ይቅርታ እየጠየቁ ያሉት ለምንድን ነው?
አብያተ ክርስቲያናት ለሠሩት ጥፋት ንስሐ መግባታቸውና ማሻሻያዎችን ማድረጋቸው እንግዳ ነገር አይደለም። ሬሊጂዮኒ ኤ ሚቲ (ሃይማኖቶችና አፈ ታሪኮች) የተባለው የሃይማኖት መዝገበ ቃላት እንዳለው የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አላት ይባል የነበረው የአቋም ጽናት በመካከለኛው ዘመን የኖሩትን ሰዎች ስቦ የነበረ ሲሆን ብዙዎች ሃይማኖታዊ ተሐድሶ እንዲደረግ ጥያቄ እንዲያቀርቡ አነሳስቷቸዋል።
በ1523 ማርቲን ሉተር ከሮም ቤተ ክርስቲያን ከወጣ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት አድሪያን ስድስተኛ በኑረምበርግ ለተደረገው የገዢዎች ስብሰባ የሚከተለውን መልእክት በመላክ አንድነት ለማምጣት ጥረት አድርገው ነበር:- “ለብዙ ዓመታት ሊወገዙ የሚገባቸው ነገሮች በቅዱሱ ባሕር ዙሪያ ተሰባስበው መቆየታቸውን እናውቃለን . . . ከሁሉም በፊት የእነዚህ ሁሉ ክፉ ነገሮች መፍለቂያ የሆነውን ምናልባትም የሮማውን የጵጵስና ማዕከል ለማደስ ማንኛውንም ጥረት ማድረግ አለብን።” ይሁን እንጂ ጥፋታቸውን ማመናቸው በጵጵስናው ማዕከል ውስጥ የነበረውን መከፋፈል በማስቀረትም ሆነ ሙስናን በመዋጋት ረገድ ሊሳካላቸው አልቻለም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አብያተ ክርስቲያናት የጀርመኑን ታላቅ እልቂት በዝምታ በመመልከታቸው ተነቅፈዋል። በተጨማሪም አባላቶቻቸው በጦርነቶች እንዳይካፈሉ ባለማድረጋቸው ተከሰዋል። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተፋፋመበት በ1941 ፕሪሞ ማትሶላሪ የተባሉ አንድ ቄስ እንዲህ ሲሉ ጠይቀው ነበር:- “እምብዛም የማያሰጉ መሠረተ ትምህርቶችን በተመለከተ ሮም ታደርገው እንደነበረና አሁንም እንደምታደርገው የካቶሊክ ትምህርት መፈራረስ የማያሳስባትና ጠንካራ እርምጃ የማትወስደው ለምንድን ነው?” እምብዛም የማያሰጉ መሠረተ ትምህርቶች የተባሉት ከየትኛው ጋር ሲወዳደሩ ነው? ቄሱ ይናገሩ የነበረው በወቅቱ ሥልጣኔን በማፈራረስ ላይ ይገኝ ስለነበረው ጦርነትን የሚቀሰቅስ የብሔርተኝነት ስሜት ነበር።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግን ሃይማኖቶች የፈጸሙትን በደል አምነው መቀበላቸው የተለመደ ነገር አልነበረም። አንዳንዶች በ1832 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ‘የቀድሞ ጥንካሬዋን እንድታገኝ’ ላቀረቡት ሐሳብ ግሪጎሪ 16ኛ መልስ ሲሰጡ እንዲህ ብለው ነበር:- “ቤተ ክርስቲያኒቱ እንከን ያለባት ተደርጋ ልትታይ የምትችል ይመስል [ለቤተ ክርስቲያኒቱ] ደህንነትና እድገት ‘የማሻሻያና የቀድሞ ጥንካሬዋን ማስገኛ’ የሚል ሐሳብ ማቅረብ ትርጉም የለሽና ክብርን የሚነካ እንደሆነ ግልጽ ነው።” ሊሸሿቸው የማይችሉ ፈጠው የሚታዩ እንከኖች የትኞቹ ናቸው? እነዚህን እንከኖች ለመሸፋፈን የተለያዩ ዘዴዎች ተፈጥረዋል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ የሃይማኖት ምሁራን ቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስም ኃጢአተኛም ነች ይላሉ። አምላክ ከስህተት ስለሚጠብቀው ተቋሙ በራሱ ቅዱስ ነው። ቢሆንም አባላቶቹ ኃጢአተኞች ናቸው ተብሏል። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የጭከና ተግባር ሲፈጸም በኃላፊነት ሊጠየቅ የሚገባው ተቋሙ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች ናቸው። ይህ ምክንያታዊ የሆነ ሐሳብ ነውን? የሮማ ካቶሊክ ምሁር ሃንስ ኩንግ እንደዚያ ስላልተሰማቸው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ከሰብዓዊው ዓለም ተለይቶ የሚገኝ ፍጹም የሆነ ቤተ ክርስቲያን የለም። መናዘዝ የማያስፈልገው ኃጢአት የሌለበት ቤተ ክርስቲያን የለም።”
