ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ የበላይ ተመልካቾች—ጸሐፊ
1 የጉባኤ ጸሐፊ ‘ሁሉ ነገር በአገባብና በሥርዓት’ መከናወኑን በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ የሆነ ሚና ይጫወታል። (1 ቆሮ. 14:40) ጸሐፊው የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ አባል እንደመሆኑ መጠን ከጉባኤው ጋር የሚደረጉ የመረጃ ልውውጦችን ያደርጋል እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ የጉባኤው መዛግብቶችን ይይዛል። ሥራው እንደ ሌሎቹ ሽማግሌዎች በጉልህ የማይታይ ቢሆንም የሚያበረክተው አገልግሎት እጅግ ጠቃሚና የሚደነቅ ነው።
2 ጸሐፊው ከማኅበሩ ወይም ከሌላ ቦታ የሚላኩ ደብዳቤዎች ሲደርሱ ጉዳዩን ይከታተላል፤ አስፈላጊ ሲሆንም በጊዜው ምላሽ መሰጠቱን ያረጋግጣል። ወደ ጉባኤው የተላኩ ደብዳቤዎችን ለሁሉም ሽማግሌዎች ካዳረሰ በኋላ በፋይል ውስጥ ያስቀምጣል። የመጽሔትና የጽሑፍ ትእዛዝ የሚላክባቸውን ቅጾች ካረጋገጠ በኋላ ወደ ማኅበሩ ይልካል። ሒሳብና ኮንትራት የሚሠሩትን ወንድሞች ሥራ እንዲሁም ከአውራጃ ስብሰባ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በቀጥታ ይቆጣጠራል።
3 ጸሐፊው ወር በገባ እስከ ስድስተኛ ቀን ድረስ የጉባኤውን ወርኃዊ የመስክ አገልግሎት ሪፖርት ወደ ማኅበሩ መላክ ስለሚኖርበት ሁላችንም የመስክ አገልግሎት ሪፖርታችንን በወሩ መጨረሻ ላይ ሳንዘገይ መመለሳችን በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚያም የአገልግሎት ሪፖርቱን በጉባኤ የአስፋፊዎች ካርድ ላይ ይመዘግባል። ማንኛውም አስፋፊ የአገልግሎት እንቅስቃሴው የሰፈረበትን የግል ሪፖርት ካርዱን ለመመልከት ሊጠይቅ ይችላል።
4 አንድ አስፋፊ ከሌላ ጉባኤ ተዘዋውሮ ሲመጣ ጸሐፊው የመጣበት ጉባኤ ሽማግሌዎች ስለ ግለሰቡ የሚገልጽ የማስተዋወቂያ ደብዳቤ ከአገልግሎት ሪፖርት ካርዱ ጋር እንዲልኩ ይጠይቃል፤ ወይም አንድ አስፋፊ ወደ ሌላ ጉባኤ ተዘዋውሮ ሲሄድ የግለሰቡን የአገልግሎት ሪፖርት ካርድ ከማስተዋወቂያ ደብዳቤ ጋር አያይዞ ወደዚያው ጉባኤ ይልካል።—አገልግሎታችን ገጽ 105
5 ጸሐፊው የአቅኚዎችን የአገልግሎት እንቅስቃሴ በመመርመር አንድ ዓይነት ችግር ገጥሟቸው ከሆነ ለሽማግሌዎች በተለይ ደግሞ ለአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ያሳውቃል። በመስክ አገልግሎት አዘውታሪ ያልሆኑት አስፋፊዎች እነማን እንደሆኑ ለጉባኤው የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች ያሳውቃል። አገልግሎት ያቆሙ አስፋፊዎች ለመርዳት የሚደረገውን ጥረት በማቀናጀት በኩል ጸሐፊውና የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ቀዳሚ ሆነው ይሠራሉ።—የመንግሥት አገልግሎታችን ኅዳር 1987 (እንግሊዝኛ) ገጽ 1
6 ጸሐፊው የሚያከናውናቸውን የሥራ ድርሻዎች በመገንዘብ የመጋቢነት ሥራውን በተቀላጠፈ መንገድ መፈጸም ይችል ዘንድ በየበኩላችን የምንችለውን ሁሉ እናድርግ።—1 ቆሮ. 4:2