ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አዲስ መሣሪያ አግኝተናል!
1 ቀናዒ የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆነች አንዲት አሜሪካዊት ነበረች። ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታስተምራቸውን ትምህርቶች በመደገፍ አጥብቃ ትከራከር ነበር። ለመሳለም ቫቲካን ድረስ ሳይቀር ሄዳለች። ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ቤትዋ ሄደው ሲያነጋግሯት መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ ፍላጎት ነበራት። ሃይማኖቷ ደግሞ ሰዎችን በቤታቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናበት ዝግጅት የለውም። ከዚህ ተሞክሮ ምን እንማራለን? መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለማስጠናት የምናቀርበውን ግብዣ የትኛው ሰው እንደሚቀበል በእርግጠኝነት ልናውቅ እንደማንችል ያሳየናል።—መክ. 11:6
2 ፍላጎት ያለውን ማንኛውም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ፈቃደኛ መሆናችንን ለሰዎች ለመንገር አመንትተህ ታውቃለህ? በአካባቢህ ያሉ ሰዎች በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን በነጻ እንደምናስጠና ያውቃሉ? ይህን እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን? አዲሱን መሣሪያ በመጠቀም ነው! ይህ መሣሪያ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? የሚል ርዕስ ያለው ባለ ስድስት ገጽ ማራኪ ትራክት ነው። እስቲ ንዑስ ርዕስ በንዑስ ርዕስ በመመልከት ከዚህ ትራክት ጋር እንተዋወቅ:-
3 “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ለምን አስፈለገ?” ትራክቱ የሚያቀርባቸው ምክንያቶች ትኩረት የሚስቡ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክን ፍቅራዊ መመሪያ” እንደያዘና አምላክ እንዲረዳን እንዴት በጸሎት ወደ እርሱ ልንቀርብ እንደምንችል እንዲሁም ያዘጋጀልንን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ለመቀበል ምን ማድረግ እንዳለብን ያብራራል። (1 ተሰ. 2:13) ትራክቱ ከሞትን በኋላ ምን እንሆናለን ወይም በምድር ላይ ችግር የበዛው ለምንድን ነው እንደሚሉት ላሉና ለሌሎችም ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን “የእውቀት ብርሃን የሚፈነጥቅ እውነት” ይጠቅሳል። ተግባራዊ ካደረግናቸው አካላዊ ጥቅም የሚያስገኙትን እንደ ደስታ፣ ተስፋና ሌሎችን ተፈላጊ ባሕርያት እንድናዳብር የሚረዱንን “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አምላካዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች” ይገልጻል። ትራክቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስፈላጊ የሆነበትን አንድ ሌላ ምክንያት የሚያቀርብ ሲሆን ይህም ከፊት ለፊታችን ምን እንደሚጠብቀን የሚያሳዩትን ስለወደፊቱ ጊዜ የሚናገሩ ትንቢቶች ለማወቅ ያስችለናል።—ራእይ 21:3, 4
4 “መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅ የሚያስችል እርዳታ”:- ትራክቱ “ሁላችንም የአምላክን ቃል ለመረዳት እርዳታ ማግኘት” እንደሚያስፈልገን ይናገራል። ከዚያም “ብዙውን ጊዜ መሠረታዊ ከሆኑ ትምህርቶች በመነሳት መጽሐፍ ቅዱስን ደረጃ በደረጃ ማጥናቱ የተሻለ ነው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናበትን ዘዴ ይገልጻል። ትራክቱ “የመጨረሻ ባለ ሥልጣን ተደርጎ የሚጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ” መሆኑን በግልጽ ካስቀመጠ በኋላ ተማሪው “የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጥቅሶችን ለማስተዋል” እንዲችል አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር እንደሚረዳው ይጠቅሳል። የሚቀጥለው ንዑስ ርዕስ ሰውዬው እንዲያስብበት የሚያደርግ ጥያቄ ያቀርባል።