የአብያተ ክርስቲያናት አንድነትና የሥነ ምግባር አቋም
አብያተ ክርስቲያናት ይቅርታ ለመጠየቅ የተነሣሡበት ምክንያት ምን ይሆን ብለህ ተገርመህ ይሆናል። በተለያዩ የሃይማኖት ቡድኖች መካከል “ቀደም ሲል ስለነበሩ ክፍፍሎች” በኃላፊነት ተጠያቂ መሆናቸውን በመጀመሪያ አምነው የተቀበሉት ፕሮቴስታንቶችና ኦርቶዶክሶች ናቸው። ይህን ያደረጉት በ1927 በስዊዘርላንድ ሎዛን በተደረገው “እምነት እና ሥርዓት” በተባለው የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ስብሰባ ላይ ነበር። ከጊዜ በኋላም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተመሳሳይ የሆነ ነገር አደረገች። በተለይ ከቫቲካን ሁለተኛa አንስቶ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ጨምሮ ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ቀሳውስት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ላለው ክፍፍል በተደጋጋሚ ይቅርታ ጠይቀዋል። ለምን ዓላማ? በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የበለጠ አንድነት እንዲኖር የሚሹ ይመስላል። ካቶሊካዊው ታሪክ ጸሐፊ ኒኮሊኖ ሳራሌ እንዳሉት በዳግማዊ ጆን ፖል “‘ይቅርታ የመጠየቅ ፕሮጀክት’ ውስጥ አንድ ዓላማ አለ፤ እሱም አብያተ ክርስቲያናትን አንድ ማድረግ ነው።”
ይሁን እንጂ አብያተ ክርስቲያናትን አንድ ከማድረግም የበለጠ ነገር ተካቶ ነበር። ዛሬ አስከፊው የሕዝበ ክርስትና ታሪክ በሰፊው ታውቋል። የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ሃንስ ኡርስ ፎን ባልታዛር እንዲህ ብለው ነበር:- “ካቶሊካውያን ይህን ሁሉ ታሪክ ዝም ብለው ሊያልፉት አይችሉም። ሊቀ ጳጳሱ አባል የሆኑበት ቤተ ክርስቲያን እኛ ዛሬ እንዲደረግ የማንፈቅዳቸውን ነገሮች አድርጓል ወይም እንዲደረግ ፈቅዷል።” በዚህም ምክንያት ሊቀ ጳጳሱ “የቤተ ክርስቲያኒቱ ጥቁር የታሪክ ገጾች እንዲመረመሩና ከዚያም ይቅርታ ለመጠየቅ እንዲቻል” አንድ ኮሚሽን አቋቁመዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ የሆነችበት ሌላው ምክንያት ደግሞ የሥነ ምግባር አቋሟን መልሳ ለመያዝ ያላት ፍላጎት ነው።
በተመሳሳይም ታሪክ ጸሐፊው አልቤርቶ ሜሎኒ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይቅርታ እንዲደረግላት ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ሐሳብ ሲሰጡ “እንደ እውነቱ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይቅርታ የምትጠይቀው በኃላፊነት ከመጠየቅ ነፃ ለመሆን ስለምትፈልግ ነው” ሲሉ ጽፈዋል። አዎን፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሕዝቡ ዘንድ ተዓማኒነትን ለማግኘት ስትል የቀድሞ የኃጢአት ሸክሟን ለማራገፍ እየሞከረች ያለች ይመስላል። ሐቁን ለመናገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ በጣም እያሳሰባት ያለው ነገር ከዓለም ጋር ሰላም መፍጠር እንጂ ከአምላክ ጋር ሰላም መፍጠር አይመስልም።
