የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 7/1 ገጽ 22-25
  • ባሳለፍኩት ሕይወት ፈጽሞ አልቆጭም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ባሳለፍኩት ሕይወት ፈጽሞ አልቆጭም
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የእናቴ መልካም ምሳሌ
  • ሥራና መንፈሳዊ እድገት
  • በአስቸጋሪ ጊዜያት በቤቴል ማገልገል
  • በጦርነት ወቅት የአቅኚነት አገልግሎት
  • ብዙ አስደሳች መብቶች
  • ‘ይሖዋ የምታመንበት አምላኬ ነው’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ራስህን በፈቃደኝነት ልታቀርብ ትችላለህ?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
  • ከሁሉ የተሻለ የሥራ መስክ ይሆንልህ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ይምጡና ይጎብኙ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 7/1 ገጽ 22-25

ባሳለፍኩት ሕይወት ፈጽሞ አልቆጭም

ፖል ኦብሪስት እንደተናገረው

በ1912 ገና የስድስት ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ አምስተኛ ልጅዋን በመውለድ ላይ ሳለች ሞተች። ሁለት ዓመት ያህል ካለፈ በኋላ ቤርታ ቪብል የምትባል ወጣት የቤት ሠራተኛ ቤታችን መሥራት ጀመረች። በቀጣዩ ዓመት አባቴ እርሷን ሲያገባ ሁላችንም ልጆች እንደገና እናት በማግኘታችን በጣም ተደሰትን።

የጀርመንኛ ተናጋሪ በሆነው የስዊዘርላንድ ክፍል በምትገኘው ብራግ በምትባል ትንሽ ከተማ እንኖር ነበር። ቤርታ በእርግጥም ክርስቲያን ሴት ነበረች፤ እኔም በጣም ወደድኳት። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን (የይሖዋ ምሥክሮችን) ጽሑፎች ማጥናት የጀመረችው በ1908 ሲሆን የተማረችውን ለሌሎች ታካፍል ነበር።

በ1915 ቤርታና አባባ ከተጋቡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ፊልም ለመመልከት አብሬያት ሄድኩ። ዓለም አቀፍ ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር ያዘጋጀው ይህ ስላይድና ተንቀሳቃሽ ፊልም በአእምሮዬና በልቤ ውስጥ የማይፋቅ ስሜት አሳድሮብኛል። ሌሎች ተመልካቾችም በጣም ተነክተው ነበር። ብራግ የሚገኘው አዳራሽ በጣም በመሙላቱ የተነሳ ፖሊሶች በሮቹን ዘግተው ዘግይ​ተው የሚመጡ ሰዎችን ይመልሱ ነበር። ብዙ ሰዎች በመሰላል ተንጠላጥለው ክፍት በሆነው መስኮት በኩል ለመግባት ቢሞክሩም የተሳካላቸው ጥቂቶች ብቻ ነበሩ።

የእናቴ መልካም ምሳሌ

በዚያን ጊዜ በአውሮፓ አንደኛው የዓለም ጦርነት ተቀጣጥሎ ስለ ነበር ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ፍርሃት ውጧቸው ነበር። ስለዚህ እናቴ ታደርግ እንደነበረው የአምላክን መንግሥት አጽናኝ መልእክት ይዞ ከቤት ወደ ቤት መሄድ ትልቅ ድፍረት የሚጠይቅ ሥራ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ይዛኝ ትሄድ ነበር። እኔም በጣም እደሰት ነበር። በመጨረሻም እማማ በ1918 ለይሖዋ አምላክ ያደረገችውን ውሳኔ በውኃ ጥምቀት አሳየች።

እማማ እስከተጠመቀችበት ጊዜ ድረስ አባባ አምልኮቷን ተቃውሞ አያውቅም ነበር። ሆኖም ከዚያን ጊዜ ወዲህ እርሷን መቃወም ጀመረ። አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቿን ሰበሰበና እሳት ውስጥ ወረወረው። እማማ ከእሳቱ ውስጥ ማዳን የቻለችው መጽሐፍ ቅዱሷን ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ ቀጥላ ያደረገችው ነገር በጣም የሚያስገርም ነበር። ወደ አባባ ሄደችና እቅፍ አደረገችው። በእርሱ ላይ ምንም ዓይነት ቂም አልያዘችም።

