የጥያቄ ሣጥን
ሌሎች ለሚሰጡን የትራንስፖርት አገልግሎት የገንዘብ መዋጮ ማድረጉ ተገቢ ነውን?
አንዳንዶቻችን ያለንበት ሁኔታ ዘወትር በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና በመስክ አገልግሎት ለመሳተፍ የሌሎችን እርዳታ የሚጠይቅ ነው። ብዙ ወንድሞችና እህቶች እኛን በትራንስፖርት ለማመላለስ ጊዜያቸውን፣ መኪናቸውንና ሌሎች ጥሪቶቻቸውን በመጠቀም ተጨማሪ ጥረት እንዲያደርጉ የሚገፋፋቸው ፍቅር ነው። ከሌላው ጊዜ ቀደም ብለው ለመነሣትና ዘግይተው ወደ ቤታቸው ለመመለስ የሚያስገድድ ቢሆንም እንኳ በፈቃደኝነት ያመላልሱናል።
እንደ ሌሎቹ ክርስቲያናዊ የአገልግሎታችን ዘርፎች ሁሉ በዚህም ረገድ “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና” የሚለው በገላትያ 6:5 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ይሠራል። በመሆኑም አንድ ሰው አዘውትሮ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠን ከሆነና አቅማችን ከፈቀደልን አድናቆታችንን ማሳየት ያለብን በቃላት ብቻ ሳይሆን የሚያወጣውን ወጪ ለመሸፈን የሚረዳ መጠነኛ መዋጮ በማድረግም ጭምር መሆን ይኖርበታል።— ማቴ. 7:12፤ 1 ቆሮ. 10:24
በመኪናው የሚያጓጉዘን ሰው የገንዘብ እርዳታ ባይጠይቅና እንዲህ ያለው እርዳታ የሚያስፈልገው መስሎ ባይታይም እንኳ በቅን ልቦና መዋጮ ለማድረግ መፈለጋችን ጥሩ ነው። በመኪናው የሚያደርሰን ሰው ምንም ለመቀበል አይፈልግ ይሆናል፤ እርግጥ ይህ ለእርሱ የተተወ ውሳኔ ነው። ይሁን እንጂ እናንተ መዋጮ ለማድረግ መጠየቃችሁ ተገቢ ነው። በዚያን ወቅት ምንም መዋጮ ማድረግ ካልቻላችሁ ይህን በአእምሮአችሁ ይዛችሁ በሚቀጥለው ጊዜ ስትሄዱ ተረፍ አድርጋችሁ ለመስጠት ትችሉ ይሆናል።— ሉቃስ 6:38
መኪና ያላቸው ወንድሞች እነርሱ ባይወስዷቸው ኖሮ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ወይም በመስክ አገልግሎት መካፈል የማይችሉትን በትራንስፖርት ማመላለሳቸው የፍቅር መግለጫ ነው። (ምሳሌ 3:27) በተመሳሳይም እንደዚህ ካለው ደግነት ተጠቃሚ የሆኑት ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውን ያህል መዋጮ በማድረግ አመስጋኝነታቸውን ማሳየታቸው ፍቅራቸውን የሚገልጹበት መንገድ ነው።— ቆላ. 3:15