ከመመሥከር ወደ ኋላ አላሉም
1 የይሖዋ ምሥክሮች የተባለው ስማችን እኛን ለይቶ ከማሳወቁም በላይ የምናደርገውንም ሥራ ይጠቁማል። ስለ አምላካችን ስለ ይሖዋ ክብር እንመሠክራለን። (ኢሳ. 43:10, 12) የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን የፈለገ ሁሉ በዚህ የመመሥከር ሥራ መሳተፍ ይኖርበታል። በአንደኛ ደረጃ ምሥክርነቱ የሚሰጠው በሕዝባዊ አገልግሎታችን ነው። ይህም ከቤት ወደ ቤት መሄድን፣ በመንገድ ላይ መመሥከርን፣ ተመላልሶ መጠየቆችን ማድረግንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራትን ይጨምራል። ሁላችንም የተሟላ ተሳትፎ እንድናደርግ መመከራችን የተገባ ነው።—1 ቆሮ. 15:58
2 ሆኖም አንዳንድ የጉባኤ አባላት ማድረግ የሚችሉት ተሳትፎ የተወሰነ ሊሆን ይችላል። ከባድ ሕመም ወይም አካለ ስንኩልነት የሚያከናውኑትን የአገልግሎት መጠን ወስኖባቸው ይሆናል። ተቃዋሚ የሆኑ ዘመዶች ልንወጣቸው የማንችል የሚመስሉ መሰናክሎችን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ወጣቶችን ደግሞ የማያምኑ ወላጆቻቸው እንዳያገለግሉ ይከለክሏቸው ይሆናል። ትራንስፖርት በሌለባቸው ገለልተኛ ስፍራዎች የሚኖሩ ወንድሞች መመሥከር በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። በተፈጥሯቸው ዓይና አፋር የሆኑትን ፍርሃት ከመመሥከር ወደኋላ እንዲሉ አድርጓቸው ይሆናል። እንደነዚህ ባሉ ሁኔታዎች ሥር ያሉ አስፋፊዎች መሥራት የቻሉት ሌሎች ከሚሠሩትና እነሱም መሥራት ከሚፈልጉት ያነሰ መሆኑን በመመልከት ክርስቲያን ለመሆን እንደማይበቁ ይሰማቸው ይሆናል። ጥረታቸውን እንዲያንኳስሱ የሚያደርግ አንድም ምክንያት የለም። (ገላ. 6:4) በምንም ዓይነት ሁኔታ ሥር ቢገኙም ምርጣቸውን በመስጠታቸው ይሖዋ እንደሚደሰት ማወቃቸው ሊያጽናናቸው ይችላል።—ሉቃስ 21:1-4
3 ተሳትፎ ማድረግ የሚቻልባቸውን መንገዶች መፈለግ፦ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር የነበሩ ወንድሞች ልዩ ልዩ መሰናክሎች ከመመሥከር እንዲያግዷቸው እንዳልፈቀዱ የሚያሳዩ በሺህ የሚቆጠሩ ተሞክሮዎች አሉ። በራሳቸው አነሣሽነት መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር የሚችሉበትን የተለያዩ መንገዶች ፈጥረዋል። ከቤት መውጣት የማይችሉት በስልክ ለመመሥከር በመሞከራቸው ሥራ የሞላበት ትልቅ የአገልግሎት በር ተከፍቶላቸዋል። እነርሱን ለመጠየቅ ወደ ቤታቸው የመጣ ሁሉ ሊያዳምጥ እንደሚችል አድርገው ይመለከቱታል። ተቃዋሚ ቤተሰብ ያሏት ሚስት ቤቷ መመሥከር አትችል ይሆናል። ሆኖም ከጎረቤቶቿ ወይም በየዕለቱ ከምታገኛቸው ሰዎች ጋር ለመነጋገር ባሏት አጋጣሚዎች ትጠቀማለች።
4 የማያምን ወላጅ አንድን ወጣት ለሕዝብ በሚሰጠው ምሥክርነት እንዳይካፈል ይከለክለው ይሆናል። ይህን ችግር ሊወጣው እንደማይችል መሰናክል አድርጎ ሊመለከት አይገባም። ከዚህ ይልቅ የክፍል ጓደኞቹንና አስተማሪዎቹን እንደ ግሉ “የአገልግሎት ክልል” በመቁጠር ጥሩ ምሥክርነት ሊሰጥ ምናልባትም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ሊመራ ይችላል። በገለልተኛ ስፍራዎች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በደብዳቤ በመመሥከር መሳተፍ ችለዋል። በክርስቲያናዊ ቅንዓት የሚገፋፉ ሁሉ ምን ጊዜም ቢሆን “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች” ከመሆን ለመዳን የሚያስችል አንድ ዓይነት መንገድ ይፈልጋሉ።—2 ጴጥ. 1:8
5 ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ባለን ተሳትፎ ረገድ ይሖዋ ለሁላችንም አንድ ዓይነት መመዘኛ አውጥቶልናል። እሱም “በሙሉ ነፍስ” አገልግል የሚል ነው። (ቆላ. 3:23 አዓት) በአገልግሎት የምናጠፋው ጊዜና የምናገኘው ፍሬ የተለያየ ቢሆንም ሁላችንም እንድናገለግል የሚያነሳሳን ነገር አንድ ነው፤ ይኸውም ‘ከፍጹም ልብ’ የሚወጣ እውነተኛ ፍቅር። (1 ዜና 28:9፤ 1 ቆሮ. 16:14) ምርጣችንን እስከሰጠን ድረስ እምነት እንደጐደለን ወይም የማንረባ የጉባኤ አባላት እንደሆንን ጨርሶ ሊሰማን አይገባም። ልክ እንደ ጳውሎስ ‘ጠቃሚ የሆነውን ነገር ሁሉ ከመናገር ወይም ሕዝብ ባለበት እየሄድን ሰዎችን ከማስተማር ወደ ኋላ እንዳላልን’ በትክክል መናገር እንችላለን።—ሥራ 20:20 አዓት