አባባም ያልጠበቀው ነገር ስለነበር ከቁጣው በረደ። ሆኖም አልፎ አልፎ በድንገት ተቃውሞ ቢያስነሳም ቁጣውን በጽናት መቋቋም ነበረብን።

ሥራና መንፈሳዊ እድገት

በ1924 ለሦስት ዓመት የሚሰጠውን የጠጉር ሥራ ሥልጠና ካገኘሁ በኋላ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ወደሚነገርበት የስዊዘርላንድ ክፍል ሄድኩና ሥራ ተቀጠርኩ። ይህም የፈረንሳይኛ ቋንቋ የመናገር ችሎታዬን ለማሻሻል እንድችል ጥሩ አጋጣሚ ከፍቶልኛል። ወደዚህ አካባቢ መምጣቴ በመንፈሳዊ እድገቴ ላይ እክል ፈጥሮብኝ የነበረ ቢሆንም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የነበረኝ ፍቅር ግን ፈጽሞ አልጠፋም ነበር። ስለዚህም ከስድስት ዓመት በኋላ ወደ ቤት ስመለስ ብራግ በሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመርኩ።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ 40 ኪሎ ሜትር ያህል ራቅ ብሎ በሚገኘው ሪንፊልድ ወደሚባል ትንሽ ከተማ ሄድኩ። እዛም በእህቴ ጠጉር ቤት ውስጥ እየሠራሁ ከአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትንሽ ቡድን ጋር በመሰብሰብ በመንፈሳዊ እድገት ማድረጌን ቀጠልኩ። አንድ ቀን በሳምንቱ መካከል የነበረንን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከደመደምን በኋላ ቡድኑን ይመራ የነበረው ሽማግሌ “እሑድ በሚደረገው የመስክ አገልግሎት ለመካፈል እቅድ ያወጣ አለ?” በማለት ጠየቀ። አንድ ሰው አብሮኝ እንደሚሆንና ሥራው እንዴት እንደሚከናወን እንደሚያሳየኝ በመተማመን ፈቃደኛ መሆኔን ገለጽኩ።

እሑድ ደርሶ ወደ ክልላችን ከሄድን በኋላ ወንድም ሶደር “አቶ ኦብሪስት በዚያ በኩል ትሠራለህ” አለ። ልቤ ከዚያ በፊት ሆኖ በማያውቅ መንገድ ምቱን ቢጨምርም የሰዎችን ቤት እያንኳኳሁ ስለ አምላክ መንግሥት መናገሬን ቀጠልኩ። (ሥራ 20:​20) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ከመምጣቱ በፊት መጠናቀቅ አለበት ብሎ በተናገረው የስብከት ሥራ ከመካፈል ወደኋላ ብዬ አላውቅም። (ማቴዎስ 24:​14) መጋቢት 4, 1934 በ28 ዓመት እድሜዬ ለይሖዋ አምላክ ያደረኩትን ውሳኔ በውኃ ጥምቀት አሳየሁ።

ከሁለት ዓመት በኋላ የጣሊያንኛ ቋንቋ በሚነገርበት የስዊዘርላንድ ክፍል ሉጋኖ በሚባል ከተማ የጠጉር አስተካካይነት ሥራ አገኘሁ። የጣሊያንኛ ቋንቋ መናገር የምችለው በጣም ትንሽ ቢሆንም እንኳ ምሥራቹን ወዲያው መስበክ ጀመርኩ። እንደዚያም ሆኖ አገልግሎት በወጣሁ በመጀመሪያው እሁድ ዕለት ይዣቸው የነበረውን 20 ቡክሌቶች በጠቅላላ አበረከትኩ። በዚህም ወቅት የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ለማድረግ ጥቂት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለመሰብሰብና አንድ ቡድን ለማቋቋም ችዬ ነበር። ውሎ አድሮ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ተጠምቀዋል። እንዲሁም የካቲት 1937 በሉጋኖ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ መሠረትን።

ከሁለት ወራት በኋላ ሚያዝያ 1937 ሕይወቴን በከፍተኛ ሁኔታ የለወጠ አንድ ደብዳቤ ደረሰኝ። ደብዳቤው ቤቴል ተብሎ በሚታወቀው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ገብቼ እንዳገለግል መጋበዜን የሚገልጽ ነበር። ወዲያውም ግብዣውን ተቀበልኩ። ይህን ውሳኔ በማድረጌም ፈጽም አልቆጭም። በዚህ መንገድ እስከ አሁን ለ60 ዓመት የቆየሁበትን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሥራ ጀመርኩ።

በአስቸጋሪ ጊዜያት በቤቴል ማገልገል

በዚያን ጊዜ የስዊስ ቤቴል ይገኝ የነበረው የስዊዘርላንድ ዋና ከተማ በሆነው በበርን ከተማ ነበር። በዚያም መጻሕፍትን፣ ቡክሌቶችንና መጽሔቶችን በ14 ቋንቋዎች እናትም ነበር። ከዚያም በመላው አውሮፓ ይላኩ ነበር። በአቅራቢያችን የጭነት መኪናዎችን እንደ ልብ ስለማናገኝ አንዳንድ ጊዜ የታተሙትን ጽሑፎች በጋሪ ጭኜ ወደ ባቡር ጣቢያ እሄድ ነበር። ቤቴል እንደገባሁ የተሰጠኝ የመጀመሪያ ምድብ ሥራዬ የቅንብር ክፍል ነበር። እዚያም ኅትመት የሚሠራባቸውን የብረት ሆሄያት እለቅም ነበር። ብዙም ሳይቆይ በእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። እንዲሁም የቤቴል ቤተሰብ ጠጉር አስተካካይ ሆኜም ሠርቻለሁ።

መስከረም 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳና ጭከና የሞላበት የናዚ ጥቃት በመላው አውሮፓ ሽብር ፈጠረ። ስዊዘርላንድ ጦርነት ከገጠሙ አገሮች መካከል ገለልተኛ አገር ነበረች። መጀመሪያ ላይ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችንን ያለምንም ችግር ቀጥለን ነበር። ከዚያም ሐምሌ 5, 1940 ከሰዓት በኋላ ስምንት ሰዓት ላይ በእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ እንዳለሁ ሳንጃ የተሰካበት ጠመንጃ የታጠቁና ፈረስ ላይ የተቀመጡ ወታደሮች ያጀቡት አንድ ሲቪል ሰው ብቅ አለ።

“ዛርከር ያለው የት ነው?” በማለት ሲቪሉ ሰው በጩኸት ጠየቀ። ፍራንዝ ዛርከር በዚያን ጊዜ ስዊዘርላንድ የሚገኘውን የስብከት ሥራችንን የሚቆጣጠረው የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች ነበር።

“ማን ይፈልግሃል ልበለው?” ብዬ ጠየኩ። ወዲያው ያዙኝና የዛርከር ቢሮ የት እንደሆነ እንዳሳያቸው እየጎተቱ ወደ ላይኛው ፎቅ ወሰዱኝ።

በዚህ ጊዜ 40 አካባቢ የምንሆነውን መላውን የቤቴል ቤተሰብ መመገቢያ ክፍል ውስጥ እንድንሰባሰብ አዘዙን። ማንም ሰው አምልጦ ለመሄድ እንዳይሞክር ለማድረግ መትረየስ የታጠቁ አራት ሰዎች ከሕንፃው በስተውጪ በኩል ቆሙ። በውስጥ በኩል 50 የሚሆኑ ወታደሮች ሕንፃውን መፈተሽ ጀመሩ። የይሖዋ ምሥክሮች የውትድርና አገልግሎትን የሚቃወም እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚካፈሉ የሚያሳይ አንድም ፍንጭ ባለማግኘታቸው የጠበቁትን ነገር ሳያገኙ ቀሩ። ሆኖም አምስት የወታደር መኪና ሙሉ ጽሑፎች ጭነው ሄዱ።

የመንግሥት ባለሥልጣናት መጠበቂያ ግንብን ሳንሱር እንዲያደርጉ ፈቃደኛ ባለመሆናችን የተነሳ ጽሑፉ በስዊዘርላንድ እንዳይሰራጨ ታገደ። ይህም ማለት በቤቴል ውስጥ የሚሠሩትን ሰዎች ቁጥር በጣም ውስን ስላደረገው ወጣት የቤተሰቡ አባላት ቤቴልን እንዲለቁና አቅኚ (በሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ የሚካፈሉት የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሆነው እንዲያገለግሉ ማበረታቻ ተሰጣቸው።

