የቆዩ መጻሕፍትን በጥሩ ሁኔታ ተጠቀሙባቸው
1 የሰው ልጅ በምድር ዙሪያ በሚገኙ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ የቆዩ መጻሕፍት አከማችቷል። ሆኖም እነዚህ መጻሕፍት ለሰው ዘር ያስገኙት ምን ዘላለማዊ ጥቅም አለ? (መክ. 12:12) ከዚህ የላቀ ጠቀሜታ የሚኖራቸው በአምላክ መንግሥትና መንግሥቱ ለሰው ልጆች በሚያደርግላቸው ነገሮች ላይ እንድናተኩር የሚረዱን ጽሑፎች ናቸው። አብዛኞቹ ጉባኤዎች ከብዙ ዓመታት በፊት የታተሙ እንደነዚህ ዓይነት መጻሕፍት አሏቸው። በጥር ወር ከእነዚህ የቆዩ መጻሕፍት ውስጥ አንዳንዶቹን ለሕዝብ እናበረክታለን።
2 ዋጋማ ናቸው፦ ምንም እንኳን አንዳንዶቻችን እነዚህን መጻሕፍት በቅርብ ከታተሙት ጽሑፎቻችን ጋር ስናስተያያቸው ጊዜ ያለፈባቸው ሊመስሉን ቢችሉም ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት መያዛቸውን መዘንጋት የለብንም። የመንግሥቱን መልእክት በተመለከተ የሚሰጡት ማብራሪያ ዛሬም ጠቃሚ ሲሆን ሥራ ላይ ከዋለ የሰዎችን ሕይወት ሊያድን ይችላል። (ዮሐ. 17:3) ስለዚህ በእነዚህ የቆዩ መጻሕፍት በጥሩ ሁኔታ ለመጠቀም ተጨማሪ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
3 በርካታ የቆዩ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎችን ከአያቷ በውርስ ስላገኘች አንዲት ሴት የሚናገረው ተሞክሮ የጽሑፎቹን ጠቀሜታ ያጎላልናል። አንዲት ምሥክር የጽሑፎቹን ትክክለኛ ጠቀሜታ ተገንዝባ እንደሆነ ሴትዮዋን ጠየቀቻት። ሴትዮዋ “ምን ያህል ዋጋማ እንደሆኑ የማውቀው ነገር የለም፣ ግን እንዴት ማወቅ እችላለሁ?” ስትል መለሰች። ሴትዮዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ፈቃደኛ ሆና ወደ እውነት ከመጣች በኋላ አያቷ በውርስ የሰጧትን መጻሕፍት ማድነቅ ጀመረች። እነዚያ የቆዩ መጻሕፍት ከፍተኛ ዋጋ ያለው ውርስ ሆነው ተገኙ!
4 በሰዎች እጅ እንዲገቡ አድርጉ፦ የቆዩ መጻሕፍትን ከቤት ወደ ቤት ከማበርከታችሁ በተጨማሪ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! ኮንትራት ያላቸውንና የመጽሔት ደንበኞቻችሁን ጨምሮ ጽሑፎቻችንን ማንበብ ለሚወዱ ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርጉበት ጊዜም ለማበርከት ጥረት አድርጉ። አንዳንዶቹ የቆዩ መጻሕፍት መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠኗቸው ሰዎች ተጨማሪ እውቀት እንዲቀስሙና እውነትን በተመለከተ ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲይዙ ያስችሏቸዋል። ከእነዚህ መካከል እናንተ የሌሏችሁ መጻሕፍት ካሉ ማሟላታችሁን እርግጠኛ ሁኑ። እንዲህ በማድረግ የግል ጥናታችሁን አመርቂ ለማድረግ ልትጠቀሙበት የምትችሉ ጠቃሚ የሆነ ቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት ታደራጃላችሁ።
5 የቆዩ መጻሕፍትን ከማከማቸት ይልቅ የምናገኛቸው ሰዎች ‘እግዚአብሔርን እንዲፈሩና ትእዛዙንም እንዲጠብቁ’ ለማነሳሳት በጥሩ ሁኔታ እንጠቀምባቸው።—መክ. 12:13