እንዲህ ያለው አድራጎት የመጀመሪያውን የእስራኤል ንጉሥ ሳኦልን ያስታውሰናል። (1 ሳሙኤል 15:1-12) የከፋ ስህተት ከፈጸመ በኋላ ሲጋለጥ መጀመሪያ ላይ ለታመነው የአምላክ ነቢይ ለሳሙኤል ስለፈጸመው በደል ሰበብ ለማቅረብ ሞከረ። (1 ሳሙኤል 15:13-21) በመጨረሻም ንጉሡ ስህተት መፈጸሙን ለመቀበል በመገደዱ ለሳሙኤል “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ . . . በመተላለፍ በድያለሁ” በማለት ተናገረ። (1 ሳሙኤል 15:24, 25) አዎን፣ ስህተቱን አምኗል። ይሁን እንጂ ቀጥሎ የተናገራቸው ቃላት በአእምሮው ውስጥ የላቀውን ቦታ የያዘው ነገር ምን እንደሆነ አሳይተዋል:- “በድያለሁ፤ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት፣ እባክህ፣ አክብረኝ።” (1 ሳሙኤል 15:30) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ሳኦል ይበልጥ ያሳሰበው ነገር ከአምላክ ጋር መታረቁ ሳይሆን በእስራኤል ሕዝብ ፊት ያለው አቋም ነበር። ይህ የሳኦል አስተሳሰብ ከአምላክ ይቅርታ አላስገኘለትም። ታዲያ ተመሳሳይ የሆነ አስተሳሰብ ያላቸውን አብያተ ክርስቲያናት አምላክ ይቅር ይላቸዋል ብለህ ታስባለህ?
የሚስማሙት ሁሉም አይደሉም
አብያተ ክርስቲያናት በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው በሚለው ሐሳብ ሁሉም ሰው አይስማማም። ለምሳሌ ያህል በርከት ያሉ የሮማ ካቶሊኮች፣ ሊቀ ጳጳሱ ስለ ባርነት ምሕረት ሲጠይቁ ወይም እንደ ሁስ እና ካልቪን ያሉትን “መናፍቃን” በመልካም እያነሡ ሲናገሩ ደስ አይላቸውም። እንደ ቫቲካን ምንጮች አባባል ስላለፈው ሺህ ዓመት የካቶሊክ ታሪክ “የሕሊና ምርመራ” እንዲደረግ ለካርዲናሎቹ የተላከውን ሰነድ በሰኔ 1994 በሊቀ ጳጳሱ መሪነት ተካሂዶ በነበረ አንድ ስብሰባ ላይ የተገኙ ካርዲናሎች ነቅፈውታል። ዳሩ ግን ሊቀ ጳጳሱ ይህን ሐሳብ ለሕዝብ በሚያቀርቡት መግለጫ ውስጥ ለመጨመር እንደሚፈልጉ በገለጹ ጊዜ የኢጣሊያው ካርዲናል ጃያኮሞ ቢፊ “ቤተ ክርስቲያኒቱ ኃጢአት የለባትም” የሚል መግለጫ አወጡ። የሆነ ሆኖ “ባለፉት መቶ ዘመናት ቤተ ክህነት ለፈጸመቻቸው ስህተቶች ምሕረት መጠየቅ . . . በሌሎች ዘንድ በመልካም ሁኔታ እንድንታይ ሊያደርገን ይችላል” በማለት መስማማታቸውን ገልጸዋል።
“በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙት እጅግ አወዛጋቢ ጉዳዮች መካከል አንዱ ኃጢአትን መናዘዝ ነው” ሲል የቫቲካኑ ዜና ዘጋቢ ሉዪጂ አካቶሊ ተናግሯል። “ሊቀ ጳጳሱ ሚስዮናውያኑ ስህተት ፈጽመዋል ብለው ማመናቸው የማይዋጥላቸው ሚስዮናውያን አሉ።” በተጨማሪም አንድ የሮማ ካቶሊክ ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሊቀ ጳጳሱ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚያሳፍር ሆኖ ከተሰማቸው ይህችኑ ቤተ ክርስቲያን ‘የሰብዓዊ መብት’ ግንባር ቀደም ተሟጋችና የሰው ዘርን ወደ ብሩህ ሦስተኛ ሺህ የምትመራ ‘እናትና አስተማሪ’ አድርገው ለማቅረብ እንዴት እንደሚችሉ ግራ የሚያጋባ ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ ከውርደት ለመዳን ሲባል ብቻ የሚደረግን ንስሐ ያወግዛል። ይህ ዓይነቱ ንስሐ ምሕረት እንዲደረግለት በሚጠይቀው ሰው ላይ ብዙውን ጊዜ ዘላቂ የሆነ የባሕርይ ለውጥ አያመጣም። (ከ2 ቆሮንቶስ 7:8-11 ጋር አወዳድር።) ንስሐ በአምላክ ፊት ዋጋ የሚኖረው ‘ለንስሐ በሚገባ ፍሬ’ ሲደገፍ ማለትም ንስሐ የገባውን ሰው ቅንነት የሚጠቁሙ ማረጋገጫዎች ሲኖሩ ነው።—ሉቃስ 3:8
