ከ1993 “መለኰታዊ ትምህርት” የወረዳ ስብሰባ ሙሉ በሙሉ ተጠቀሙ
1 “አቤቱ ይሖዋ፣ . . . አስተምረኝ።” (መዝ. 86:11 አዓት) ይህ ሕይወቱን ለአምላክ የወሰነ የእያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ ጽኑ ልመና መሆን ይኖርበታል። መማራችንንና የተማርነውንም በሥራ ላይ ማዋላችንን በፍጹም ላለማቆም ቆርጠናል። አንዳንድ ጊዜ ማስተካከያዎች ማድረግ ያስፈልገናል። መዝሙራዊው እንዳደረገውም ልባችን እንዳይከፋፈል አንድ እንዲያደርግልን አምላክን መለመን ያስፈልገናል። “መለኰታዊ ትምህርት” በተባለው የወረዳ ስብሰባ ላይ የሚኖረው ፕሮግራም የዚህ የነገሮች ሥርዓት ተፅዕኖ ቢኖርብንም ይሖዋን በታማኝነት እናገለግለው ዘንድ የሚያስፈልገንን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያና ማስተካከያ ይሰጠናል።
2 የአራት ቀናት ስብሰባ፦ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ፕሮግራሙ አመቺ በሆኑ 13 ቦታዎች ይቀርባል። የግንቦት 1993 የመንግሥት አገልግሎታችን የነዚህን ቦታዎች ዝርዝር አሟልቶ ይዟል። ሙሉው ፕሮግራም ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ በአማርኛ፣ በኪኛሩዋንዳ፣ በሉጋንዳ፣ በትግርኛ እና በስዋሂሊ ይቀርባል። በ2 ቦታዎች ፕሮግራሙ በምልክት ቋንቋ ይተረጎማል። ፕሮግራሙ ሐሙስ 7:20 ላይ ተጀምሮ እሁድ ከሰዓት በኋላ ወደ 10:15 ላይ ያበቃል። (በአዲስ አበባ ግን ሐሙስ ጠዋት ይጀምርና ቅዳሜ ያበቃል።) ስብሰባው በሚካሄድባቸው ቀናት ሁሉ ጠዋት በ1:30 ላይ በር ይከፈታል። ለሥራ የተመደበ ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ከ1:30 በፊት እንዲገባ እንደማይፈቀድለት እባካችሁ አስታውሱ።
3 በፕሮግራሙ ላይ ምን ሊቀርብልን ነው? በተለያየ መንገድ ማለትም በንግግሮች በትዕይንቶች፣ በቃለ ምልልሶችና በሁለት ድራማ መልክ የተዘጋጀ የተትረፈረፈ ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ ይቀርብልናል። ከእነዚህ እጅግ አስፈላጊ ትምህርቶች አንዱም አያምልጣችሁ! ከዚህም በተጨማሪ ከድሮ ወዳጆቻችን ጋር ለመገናኘትና አዳዲስ ጓደኞች ለማፍራት ተስፋ እናደርጋለን። በውጭ አገሮች ተመድበው ሲያገለግሉ የነበሩ ሚስዮናውያን በስብሰባችሁ ላይ ይገኙ ይሆናል። ይህን አጋጣሚ ከእነዚህ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ጋር ለመተዋወቅ ተጠቀሙበት። ወላጅ ከሆንክ ልጆችህም በውይይቱ ውስጥ እንዲሳተፉ አድርግ። የእነዚህ ሚስዮናውያን ደስተኛና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ልጆችህ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን የወደፊት ቋሚ ሥራቸው አድርገው እንዲያስቡበት መሠረት ይጥልላቸው ይሆናል።
4 አሥራቱን በሙሉ ወደ ጎተራው ታመጣላችሁን? በሚልክያስ 3:10 [አዓት] ላይ እስራኤላውያን ይሖዋን ለመፈተን ፈቃደኛ ቢሆኑና አሥራቱን በሙሉ ወደ ጎተራው ቢያገቡ ምንም እስከማይጎድላቸው ድረስ በረከቱን እንደሚያፈስላቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር።
