የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 34 ገጽ 202-ገጽ 205 አን. 4
  • አዎንታዊና የምታበረታታ ሁን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አዎንታዊና የምታበረታታ ሁን
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሚያንጽ ውይይት
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ከሰዎች ጋር የመወያየት ችሎታህን ማሻሻል
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • የምታንጹ ሁኑ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1995
  • አዎንታዊና የሚያበረታታ
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 34 ገጽ 202-ገጽ 205 አን. 4

ጥናት 34

አዎንታዊና የምታበረታታ ሁን

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

አሉታዊ ስለሆኑ ነገሮች ብዙ ከመዘርዘር ይልቅ መፍትሔ የሚሆነውን ነገር ወይም የአድማጮችን ትምክህት የሚገነባ ሐሳብ ተናገር።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ሰዎች ፍቅር የጠፋበት ይህ ዓለም በሚያሳድረው ተጽዕኖ ዝለዋል። ብዙዎች ከባድ ችግሮች አሉባቸው። የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በሚስብ መንገድ በማቅረብ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ብሩህ አመለካከት እንዲኖራቸው መርዳት እንችላለን።

የምንሰብከው መልእክት ምሥራች ነው። ኢየሱስ “የምሥራቹ ቃል ለዓለም ሕዝብ ሁሉ መዳረስ ይገባዋል” ብሏል። (ማር. 13:​10 የ1980 ትርጉም ) እርሱ ራሱ ‘የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥራች’ በማብሰሩ ሥራ ግንባር ቀደም ነበር። (ሉቃስ 4:​43) ሐዋርያት ይሰብኩት የነበረውም መልእክት ‘የእግዚአብሔር ምሥራች’ እና ‘ስለ ክርስቶስ የሚናገር ምሥራች’ ተብሎ ተጠርቷል። (1 ተሰ. 2:​2፤ 2 ቆሮ. 2:​12) እንዲህ ያለው መልእክት አዎንታዊና የሚያበረታታ ነው።

‘በሰማይ መካከል የሚበርረው መልአክ’ በሚያውጀው ‘የዘላለም ምሥራች’ መሠረት “እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት” እያልን ሰዎችን እናሳስባለን። (ራእይ 14:​6, 7) በየትኛውም የምድር ክፍል ለሚገኙ ሰዎች ስለ እውነተኛው አምላክ፣ ስለ ስሙ፣ ድንቅ ስለሆኑት ባሕርያቱ፣ አስገራሚ ስለሆኑት የእጁ ሥራዎች፣ በፊቱ ስላለን ተጠያቂነት እንዲሁም ከእኛ ስለሚፈልገው ነገር እንናገራለን። የምንናገረው ምሥራች ይሖዋ አምላክ ለእርሱ አክብሮት የሌላቸውንና የሌሎችን ሰዎች ሕይወት የሚያመሰቃቅሉትን ክፉዎች እንደሚያጠፋም ይገልጻል። ሆኖም በምንሰብክላቸው ሰዎች ላይ የመፍረድ ሥልጣን የለንም። እንዲያውም ብዙ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በጎ ምላሽ ሰጥተው ከምሥራቹ ቢጠቀሙ ደስ ይለናል።​—⁠ምሳሌ 2:​20-22፤ ዮሐ. 5:​22

ስለ ችግር ብዙ አትዘርዝር። እርግጥ የሰው ልጅ ሕይወት ከችግር ነፃ እንዳልሆነ አይካድም። በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ያሉትን ሰዎች የሚያሳስባቸውን አንድ ችግር በአጭሩ በመጥቀስ ውይይት መጀመር ትችላለህ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ስለ ችግሩ ብቻ መዘርዘር ይህን ያህል ጥቅም የለውም። ሰዎች በየጊዜው መጥፎ ዜና ስለሚሰሙ ስለ ችግር ብናወራላቸው ላያዳምጡን ይችላሉ። ውይይታችሁን እንደጀመራችሁ ወዲያውኑ በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው የሚያጽናና እውነት ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ ጣር። (ራእይ 22:​17) ሰውዬው በውይይቱ መቀጠል ባይፈልግ እንኳ ሊያስብበት የሚችል አንድ ጥሩ ነጥብ ነግረኸዋል ማለት ነው። ይህም በሌላ ጊዜ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያዳምጥ ሊያነሳሳው ይችላል።

