1 በካሊፎርኒያ የሚኖር አንድ የ11 ዓመት ልጅ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? ለተባለው መጽሐፍ ያለውን አድናቆት ገልጿል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “መጽሐፉ በመዘጋጀቱ በጣም አመስጋኝ ነኝ፤ በጣም ምርጥ መጽሐፍ ስለሆነም ሌሎች ቤተሰቦች እንዲያነቡት አበረታታቸዋለሁ። . . . መጽሐፉ ቤታችን ውስጥ ሰላምና ደስታ እንዲሰፍን ለማድረግ ጠቅሞናል።” የዚህ ልጅ ተሞክሮ የቤተሰብ ደስታ መጽሐፍን በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች እንድናበረክት ሊያበረታታን ይገባል። በየካቲት ወር አገልግሎት ላይ ልትጠቀሙባቸው የምትችሉ ጥቂት ሐሳቦች ቀጥሎ ቀርበዋል።
2 አንድ ወጣት ስታገኝ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “ባንተ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ብዙዎች ስለ ትዳር ያስባሉ። ይሁን እንጂ ይህን ጉዳይ በሚመለከት አስተማማኝ የሆነ መረጃ ከየት ማግኘት ትችላለህ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች ትዳር ለመመሥረት ዝግጁ ስለመሆናቸው እርግጠኛ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። ይህ መጽሐፍ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረውን ባካፍልህ ደስ ይለኛል።” የቤተሰብ ደስታ መጽሐፍ ገጽ 14ን ገልጠህ አንቀጽ 3ን አንብብ። ከዚያም በምዕራፉ ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ንዑስ ርዕስ ጥቀስ። መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘውና ተመልሰህ የምትመጣበትን ቀጠሮ ያዝ።
3 ከወላጅ ጋር ስትነጋገር እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “ልጆችን በማሳደግ ረገድ ውጤታማ የሆኑ አንዳንድ ተግባራዊ መመሪያዎችን ለወላጆች እያካፈልን ነው። እነዚህ መመሪያዎች ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? በተባለው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቀርበዋል።” ገጽ 55ን ግለጥ። አንቀጽ 10ን፣ ቀጥሎም አንቀጽ 11 ላይ የሚገኘውን ዘዳግም 6:6, 7ን አንብብ። ከዚያም ከአንቀጽ 12 እስከ 16 ላይ የሚገኙትን በሰያፍ የተጻፉትን ዓረፍተ ነገሮች ጥቀስ። በመቀጠልም “ይህ መጽሐፍ የወላጅነት ኃላፊነታቸውን በመወጣት ረገድ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆኑ ብዙዎችን ረድቷል” ካልክ በኋላ መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘው።
4 በዕድሜ ከገፋ ሰው ጋር ስትነጋገር እንዲህ ለማለት ትችል ይሆናል:-
◼ “አንድ አጭር ሐሳብ ላንብለዎትና ምን ሐሳብ እንዳለዎት እስቲ ይንገሩኝ።” የቤተሰብ ደስታ መጽሐፍን ገጽ 169 ላይ ገልጠህ የ17ኛውን አንቀጽ የመጀመሪያ ሁለት ዓረፍተ ነገሮች አንብብ። ከዚያም ምን እንደሚሰማው ጠይቀው። መጽሐፉን እንዲወስድ ከመጋበዝህ በፊት በሰጠው ምላሽ ላይ ተመርኩዘህ ተጨማሪ ሐሳቦችን ከመጽሐፉ ማንበብ ትችል ይሆናል።
5 የቤተሰብ ደስታ መጽሐፍ ላበረከትክላቸው ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር ግብ ይኑርህ። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር ላይ ያለው ትምህርት 8 ወይም የእውቀት መጽሐፍ 15ኛ ምዕራፍ ጥናት ለመጀመር ተስማሚ ሊሆን ይችላል። እንዲህ በማድረግ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ደስተኛ ክርስቲያናዊ የቤተሰብ ሕይወት እንዲመሠርቱ ለመርዳት ጥረት እናድርግ።