5 ለአንዳንዶች ይሖዋን መፈተን ማለት የወረዳ ስብሰባውን ለመካፈል የእረፍት ጊዜ ወይም ፈቃድ እንዲሰጣቸው በተቻላቸው ፍጥነት አሠሪያቸውን መጠየቅ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ወንድሞች አሠሪያቸው ስብሰባ ለመካፈል ፈቃድ ፈጽሞ የማይሰጣቸው ስለሚመስላቸው ለመጠየቅ ያመነታሉ። መንፈሳዊ ነገሮችን በማይመለከቱ ጉዳዮች ግን ሊያደርጉ የፈለጉትን ነገር ለአሠሪያቸው ለመንገር ምንም ያህል አይቸገሩም።
6 ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ ይገባናል:- በሌላ አካባቢ የሚኖር የአንድ ወዳጃችን ሠርግ ቢኖር ኖሮ ሠርጉ ላይ ለመገኘት አሠሪያችንን ፈቃድ አንጠይቀውም ነበር? ላለመፍቀድ ቢያቅማማ ሠርጉ ላይ መገኘት በጣም እንደሚያስፈልገን በአክብሮት አናስረዳውም ነበርን? ከይሖዋ መማር ሠርግ ከመሄድ ይልቅ በጣም አስፈላጊ መሆኑ የተረጋገጠ ነው! የስብሰባው ፕሮግራም ለመንፈሳዊ ዕድገታችን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ካመንንበት አሠሪያችን ስብሰባው ላይ ለመገኘት እንድንችል ፈቃድ እንዲሰጠን ማሳመኑ ቀላል ይሆንልናል። — ያዕቆብ 1:7, 8
7 እስራኤላውያን የሚሰጡት አሥራት የይሖዋን የአምልኮ ቦታ የሚደግፍ ቁሳዊ ነገር ነበር። በዘመናችን አሥራት በቀጥታ ለይሖዋ አገልግሎትና የመንግሥቱን ሥራዎች ለመደገፍ የሚውለውን ሰዓት፣ ጉልበትና ገንዘብ ይወክላል። አሥራቱ በስብሰባዎች፣ በትልልቅ ስብሰባዎችና በወረዳ ስብሰባዎች ላይ የምናሳልፈውንና የስብሰባ ቦታዎቻችንን ለመጠገንና ለማጽዳት የምናውለውን ጊዜ ያጠቃልላል። “መለኰታዊ ትምህርት” የወረዳ ስብሰባ አሥራቱን በሙሉ ወደ ይሖዋ መንፈሳዊ ጎተራ ለማምጣት የምንችልባቸውን ብዙ አጋጣሚዎች ይሰጠናል። ከነዚህ አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
8 የስብሰባውን ፕሮግራም በትኩረት በመከታተል፣ እያንዳንዱን የመንግሥት መዝሙር በጋለ ስሜት በመዘመር፣ እንዲሁም ከጸሎቱ በኋላ ከልባችን አሜን ለማለት እንድንችል ዘንድ እያንዳንዱን ጸሎት በደንብ በመስማት አሥራቱን ልናመጣ እንችላለን።
9 በእውነት ውስጥ የምናደርገው ዕድገት በጥሩ አዳማጭነታችን ላይ በጣም የተመካ ነው። በትልልቅ የስብሰባ አዳራሾች ወይም ስታዲየሞች ውስጥ በአካባቢያችን ያሉ ሌሎች ሰዎች በሚያደርጓቸው ነገሮች በቀላሉ ልንረበሽ እንችላለን። በዚህ ምክንያት አስተሳሰባችን ከመስመሩ እንዳይወጣ መጠበቅ አለብን። ወደ ስብሰባው ስትመጡ መጽሐፍ ቅዱሳችሁን፣ የመዝሙር መጽሐፋችሁን፣ ብዕራችሁንና ማስታወሻ ወረቀታችሁን እንዲሁም በዚያ ሳምንት የሚጠናውን የመጠበቂያ ግንብ እትም ይዛችሁ በደንብ ተዘጋጅታችሁ መምጣትን አትዘንጉ። እያንዳንዱ ተናጋሪ የተናገራቸውን ነጥቦችና የተጠቀመባቸውን ጥቅሶች በማስታወሻ ላይ መጻፍ ጠቃሚ ነው። የምትወስዱት ማስታወሻ አጭር ይሁን። ብዙ ማስታወሻ መጻፍ አሳባችሁን አሰባስባችሁ እንዳትሰሙ እንቅፋት ሊሆንባችሁ ይችላል። ልጆችንም ቢሆን በትኩረት እንዲያዳምጡ ማሠልጠን ይቻላል። ፕሮግራሙን የሚችሉትን ያህል በደንብ በመከታተል ልጆችም ከወላጆቻቸው ጋር በመሆን አሥራቱን ሊያመጡ ይችላሉ።
10 አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው እቤት ውስጥ በየቀኑ ለተወሰነ ጊዜ ዝም ብለው እንዲያነቡ ወይም ከማኅበሩ ጽሑፎች በአንዱ ላይ ያለውን ስዕል እንዲመለከቱ ዝግጅት ያደርጋሉ። ይህ ዓይነቱ ጥሩ ሥልጠና ልጆቹ በስብሰባዎችና በወረዳ ስብሰባዎች ላይ ዝም ብሎ መቀመጥ የበለጠ ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ልጆቻቸው ስብሰባ ሲሄዱ አሻንጉሊቶችን ወይም የሥዕል መለማመጃ መጽሐፎችን ይዘው እንዲሄዱ በጭራሽ እንደማይፈቅዱላቸው ተናግረዋል። በጣም ትንንሽ የሆኑ ልጆች እንኳን ስብሰባ የሚገኙበት ምክንያት ይሖዋን ለማምለክ መሆኑን መማር ይችላሉ። አሥራቱን በሙሉ ወደ ጎተራ ማምጣት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች በእውነት ሊመሰገኑ የሚገባቸው ናቸው!
11 የስብሰባውን አደረጃጀት ለማገዝ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን በፈቃደኝነት መስጠትም አሥራቱን ከምናመጣባቸው መንገዶች አንዱ ነው። በብዙ ቦታዎች የመሰብሰቢያውን ቦታ ለማጽዳት ሲባል ስብሰባው ከመደረጉ አንድ ወይም ሁለት ቀን ቀደም ብሎ የቅድመ ስብሰባ የጽዳት ፕሮግራም ይወጣል። ስብሰባው በሚደረግበት አካባቢ የምትኖር ከሆነ መላው ቤተሰብህ በጽዳት ፕሮግራሙ ውስጥ እንዲካፈል ለምን ዝግጅት አታደርግም? አንዳንድ ወንድሞች ዕድገት ያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸውንም ይዘዋቸው በመምጣት እነዚህ አዲሶች ከመጠመቃቸው በፊትም ቢሆን የይሖዋን አምልኮ መደገፍ ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ለመማር እንዲችሉ አድርገዋል። ስብሰባው በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ልናደርግ የምንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ለምን በቤተሰብ ደረጃ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆናችሁ አትሠሩም?
12 ለስብሰባው የምናደርገው የገንዘብ ድጋፍም አሥራቱን የምናመጣበት ሌላው መንገድ ነው። ይሖዋ ንጹሑን አምልኮ ለመደገፍ ቁሳዊ ስጦታዎች እንዴት ሊቀርቡ እንደሚችሉ ሲገልጽ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲህ ሲል አዝዟል:- “በእግዚአብሔር ፊት ባዶ እጃቸውን አይታዩ። አምላክህ እግዚአብሔር በረከት እንደ ሰጠህ መጠን እያንዳንዱ ሰው እንደ ችሎታው ይስጥ።” (ዘዳ. 16:16, 17) ሊሰጡ ያቻሉት መጠን ትንሽም ይሁን ብዙ አስቀድመው ያዘጋጁት ስጦታ ይሖዋን ደስ ያሰኘው ነበር። በተመሳሳይም ብዙ ወንድሞች በጥሬ ገንዘብም ይሁን በቼክ (ለ“ይሖዋ ምስክሮች” የሚሰጥ) ስለሚሰጡት መዋጮ በጸሎት ያስባሉ። ትንንሽ ልጆቻችሁ በመዋጮ ሣጥን ውስጥ ገንዘብ እንዲከቱ አድርጋችሁ ታውቃላችሁን?
13 የአዳኛችንን የአምላክ ትምህርት አስከብሩ፦ በጥሩ ምግባራችንና በመልካም ጠባያችን “የአዳኛችን የእግዚአብሔር ትምህርት በሁሉ ነገር እንዲከበር” ልናደርግ እንችላለን። (ቲቶ 2:10 የ1980 ትርጉም) በሌላ አነጋገር በስብሰባው ላይ መለኰታዊውን ትምህርት በሕይወታችን ውስጥ እየሠራንበት እንዳለን ልናሳይ እንችላለን።
14 ጠባያችን እንዴት ሊሆን ይገባል? ዛሬ በዓለም ውስጥ ለሌሎች አሳቢ መሆን እምብዛም አይታይም። በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመሩት የይሖዋ ሕዝቦች ግን የሚያስቡት የራሳቸውን ጥቅም ሳይሆን የባልንጀሮቻቸውን ጥቅም ነው። (ፊል. 2:4) በአካባቢያችን ስላሉ ሰዎች እናስባለን። ምግብ ወይም ጽሑፍ ለማግኘት በምንሰለፍበት ጊዜ አንጋፋም ወይም አንገፋተርም። አረጋውያንና ትንንሽ ልጆች ተሰልፈው እንደቆሙ በቀላሉ ሊገፈተሩ ስሚችሉ እናስብላቸዋልን። በምግብ ቤቶች ለምግብ ቤቱ ሠራተኞች ትሁቶች እንሆናለን እንጂ መስተንግዶው የጠበቅነውን ያህል ባይሆን አናመናጭቃቸዋውም ወይም ከሚገባ በላይ አድርጉልን ባዮች አንሆንም።እንዲሁም ከምንከፍለው ገንዘብ 15 በመቶ የሚሆን መጠነኛ ጉርሻ ትተን በመሄድ በአካባቢው የተለመደውን በደስታ እናደርጋለን።
15 አምላካዊ ጠባያችን በአካባቢያችን ባሉ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው። አምና የወረዳ ስብሰባ በተደረገበት አንድ ከተማ ውስጥ ለ21 ዓመታት በፖሊስ ሠራዊት ውስጥ ሲያገለግል የቆየ አንድ ፖሊስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ሰዎቻችሁ ባሳዩት ሥነ ሥርዓት ተገርሜአለሁ። ተወዳዳሪ የላቸውም፤ ማንም ሳይነግራቸው ቆሻሻዎችን ከመንገድ ያነሳሉ፤ እንዲሁም ሥርዓታሞች ናቸው፤ ስብሰባችሁም በሚገባ የተቀናጀ ነው።” ጨምሮም “ሰዎቻችሁ እኛን ሲያዩ ፈገግ ይላሉ። ይህ ደግሞ ጥሩ ምልክት ነው። እኛ የምንፈልገው ይህንን ነው። ይህ የወዳጅነት ምልክት ነው። ምንም የሚደብቁት ነገር እንደሌለ ያሳያል። ልጆቹ ከወላጆቻው እንደማይለዩና በሚገባ ተቀጥተው ያደጉ መሆናቸውንም አስተውለናል። እውነቴን ነው የምላችሁ በጣም ነው የተገረምኩት። እዚህ መመደብ የሚያስደስት ነው” ብሏል።
16 አንዳንድ ባለ ሥልጣኖች በከተማቸው ውስጥ ስብሰባ እንዲደረግ ለመጋበዝ ቤቴል ድረስ መጥተዋል። ማኅበሩም ይህን የደግነት ግብዣ በመቀበል ሳያሳፍር መልሷቸዋል። የከተማው ምክትል ከንቲባ እንዲህ ብለዋል:- “እንደናንተ ያለ ስመ ጥር ቡድን በከተማችን ውስጥ ስብሰባ በማድረጉ በጣም ተደስተናል። እዚህ እንድትሰበሰቡ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገን ነበር፤ . . . ከዚህ ይበልጥ ያስደሰተን ነገር የለም።” የእያንዳንዱ ወንድምና እህት ጥሩ ጠባይ እዚያ ከተማ ለተሰጠው እጅግ በጣም ጥሩ ምስክርነት አስተዋጽኦ አድርጓል።
17 ጥሩ ምሳሌ ሊሆን በሚችል ጠባይህ አዳኛችን የሆነው አምላክ የሚሰጠንን ትምህርት በግለሰብ ደረጃ ታስከብራለህን? እንዲህ ልታደርግ የምትችልባቸው በርካታ መንገዶች እነሆ:-
አለባበስ፣ አበጣጠርና አጋጌጥ፦ የወረዳ ስብሰባ ላይ በምንገኝበት ጊዜ ሽርሽር ላይ እንደሆንን ሊሰማን አይገባም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ለመማር ራሳችንን የምናቀርብበት ጊዜ ነው። እንዲህ ከሆነ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ የምንለብሰውን ዓይነት ልብስ መልበስ አይገባንምን? (1 ጢሞ. 2:9, 10) ከዚህም በተጨማሪ ፕሮግራሙ ካበቃ በኋላ ስለምንለብሰው ልብስ መጠንቀቅ ይገባናል። በየትኛውም ዕድሜ ላይ የምንገኝ ብንሆን ወዳረፍንባቸው ቦታዎች ከተመለስን በኋላ በስብሰባው ላይ የለበስነውን ልከኛና ክብር ያለው ልብስ አውልቀን የተዝረከረከና ንጹሕ ያልሆነ ልብስ የሚለብሱ ዓለማውያን የሚያስመስለንን ልብስ ብንለብስ አቋማችን የማይለዋወጥ እንደሆነ ያሳያልን? እንዲህ ማድረጋችን በስብሰባዎች ላይ የምንለብሳቸው ልብሶች የአኗኗር መንገዳችንን የሚያንጸባርቁ ሳይሆኑ ለጊዜው ብቻ የተለበሱ ልብሶች እንደሆኑ አያስመስልብንምን? የይሖዋን ስም እንደተሸከምን አትርሱ። በእውነት መንገድ ላይ ተገቢ ያልሆነ ክስ እንዲመጣ እንዳናደርግ እያንዳንዳችን መጠንቀቅ አለብን።
የጥምቀት እጩዎች ይህን በመሰለ የተቀደሰ ስብሰባ ላይ ዓለማዊ መፈክሮች፣ አርማዎች ወይም የንግድ ማስታወቂያዎች ያሉባቸው ካናቴራዎች (ቲ–ሸርቶች) ለብሶ መምጣት ተገቢ እንዳልሆነ ሊነገራቸው ይገባል። ሽማግሌዎች የጥምቀት ዕጩዎቹ የጥምቀት ጥያቄዎቹን በቅድሚያ በሚገባ የተወያዩባቸውና እያንዳንዱ ዕጩ እንዲጠመቅ የተፈቀደለት መሆን አለመሆኑ የተነገረው መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው። (ጥያቄዎቹ ላይ ሲወያዩ በሚጠመቁበት ጊዜ ለጥምቀት የሚሆኑ ተገቢና ልከኛ ልብሶችን መልበስ እንደሚያስፈልግ ሐሳብ ማቅረብ ይችላሉ።) በሽማግሌዎች የተፈቀደላቸው የጥምቀት ዕጩዎች ስብሰባው ላይ ስማቸውን ማስመዝገብ አያስፈልጋቸውም።
ሆቴሎችና ሞቴሎች፦ በምታርፉበት ሆቴል ወይም ሞቴል ውስጥ የመንፈስ ፍሬዎች አሳዩ። የሆቴሉ ሠራተኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሰዎችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ በቂ የመገልገያ መሣሪያዎች ላይኖሯቸው ይችላሉ። ትዕግሥተኞች ሁኑ፤ ራሳችሁን በሌሎች ቦታ አስቀምጡ፤ እንዲሁም ተገቢውን የአገልግሎት ጉርሻ ስጧቸው።
ልጆችም የሆቴሉን ዕቃ በጥንቃቄ በመያዝ እንዲሁም ስለመዋኛ ቦታውና ሌሎች ዕቃዎች አጠቃቀም የተሰጡ ሕጎችን በመታዘዝ የበኩላቸውን ሊያደርጉ ይችላሉ። ወላጆች ከስብሰባው በፊት ልጆቻቸው ምን ዓይነት ጠባይ እንዲያሳዩ እንደሚፈልጉ በመንገር እነሱም ክርስቲያናዊ ጠባይ የማሳየት የግል ኃላፊነት እንዳለባቸው ቢያሳስቧቸው ሊጠቅማቸው ይችላል።
የድምፅና የምስል መቅረጫ መሣሪያዎች፦ ፕሮግራሙን በቪድዮ ካሜራ መቅረጽ የተፈቀደ ቢሆንም በምትቀርጹበት ጊዜ ለሌሎች አሳቢዎች እንደምትሆኑ እናውቃለን። ፕሮግራሙን በምትቀርጹበት ጊዜ ሌላውን ተሰብሳቢ መከለል ፍቅር እንዳለን አያሳይም። በመቀመጫችሁ ላይ ሆናችሁ ፕሮግራሙን ብትቀዱ አንቃወምም። ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት ካሜራም ይሁን የድምፅ መቅረጫ በስብሰባው ቦታ ካለው የኤሌክትሪክ መሥመር ወይም የድምፅ ማስተላለፊያ ጋር እንዲያያዝ አይፈቀድም። እንዲሁም በመተላለፊያዎች ወይም መኪና በሚተላለፍባቸው ቦታዎች ላይ ምንም ዓይነት መሣሪያ ማስቀመጥ አይቻልም።
መቀመጫዎች፦ መቀመጫ መያዝ የሚፈቀደው ለቤተሰባችሁና ከእናንተ ጋር በመኪናችሁ አብሮ ለሚጓዝ ሰው ብቻ መሆኑን እባካችሁ አስታውሱ። በሁሉም ስብሰባዎች ላይ አረጋውያንና አካለ ስንኩል ለሆኑ ልዩ ቦታ ይዘጋጃል። እባካችሁ ለአረጋውያን አሳቢዎች ሁኑ። ባለፉት ጊዜያት ለአረጋውያን የተዘጋጁት ቦታዎች በወጣቶች በመሞላታቸው አንዳንድ አረጋውያን ወንድሞች በማይመቹ አካባቢዎች ቦታ ፈልገው ለመቀመጥ ተገደዋል። የተለየ ቦታ ወይም ክፍል እንዲዘጋጅላቸው ለሚጠይቁ እንደ አለርጂ ያሉ ችግሮች ላሉባቸው ሰዎች ግን ቦታ ልናዘጋጅ የማንችል በመሆናችን እናዝናለን።
የግል ዕቃዎች፦ ወደ ስብሰባው የምታመጧቸውን የግል ዕቃዎች በተቻለ መጠን እንድትቀንሱ ሐሳብ እናቀርባለን። ዕቃው ከመቀመጫችሁ ሥር ሊቀመጥ የማይችል ከሆነ ባታመጡት ወይም በመኪናችሁ ኮፈን ውስጥ ብትተዉት ይሻላል። አደጋ እንዳይደርስ ለመከላከል ሲባል ትልልቅ ማቀዝቀዣዎችን በመተላለፊያዎች ላይ ማስቀመጥ የተከለከለ ነው። ከመቀመጫችሁ ቀጥሎ ባለው መቀመጫ ላይ ብታስቀምጡት ደግሞ አንድ ሰው መቀመጫ ያጣል ማለት ነው።
የጽሑፍና የምግብ አገልግሎት፦ ምንም ነገር ባለማባከን አምላክ ለሰጠን መልካም ስጦታ ያለንን አድናቆት ልናሳይ እንችላለን። (ዮሐ. 6:12 የ1980 ትርጉም) እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ የምግብ ትኬታችሁን በቅድሚያ እንድትገዙ ሐሳብ እናቀርባለን። ከአሁን ጀምራችሁ ለጽሑፍ የሚሆን ገንዘብ ለማጠራቀም ዕቅድ ልታወጡ ትችላላችሁ። ምግብና ጽሑፍ ለመግዛት በምትሰለፉበት ጊዜ እባካችሁ ለሌሎች ፍቅራዊ አሳቢነት አሳዩ።
18 ለሌሎች ፍቅራዊ የሆነ አሳቢነት በማሳየት በየቀኑ በተለይም መኪና ማቆሚያና መቀመጫ ለመፈለግ ረዥም ጊዜ በሚወስድበት ሐሙስ ዕለት በስብሰባው ቦታ ቀደም ብላችሁ ለመድረስ ዕቅድ አውጡ።
19 ከይሖዋ ለመማር በመቻላችን እንዴት ታድለናል! “መለኰታዊ ትምህርት” የተባለውን የወረዳ ስብሰባ በጊዜያችን፣ በጉልበታችንና በቁሳዊ ንብረታችን መደገፋችን ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰቦቻችን ዘላቂ መንፈሳዊ ጥቅም ያመጣል።
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል5]
7 የመንግሥት አገልግሎታችን፣ ጥቅምት 1993
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል6]
8
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል7]
9
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል8]
10