በተመሳሳይም ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ ዛሬ ስላሉት ችግሮች የሚገልጽ መረጃ እንደ ልብ ማግኘት ስለቻልክ ብቻ ብዙ መዘርዘር አለብህ ማለት አይደለም። አንድ ተናጋሪ ስለ ሰብዓዊ መሪዎች ድክመት፣ ስለ ዓመፅና ወንጀል ሪፖርቶች እንዲሁም ብልግና በጣም ስለ መስፋፋቱ ብዙ የሚያትት ከሆነ አድማጮችን ተስፋ ሊያስቆርጣቸው ይችላል። አንድን ችግር ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር አያይዘህ የምትጠቅሰው ለንግግርህ በጣም ጠቃሚ ሆኖ ካገኘኸው ብቻ ሊሆን ይገባል። ሳይበዛ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ መጥቀስ አድማጮችህ የንግግሩን ወቅታዊነት እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል። ለችግሩ ዋነኛ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ለይቶ ለማስተዋልና መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርበው የመፍትሔ ሐሳብ ጠቃሚ የሆነው ለምን እንደሆነ ለማስገንዘብም ሊረዳ ይችላል። ስለ ችግሩ አንድ በአንድ ከመተንተን ይልቅ በተቻለ መጠን በአጭሩ ብቻ ጠቅሰህ እለፍ።

ብዙውን ጊዜ ስለ ችግር የሚጠቅሱ ሐሳቦችን ከአንድ ንግግር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ማውጣት አይቻልም ደግሞም አያስፈልግም። አንድ ተናጋሪ በንግግሩ ውስጥ አዎንታዊም አሉታዊም ነገሮችን ሊጠቅስ ይችላል። ዋናው ቁም ነገር ግን የንግግሩ አጠቃላይ መንፈስ የሚያበረታታ መሆኑ ነው። የንግግሩ አጠቃላይ መንፈስ የሚያበረታታ እንዲሆን ምን እንደምትጨምር፣ ምን እንደምትቀንስ እንዲሁም የትኛውን ነጥብ እንደምታጎላ መወሰን ይኖርብሃል። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ አድማጮቹ ራሳቸውን ያመጻድቁ የነበሩትን ጻፎችና ፈሪሳውያን አርዓያ እንዳይከተሉ ካሳሰበ በኋላ ነጥቡን ይበልጥ ግልጽ የሚያደርጉ ጥቂት ምሳሌዎችን ጠቅሷል። (ማቴ. 6:​1, 2, 5, 16) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በእነዚያ ሃይማኖታዊ መሪዎች መጥፎ ምሳሌነት ላይ ብቻ አላተኮረም። ከዚህ ይልቅ በሰፊው ያብራራው እውነተኛውን የአምላክ መንገድ ስለ ማወቅና በዚያ ስለ መመላለስ ነው። (ማቴ. 6:​3, 4, 6-15, 17-34) ከዚህ የተነሣ ንግግሩ በጣም አበረታች ነበር።

አዎንታዊ አቀራረብ ይኑርህ። ክርስቲያኖች ሊያከናውኑት ስለሚገባ አንድ ሥራ ለጉባኤህ ንግግር እንድታቀርብ ከተመደብህ አድማጮችህን በሚነቅፍ ሳይሆን በሚያበረታታ መንገድ ለማቅረብ ጥረት አድርግ። ሌሎችን ለሥራ ለማበረታታት መጀመሪያ አንተ ራስህ በዚያ ረገድ ምሳሌ ሆነህ መገኘት ይኖርብሃል። (ሮሜ 2:​21, 22፤ ዕብ. 13:​7) የምትናገረው በፍቅር ተነሳስተህ እንጂ በቁጣ ስሜት መሆን የለበትም። (2 ቆሮ. 2:​4) ክርስቲያን ወንድሞችህ ይሖዋን የማስደሰት ፍላጎት እንዳላቸው የምትተማመን ከሆነ በእነርሱ ላይ ያለህ እምነት በአነጋገርህ መንጸባረቁ አይቀርም። ይህ ደግሞ በጎ ውጤት ይኖረዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ወንድሞቹ ያለውን ተመሳሳይ ትምክህት እንዴት እንደገለጸ 1 ተሰሎንቄ 4:​1-12፤ 2 ተሰሎንቄ 3:​4, 5 እንዲሁም ፊልሞና 4, 8-14, 21 ላይ ተመልከት።

አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች አንድ ሰው ጥበብ የጎደለው አካሄድ እንደጀመረ ሲያስተውሉ ማስጠንቀቂያ መስጠት ይኖርባቸዋል። ሆኖም ትሕትና ወንድሞቻቸውን በየዋህነት እንዲረዱ ያስችላቸዋል። (ገላ. 6:​1) የሚናገሩበት መንገድ በጉባኤ ውስጥ ላሉ ወንድሞች አክብሮት እንዳላቸው የሚያሳይ መሆን ይኖርበታል። (1 ጴጥ. 5:​2, 3) መጽሐፍ ቅዱስ በተለይ በኃላፊነት ላይ ያሉ ወጣት ወንድሞች ለዚህ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡት ያሳስባል። (1 ጢሞ. 4:​12፤ 5:​1, 2፤ 1 ጴጥ. 5:​5) ሌሎችን መገሰጽ፣ መምከርና ማቅናት አስፈላጊ በሚሆንበትም ጊዜ የሚሰጡት ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። (2 ጢሞ. 3:​16) አንድ ተናጋሪ እርሱ ያመነበትን ሐሳብ እንዲደግፍለት ለማድረግ ሲል ጥቅሱን እንደምንም ብሎ ከሐሳቡ ጋር ለማገናኘት መሞከር ወይም አጣምሞ ማቅረብ አይገባውም። ከኃጢአት መራቅ፣ ችግሮችን መወጣትና ከተሳሳተ ጎዳና መመለስ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም የይሖዋን ትእዛዛት መጠበቅ ምን ጥቅም እንዳለው አበክረህ የምትገልጽ ከሆነ ለማረም ብለህ ምክር በምትሰጥበት ጊዜም እንኳ ቢሆን አቀራረብህ አዎንታዊ ሊሆን ይችላል።​—⁠መዝ. 119:​1, 9-16

ንግግርህን ስትዘጋጅ እያንዳንዱን ዋና ነጥብና ጠቅላላውን ንግግር እንዴት እንደምትቋጭ በቁም ነገር ልታስብበት ይገባል። ብዙውን ጊዜ ቶሎ የማይረሳው መጨረሻ የተናገርኸው ነው። ታዲያ መደምደሚያህ ላይ የምትናገረው ሐሳብ አዎንታዊ ይሆን?

ከክርስቲያን ወንድሞችህ ጋር ስትጨዋወት። የይሖዋ አገልጋዮች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እርስ በርስ መጨዋወት የሚችሉበት አጋጣሚ በማግኘታቸው ደስ ይላቸዋል። እነዚህ አጋጣሚዎች በመንፈሳዊ እንድንታደስ ይረዱናል። መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስንገናኝ ‘እርስ በርስ መበረታታት እንዳለብን’ ያሳስበናል። (ዕብ. 10:​25) እርስ በርስ የምንበረታታው በስብሰባ ላይ በሚቀርቡት ክፍሎችና በሚሰጡት መልሶች ብቻ ሳይሆን ከስብሰባ በፊትና በኋላ በምናደርጋቸው ጭውውቶች ጭምር ነው።

ጭውውታችን አብዛኛውን ጊዜ በዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ቢሆንም ይበልጥ እርስ በርስ የምንበረታታው ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ስንወያይ ነው። እንዲህ ያለው ውይይት በአገልግሎት ያገኘናቸውን ተሞክሮዎች መለዋወጥን ይጨምራል። አንዳችን ለሌላው አሳቢነት ማሳየታችንም የሚያበረታታ ነው።

ዓለም ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩ ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፣ . . . እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ” ብሏል። (ኤፌ. 4:​25) ውሸትን አስወግዶ እውነት መነጋገር ዓለም እንደ ጣዖት የሚያያቸውን ሰዎችና ሌሎች ነገሮች ከማወደስ መራቅን ይጨምራል። ኢየሱስም በተመሳሳይ ‘ባለጠግነት የማታለል ኃይል’ እንዳለው አስጠንቅቋል። (ማቴ. 13:​22) ስለሆነም እርስ በርስ በምናደርገው ጭውውት ቁሳዊ ነገሮችን አጓጊ አድርገን በማውራት ሌሎች ለባለጠግነት መታለል እንዲሸነፉ ምክንያት እንዳንሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል።​—⁠1 ጢሞ. 6:​9, 10

