“ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ”
ቃሉን መስበክ እረፍት ያስገኛል
ልዩ ተልዕኮ የተሰጠው ፍጹም ሰው ነበር። የማስተማሪያ ዘዴዎቹ ውጤታማ ከመሆናቸው የተነሳ ‘ሕዝቡ በትምህርቱ ተገርመዋል።’ (ማቴዎስ 7:28) ደከመኝ ሰለቸኝ የማይል ሰባኪም ነበር። ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ጥሪቱን ሁሉ ያዋለው ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበኩ ሥራ ነበር። በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ አቻ የማይገኝለት አስተማሪና ሰባኪ ነበር። በዚህ ሥራው በትውልድ አገሩ ውስጥ ያልረገጠው ቦታ የለም።—ማቴዎስ 9:35
ኢየሱስ በጥድፊያ ስሜት ያከናወነው ተልዕኮ በዘመኑ ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ መስበክና ለደቀ መዛሙርቱም ይህንኑ ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማከናወን የሚያስችላቸውን ሥልጠና መስጠት ነበር። (ማቴዎስ 4:23፤ 24:14፤ 28:19, 20) የስብከት ተልዕኮው ክብደትና አጣዳፊነቱ እንዲሁም የሥራው ስፋት ፍጽምና የሌላቸውንና የአቅም ገደብ ያለባቸውን ተከታዮቹን ይብሱኑ ያዝላቸው ይሆን?
በጭራሽ! ኢየሱስ ‘የመከሩ ጌታ’ የሆነው ይሖዋ አምላክ ሠራተኞች እንዲጨምርላቸው እንዲለምኑት ደቀ መዛሙርቱን ከነገራቸው በኋላ ሄደው ሕዝቡን እንዲያስተምሩ ላካቸው። (ማቴዎስ 9:38፤ 10:1) ከዚያም የመስበኩን ተልእኮ ጨምሮ የእርሱ ተከታይ መሆን የሚያስከትለው ኃላፊነት እውነተኛ እረፍትና መጽናኛ እንደሚያስገኝላቸው ማረጋገጫ ሰጣቸው። ኢየሱስ “ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ብሏቸዋል።—ማቴዎስ 11:28
የደስታ ምንጭ
ይህ ምንኛ ርኅራኄ፣ ፍቅር እና ደግነት የተሞላበት ግብዣ ነው! ግብዣው ኢየሱስ ለተከታዮቹ ከልብ እንደሚያስብ ያሳያል። ደቀ መዛሙርቱ የአምላክን መንግሥት ‘ምሥራች’ እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመወጣት እረፍት ያገኛሉ። ይህ ደግሞ እውነተኛ ደስታና እርካታ ያስገኝላቸዋል።—ዮሐንስ 4:36
ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ በፊት ቅዱሳን ጽሑፎች ደስታ ለአምላክ የሚቀርበው ቅዱስ አገልግሎት አንዱ ገጽታ መሆን እንዳለበት ጠበቅ አድርገው ገልጸዋል። ይህ መዝሙራዊው “ምድር ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፣ እግዚአብሔርን በደስታ አገልግሉት፤ በፍስሓ ዝማሬ ፊቱ ቅረቡ” ብሎ በዘመረው መዝሙር ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል። (መዝሙር 100:1, 2 አ.መ.ት ) ዛሬ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሕዝቦች በይሖዋ ደስ የሚላቸው ሲሆን የሚያሰሙት የውዳሴ ቃል ልክ ድል የቀናው ሠራዊት እንደሚያሰማው የሆታ ድምፅ ያለ ነው። ራሳቸውን ለአምላክ የሚያስገዙ ሰዎች ‘በፍስሓ በመዘመር’ ወደ ፊቱ ይቀርባሉ። በእርግጥም ይሖዋ አገልጋዮቹ ራሳቸውን ለእርሱ በመወሰን ኃላፊነታቸውን በሚወጡበት ጊዜ ደስታ እንዲያገኙ የሚፈልግ “ደስተኛ አምላክ” በመሆኑ እንዲህ መባሉ የተገባ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW
እረፍት ያገኙ አገልጋዮች
በመስክ አገልግሎት ጠንክረን መሥራታችን ይበልጥ የሚያዝል ሳይሆን እረፍት የሚያስገኝ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ለኢየሱስ የይሖዋን ሥራ መሥራት ኃይልን እንደሚያድስ ምግብ ሆኖለት ነበር። “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 4:34
በተመሳሳይም ዛሬ ቀናተኛ ክርስቲያን ሰባኪዎች ‘ቃሉን ሲሰብኩ’ ደስታ ያገኛሉ። (2 ጢሞቴዎስ 4:2) በስብከቱ ሥራ በወር ከ70 ሰዓት በላይ የምታሳልፍ በዕድሜ ጠና ያለች ኮኒ የምትባል ክርስቲያን ሴት “በአገልግሎት ከተካፈልኩ በኋላ አመሻሹ ላይ ድካም የሚጫጫነኝ ቢሆንም እንኳ ደስታና እርካታ አጥቼ አላውቅም” በማለት ተናግራለች።
