሕዝብ ሁሉ ፊት አወድሶታል