በጦርነት ወቅት የአቅኚነት አገልግሎት

ሐምሌ 1940 ቤቴል ከመግባቴ በፊት እኖርበት ወደነበረው በስዊዘርላንድ የጣሊያንኛ ቋንቋ በሚነገርበት ሉጋኖ ወደሚባል አካባቢ ተመልሼ ሄድኩ። በዚያን ጊዜ በፋሺዝም ተጽዕኖ ሥር በወደቀውና አጥባቂ ካቶሊኮች በሚኖሩበት ክልል ውስጥ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ።

የስብከት ሥራዬን እንዳቆም ለማስገደድ ፖሊስ እየደጋገመ አስቁሞ ያነጋግረኝ ነበር። አንድ ቀን በአንድ መናፈሻ መግቢያ በር ላይ አንዲትን ሴት እያነጋገርኩ ሳለሁ ሲቪል የለበሰ አንድ ሰው ከኋላዬ በኩል ያዘኝና አንድ መኪና ውስጥ አስገብቶ ወደ ሉጋኖ ወሰደኝ። እዛም ፖሊስ ፊት አቀረበኝ። ቃሌን እንድሰጥ ስጠየቅ ይሖዋ አምላክ እንድንሰብክ አዞናል በማለት አብራራሁ።

“አምላክ በሰማይ ማዘዝ ይችላል!” “እዚህ ምድር ላይ ግን የምናዘው እኛ ነን” በማለት የፖሊስ መኮንኑ በድንፋታ መለሰ።

በጦርነቱ ጊዜያት በተለይ ኢየሱስ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ” በማለት የሰጠውን ምክር መከተል በጣም አስፈላጊ ነበር። (ማቴዎስ 10:​16) ስለዚህም አብዛኞቹን ጽሑፎቼን በሸሚዜ በውስጠኛው በኩል ባለው ኪስ ውስጥ ደበቅሁ። ምንም ዓይነት ጽሑፍ ሾልኮ እንዳይወድቅ ለማድረግ እግረ ጠባብ ሱሪ እለብስ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ኢንጋዲን ሸለቆ እንድሄድ መመሪያ ተሰጠኝ። እዛም ቢሆን ከፖሊሶች ጋር ድብብቆሹ ቀጠለ። ይህ ከስዊስ አልፕስ በስተ ምሥራቅ የሚገኝ እጅግ የሚያምር ሸለቋማ ቦታ ነው። በክረምት ወራት ከፍተኛ የበረዶ ግግር ስለሚፈጠር በክልሉ ውስጥ እንደ ልብ መዘዋወር እንድችል የበረዶ መንሸራተቻዬን እንዲልኩልኝ አደረግሁ።

በቀዝቃዛው የክረምት ወር በበረዶ ላይ እየተንሸራተቱ በሚኬድበት ጊዜ ሙቀት የሚሰጥ ጓንት ማጥለቅ የግድ አስፈላጊ ነው። ጓንቴን አዘውትሬ ስለተጠቀምኩበት ወዲያው አረጀ። አንድ ቀን ሹራቦችና ሙቀት የሚሰጡ ጓንቶች በውስጡ የያዘ አንድ ጥቅል በፖስታ ቤት በኩል በድንገት ሲደርሰኝ ይህ ነው የማይባል ከፍ ያለ ደስታ ተሰማኝ! ቀድሞ በነበርኩበት በርን በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ የምትኖር አንዲት እህት የሠራችልኝ ነበሩ። አሁንም እንኳ ይህን ሳስብ ልቤ በአመስጋኝነት ይሞላል።

ብዙ አስደሳች መብቶች

በ1943 በስዊዘርላንድ የነበረው ሁኔታ ቀስ በቀስ መረጋጋት ጀመረ። ስለዚህም ቤቴል ገብቼ እንዳገለግል ድጋሚ ተጠራሁ። 100 ኪሎ ሜትር ላይ ራቅ ብሎ ላውሳን በሚገኘው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤ አንዳንድ ችግሮች በመኖራቸው ምክንያት አስፋፊዎቹ የአምላክን ድርጅት በሚመለከት ትክክለኛ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለመርዳት ያንን ከተማ አዘውትሬ እንድጎበኝ ተመደብኩ።

