“አስፈላጊ በሆነ ወቅት የተገኘ እርዳታ”
1 አስፈላጊ በሆነ ወቅት ላይ እርዳታ ማግኘት ምንኛ መንፈስን ያነቃቃል! (ዕብ. 4:16) “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ እርዳታዎች ልክ አስፈላጊ በሆነ ወቅት ላይ በማግኘታችን በደስታ ተፍለቅልቀን ነበር።
2 ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለው መጽሐፍ ብዙ ችግሮች ፊታቸው ላይ ለተጋረጡባቸው በመስክ ለምናገኛቸው ወጣቶች ወደር የማይገኝለት እርዳታ ያበረክታል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያለው አምላካዊ ጥበብ ወጣቶች ሥቃይ የሚያስከትል ስህተት ከመፈጸም እንዲርቁ መርዳት ብቻ ሳይሆን አዋቂ የሆኑ ሰዎችም ለልጆቻቸውና ለወጣት ዘመዶቻቸው ጠቃሚ መመሪያዎችን እንዲሰጡ ያስችላቸዋል። ስለዚህም ሁሉም መጽሐፉን እንዲያነቡ፣ እንዲያውም እንዲያሰምሩበት በመስክ ለሚያገኟቸውም ሰዎችና ለዘመዶቻቸው እንዲያበረክቱ እናበረታታለን። በተመሳሳይም ለየት ያለ ይዘት በመያዙ ምክንያት አሁንም ጠቃሚነቱ ያልቀነሰውና በአነስተኛ ዋጋ የሚበረከተው ወጣትነትህ የተባለውንም መጽሐፍ ማበርከታችንን እንቀጥል።
3 ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተሰኘውን መጽሐፍ በማንበብና ውስጡ ባሉት ሥዕላዊ ማብራሪያዎች ላይ በማሰላሰል ደስታ ማግኘት ይችላሉ። በጣም ከሚወዷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መካከል አጠቃላይ ሐሳቦችን በቃላቸው መውጣት የሚችሉ እድሜአቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት እንዳሉ እናውቃለን! ልጆቻችንን ከጨቅላነታቸው ጀምሮ ለማሠልጠን የሚያስችለን እንዴት ያለ ግሩም መሣሪያ አግኝተናል! (2 ጢሞ. 3:15) ዋጋው አነስተኛ መሆኑ መጽሐፉን ለብዙ ሰዎች እንድታበረክቱ ያስችላችኋል። እነርሱም እንዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ብቻ ሳይሆን በጊዜያችንና ወደፊት ስለሚፈጸሙ ትንቢቶች አጠቃላይ ሐሳቦችን እንዲያውቁ ያስችላቸዋል!
4 አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተሰኘው አዲስ ብሮሹር ደቀ መዝሙር የማድረግ ሥራችንን የሚያፋጥን አስፈላጊ በሆነ ወቅት ላይ ያገኘነው እርዳታ ነው። ብሮሹሩ የተዘጋጀው በተለይ የማንበብ ችሎታቸው ውስን የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ታስቦ ቢሆንም መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ቀለል ባለ መንገድ የሚያብራራ ስለሆነ የተማሩ አዋቂ ሰዎችም ሆኑ ወጣቶች ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ከዚህም በላይ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ጥናት ለማስጀመር የመሸጋገሪያ ድልድይ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ይህ ዝግጅት ብዙ ተጨማሪ ሰዎች አምላክ የሚፈልግባቸውን ነገሮች በማድረግ እንዴት የተትረፈረፉ በረከቶችን ሊያገኙ እንደሚችሉ እንዲገነዘቡ እንደሚረዳ የተረጋገጠ ነው።
5 ዳዊት ‘ምንም እንዳላጣ፣ ነፍሱ እንደረካና ጽዋው እንደሞላ’ ሲናገር የእኛንም ስሜት በትክክል ገልጿል። (መዝ. 23:1, 3, 5) እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ለማወቅና ለማገልገል በቅን ልቦና ለተነሳሱ ሁሉ ይህን ግሩም የሆነ መንፈሳዊ መርጃ ለማስተላለፍ የምንችልበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን።