ለአምላክ ቤት አድናቆት አሳዩ
1 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሖዋ ሕዝቦቹ አዘውትረው በቤቱ እንዲሰበሰቡ አዟቸው ነበር። (ዘሌ. 23:2) እነዚህ ስብሰባዎች አእምሮአቸው በአምላክ ቃል ላይ እንዲያተኩር፣ በተመስጦ የሚያሰላስሉበት ጊዜ እንዲያገኙ፣ አዘውትረው እንዲገናኙና የይሖዋን ሕግ እንዲወያዩ የሚረዷቸው ነበሩ። እንደዚህ ካደረጉ አእምሮአቸው በአምላክ ሐሳብ ይሞላል። ይህም የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት ያመጣላቸዋል። እውነትም እንዴት ያሉ አስደሳች ጊዜያት ነበሩ። ይህ ዝግጅት አንድነትንና ንጹሕ አምልኮን ለማስፋፋት የሚረዳ ነበር። በዛሬው ጊዜ በአምላክ ቤት ውስጥ የሚደረጉት ስብሰባዎችም አስፈላጊነታቸው ከዚህ ያነሰ አይደለም።
2 ስብሰባዎችን እንደምናደንቅ እንዴት ማሳየት እንችላለን? አንዳንድ ጉባኤዎች የተሰብሳቢዎቻቸው ቁጥር አነስተኛ እንደሆነ ሪፖርት አድርገዋል። አልፎ አልፎ የግለሰቦች ሁኔታ ከስብሰባ እንዲቀሩ ሊያደርጋቸው ይችላል። ነገር ግን ትንንሽ ችግሮች አዘውትረህ በስብሰባዎች ላይ እንዳትገኝ ሳንካ እንዲሆኑብህ ትፈቅዳለህን? አንዳንዶች ምናልባት ትንሽ ራስ ምታት ስላመማቸው ወይም ሲሠሩ ውለው ስለደከማቸው እቤት ለመቅረት ይወስኑ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ እቤት ሊጠይቋቸው የመጡትን የማያምኑ ዘመዶቻቸውን ማስደሰት የተገባ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ በጣም የሚወዱትን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመመልከት ወይም አንዳንድ የስፖርት ጨዋታዎች እንዳያመልጧቸው ሲሉ እንኳ ከጉባኤ ይቀራሉ። በዚህ ሁኔታ የተገለጸው የአድናቆት ደረጃ የቆሬ ልጆች “ነፍሴ የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን” አዓት ] አደባባዮች ትወዳለች ትናፍቅማለች” በማለት ከገለጹት ልባዊ ስሜት በጣም ያነሰ ነው።— መዝ. 84:2
3 ምንም እንኳ በስብሰባዎቻችን ላይ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ቢቀርብም አንዳንድ ተሰብሳቢዎች በትኩረት በማዳመጥ ረገድ ችግር አለባቸው። ምናልባት የቀን ሕልም ይይዛቸዋል አሊያም በቀን ውስጥ ስላጋጠሟቸው ነገሮች እያሰቡ ነው ወይም ከናካቴው እንቅልፍ ሸለብ አድርጓቸው ሊሆን ይችላል። ብዙዎች ግን አጠር ያሉ ማስታወሻዎችን መያዝ ንቁ ሆኖ ለመከታተል የሚያስችል ሆኖ አግኝተውታል። ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ነጥቦችን መጻፍ በማይረሳ ሁኔታ ትምህርቱን በአእምሮ ላይ ለመቅረፅ ይረዳል። በደንብ ከተዘጋጀን ደግሞ የሚነገረውን ለመከታተል በይበልጥ “ልንጠነቀቅ” እንችላለን።— ዕብ. 2:1
4 ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች በስብሰባዎች ላይ የሚሰጡትን ትምህርቶች መቅሰም አለባቸው። ወላጆች ትኩረታቸውን ለመሳብና ጸጥ እንዲሉ ብለው ለልጆቻቸው አሻንጉሊት የሚሰጡ ከሆነ ወይም እርሳስ ሰጥተው እየሳሉ እንዲጫወቱ የሚያደርጉ ከሆነ ልጆቹ የሚማሩት ነገር የጣም የተወሰነ ይሆናል። ልጆች እንዲጫወቱ፣ እንዲያወሩ፣ እንዲጮሁ ወይም በአካባቢው የተቀመጡትን የሚረብሹ ሌሎች ነገሮችን እንዲያደርጉ የሚፈቅዱላቸው ከሆነ ተገቢ ተግሣጽ እንደጎደላቸው ያሳያል። በስብሰባ ጊዜ ተደጋጋሚና አላስፈላጊ የሆነ ወደ መጸዳጃ ቤትና ውኃ ለመጠጣት የሚደረግ ምልልስ ልጁ በዚህ ጊዜ ከወላጆቹ አንዱ እንደሚከተለው ካወቀ ምልልሱ ሊቀንስ ይችላል።
5 በሰዓቱ መገኘት አስፈላጊ ነው፦ አልፎ አልፎ ልናስቀረው የማንችለው ሁኔታ ያጋጥመንና በስብሰባ ላይ በወቅቱ እንዳንገኝ ሊያደርገን ይችላል። ነገር ግን ሳያስፈልግ ከመክፈቻው መዝሙርና ጸሎት በኋላ መድረስን ልማድ ካደረግነው ለስብሰባዎቻችን ቅዱስ ዓላማ እንዲሁም ሌሎችን እንዳንረብሽ ላለብን ኃላፊነት አክብሮት እንደጎደለን ያሳያል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከወንድሞቻችን ጋር መዘመርና መጸለይ ከአምልኮታችን ክፍል አንዱ መሆኑን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። አላስፈላጊ አርፋጅነት በጥሩ ሁኔታ ያለመደራጀት ወይም በቅድሚያ እቅድ ያለማውጣት ውጤት ነው። በሰዓቱ መገኘት ለስብሰባዎቻችን አክብሮትና አድናቆት እንዳለን ያሳያል።
6 መጨረሻው ይበልጥ እየቀረበ በሄደ መጠን አብሮ የመሰብሰብም አስፈላጊነት በዛው ልክ ከፍ ይላል። (ዕብ. 10:24, 25) እንግዲያው ዘወትር በስብሰባዎች በመገኘት፣ በቅድሚያ በመዘጋጀት፣ በሰዓቱ በመድረስ፣ በተመስጦ በማዳመጥና ከዚያም በሥራ በማዋል አድናቆታችንን እናሳይ።