ዘንድሮም ጥሪውን ትቀበላላችሁን?—ለረዳት አቅኚነት በድጋሚ የቀረበ ጥሪ
1 ምን እንድናደርግ ነው ጥሪ የቀረበልን? በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ረዳት አቅኚ ለመሆን አስባችኋልን? የየካቲት 1997 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ “1,000 ረዳት አቅኚዎች ይፈለጋሉ” የሚል ትኩረት የሚስብ በጉልህ የተጻፈ ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። ጥሪውን በቁም ነገር እንደምትመለከቱት እርግጠኞች ነበርን። የመጋቢት 1997 የአገልግሎት ሪፖርት ሲጠናቀር 1,104 ወንድሞችና እህቶች ረዳት አቅኚ እንደነበሩ ስናውቅ በጣም ተደስተን ነበር! በዚህ ቁጥር ላይ በዚያው ወር ሪፖርት ያደረጉ 420 የዘወትር አቅኚዎችንና 144 ልዩ አቅኚዎችን ስንደምር በአጠቃላይ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት አስፋፊዎች በአቅኚነት ተካፍለው ነበር። በዚህኛው የመታሰቢያው በዓል ሰሞንስ ተመሳሳይ መንፈስ ታሳዩ ይሆን?
2 ባለፈው ዓመት የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ከፍ ለማድረግ ልዩ ጥረት ያደረጉትን ሁሉ ከልብ ልናመሰግናቸው እንወዳለን። ለይሖዋ አምላክና ለሰዎች ያላችሁ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ይህን ለማድረግ እንዳንቀሳቀሳችሁ ግልጽ ነው። (ሉቃስ 10:27፤ 2 ጴጥ. 1:5-8) በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ያሉ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ በመሆን አገልግለዋል። በአንድ ጉባኤ ውስጥ 51 አስፋፊዎች በተመሳሳይ ወር ረዳት አቅኚ ሆነዋል። ከእነዚህም ውስጥ ከጉባኤው ሽማግሌዎች አብዛኞቹ፣ የአንድ ዓመት ከሦስት ወር ልጅ ያለቻት አንዲት እናት፣ የሙሉ ቀን ሥራዋን ትታ አቅኚ ለመሆን የሚያስችላትን የግማሽ ቀን ሥራ የጀመረች አንዲት እህት እንዲሁም ከዚህ በፊት አቅኚነትን ሞክረው የማያውቁ አንዲት በዕድሜ የገፉ እህት ይገኙበታል። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በስብከቱ ሥራ ረገድ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። . . . የዚህ ጥረት ውጤት የተንጸባረቀው በአገልግሎት ክልሎች ላይ ብቻ ሳይሆን ጉባኤዎችም ቅንዓታቸው እንዲጨምር አድርጓል። ወንድሞች የበለጠ እርስ በእርሳቸው በመተዋወቃቸው እንዲሁም በአገልግሎቱ ጥሩ ውጤት በማየታቸው ተደስተዋል።”
3 ባለፈው ዓመት ትንንሽ ልጆች እንኳ ሳይቀሩ በዚህ ሥራ ተካፍለዋል። አንዲት የ13 ዓመት ያልተጠመቀች አስፋፊ ራሷን ለይሖዋ መወሰኗን በጥምቀት የምታሳይበትን ቀን በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ነበረች። በየካቲት ወር ከተጠመቀች በኋላ በመጋቢት ረዳት አቅኚ ለመሆን ያላትን ፍላጎት እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “አሁን ረዳት አቅኚ እንዳልሆን ምንም የሚከለክለኝ ነገር ስለሌለ ወዲያው ማመልከቻዬን ሞልቼ እሰጣለሁ። . . . አቅኚ እንድንሆን ያቀረባችሁትን ፍቅራዊ ግብዣ ባንቀበል ኖሮ የምንሰማቸው አስደሳች ተሞክሮዎች ሊገኙ አይችሉም ነበር። ይሖዋ ለጥሪው አዎንታዊ ምላሽ ከሰጡት መሃል እንድቆጠር ስላደረገኝ በጣም አመሰግነዋለሁ።” ይህቺ የ13 ዓመት ልጅ ረዳት አቅኚ ለመሆን በድጋሚ ግብ አውጥታለች።
4 በመጋቢት ወር ከነበሩት 1,104 ወይም በሚያዝያ ወር ከነበሩት 609 ወይም በግንቦት ወር ከነበሩት 399 ረዳት አቅኚዎች መሃል አንዱ ልትሆን ትችላለህ። በዚህ ዓመት በድጋሚ ረዳት አቅኚ ትሆናለህን? ባለፈው ዓመት ረዳት አቅኚ መሆን ያልቻልክ ከሆነ በዚህ ዓመት መሆን ትችላለህን? ባለፈው ዓመት ያሳየነውን መልካም ጥረት ዘንድሮም ልንደግመው እንችላለንን?