ከዚያም ስዊዘርላንድ በሚገኙ ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ ጉባኤዎች የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ለተወሰነ ጊዜ አገለገልኩ። በሳምንቱ ውስጥ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ቤቴል እሠራና ዓርብ፣ ቅዳሜና እሑድ ደግሞ መንፈሳዊ እርዳታ ለማድረግ በየሳምንቱ የተለያዩ ጉባኤዎችን እጎበኝ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በ1960 የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ጉባኤ በበርን በተቋቋመ ጊዜ የጉባኤው ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። ቤቴል ከበርን አሁን ወዳለበት ተን ወደሚባለው ውብ አካባቢ እስከተዘዋወረበት እስከ 1970 ድረስ በዚሁ መብት አገልግያለሁ።

በተን የጣሊያንኛ ቋንቋ የሚናገሩ አንድ ትንሽ የምሥክሮች ቡድን በማግኘቴ በጣም ተደሰትኩ። ወዲያውም ከእነርሱ ጋር መሥራት ጀመርኩ። ውሎ አድሮ በዚህ ቦታ ጉባኤ ተቋቋመና ወጣት ወንድሞች ይህን ኃላፊነት መሸከም ወደሚችሉበት ቦታ እስኪደርሱ ድረስ ለረዥም ዓመታት የጉባኤው ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገልግያለሁ።

በተለይ በጣም አስደሳች መብት እንደሆነ አድርጌ የምቆጥረው ነገር ቢኖር ዓለም አቀፍ በሆኑ ስብሰባዎች ላይ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር አብሬ መሰብሰቤ ነው። ለምሳሌ ያህል በ1950 ኒው ዮርክ በሚገኘው ያንኪ ስታዲዮም በማይረሳው የቲኦክራሲው እድገት ስብሰባ ላይ ተገኝቻለሁ። ኒው ዮርክ የሚገኘውን ዓለም አቀፉን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት መጎብኘቴ የማይፋቅ ትዝታ ጥሎብኛል። በተጨማሪም በቀጣዩ ዓመት “እላችኋለሁ፣ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት በማጉላት በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ንጹሕ አምልኮ በተባለው ስብሰባ ላይ ወንድም ሚልተን ጂ ሄንሼል ያቀረበውን ንግግር በጭራሽ አልረሳውም። (ሉቃስ 19:​40) ወንድም ሄንሼል “ድንጋዮች መጮህ ይኖርባቸዋል ብላችሁ ታስባላችሁ?” በማለት ጥያቄ አቀረበ። “በጭራሽ!” የሚለውን በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ያሰሙት ከፍተኛ ድምፅ አሁንም በጆሮዬ ያቃጭላል።

በ1937 ተመልሼ ቤቴል በገባሁ ጊዜ ጥቂት የወጪ መሸፈኛ ብቻ እንደምናገኝ የተረዳው አባቴ በጭንቀት ስሜት “ልጄ፣ ወደፊት በዕድሜ ስትገፋ እንዴት ትኖራለህ?” በማለት ጠየቀኝ። እኔም “ጎለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም” የሚሉትን የመዝሙራዊውን ዳዊት ቃላት በመጥቀስ መለስኩለት። (መዝሙር 37:​25) እነዚህ ቃላት በኔ ላይ በትክክል ሠርተዋል።

ከ80 ዓመታት በፊት ቤርታ ቪብል አባባን በማግባቷ፣ ባሳየችው ምሳሌና ትሰጠኝ በነበረው መመሪያ በኩል ይሖዋንና የእርሱን ባሕርያት በማወቄ በጣም ደስተኛ ነኝ! ምንም እንኳ ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት ቢዘብቱባትም በ1983 እስከ ሞተችበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግላለች። አምላኳን ይሖዋን በማገልገሏ ምንም ዓይነት የቁጭት ስሜት አላደረባትም። እኔም ብሆን ነጠላ ሆኜ በመኖሬና መላ ሕይወቴን ለይሖዋ አገልግሎት ሳልቆጥብ በማዋሌ በጭራሽ አልቆጭም።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤቴል ውስጥ እየሠራሁ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