የጥያቄ ሣጥን
◼ በድምጽ ብልጫ የሚወሰን ጉዳይ ለጉባኤው ማቅረብ ቢያስፈልግ መጠበቅ ያለበት ሥርዓት ምንድን ነው?
በድምጽ ብልጫ እንዲወሰኑ የሚያስፈልጉ ጉዳዮች የመንግሥት አዳራሽ ማደስ ወይም አዲስ የመንግሥት አዳራሽ መሥራት፣ ለማኅበሩ ልዩ መዋጮ መላክ አለበለዚያም የክልል የበላይ ተመልካቹን ወጪ መሸፈንን የመሳሰሉ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ከጉባኤው ሒሳብ አንዳንድ ወጪዎች ሲደረጉ ድምጽ በመስጠት እንዲያጸድቁት ብዙውን ጊዜ አስቀድሞ ጥያቄውን ለጉባኤው ማቅረቡ የተሻለ ነው።
አስፈላጊ ከሆኑ ፕሮጄክቶችና የሥራ እንቅስቃሴዎች ጋር በቀጥታ በተያያዘ መንገድ መሟላት የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ሲኖሩ ግን ከዚህ የተለየ ነገር ሊደረግ ይችል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ጉባኤው በዓለም ዙሪያ ለሚደረገው የስብከት ሥራ የሚሆን ገንዘብ በየወሩ ለማኅበሩ መዋጮ እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፎ ሊሆን ይችላል። ለአንዳንድ የመገልገያ መሣሪያዎችና የጽዳት ዕቃዎች እንዲሁም የተለመዱት የመንግሥት አዳራሽ ወጪዎችን ለመሸፈን የጉባኤው የድምጽ ብልጫ ውሳኔ አያስፈልግም።
አንድ ነገር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሽማግሌዎች አካል ጉዳዩን በጥልቀት ሊወያይበት ያስፈልጋል። አብዛኛዎቹ ሽማግሌዎች ከተስማሙ አንድ ሽማግሌ ምናልባትም ከጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ አባላት አንዱ በአገልግሎት ስብሰባው ላይ የጉባኤውን ውሳኔ የሚጠይቅ ጽሑፍ አዘጋጅቶ ይቀርባል።
የስብሰባው ሊቀመንበር የሆነው ሽማግሌ በአጭሩ ምን ነገር አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘና የሽማግሌዎች አካል ተወያይቶበት መፍትሔ ይሆናል ያለውን ሐሳብ በሚገባ መንገድ ያቀርባል። ከዚያ በኋላ ጉባኤው ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን እንዲጠይቅ አጋጣሚ ይሰጠዋል። ጉዳዩ አወዛጋቢ ከሆነ እያንዳንዱ ሰው በነገሩ እንዲያስብበት ጊዜ ለመስጠት ድምጽ የሚሰጥበትን ቀን ለሚቀጥለው የአገልግሎት ስብሰባ ማዘግየቱ የተሻለ ሊሆን ይችላል። በመጨረሻ ለውሳኔ ድምጽ የሚሰጠው እጅ በማውጣት ይሆናል።
ሕጋዊ ነገሮችን ወይም የመንግሥት አዳራሹን ለመስራት ከተጠየቀው ብድር ጋር ግንኙነት ያላቸው ጉዳዮች እስካልሆኑ ድረስ ድምጽ መስጠት የሚችሉት ራሳቸውን የወሰኑና የተጠመቁ የጉባኤው አባላት ብቻ ናቸው። ከሌላ ጉባኤ በእንግድነት የመጡ ካሉ ድምጽ በመስጠት መሳተፋቸው ተገቢ አይሆንም።
የቀረበው ጥያቄ ውሳኔ ካገኘ በኋላ ቀን ተጽፎበትና ተፈርሞበት በጉባኤው ፋይል ውስጥ መቀመጥ ይኖርበታል።