5 በሚያዝያና በግንቦት ወር ላይ ትኩረት አድርጉ፦ በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል የሚውለው ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 11 ነው። ይህም የሚያዝያን ወር የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ለማስፋት በጣም ጥሩ አጋጣሚ ይሆንልናል። (2 ቆሮ. 5:14, 15) በዚህ ወር የመጀመሪያዎቹ 11 ቀናት ውስጥ ፍላጎት ያላቸውን ብዙ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ የተቻለንን ጥረት እናድርግ። ረዳት አቅኚ የመሆን ግብ ካለህ እባክህን ለመጀመር ካሰብክበት ቀን በጣም ቀደም ብለህ ማመልከቻውን አስገባ።—1 ቆሮ. 14:40
6 በግንቦት ወር አምስት ቅዳሜና እሁዶች ስላሉ ተማሪዎች ወይም ሙሉ ቀን የሚሠሩ አስፋፊዎች በዚህ ወር አቅኚ ለመሆን ቀላል ይሆንላቸዋል። በእያንዳንዱ ሳምንት ቅዳሜና እሁድ አሥር ሰዓት ለማገልገል ግብ ብታወጣ የሚጠበቅብህን 60 ሰዓት ለማምጣት ፕሮግራም ማውጣት የሚያስፈልግህ የሚቀርህን አሥር ሰዓት ለማገልገል ብቻ ይሆናል።
7 በሚያዝያና በግንቦት ወራት የምናበረክተው የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ነጠላ ቅጂዎችን ይሆናል። እንዲያውም ይህ አብዛኞቻችን አቅኚ ለመሆን እንድንጣጣር ሊያበረታታን ይገባል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? መጽሔቶች በቀላሉ ስለሚበረከቱ በአገልግሎት መሳተፍ አስደሳች ይሆናል። መጽሔቶች በሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች ለመካፈል አመቺ ናቸው። ከቤት ወደ ቤትና ከሱቅ ወደ ሱቅ እንዲሁም በመንገድ ላይ፣ በገበያ ቦታ፣ በመናፈሻ እና በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰዎችን ስናገኝ ልናበረክትላቸው እንችላለን። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች አስፈላጊ የሆነውን የመንግሥቱን እውነት ይዘዋል። እነዚህ መጽሔቶች የአምላክ መንግሥት በመግዛት ላይ መሆኑን የሚያሳየው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ መሆኑን ይገልጹልናል። የሰው ልጆች በእርግጥ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በግልጽ ስለሚያስቀምጡ በቀላሉ የአንባቢዎችን ሕይወት ይነካሉ። የእኛ ሕይወት በእነዚህ ውድ መጽሔቶች ምን ያህል እንደተነካ ካሰብን በሚያዝያና በግንቦት ወር በተቻለን መጠን ብዙ ለማሰራጨት እንነሳሳለን።
8 ለዚህ የተጠናከረ መጽሔት የማበርከት እንቅስቃሴ የሚከተሉትን ጽሑፎች መለስ ብሎ መከለሱ ይጠቅማል:- “መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ለእውነት የቆሙ ወቅታዊ መጽሔቶች” (ጥር 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ)፣ “መጽሔቶቻችንን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙባቸው” (መስከረም 1995 የመንግሥት አገልግሎታችን) እና “መጽሔት ለማበርከት የሚያስችልህን የራስህን አቀራረብ አዘጋጅ” (ጥቅምት 1996 የመንግሥት አገልግሎታችን)።
