የመንግሥቱን ቃል ትርጉም ማስተዋል
1 ኢየሱስ ስለ ዘሪው በተናገርው ምሳሌ ላይ “በመልካም መሬት” ላይ የተዘራው ዘር ‘ቃሉን ሰምቶ ትርጉሙን የሚያስተውል ሰውን ያመለክታል’ ብሎ ነበር። (ማቴ. 13:23 አዓት ) ስለ መንግሥቱ ከሰማን በኋላ ‘ትርጉሙን አስተውለናልን’? መንግሥቱ ሕይወታችንን የለወጠው ምን ያህል ነው? የመልእክቱን ትርጉም እንዳስተዋልን በማሳየት የመንግሥቱን ጥቅሞች በሕይወታችን ውስጥ አንደኛ ቦታ ሰጥተናቸዋልን?
2 የመንግሥቱን መልእክት በትክክል መረዳት የግል ጥናት ማድረግን ይጠይቃል። በሚቀርቡልን መንፈሳዊ ምግቦች ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መውስድ አለብን። መጠበቂያ ግንብ ን በችኮላ ማንበብ ጣፋጭና ተመጣጣኝ የሆነ ምግብን በጥድፊያ እንደ መብላት ነው። መንፈሳዊ ምግቦችን አንድ ባንድ ለመመርመር ጊዜ ትመድባለህን? ከጥናቱ ይበልጥ ለመጠቀም አንድ የሚገፋፋ ነገርና ጤናማ መንፈሳዊ ፍላጎት ያስፈልጋል። ይህ ከሌለ ሌሎች ተግባራት ከግል ጥናት የምናገኘውን ጥቅም ሊያሳጡን ወይም ለጥናቱ የሚያስፈልገንን ጊዜ ሊያባክኑብን ይችላሉ። ጥሩ የጥናት ፕሮግራምን የሙጥኝ ብሎ መያዝ ቀላል አይደለም። ምንም እንኳ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ለመወሰን በጥንቃቄ ማመዛዘን የሚጠይቅ ቢሆንም የሚገኙት መንፈሳዊ በረከቶች ዋጋ አይተመንም።— ምሳሌ 3:13–18፤ ቆላ. 1:27
3 ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር የተባለው ቡክሌት በየቀኑ ስለ መንግሥቱ የሚገልጹ ገንቢና የሚያንጹ ሐሳቦችን እንድናስብ ይረዳናል። “በመንፈሳዊ የጎደላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው” በየቀኑ የዕለት ጥቅሱንና ሐሳቦቹን ለማንበብ ጥቂት ደቂቃዎችን ይወስዳሉ። (ማቴ. 5:3 አዓት ) ብዙዎቹ ጥቅሶች የመንግሥቱን ልዩ ልዩ ገጽታዎች ያብራራሉ። ለምሳሌ ያህል የኅዳር 22, 1994 የዕለት ጥቅስ ማቴዎስ 13:4 ነበር። ለዕለት ጥቅሱ የተሰጠው ሐሳብ የመንግሥቱን ተስፋ ይገልጽና ከዘመዶቻችንና ከጎረቤቶቻችን ጋር ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት መፍጠር ስለሚያስከትለው አደጋ ያሳስበናል። በዓለም ዙሪያ ባሉ የቤቴል ቤቶች በእያንዳንዱ የሥራ ቀን ጠዋት በዕለት ጥቅስ ላይ 15 ደቂቃ የሚፈጅ ውይይት መደረጉ የቀኑን ጥቅስ አንድ ላይ ሆኖ የመመርመርን አስፈላጊነትና አሳሳቢነት ያጎላል። ቤተሰብህ በየቀኑ ተመሳሳይ ምርምር የማድረግ ልማድ አለውን?
4 ለመንግሥቱ ያለን አድናቆት ባደገ መጠን የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ለማካፈል ይበልጥ እንገፋፋለን። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! አእምሯችንን በአዲስና ወቅታዊ በሆነ እውቀት ከሚሞላ የአእምሮ ነዳጅ ጋር ሊመሳሰል የሚችል ነገር ያቀርቡልናል። ይህ ዓለም ምን ያህል የአምላክ መንግሥት እንደሚያስፈልገው በጥልቅ እንድንረዳ ይረዱናል። ‘የክርስቶስ አስተሳሰብ ያለው’ መንፈሳዊ ሰው እንድንሆን ይረዱናል። (1 ቆሮ. 2:15, 16) ይህ ሁሉ ተስፋችንን ሊያጠነክርልንና የመንግሥቱን ተስፋ ለሌሎች ለማካፈል ያለንን ቅንዓት ከፍ ሊያደርግልን ይችላል።— 1 ጴጥ. 3:15
5 በግላችን የመንግሥቱን መልእክት ትርጉም ማስተዋላችን በጣም አስፈላጊ ነው። መንግሥቱ አምላክ ሉዓላዊነቱን ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ ክፋትን ለማስወገድና ገነት የምትሆነውን አዲስ ዓለም ለማምጣት የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው። ኢየሱስ መንግሥቱን በሕይወታችን ውስጥ አንደኛ ቦታ እንድንሰጠው አዞናል። ለዚህ መንግሥት መገዛት የምንፈልግ በግ መሰል ሰዎች መሆን አለብን። (ማቴ. 6:10, 33) ከመንግሥቱ በረከቶች ለመካፈል የሚያስችልህን አጋጣሚ ሁሉ ሙሉ በሙሉ ተጠቀምበት።