የአውራጃ ስብሰባው ቀስቃሽ ጥሪ አቅርቧል!
ዕለት ዕለት ይሖዋን በደስታ አወድሱ!
1 ሐዋርያው ጳውሎስ “መለከት የማይገለጥን ድምፅ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል?” በማለት ጠይቋል። (1 ቆሮ. 14:8) “ደስተኛ አወዳሾች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የቀረበው ጥሪ ግልጽና የማያሻማ ነበርን? አዎን፣ ግልጽ ነበር። ‘ይሖዋን በየዕለቱ በደስታ አወድሱት’ የሚል ስሜት ቀስቃሽ መልእክት ተላልፏል! ልብህ በዚህ ጥሪ ለሥራ ተነሳስቷልን? ስብሰባው ዘላለማዊውን ንጉሥ ይሖዋን ሳናሰልስ የምናወድሰው ለምን እንደሆነ ብዙ ጠንካራ ምክንያቶች አቅርቦልናል።— መዝ. 35:27, 28
2 ግርማ ሞገስ የተላበሱት ሰማያት ‘በየቀኑ’ የይሖዋን ክብር ያውጃሉ። (መዝ. 19:1–3) ድምፅ አልባ የሆኑት ግዑዝ ፍጥረታት ሳያቋርጡ ለይሖዋ ውዳሴ የሚያቀርቡ ከሆነ የማሰብ ችሎታ ያለን ሰዎች ይሖዋን አቻ ለሌላቸው ባሕርያቱና ላደረጋቸው ነገሮች ሁልጊዜ ማወደስ የለብንምን? ከታላቁ ፈጣሪያችን የበለጠ በደስታ ልናወድሰው የሚገባን ማን ይኖራል?— መዝ. 145:3, 7
3 ዕለት ዕለት፦ መዝሙራዊው በመንፈስ ተገፋፍቶ “ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ። እግዚአብሔር ታላቅ ምስጋናውም ብዙ ነውና” በማለት ጽፏል። (መዝ. 96:2, 4) ይህ የሚሠራው ለአቅኚዎች ብቻ ነውን? አይደለም! ይህ ማለት ሁላችንም በማንኛውም ጊዜና አጋጣሚ ሌላው ቀርቶ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በማንካፈልባቸው ቀናት እንኳ ለሰዎች ስለ ይሖዋ መናገር አለብን ማለት ነውን? አዎን! ይሖዋን በየዕለቱ የማወደሱና ስለ መዳን ዝግጅቱ ለሌሎች የመናገሩ አስፈላጊነት አጣዳፊ ነው። ሰዎች ይሖዋ ዘላለማዊ ንጉሥ እንደሆነና ክብር ለተጎናጸፈው ልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን የመግዛት ሥልጣን እንደሰጠው ማወቅ አለባቸው። ለይሖዋና ለሰዎች ያለን ፍቅር ሰዎችን ማግኘት በምንችልባቸው ቦታዎች ሁሉ ስለዚህ መልእክትና ስለ መዳን ዝግጅቱ መናገራችንን እንድንቀጥል ይገፋፋናል።— መዝ. 71:15
4 ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት በየቀኑ ይሖዋን በግልጽ በማወደስ ከሁሉ የላቀ ግሩም ምሳሌ ትቷል። “የሰማይና የምድር ጌታ የሆንህ አባት ሆይ፣ በሕዝብ ፊት አወድስሃለሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 11:25 አዓት) ኢየሱስ ከተናገረው ቃል ጋር በመስማማት በሄደበት ሁሉ ይሖዋን በሕዝብ ፊት አወድሷል። በምኩራብ፣ ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ፣ በተራራ ላይ ወይም የባሕር ዳርቻ በመሳሰሉ ሰዎች ይሰባሰቡባቸው በነበሩ ቦታዎች ሁሉ ይሖዋን አወድሷል። ይሖዋን በሕዝብ ፊት በማወደሱ ሥራ ሳናቋርጥ በየዕለቱ በመካፈል የኢየሱስን ፈለግ በቅርብ የምንከተል ከሆነ አስደሳች ውጤቶች እናገኛለን።
5 ለጥሪው ምላሽ መስጠት፦ ይሖዋን በየቀኑ በሕዝብ ፊት እንድታወድስ ለቀረበልህ ጥሪ ምላሽ ትሰጣለህን? ዕድሜ መሰናክል እንደማይሆን አስታውስ። መዝሙር 148:12 ጎልማሶች፣ ቆነጃጅት፣ ሽማግሌዎችና ልጆች ይሖዋን እንዲያወድሱ ይጋብዛል። ወጣቶች፣ ከፊታችን ባለው በአዲሱ የትምህርት ዓመት በትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁና አስተማሪዎቻችሁ ፊት ይሖዋን ታወድሱታላችሁን? አዋቂዎች የሆናችሁ ደግሞ ለመነጋገር የሚያስችል አጋጣሚ ሲፈጠር አብረዋችሁ የሚሠሩትን ሰዎች ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው እየነገራችኋቸው ነውን? ሁላችንም ልክ እንደ መተንፈስና እንደ መብላት ስለ ይሖዋ መናገርንም የሕይወታችን ክፍል ማድረግ አለብን። ግድ የለሽ የሆኑ ሰዎች የምንናገረውን ነገር ጆሮ ዳባ ልበስ ቢሉትም ለምንናገረው ነገር ትኩረት የሚሰጥ አለ፤ እርሱ መልሶ ይክሰናል።— ሚል. 3:16
6 የሥርዓቱ ፍጻሜ እየተቃረበ ሲሄድ “እናንተ ሕዝቦች፣ ያህን አወድሱ” የሚለው ጥሪ እስከ ምድር ዳርቻ ይሰማል። (መዝ. 106:1 አዓት) ሰዎች ሁሉ ስሙ ይሖዋ የሆነው አምላክ በምድር ላይ የሁሉ የበላይ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ የውዳሴ ድምፃችን ከቀን ወደ ቀን እየጎላ ይሂድ።— መዝ. 83:18 አዓት