መጽሐፍ ቅዱስ ንስሐ የሚገባ ወይም የሚናዘዝ ሰው መጥፎ ሥራዎችን መተው ማለትም መጥፎ ነገር ማድረጉን ማቆም እንዳለበት ይናገራል። (ምሳሌ 28:13) ይህ ተፈጽሟልን? የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ስህተቶቻቸውን ከተናዘዙ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው “ክርስቲያን” የሆኑ ሰዎች ተካፋይ በሆኑባቸው በመካከለኛው አፍሪካና በምሥራቅ አውሮፓ በቅርቡ በተነሡ የጎሣ ግጭቶች የተፈጸመው ምንድን ነው? አብያተ ክርስቲያናት ሰላም ለማምጣት አገልግለዋልን? መሪዎቻቸው በሙሉ አባላቶቻቸው የሚፈጽሙትን ግፍ በመቃወም በአንድነት ድምፃቸውን አሰምተዋልን? እንደዚያ አላደረጉም። ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ሃይማኖታዊ አገልጋዮች እንኳን ሳይቀር በእልቂቱ ተካፍለዋል!
መለኮታዊ ፍርድ
ካርዲናል ቢፊ ሊቀ ጳጳሱ በተደጋጋሚ ጊዜያት ይቅርታ መጠየቃቸውን አስመልክተው እንዲህ ሲሉ በምጸት ጠይቀዋል:- “ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ኃጢአቶችን በተመለከተ ዓለም አቀፉን የፍርድ ቀን መጠበቅ አይሻልምን?” እርግጥ የሰው ዘር በሙሉ ለፍርድ መቅረቡ የማይቀር ነገር ነው። ይሖዋ አምላክ ብልሹ የሆኑትን የሃይማኖት ታሪኮች በሙሉ በደንብ ያውቃል። በቅርቡ ጥፋተኞቹን ወደ ፍርድ ያመጣቸዋል። (ራእይ 18:4-8) እስከዚያ ድረስ ግን ከደም ዕዳ፣ አጥፊ ከሆነው አለመቻቻል እንዲሁም የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ይቅርታ ከሚጠይቁባቸው ሌሎች ወንጀሎች ነፃ የሆነ አምልኮ ይኖር ይሆን? አዎን አለ።
ይህን ለማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” በማለት ያወጣውን መመሪያ በመጠቀም ነው። አንዳንድ ሃይማኖቶች ተረስቶ እንዲቀር የሚፈልጉት የታሪክ መዝገብ ኢየሱስ “ሐሰተኛ ነቢያት” ብሎ የጠራቸውን ብቻ ሳይሆን “መልካም ፍሬ” ያፈሩትንም ጭምር ለይቶ ለማወቅ ያስችለናል። (ማቴዎስ 7:15-20) እነዚህ እነማን ናቸው? ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በመመርመር እነማን መሆናቸውን ራስህ ለይተህ እንድታውቅ እንጋብዝሃለን። ዛሬ በዓለም ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚያስችል ቦታቸውን ይዘው ለመቆየት ከመጣር ይልቅ የአምላክን ቃል ለመከተል ጥረት የሚያደርጉ እነማን እንደሆኑ ለመረዳት ጣር።—ሥራ 17:11
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሮም ውስጥ ከ1962-65 በአራት ክፍሎች የተሰበሰበው 21ኛው የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ስብሰባ ነው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ለመሰሉ የጭከና ድርጊቶች ይቅርታ እየጠየቁ ነው
[ምንጭ]
The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck