መንግሥቱን ስበኩ
1 በዕብራውያን 10:23 ላይ ‘የተስፋችንን ምሥክርነት አጥብቀን እንድንይዝ’ ተመክረናል። ተስፋችን ያተኮረው ደግሞ በአምላክ መንግሥት ላይ ነው። ኢየሱስ የመንግሥቱ ምሥራች ለአሕዛብ ሁሉ ሊሰበክ ይገባል ሲል ቀጥተኛ ትእዛዝ ሰጥቷል። (ማር. 13:10) በአገልግሎት በምንሠማራበት ጊዜ ይህንን መዘንጋት የለብንም።
2 ከሰዎች ጋር ስንገናኝ ፍላጎታቸውን የሚቀሰቅስ ወይም አንድ የሚያሳስባቸውን ነገር በመግለጽ ውይይት ለመጀመር እንሞክራለን። ብዙውን ጊዜ የምንጠቅሰው እነርሱም ጭምር የሚያውቋቸውን ነገሮች ሲሆን ከእነዚህም መካከል በአካባቢው የተፈጸመ ወንጀል፣ የወጣቶች ችግር፣ የዕለት ጉርስና ልብስ ለማግኘት ያለው ጭንቀት ወይም በዓለም መድረክ የታየ አንድ ችግርና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ይገኙበታል። የብዙዎቹ ሰዎች ልብ ያተኮረው በእነዚህ ‘የኑሮ ሐሳቦች’ ላይ ስለሆነ ብዙውን ጊዜ ጉዳዩ እንደሚያሳስበን ወይም ችግሩ እንደሚገባን ሆነን ስንቀርብ ብዙውን ጊዜ በልባቸው ያለውን ይነግሩናል። (ሉቃስ 21:34) ይህም ተስፋችንን ለማካፈል በር ሊከፍትልን ይችላል።
3 ይሁን እንጂ ካልተጠነቀቅን ውይይቱ አሉታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ብቻ ያተኮረ ይሆንና ወደ ሰዎቹ የሄድንበትን ስለ መንግሥቱ መልእክት የመናገር ዓላማችንን ሳንፈጽም ልንቀር እንችላለን። ከፍተኛ ችግር ስላስከተሉት መጥፎ ሁኔታዎች ብንጠቅስም እንኳ ግባችን የሰው ልጆችን ችግሮች በሙሉ ጠራርጎ በሚያስወግደው መንግሥት ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ነው። በእርግጥም ሁሉም ሰዎች ሊሰሙት የሚገባ ድንቅ ተስፋ አለን። በመሆኑም በመግቢያችን ላይ ስለ እነዚህ ‘አስጨናቂ ቀናት’ አንዳንድ ገጽታዎች ብንጠቃቅስም ወዲያው በዋናው መልእክታችን ማለትም ‘በዘላለሙ ወንጌል’ ላይ ማተኮር ይኖርብናል። በዚህ መንገድ አገልግሎታችንን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም እንችላለን።— 2 ጢሞ. 3:1፤ 4:5፤ ራእይ 14:6