9 ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም ሁኑ፦ ባለፈው ዓመት አቅኚ የሆኑትን ብዙ አስፋፊዎች ለመርዳት በአንድ ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች በወሩ ውስጥ አንዱን ቅዳሜ ልዩ የአገልግሎት ቀን እንዲሆን አድርገዋል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ አስፋፊዎች ሁሉ በተለያዩ የስብከት ዘርፎች እንዲካፈሉ ለማድረግ በቀኑ ውስጥ በተለያየ ሰዓት ለመገናኘት ዝግጅት ተደርጎ ነበር። ይህም በንግድ ቦታዎች፣ በመንገድ ላይ፣ ከቤት ወደ ቤት፣ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ፣ በደብዳቤ እና በስልክ ምስክርነት መስጠት ያጠቃልላል። በዚህ ልዩ የአገልግሎት ቀን 117 አስፋፊዎች በመስክ አገልግሎት በመካፈል አስደናቂ ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህ የአገልግሎት ቀን በድምሩ 521 ሰዓት ሲያገለግሉ 617 መጽሔቶች፣ ብሮሹሮችና መጽሐፎች አበርክተዋል! ቅዳሜ ዕለት የነበረው ልዩ የአገልግሎት ስሜት እሁድ በሕዝባዊ ስብሰባና በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር እንዲኖር አስችሏል።
10 በሚያዝያና በግንቦት ወር በሚደረገው በእያንዳንዱ የአገልግሎት ስብሰባ በተለይም ልዩ የአገልግሎት ስምሪት ዝግጅት ከተደረገ በሚቀጥለው ሳምንት የስምሪት ስብሰባ መቼ እና የት እንደሚካሄድ ጉባኤው ማስታወቅ አለበት። የዘወትር አቅኚዎችና ረዳት አቅኚ ያልሆኑ አስፋፊዎች ሁኔታቸው በፈቀደ መጠን ለእነዚህ ዝግጅቶች ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ይበረታታሉ።
11 በተደጋጋሚ ጊዜ ባልተሸፈኑ የአገልግሎት ክልሎች ለመሥራት የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ክልል ከሚያድለው ወንድም ጋር መነጋገር ያስፈልገዋል። ቤታቸው ያልተገኙ ሰዎችን ለማግኘት፣ በመንገድ ላይ እንዲሁም ከሱቅ ወደ ሱቅ ለሚደረገው ምስክርነት ትኩረት መስጠት ያስፈልግ ይሆናል። የምሽት አገልግሎትም ሊጠናከር ይችላል። በጉባኤ ውስጥ የተከማቹትን መጽሔቶች ለማቃለል ከፍተኛ ጥረት የሚደረግበት ልዩ የመጽሔት ቀን ማዘጋጀት ይቻላል። በሚያዝያና በግንቦት ወር የአገልግሎቱ እንቅስቃሴ ከሌላው ጊዜ ከፍ እንደሚል ግምት ውስጥ በማስገባት በቂ መጠን ያላቸው መጽሔቶች መታዘዝ ይኖርባቸዋል።
12 ብዙ አስፋፊዎች ብቃቱን ሊያሟሉ ይችላሉ፦ የረዳት አቅኚነት አገልግሎት ማመልከቻ የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር እንዲህ ይላል:- “ለይሖዋ ባለኝ ፍቅርና ሌሎች ሰዎች ስለ እርሱና ስለ ፍቅራዊ ዓላማዎቹ እንዲያውቁ ለመርዳት ባለኝ ፍላጎት ተነሳስቼ ከዚህ በታች ለተገለጸው ጊዜ ረዳት አቅኚ ሆኜ በማገልገል በመስክ አገልግሎት ያለኝን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ እፈልጋለሁ።” ራሳችንን ለይሖዋ ለመወሰን ያበቃን ዋና መሰረታዊ ነገር ለይሖዋ ያለን ፍቅርና ሌሎች ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ያለን ፍላጎት ነው። (1 ጢሞ. 4:8, 10) የረዳት አቅኚነትን ብቃት ለማሟላት አንድ ሰው የተጠመቀ፣ ጥሩ የሥነ ምግባር አቋም ያለውና በወር ውስጥ 60 ሰዓት በአገልግሎት ለማሳለፍ የሚችል መሆን አለበት። ከዚህ በፊት አቅኚ ሆነን የማናውቅ ብንሆንም እንኳ ሁኔታችንን ግምት ውስጥ በማስገባት በሚያዝያ ወይም በግንቦት ወር መሆን እንችላለንን?
