በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመዝገብ
1 በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች የተዋጣላቸው የምሥራቹ አገልጋዮች እንዲሆኑ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በዚህ ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ክፍል ስናቀርብ ምን ያህል ፈርተንና ብቃት እንደሌለን ተሰምቶን እንደነበር ብዙዎቻችን አናስታውሳለን። አሁንም ቢሆን የአምላክን ቃል በመናገርና በማስተማር በኩል መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ትምህርት ቤቱ ያበረከተልንን አስተዋጽኦ የምንዘነጋው አይደለም። (ከሥራ 4:13 ጋር አወዳድር።) በዚህ አስደናቂ ትምህርት ቤት ክፍል ለማቅረብ ተመዝግበሃል?
2 በትምህርት ቤቱ ክፍል ለማቅረብ እነማን ሊመዘገቡ ይችላሉ? አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት የተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 73 ላይ እንዲህ የሚል መልስ ይሰጠናል:- “ከጉባኤው ጋር በትጋት የሚተባበሩ ሁሉ በትምህርት ቤቱ ሊመዘገቡ ይችላሉ። በስብሰባ መገኘት የጀመሩ አዲሶችም ከክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚጋጭ መንገድ የሚኖሩ ካልሆነ በስተቀር በትምህርት ቤቱ ሊመዘገቡ ይችላሉ።” ብቃት ያላቸው ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች የትምህርት ቤቱን የበላይ ተመልካች ቀርበው በማነጋገር እንዲመዘገቡ እንጋብዛቸዋለን።
3 የ1997 የትምህርት ቤት ፕሮግራም፦ የ1997 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በስፋት ይሸፍናል። የመናገርና የማስተማር ችሎታችንን ከማሻሻላቸውም በተጨማሪ በየሳምንቱ ከሚቀርበው ሥርዓተ ትምህርት ብዙ መንፈሳዊ እንቁዎችን እናገኛለን። (ምሳሌ 9:9) ሳምንታዊውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጨምሮ ለትምህርት ቤቱ የምንዘጋጅና አዘውትረንም በስብሰባው ላይ የምንገኝ ከሆነ ከፕሮግራሙ ከፍተኛ የሆኑ መንፈሳዊ ጥቅሞችን ማግኘት እንችላለን።
4 በ1997 ፕሮግራም ክፍል ቁጥር 2 ላይ ያሉት አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች ባለፉት ዓመታት ከነበሩት አጠር ያሉ ናቸው። ይህን ክፍል እንዲያቀርብ የተመደበው ተማሪ ንባቡ ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ በጥንቃቄ ካረጋገጠ በኋላ ከተሰጠው አምስት ደቂቃ ውስጥ ደግሞ ለመግቢያና ለመደምደሚያ ምን ያህሉን እንደሚጠቀም አስቀድሞ መወሰን ይኖርበታል። ይህም የተፈቀደለትን ሰዓት ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀምበትና የንባቡንና በራስ አገላለጽ ንግግር የማቅረብ ችሎታውን እንዲያዳብር ይረዳዋል።— 1 ጢሞ. 4:13
5 እውቀት በተባለው መጽሐፍ ላይ የተመሠረተው ክፍል ቁጥር 3 በሚቀርብበት ጊዜ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ሲሰጥ የሚያሳይ መቼት እንደ አማራጭ ሆኖ መጠቀም ይቻላል። በመሆኑም ክፍሉን የምታቀርበው እህት ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ ወይም መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ስትሰጥ የሚያሳይ መቼት ልታዘጋጅ ትችላለች። እርግጥ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት ያለበት በውጤታማ የማስተማር ዘዴው ላይ እንጂ በመቼቱ ላይ አይደለም።
6 የማስተማሪያ ንግግር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጎላ ያሉ ነጥቦች ወይም የተማሪ ንግግር እንድታቀርብ መብት ከተሰጠህ ጥሩ አድርገህ በመዘጋጀትና አስቀድመህ በመለማመድ፣ በጽኑ እምነትና ሞቅ ባለ መንፈስ በማቅረብ፣ የተሰጠህን የጊዜ ገደብ ባለማለፍ፣ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች የሚሰጠውን ምክር በማዳመጥና ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም የተሰጠህን ክፍል በቁም ነገር በመመልከት ለቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት አድናቆት እንዳለህ ልታሳይ ትችላለህ። በዚህም ምክንያት በትምህርት ቤቱ ተመዝግበህ ክፍል ማቅረብህ ለአንተም ሆነ ለሁሉም አዳማጮች በረከት የሚያመጣ ይሆናል።