ሐዋርያው ጳውሎስ ሌሎችን የምናበረታታ እንድንሆን ምክር ሲሰጥ አንድ ወንድም ‘እምነቱ ባለመጠንከሩ’ ወይም በሌላ አባባል ስለ ክርስቲያናዊ ነፃነት ያለው ግንዛቤ ውስን በመሆኑ ከአንዳንድ ነገሮች ቢቆጠብ በእርሱ ላይ ከመፍረድ ወይም እርሱን ከማንኳሰስ እንድንርቅ አሳስቦናል። ጭውውታችን የሚያበረታታ እንዲሆን ከፈለግን የሰዎቹን አስተዳደግና መንፈሳዊ እድገታቸውን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። ‘ለአንድ ወንድም [ወይም ለአንዲት እህት] እንቅፋት ወይም ማሰናከያ ብናኖር’ ምንኛ የሚያሳዝን ይሆናል!​—⁠ሮሜ 14:​1-4, 13, 19

ሥር የሰደደ ሕመምን የመሰለ ከባድ የግል ችግር ያለባቸውን ሰዎች የሚያበረታታ ነገር አንስተን ብናጫውታቸው ደስ ይላቸዋል። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በጉባኤ ስብሰባ ላይ መገኘት ብዙ ትግል ይጠይቅባቸው ይሆናል። ችግሩን የሚያውቁ ሰዎች “እንዴት ነህ?” ብለው ይጠይቁት ይሆናል። አሳቢነት በማሳየታቸው እንደሚደሰት የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ይበልጥ የሚያበረታታው ስለ በሽታው ማውራታቸው ላይሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ የሚያደርገውን ጥረት አንስተው ቢያደንቁትና ቢያመሰግኑት የበለጠ ደስ ይለው ይሆናል። ለይሖዋ ያለው ፍቅር ሳይጠፋ ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ተቋቁሞ እንደጸና የሚጠቁም ምን ያስተዋልከው ነገር አለ? መልስ ሲሰጥ ስትሰማ ትበረታታለህ? ስለ ችግሩ አንስቶ ከማጫወት ይልቅ ጠንካራ ጎኑን ወይም ለጉባኤው የሚያበረክተውን ድርሻ መጥቀሱ ይበልጥ የሚያበረታታው ይሆን?​—⁠1 ተሰ. 5:​11

ጭውውታችን የሚያበረታታ እንዲሆን ከሁሉ በላይ ስለምንወያይበት ጉዳይ ይሖዋ ያለውን አመለካከት ግምት ውስጥ ማስገባት በጣም አስፈላጊ ነው። ጥንት በእስራኤል ዘመን አምላክ የሾማቸውን ወንዶች የተቃወሙና ከሰማይ የወረደውን መና በተመለከተ ያጉረመረሙ ሰዎች የይሖዋ ቁጣ ወርዶባቸዋል። (ዘኍ. 12:​1-16፤ 21:​5, 6) ሽማግሌዎችን ማክበራችን እንዲሁም በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ ማድነቃችን ከእነዚህ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች ትምህርት እንዳገኘን ያሳያል።​—⁠1 ጢሞ. 5:​17

ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ስንሆን የምንጫወተው የሚያበረታታ ነገር አናጣም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ሌሎችን የሚነቅፍና የሚተች ከሆነ ርዕሱን በማስቀየር ጭውውቱ ገንቢ እንዲሆን የበኩልህን ጥረት አድርግ።

ለሌሎች ስንመሰክር፣ ንግግር ስንሰጥ እንዲሁም ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ስንጨዋወት ከልባችን የምናፈልቀው ሐሳብና ንግግራችን ‘ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም’ እንዲሆን ማስተዋል ሊኖረን ይገባል።​—⁠ኤፌ. 4:​29

ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

  • ተልእኳችን ምሥራቹን መስበክ እንደሆነ አትዘንጋ።

  • የምታበረታታ እንጂ የምትነቅፍ አትሁን።

  • ስለ አድማጮችህ አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ።

  • በምትጨዋወትበት ጊዜ የምትናገረው ነገር ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አስብ።

መልመጃ፦ የአካል ጉዳተኛ የሆነ ወይም በሕመም ምክንያት ከቤቱ የማይወጣ ሰው ሄደህ ጠይቅ። የሚያበረታታ ነገር አጫውተው። ልታዝንለት የሚገባ ቢሆንም የምትሰጠው አስተያየት ገንቢ መሆን አለበት። ይህን ዓላማህን ማሳካት እንድትችል አስቀድመህ ተዘጋጅ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