መስበካችሁን ቀጥሉ!
1 “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ” እንዲደርሱ የአምላክ ፈቃድ ነው። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ስለሆነም ምሥራቹን የመስበክ ሥራ ሰጥቶናል። (ማቴ. 24:14) መስበካችንን መቀጠል ያለብን ለምን እንደሆነ ከተገነዘብን የሚያጋጥመን ማንኛውም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ወይም ሐሳብ የሚከፋፍል ነገር እንቅፋት አይሆንብንም።
2 መስበካችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው? ሰዎች የነገርናቸውን እንዲረሱ ወይም አቅልለው እንዲመለከቱ የሚያደርጉ ሐሳብ የሚከፋፍሉ ብዙ ነገሮች በዚህ ዓለም ውስጥ አሉ። ስለዚህ ስለ አምላክ የመዳን መልእክት በየጊዜው ልናሳስባቸው ይገባናል። (ማቴ. 24:38, 39) ከዚህም በተጨማሪ በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸው ነገሮች በየጊዜው ይለዋወጣሉ። ሌላው ቀርቶ የዓለም ሁኔታዎች እንኳ በአንድ ጀንበር ሊለወጡ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 7:31) የምንሰብክላቸው ሰዎች ነገ፣ በሚቀጥለው ሳምንት፣ ወይም በሚቀጥለው ወር አዳዲስ ችግሮች ወይም አሳሳቢ ነገሮች ሊያጋጥሟቸውና የምንነገራቸውን ምሥራች በቁም ነገር ያስቡበት ይሆናል። እውነትን የነገረህ ምሥክር አንድ ጊዜ ብቻ ሰብኮልህ አለመተዉ አመስጋኝ እንድትሆን አላደረገህምን?
3 የአምላክን ምህረት መኮረጅ:- ይሖዋ በክፉዎች ላይ የቅጣት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ በመፍቀድ ትዕግሥት አሳይቷል። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ እርሱ ዞር እንዲሉና እንዲድኑ ለማሳሰብ በእኛ መጠቀሙን ቀጥሏል። (2 ጴጥ. 3:9) የአምላክን የምሕረት መልእክት ለሰዎች መናገራችንን ካልቀጠልንና ከክፉ መንገዳቸው በማይመለሱ ሰዎች ላይ አምላክ በቅርቡ ስለሚወስደው የቅጣት እርምጃ ማስጠንቀቂያውን ካልተናገርን በደም ዕዳ ተጠያቂዎች እንሆናለን። (ሕዝ. 33:1-11) ምንም እንኳ ስብከታችን ሁልጊዜ ሰሚ ጆሮ ያገኛል ማለት ባይሆንም ቅን ሰዎች የአምላክን ታላቅ ምሕረት እንዲያደንቁ ለመርዳት የተቻለንን ጥረት ከማድረግ ፈጽሞ ቸልተኞች መሆን አኖርብንም።—ሥራ 20:26, 27፤ ሮሜ 12:11
4 ፍቅራችንን ለመግለጽ:- ምሥራቹ በመላው ምድር ላይ እንዲሰበክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ትእዛዝ ያስተላለፈው ይሖዋ አምላክ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ሰዎች ለመስማት ፈቃደኞች ባይሆኑ እንኳ ትክክል የሆነውን ማድረጋችንን በመቀጠል አምላክን እንደምናፈቅርና ለእርሱ ያደርን መሆናችንን የማሳየት አጋጣሚ እናገኛለን።—1 ዮሐ. 5:3
5 ምሥራቹን መስበካችንን መቀጠል ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን! የይሖዋ “የመዳን ቀን” ከማለፉ በፊት ይህንን በቅንዓት እናከናውን።—2 ቆሮ. 6:2