5 “መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት በየሳምንቱ የተወሰነ ጊዜ ለመመደብ ፈቃደኛ ነህ?” ትራክቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ለተማሪው አመቺ በሆነ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ካስፈለገም በራሱ ወይም በራሷ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሌላው ቀርቶ በስልክም ጭምር ማድረግ እንደሚቻል ይገልጻል። በውይይቱ ላይ ማን መገኘት ይችላል? ትራክቱ እንዲህ በማለት መልስ ይሰጣል:- “መላው ቤተሰብህ መገኘት ይችላል። ልትጋብዛቸው የምትፈልጋቸው ጓደኞች ካሉህ መገኘት ይችላሉ። ካልፈለግህ ደግሞ ውይይቱን ከአንተ ጋር ብቻ ማድረግ ይቻላል።” እያንዳንዱ የጥናት ፕሮግራም ርዝመት ምን ያህል መሆን አለበት? “ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በየሳምንቱ አንድ ሰዓት መድበዋል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በየሳምንቱ ከዚህ የበለጠ ወይም ያነሰ ሰዓት መመደብ የምትችል ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች አንተን ለመርዳት ፕሮግራማቸውን ያስተካክላሉ” በማለት ይገልጻል። ዋናው ነጥብ ያለው እዚህ ላይ ነው! እንደ ተማሪዎቻችን ሁኔታ ፕሮግራማችንን ለማስተካከል ፈቃደኞች ነን።
6 “መጽሐፍ ቅዱስን እንድትማር የቀረበ ግብዣ”፦ ትራክቱ የደረሰው ሰው አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር እንዲላክለት ወይም በነጻ ስለሚደረገው የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አንድ ሰው መጥቶ ማብራሪያ እንዲሰጠው የሚጠይቅበት ቅጽ በትራክቱ ላይ ይገኛል። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር በሙሉ ቀለም በትራክቱ ላይ ይታያል። ይህ ትራክት ልበ ቅን የሆኑ ተጨማሪ ሰዎች እርዳታችንን እንዲቀበሉ የሚያበረታታቸው አይመስልህም? እንግዲያው ይህን አዲስ መሣሪያ በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
7 ትራክቱን ለእነማን ማበርከት ትችላለህ? በአካል ለምታገኛቸው ሰዎች ልትሰጣቸው ወይም ቤታቸው ላላገኘሃቸው ሰዎች አስቀምጠህላቸው ልትሄድ ትችላለህ። ከቤት ወደ ቤት፣ በመንገድ ላይ ወይም በንግድ አካባቢዎች ማሰራጨት ይቻላል። ጽሑፎቻችንን ለወሰዱም ሆነ ላልወሰዱ ሰዎች አበርክተው። በመጽሔቶች ወይም በሌሎች ጽሑፎች ውስጥ አድርገህ አበርክተው። ደብዳቤ ስትጽፍ አብረህ ላከው። በስልክ ለምታገኛቸው ሰዎች ትራክቱን በፖስታ እንድትልክላቸው ይፈልጉ እንደሆነ ጠይቅ። ገበያ ስትወጣ፣ በሕዝብ መጓጓዣ ስትጠቀምና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስትመሠክር ማበርከት እንድትችል ምንጊዜም ትራክቱ ከእጅህ አይጥፋ። ቤትህ ለሚመጣ ለማንኛውም ሰው ልትሰጥ ትችላለህ። ለዘመዶችህ፣ ለጎረቤቶችህ፣ ለሥራ ባልደረቦችህ፣ አብረውህ ለሚማሩትና ለሌሎች ለምታውቃቸው ሰዎች አበርክተው። ይህን ትራክት ለምታገኘው ለማንኛውም ሰው ለመስጠት ጥረት አድርግ። ትራክቱን ካበረከትክ በኋላስ?
8 ወዲያው ምላሽ ካገኘህስ:- አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደሚፈልጉ ወዲያው ሊገልጹ ይችላሉ። ስለዚህ ምንጊዜም ወደ መስክ አገልግሎት ስትሰማራ ለአንተም ለተማሪውም የሚሆኑ ሁለት አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ብሮሹር መያዝ አትርሳ። ግለሰቡ ፈቃደኛ ከሆነ ጥናቱን እዚያው ጀምርለት። የብሮሹሩን ሽፋን ውስጠኛውን ገጽ ግለጥና “ይህን ብሮሹር መጠቀም የሚቻልበት መንገድ” የሚለውን አንብብ። ከዚያም በቀጥታ ወደ ትምህርት 1 በመሄድ ጥናቱ የሚካሄድበትን መንገድ አሳየው። ይህ ቀላል አቀራረብ አይደለም?
