አብያተ ክርስቲያናት እየተናዘዙ ነው
“ሊቀ ጳጳሱ ቤተ ክርስቲያኒቱን ፈተና ላይ ጣሉ።” “ኢንኩዊዝሽን እና ፀረ-ሴማዊነት—ቤተ ክርስቲያን ጥፋተኛ መሆኗን ለመግለጽ በዝግጅት ላይ ነች።”a “ለጀርመኑ ታላቅ እልቂት ይቅርታ ጠይቁ።” “ሜቶዲስቶች በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙትን ሕንዳውያን ይቅርታ ጠየቁ።”
እነዚህን የመሳሰሉ ርዕሰ ዜናዎች አንብበህ ታውቃለህ? አብያተ ክርስቲያናት የሚሰነዘርባቸውን ወቀሳ መቀበላቸውና እነርሱ ራሳቸው ባለፉት መቶ ዘመናት ለፈጸሙት በደል የሚጠይቁት ይቅርታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ይመስላል። መገናኛ ብዙኃን ሊቀ ጳጳሱ የቤተ ክርስቲያናቸውን ጥፋት ማመናቸውን የሚገልጹ አዳዲስ ዘገባዎችን ያለማቋረጥ በማውጣት ላይ ናቸው።
ሊቀ ጳጳሱ ይቅርታ በሚጠይቁበት ጊዜ
የቫቲካኑ ዜና ዘጋቢ ሉዪጂ አካቶሊ ክዋንዶ ኢል ፓፓ ኪዬዴ ፐርዶኖ (ሊቀ ጳጳሱ ይቅርታ በሚጠይቁበት ጊዜ) በተባለው መጽሐፉ ከ1980 እስከ 1996 ባለው ጊዜ ውስጥ ዳግማዊ ጆን ፖል ቢያንስ 94 ጊዜ ‘የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪካዊ ስህተቶች አምነዋል’ ወይም ‘ይቅርታ ጠይቀዋል’ ብሏል። እንደ አካቶሊ አባባል “በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጥፋተኛነትን አምኖ ለመግለጽ መብት ያላቸው ሊቀ ጳጳሱ ብቻ ናቸው።” የመስቀል ጦርነቶችን፣ ውጊያዎችን፣ አምባገነንነትን መደገፍን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ክፍፍል፣ ፀረ-ሴማዊነትን፣ ኢንኩዊዝሽንን፣ ከማፊያ ጋር ማበርን እንዲሁም የዘር መድልዎ የመሳሰሉትን በካቶሊክ የታሪክ ገጾች ላይ ሠፍረው የሚገኙ እጅግ አወዛጋቢ ጉዳዮችን በተመለከተ ባላቸው መብት ተጠቅመው ሊቀ ጳጳሱ ይቅርታ ጠይቀዋል። በ1994 ለካርዲናሎች በተላከ አንድ ማስታወሻ ላይ (አንዳንዶች ይህን ማስታወሻ ከሊቀ ጳጳሱ ቢሮ የተገኘ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ሰነድ አድርገው ይመለከቱታል) ዳግማዊ ጆን ፖል “በክርስትና የሁለተኛው ሺህ ዘመን ላይ የተፈጸሙ ኃጢአቶችን በአጠቃላይ ስለ መናዘዝ” ሐሳብ አቅርበዋል።
በርካታ ቀሳውስትም የጳጳሱን ፈለግ ተከትለዋል። በታኅሣሥ 1994 ኢል ጆርናሌ የተባለው የኢጣሊያ ጋዜጣ “ብዙ አሜሪካውያን ቀሳውስት በቴሌቪዥን ቀርበው በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል” ብሎ ነበር። ለምን? ሕፃናት የሚያስነውሩ ቀሳውስት የፈጠሩትን ችግር አቅልለው በመመልከታቸው ምክንያት ብዙ ልጆች ጉዳት ስለደረሰባቸው ነው። በጥር 1995 ላ ረፑብሊካ የተባለው ጋዜጣ ሊቀ ጳጳስ ፓየስ አሥራ ሁለተኛ የጀርመኑን ታላቅ እልቂት ዝም ብለው ማየታቸው ያስከተለውን ችግር “በግልጽ መናገር በዘመናዊው የካቶሊክ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ” መሆኑን ዘግቦ ነበር። የናዚ አባላት የፈጸሙትን ወንጀል በመደገፍ የሮማ ካቶሊኮች ስለ ሠሩት “ብዙ ስህተት” የጀርመን ሊቃነ ጳጳሳት ይቅርታ መጠየቃቸውን ይኸው ጋዜጣ በጥር 1995 ዘግቧል። የተለያዩ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናትም ስህተታቸውን አምነዋል።
ይቅርታ የሚጠይቁት ለምንድን ነው?
ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ይቅርታ እንድንጠይቅ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምረን ስህተታቸውን በማመናቸው ብዙ ሰዎች አብያተ ክርስቲያናቱን አወድሰዋል። (ያዕቆብ 5:16) ይሁን እንጂ አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ይህስ ለእርነሱ ያለንን አመለካከት የሚነካው እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሜአ ኩልፓ “የራሴ ስህተት” የሚል ትርጉም ያለው የላቲን ቃል ሲሆን የቤተ ክርስቲያን አባላት የሚደግሙት (ኮንፊቴዎር ወይም “እናዘዛለሁ”) የሚለው የካቶሊክ ጸሎት ክፍል ነው።