ማስታወቂያዎች
◼ በአገልግሎት የምንጠቀምባቸው ጽሑፎች በየካቲት፦ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ። በመጋቢት፦ ራእይ — ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! በሚያዝያና በግንቦት፦ መጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች ኮንትራት ማስገባት። ማሳሰቢያ:- ከላይ የተጠቀሱት ጽሑፎች የሚያስፈልጓቸው ጉባኤዎች በሚቀጥለው ወር በሚልኩት የጽሑፍ መጠየቂያ ቅጽ (S-14-AM) ላይ ማዘዝ ይችላሉ።
◼ ጸሐፊውና የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ የሁሉንም የዘወትር አቅኚዎች እንቅስቃሴ መገምገም ይኖርባቸዋል። የሚፈለግባቸውን ሰዓት ማሟላት ያስቸገራቸው ካሉ ሽማግሌዎች አቅኚዎቹን ለመርዳት ዝግጅት ማድረግ ይገባቸዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳብ ለማግኘት ጥቅምት 1, 1993 እና ጥቅምት 1, 1992 ከማኅበሩ የተላኩትን ደብዳቤዎች (S-201-AM) እንደገና ተመልከቱ። በተጨማሪም በ9–68 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣውን “ጭማሪው ስለቀጠለ የአሠራር ደንቦችን ማቃለል አስፈልጓል” የሚለውን ርዕስ ከአንቀጽ 12 እስከ 20 ተመልከቱ።
◼ የመታሰቢያው በዓል ቅዳሜ መጋቢት 26, 1994 ይከበራል። ምንም እንኳን ንግግሩ ቀደም ብሎ ሊጀመር ቢችልም የመታሰቢያውን ቂጣና ወይን ግን ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ መዞር እንደሌለባቸው እባካችሁ አስታውሱ። ፀሐይ የምትጠልቅበትን ሰዓት በአካባቢያችሁ ካሉ ምንጮች ጠይቃችሁ አረጋግጡ። ከመስክ አገልግሎት ሥምሪት ስብሰባ በስተቀር በዚያን ቀን ሌላ ስብሰባ መደረግ አይኖርበትም። ጉባኤያችሁ ዘወትር ቅዳሜ ስብሳባ የሚያደርግ ከሆነና ያልተያዘ የመንግሥት አዳራሽ ካገኛችሁ ስብሰባውን በሳምንቱ ውስጥ በሌላ ቀን ልታደርጉት ትችላላችሁ።
◼ በመጋቢትና በሚያዝያ ረዳት አቅኚዎች ሆነው ለማገልገል የሚፈልጉ አስፋፊዎች ካሁኑ እቅድ ማውጣትና ማመልከቻቸውን አስቀድመው መስጠት ይኖርባቸዋል። ይህም ሽማግሌዎች አስፈላጊውን የመስክ አገልግሎት ዝግጅት እንዲያደርጉና በቂ ጽሑፍ እንዲኖር ለማድረግ እንዲችሉ ይረዳ ቸዋል።
◼ አዲስ የወጡ የኮምፒዩተር ዲስኬቶች:- ጌትቨርስ የተባለ ፕሮግራም። ይህ አዲስ ፕሮግራም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቀጥታ ወደ አብዛኞቹ የዶስ ወርድ ፕሮሰሰሮች ለማስገባት ያገለግላል። ፕሮግራሙ ንግግሮችን ለመዘጋጀትና የጥቅስ ዝርዝሮችን ለመጻፍ ይረዳል። ጌትቨርስ በእንግሊዝኛ ብቻ የተዘጋጀ ፕሮግራም ሲሆን በ5 1/4 ኢንች 360 ኪሎባይት ወይም በ3 1/2 ኢንች 720 ኪሎባይት ዲስኬቶች ማግኘት ይቻላል። ይህንን ፕሮግራም ለመጠቀም ኮምፒዩተራችሁ ውስጥ ባለ ማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ወይም ባለ ማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም/ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል መኖር አለበት።
◼ አዲስ የመጡ ጽሑፎች:-
በአማርኛ፦ እንደ አንድ አካል ሆነው በዓለም ዙሪያ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት የይሖዋ ምስክሮች (ብሮሹር)፤ የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው። በእንግሊዝኛ፦ የ1994 የቀን መቁጠሪያ፣ ዘፍጥረት (በ4 ካሴቶች)፣ ዕዝራ፣ ነህምያ፣ አስቴር (በ2 ካሴቶች)፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተባለው ቪድዮካሴት (ክፍል 1) ።
የሌሉ ጽሑፎች፦ ከጥቂት ጊዜ በፊት በእንግሊዝኛና በሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች መጥቶልን በነበረበት ወቅት አንድ ሣጥን በመጥፋቱ ምክንያት በማስታወቂያ የተነገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ካሴቶች፣ የመንግሥቱ ዜማዎች ቁጥር 1 እና ቪድዮ ካሴቶች ለጊዜው የሌሉን በመሆናቸው እናዝናለን። እነዚህን ካሴቶች ከማዘዛችሁ በፊት ሌላ ማስታወቂያ እስኪወጣ ጠብቁ።
◼ “መለኮታዊ ትምህርት” በተባለው የወረዳ ስብሰባችን ላይ በቤቴል ለማገልገል ለሚፈልጉ የተዘጋጀ ስብሰባ አልነበረንም። ስለዚህ በአዲስ አበባ በሚገኘው ቢሮአችን ለማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ የሚከተሉትን መረጃዎች በማሟላት እንዲጽፉልን እንጠይቃለን። እነርሱም:- ስም፣ ዕድሜ፣ የተጠመቁበት ቀን፣ ልዩ ችሎታ፣ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመሩበት ጊዜ (የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከሆኑ)፣ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙበት ጉባኤ። አመልካቾች ዕድሜያቸው ከ19 እስከ 35 ዓመት ድረስ የሆነ፣ ነጠላ ወይም ባለትዳሮች ሆነው የሚያሳድጓቸው ልጆች የሌሏቸው ሊሆኑ ይገባል። በተለይ አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና ትግርኛ በመተርጎም የሚረዱን በጣም ያስፈልጉናል።