9 አድማጭህ በጉዳዩ ለማሰብ ጊዜ የሚፈልግ ከሆነስ፦ ብዙ ሳትቆይ በድጋሚ አግኝተህ ለማነጋገር ጥረት አድርግ። በዚህ ጊዜ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ይዘህ መሄድ አትርሳ። በሽፋኑ ውስጠኛ ገጽ ላይ የሚገኘውን የአርዕስት ማውጫ አሳየውና ይበልጥ የሳበውን ርዕሰ ጉዳይ እንዲመርጥ አድርገው። ከዚያም የመረጠውን ትምህርት ግለጽና በዚያ ላይ ውይይት ጀምር።
10 መጽሔት ያበረከትክላቸውን ሰዎች ተከታትሎ መርዳት:- ትራክቱን ከመጽሔት ጋር አበርክተኸው ከነበረ ተመልሰህ ስትሄድ እንደዚህ ለማለት ትችላለህ:- “ባለፈው ስንገናኝ አንድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሰጥቼዎት ነበር። የመጽሔቱ ሙሉ ስም የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ እንደሚል ምናልባት ሳያስተውሉ አይቀሩም። ዛሬ ይህ ምን ዓይነት መንግሥት እንደሆነና ለእርስዎና ለቤተሰብዎ ምን ትርጉም እንዳለው ባወያይዎት ደስ ይለኛል።” ከዚያም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ትምህርት 6 ግለጥና የቤቱ ባለቤት ጊዜ እስከፈቀደለት ድረስ ከአንቀጽ አንድ በመጀመር አወያየው። ከዚያም በሌላ ጊዜ ተመልሰህ ትምህርቱን ለመጨረስ ቀጠሮ ያዝ።
11 በቂ ትራክት ያዝ:- የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹና በሥነ ጽሑፍ ክፍል የሚሠሩት ወንድሞች ጉባኤው ምንጊዜም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ የተባለው ትራክት በቂ አቅርቦት እንዲኖረው ያደርጋሉ። ትራክቱን በቀላሉ ልታገኘው በምትችልበት ስፍራ ማለትም በኪስህ ወይም በቦርሳህ ውስጥ፣ በመኪናህ ውስጥ፣ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት እንዲሁም በቤትህ ውስጥ በመግቢያው አካባቢ አስቀምጠው። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ልታወያየው የምትችለው ሰው ሲያጋጥምህ እንድትጠቀምበት በአገልግሎት ቦርሳህም ያዝ።
12 ይሖዋ ጥረታችንን ይባርከው:- እውነትን ለሌሎች ማስተማር ሁሉም ክርስቲያኖች ሊኖራቸው የሚገባ ግብ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) አሁን የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አለህ? ካለህ በሳምንቱ ፕሮግራምህ ውስጥ ተጨማሪ ጥናት የምትመራበት ጊዜ ማግኘት ትችላለህ? የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሌለህ እንዲኖርህ እንደምትመኝ የተረጋገጠ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንዲባርክልህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ከዚያም ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ ነገር አድርግ።—1 ዮሐ. 5:14, 15
13 ጥናቶችን ለማስጀመር የሚረዳ አዲስ መሣሪያ አግኝተናል! ከትራክቱ ይዘት ጋር በሚገባ ተዋወቁ። ሳትቆጥቡ አሰራጩት። ‘መልካምን ለማድረግ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች ለመሆን፣ ለመርዳትና ስለ አምላክ ቃል የተማራችሁትን ለማካፈል የተዘጋጃችሁ እንድትሆኑ’ የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።—1 ጢሞ. 6:18
[ገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ትራክቱን ለማሰራጨት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች
◼ ከሰዎች ጋር ስለ ዕለታዊ ጉዳዮች ስንጨዋወት
◼ ጽሑፎቻችንን ለወሰደ ሰው
◼ ሰዎችን ቤታቸው ሳናገኝ ስንቀር
◼ ተመላልሶ መጠይቅ ስናደርግ
◼ በመንገድ ላይ ስናገለግል
◼ በንግድ አካባቢዎች ስንመሰክር
◼ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስንመሰክር
◼ ለሰዎች ደብዳቤ ስንጽፍ
◼ በሕዝብ መጓጓዣ ስንጠቀም
◼ ሰዎች ቤታችን ሲመጡ
◼ ከዘመዶቻችን፣ ከጎረቤቶቻችን፣ ከሥራ ባልደረባዎቻችን፣ አብረውን ከሚማሩትና ከሌሎች የምናውቃቸው ሰዎች ጋር ስንነጋገር