13 በጉባኤ ውስጥ ያሉ ብዙዎች ከእነሱ ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች አቅኚ እንደሆኑ ሲመለከቱ እነሱም አቅኚ ሊሆኑ ይችላሉ። ተማሪዎች፣ በዕድሜ የገፉ፣ የሙሉ ቀን ሥራ ያላቸው፣ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች እንዲሁም ሌሎች ወንድሞች ጭምር በተሳካ ሁኔታ ረዳት አቅኚ መሆን ችለዋል። የሙሉ ቀን ሥራ ያላት አንዲት የቤት እመቤትና የሁለት ልጆች እናት 60 ሰዓት ለማገልገል፣ 108 መጽሔቶች ለማበርከት፣ 3 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለመምራት ችላለች። እንዴት ሊሳካላት ቻለ? የምሳ ሰዓት እረፍቷን ከሥራ ቦታዋ አጠገብ ባለው የአገልግሎት ክልል ለማገልገል ስለተጠቀመችበት፣ በደብዳቤ ስለ መሰከረችና በመንገድ ላይ ምስክርነት ስለ ተካፈለች ነው። እንዲሁም በየሳምንቱ ከሥራ እረፍት የምትሆንበትን ቀን በጉባኤዋ መስክ ስምሪት በመገኘት በአገልግሎት አብራ ትሳተፍ ነበር። ምንም እንኳ መጀመሪያ ላይ ረዳት አቅኚነት ሊደረስበት የማይቻል ግብ አድርጋ ብታስብም ከሌሎች ባገኘችው ማበረታቻና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ፕሮግራም ችግሮችን ተቋቁማ ለማለፍ ችላለች።
14 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 11:30) በነሐሴ 15, 1995 መጠበቂያ ግንብ ላይ በዚህ ጭብጥ የሚያነቃቃ ትምህርት ወጥቶ ነበር። መጽሔቱ ከፍተኛ ጭንቀት የነበረባትና ሰብዓዊ ሥራ ሙሉ ቀን ትሠራ ስለነበረች አንዲት እህት ይነግረናል። ይሁን እንጂ ረዳት አቅኚ መሆን እንደማትችል አስባ ይሆን? በፍጹም አላሰበችም፤ እንዲያውም በየወሩ ረዳት አቅኚ ሆና ማገልገል ችላለች። ለምን? ምክንያቱም ሚዛኗን እንድትጠብቅ የረዳት፣ አቅኚነቱ እንደሆነ ይሰማታል። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ መርዳቷና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ ሕይወታቸውን ሲለውጡ ማየቷ በሥራ በተጠመደ ሕይወቷ ውስጥ የላቀ ደስታ እንድታገኝ ረድቷታል።—ምሳሌ 10:22
15 አንድ ሰው አቅኚ ለመሆን የሚከፍለው ማንኛውም መሥዋዕትነትና የሚያደርገው ማስተካከያ ከሚያገኘው ወሮታ ጋር ሲወዳደር ኢምንት ነው። አንዲት እህት በረዳት አቅኚነት ያገኘችውን ተሞክሮ እንዲህ በማለት ጽፋለች:- “ረዳት አቅኚነት ስለራሴ ከመጠን በላይ ከማሰብ ይልቅ ሌሎችን በመርዳት ላይ እንዳተኩር አድርጎኛል። . . . ረዳት አቅኚ መሆን የሚችሉ እንዲሆኑ እመክራቸዋለሁ።”
16 ጥሩ ፕሮግራም ማውጣት ይጠይቃል፦ በዚህ አባሪ የመጨረሻ ገጽ በየካቲት 1997 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የነበረው የናሙና ፕሮግራም እንደገና ወጥቷል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ከአንተ ፕሮግራም ጋር ሊስማማ ይችል ይሆናል። ፕሮግራሙን በምትከልስበት ጊዜ በወሩ ውስጥ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ግምት ውስጥ አስገባ። አቅኚነትን ከመጀመርህ በፊት ወይም ለጊዜው አዘግይተኸው አቅኚነቱን ከጨረስክ በኋላ ልትሠራው የምትችለው በቤት አካባቢ የሚሠራ ሥራ አለህን? በመዝናናት፣ በሽርሽር ወይም በሌሎች የመዝናኛ ዓይነቶች የምታጠፋውን ጊዜ ልትጠቀምበት ትችላለህን? የሚጠበቅብህን 60 ሰዓት ለማምጣት እንዲሁ ከመሞከር ይልቅ ለየዕለቱ ወይም ለሳምንቱ ፕሮግራም አውጣ። ረዳት አቅኚ ለመሆን የሚያስፈልገው በቀን 2 ሰዓት ወይም በሳምንት 15 ሰዓት ብቻ ነው። እርሳስህን አዘጋጅና ለናሙና የቀረቡትን ፕሮግራሞች እያየህ ለአንተና ለቤተሰብህ ይበልጥ ተስማሚ የሆነ የአገልግሎት ፕሮግራም ለማውጣት ሞክር።
