የ2001 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት
1 ሁላችንም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት አቅማችን የፈቀደውን ያህል ተሳትፎ ማድረግ የሚገባን ለምን እንደሆነ የሚገልጹ በቂ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች አሉ።—ምሳሌ 15:23፤ ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 15:32፤ 1 ጢሞ. 4:12, 13፤ 2 ጢሞ. 2:2፤ 1 ጴጥ. 3:15
2 ሳምንታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ለብዙ ዓመታት የትምህርት ቤቱ አንድ ገጽታ ሆኖ ቆይቷል። በየዕለቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ገጽ የሚያክል ማንበብ ይጠይቃል። ከዚህ ዓመት ጀምሮ የጽሑፍ ክለሳ በሚደረግበት በእያንዳንዱ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ወጥቷል። ባለፉት ሦስት ዓመታት አንብበን ለመጨረስ ታቅዶ የነበረው ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ተጠናቋል። ሆኖም በፕሮግራሙ ላይ ካለው የበለጠ ማንበብ የምትፈልግ ከሆነ የራስህን ፕሮግራም ማውጣት ትችላለህ።
3 ክፍል ቁ. 2 ወንድሞች የአምላክን ቃል “በሕዝብ ፊት እንዲያነቡ” ስልጠና የሚያገኙበት ነው። (1 ጢሞ. 4:13 NW ) በንባብ የምታቀርበው ክፍል ሲሰጥህ ድምፅህን ከፍ አድርገህ በማንበብ በተደጋጋሚ ልምምድ አድርግ። የቃላት አነባበብ፣ ድምፅ መለዋወጥ እንዲሁም ለጥሩ ንባብ አስፈላጊ የሆኑትን ሌሎች ነጥቦች ለማሻሻል ማኅበሩ ያዘጋጃቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክሮች መጠቀም ትችላለህ።
4 ክፍል ቁ. 3 የተመሠረተው ታላቅ ሰው በተባለው መጽሐፍ ላይ ነው። ክፍል ቁ. 4 የተመሠረተው ደግሞ በመስክ አገልግሎት እንድንጠቀምበት ታስቦ በተዘጋጀው ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ላይ ነው። ለሳምንቱ የተመደበውን ትምህርት በተወሰነው ደቂቃ ውስጥ መሸፈን የማትችል ከሆነ በጉባኤህ የአገልግሎት ክልል ውስጥ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉትን ነጥቦች ብቻ መርጠህ አቅርብ። ለአገልግሎት ክልልህ ተስማሚ የሚሆን ማንኛውንም ዓይነት መቼት መጠቀም ትችላለህ።
5 በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚሰጥህን ክፍል በጥሩ ሁኔታ ለማቅረብ አቅምህ የሚፈቅደውን ጥረት አድርግ። ጊዜ ወስደህ ጥሩ ዝግጅት አድርግ፤ እንዲሁም ከልብ በመነጨ ስሜት ተናገር። እንዲህ በማድረግ ለጉባኤው የማበረታቻ ምንጭ ትሆናለህ፤ እንዲሁም በ2001 በምንወስደው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በሙሉ ልብ ተሳትፎ በማድረግ አንተም ጥቅም ታገኛለህ።