የመንግሥቱ መልእክት ሰሚ ጆሮ ባያገኝስ? ኮኒ ቀጥላ እንዲህ ብላለች:- “የሰዉ ምላሽ ምንም ይሁን ምን በአገልግሎት በመካፈሌ የተቆጨሁበትን ቀን አላስታውስም። ይሖዋን የሚያስደስት ሥራ እየሠራሁ እንደሆነ ከማወቄ በተጨማሪ ስለ እውነት መናገሩ ራሱ አስደሳች እንደሆነ ይሰማኛል። ምክንያቱም እንዲህ በማደርግበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው አስደናቂ ተስፋ በልቤ ውስጥ ይበልጥ ይጠናከራል።”
ሌሎች ደግሞ የአምላክን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ሰዎችን መርዳት ሕይወታቸውን ትርጉም ያለው እንደሚያደርግላቸው የሚሰማቸው አሉ። በስብከቱ ሥራ ሳታቋርጥ በየወሩ ከ50 ሰዓት በላይ የምታሳልፍ ሜሎኒ የምትባል ወጣት እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “አገልግሎት ሕይወቴን አቅጣጫ ስለሚያስይዝልኝና ዓላማ እንዲኖረኝ ስለሚያደርግ እረፍት ያስገኛል ለማለት እችላለሁ። በአገልግሎት ስካፈል የግል ችግሬንና የዕለት ተዕለት ጭንቀቴን እረሳለሁ።”
ሚሊሰንት የምትባለው ሌላዋ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር አገልጋይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥታለች:- “አገልግሎት አምላክ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማና ምድር እንደገና ገነት የምትሆነው እንዴት እንደሆነ ለሌሎች በመንገር የማሳልፈውን እያንዳንዱን ዕለት ትርጉም አዘል ያደርገዋል። በየዕለቱ ይሖዋ እውን እንዲሆንልኝ እንዲሁም በሌላ በምንም መንገድ ማግኘት የማልችለውን ሰላምና ይህ ነው የማይባል ውስጣዊ ደስታ እንዳገኝ ይረዳኛል።”
መልእክቱን የሚቀበሉም እረፍት ያገኛሉ
የመንግሥቱ ሰባኪዎች በክርስቲያናዊ አገልግሎት እረፍት የማግኘታቸው ጉዳይ አሌ የማይባል ሲሆን ሕይወት ሰጪ የሆነውን መልእክት የሚቀበሉ ሰዎችም መጽናኛ ያገኛሉ። በፖርቱጋል የምትኖር አንዲት መምህር በመነኮሳትና በቀሳውስት የሠለጠነች ብትሆንም ያለችበት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ፍላጎቷን እንዳላረካላት ተሰማት። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቿ ምላሽ አላገኙም ነበር። አንዲት የይሖዋ ምሥክር ዘወትር የምትመራላት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ግን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀቷ እያደር እየሰፋ እንዲሄድ ረዳት። መምህሯ በሁኔታው በጣም ተደሰተች። “የማቀርባቸው ጥያቄዎች አሳማኝ በሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች አንድ በአንድ መልስ ያገኙ ስለነበር ሳምንታዊውን የረቡዕ ጥናት የምጠባበቀው በጉጉት ነበር” በማለት ተናግራለች። ዛሬ ይህች ሴት ራስዋን የወሰነች የይሖዋ አገልጋይ ስትሆን እሷ ራሷም በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አማካኝነት ለሌሎች የእረፍት ምክንያት ሆናለች።
ከዚህ እንደምንረዳው የይሖዋ ምሥክሮች የተሰጣቸው የስብከት ተልዕኮ ክብደት ወይም ዓለም አቀፉ የአገልግሎት ክልላቸው ስፋት ተስፋ አያስቆርጣቸውም። የሰዎች ግዴለሽነት ወይም ተቃውሞ መንፈሳቸውን አያዳክመውም። መንግሥቱን እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለመወጣት ራሳቸውን በደስታ አቅርበዋል። ምሥራቹን በማንኛውም ቦታ ለሚያገኟቸው ሰዎች ያካፍላሉ። ለምሳሌ ያህል:- ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ የከባድ መኪናዎች ማቆሚያ ቦታ (1) ኮርያ በሚገኝ የአውሮፕላን ማረፊያ (2) በአንዲስ (3) ወይም ለንደን በሚገኝ አንድ የገበያ ቦታ (4)። በዚህ ዘመን ያሉ የኢየሱስ ተከታዮች መልሶ በሚክሰው በዚህ ዓለም አቀፍ ሥራ በደስታ ይካፈላሉ። አስቀድሞ ቃል እንደገባው እነርሱን አሳርፏቸዋል እንዲሁም ለሌሎች ለብዙ ሰዎች የእረፍት ምንጭ እንዲሆኑ ተጠቅሞባቸዋል።—ራእይ 22:17