17 ባለፈው ዓመት ለቀረበው ጥሪ ጉባኤዎች ያሳዩት አስደናቂ ምላሽና ተጨማሪ እርዳታ ቅንዓቱን ያነሳሳለት አንድ የዘወትር አቅኚ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ረዳት አቅኚዎችን ለመርዳት ላደረጋችሁት ተጨማሪ ፍቅራዊ እርዳታ በጣም ላመሰግን እወዳለሁ። . . . የናሙና ፕሮግራሙ ከዚህ በፊት አቅኚ ሆነው የማያውቁትን እንኳ መሆን እንደሚቻል እንዲያስተውሉ ረድቷቸዋል። . . . በይሖዋ ድርጅት በመታቀፌና የታማኝና ልባም ባሪያን አስደሳችና ፍቅራዊ አመራር በመከተሌ በጣም ደስተኛ ነኝ።”
18 ምሳሌ 21:5 NW “የትጉህ ሰው ዕቅድ ውጤቱ ያማረ ነው” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። ምሳሌ 16:3 (የ1980 ትርጉም) “የምታደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ ዕቅድህም ሁሉ ይሳካልሃል” በማለት ያበረታታናል። አዎን፣ ይሖዋ ውሳኔያችንን እንዲደግፍልን በጸሎት በመጠየቅና ስኬታማ እንድንሆን እንደሚያግዘን በእሱ ላይ ጽኑ እምነት በማሳደር ረዳት አቅኚ ለመሆን ያወጣነውን ግብ በተመለከተ አዎንታዊ አመለካከት ሊኖረን ይችላል። አንድ ወይም ሁለት ወር ረዳት አቅኚ በመሆን ፕሮግራማችን ምን ያህል እንደተሳካልን ካየን በኋላ የረዳት አቅኚ ማመልከቻ ላይ “ማቆምህን እስክታሳውቅ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ ረዳት አቅኚ ሆነህ ለማገልገል የምትፈልግ ከሆነ እዚህ ላይ ምልክት አድርግ” በሚለው ሳጥን ውስጥ ምልክት ማድረግ እንችላለን። አሊያም ደግሞ የነሐሴ ወር አምስት ቅዳሜና እሁዶች ስላሉት በዚህ ወር እንደገና ረዳት አቅኚ ሆነን ልናገለግል እንችላለን። ይህ ወር የአገልግሎት ዓመቱ የሚጠናቀቅበት ወር ስለሆነ እያንዳንዱ ሰው በተቻለው መጠን ሙሉ በሙሉ በአገልግሎቱ መካፈል እንዲችል ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል።
19 ኢየሱስ “በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ዮሐ. 14:12) ይህ ትንቢት ታላቅ ፍጻሜውን እያገኘ ባለበት ወቅት የአምላክ የሥራ ባልደረባ በመሆን ማገልገል አስደሳች መብት ነው። አሁን ከምንጊዜውም በበለጠ ምስራቹን በግለት የምንሰብክበት ጊዜ ስለሆነ ይህን ሥራ ለመሥራት ጊዜ እንዋጅ። (1 ቆሮ. 3:9፤ ቆላ. 4:5) መንግሥቱን በማወጁ ሥራ የበኩላችንን ማድረግ የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ በተቻለን መጠን በተደጋጋሚ ጊዜ ረዳት አቅኚ ሆኖ ማገልገል ነው። በዚህ የመታሰቢያው በዓል ሰሞን ከረዳት አቅኚዎች የሚሰማው የውዳሴ መዝሙር ምን ያህል ታላቅ እንደሚሆን ለማየት በጉጉት እንጠባበቃለን። (መዝ. 27:6) ባለፈው ዓመት የተገኘውን ውጤት በማሰብ ‘ዘንድሮም ጥሪውን ትቀበላላችሁ?’ ብለን እንጠይቃለን። ተመሳሳይ ምላሽ እንደምትሰጡ አንጠራጠርም!
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል1]
ረዳት አቅኚ መሆን ትችላለህ?
“የግል ሁኔታህ የቱንም ዓይነት ይሁን፣ የተጠመቅህ ከሆንክ፣ ጥሩ ሥነ ምግባራዊ አቋም ካለህ፣ በወሩ ውስጥ በመስክ አገልግሎት የሚፈለግብህን 60 ሰዓት ማምጣት የምትችል ከሆነና ለአንድ ወር ወይም ከዚያ በላይ ረዳት አቅኚ ሆነህ ለማገልገል እንደምትችል የምታምን ከሆነ የጉባኤው ሽማግሌዎች ለዚህ የአገልግሎት መብት ያቀረብከውን ማመልከቻ በደስታ ይቀበሉታል።”—አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት ገጽ 114
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የረዳት አቅኚነት ፕሮግራም
በእያንዳንዱ ሳምንት 15 ሰዓት በአገልግሎት ላይ ለማሳለፍ የሚያስችሉ የተለያዩ የናሙና ፕሮግራሞች
ጠዋት—ከሰኞ እስከ ቅዳሜ
እሑድን በማንኛውም ቀን መተካት ይቻላል
ቀን ክፍለ ጊዜ ሰዓት
ሰኞ ጠዋት 2 1⁄2
ማክሰኞ ጠዋት 2 1⁄2
ረቡዕ ጠዋት 2 1⁄2
ሐሙስ ጠዋት 2 1⁄2
ዐርብ ጠዋት 2 1⁄2
ቅዳሜ ጠዋት 2 1⁄2
ጠቅላላ ሰዓት፦ 15
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሁለት ሙሉ ቀን
ከሳምንቱ ቀናት መካከል ማናኛውንም ሁለት ቀን መምረጥ ይቻላል
ቀን ክፍለ ጊዜ ሰዓት
ረቡዕ ሙሉ ቀን 7 1⁄2
ቅዳሜ ሙሉ ቀን 7 1⁄2
ጠቅላላ ሰዓት: 15
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሁለት ምሽቶች እና ቅዳሜና እሑድ
ከሳምንቱ መካከል ማናቸውንም ሁለት ምሽቶች መምረጥ ይቻላል
ቀን ክፍለ ጊዜ ሰዓት
ሰኞ ምሽት 1 1⁄2
ረቡዕ ምሽት 1 1⁄2
ቅዳሜ ሙሉ ቀን 8
እሑድ ግማሽ ቀን 4
ጠቅላላ ሰዓት፦ 15
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሰኞ እስከ ዐርብ ከሰዓት በኋላና ቅዳሜ
እሑድን በማንኛውም ቀን መተካት ይቻላል
ቀን ክፍለ ጊዜ ሰዓት
ሰኞ ከሰዓት በኋላ 2
ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ 2
ረቡዕ ከሰዓት በኋላ 2
ሐሙስ ከሰዓት በኋላ 2
ዐርብ ከሰዓት በኋላ 2
ቅዳሜ ሙሉ ቀን 5
ጠቅላላ ሰዓት፦ 15
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል6]
የአገልግሎት ፕሮግራሜ
ለእያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ የሚሆን ሰዓት መድብ
ቀን ክፍለ ጊዜ ሰዓት
ሰኞ
ማክሰኞ
ረቡዕ
ሐሙስ
ዐርብ
ቅዳሜ
እሑድ
ጠቅላላ ሰዓት፦ 15