የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ምንጊዜም ንቁዎች ሁኑ
1. ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ የሰጠንን ተልዕኮ መፈጸም ምን ነገርን ይጨምራል?
1 ኢየሱስ፣ ሰዎችን ‘እያስተማርን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ’ ተልዕኮ ሰጥቶናል። (ማቴ. 28:19, 20) ስለሆነም በወር አንድ ጊዜ ሰዎች ጥናት እንዲጀምሩ መጋበዝ እንድንችል ታስቦ በተመደበው ልዩ ቀን ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ምንጊዜም ንቁ መሆን እንፈልጋለን። የሚከተሉት ሐሳቦች በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።
2. መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ለእነማን ግብዣ ማቅረብ እንችላለን?
2 ሰዎች ጥናት እንዲጀምሩ ጋብዙ፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ለብዙ ሰዎች ግብዣ ባቀረብን መጠን አንድ ጥናት የማግኘታችን አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል። (መክ. 11:6) ሰዎች ጥናት እንዲጀምሩ በቀጥታ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ? በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ ጉባኤ አንድ ወር ሙሉ ጥናት ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት አድርገው ነበር። ወንድሞችና እህቶች 42 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ፈቃደኛ መሆናችሁን ያውቃሉ ብላችሁ አታስቡ። በሚቀጥለው ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ስትሄዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ለምን አትጠይቋቸውም? እንደማይፈልጉ ቢነግሯችሁ ምንም ጉዳት የለውም። የእነዚህን ሰዎች ፍላጎት ለማሳደግ የምታደርጉትን ጥረት መቀጠል ትችላላችሁ። ጎረቤቶቻችሁን፣ ዘመዶቻችሁን፣ የሥራ ባልደረቦቻችሁንና አብረዋችሁ የሚማሩትን ልጆች መጽሐፍ ቅዱስ ከእናንተ ጋር እንዲያጠኑ ግብዣ አቅርባችሁላቸው ታውቃላችሁ? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚፈልጉ ጓደኞች ወይም ዘመዶች እንዳላቸው መጠየቅ ትችላላችሁ።
3. ጥናት ለማስጀመር የሚያስችል ምን ጠቃሚ መሣሪያ አለን? መቼ መቼስ ልንጠቀምበት እንችላለን?
3 ጠቃሚ መሣሪያ፦ እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? የተባለው ትራክት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ጠቃሚ መሣሪያ ነው። የቤቱ ባለቤት ሌላ ጽሑፍ ወሰደም አልወሰደ ይህን ትራክት መስጠት ትችላላችሁ። በተጨማሪም በንግድ አካባቢ ስታገለግሉ፣ በመንገድና በደብዳቤ ስትመሠክሩ እንዲሁም ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርጉ ይህን ትራክት መጠቀም ትችላላችሁ። ቤታቸው ላልተገኙ ሰዎችም ትራክቱን ትተንላቸው ልንሄድ እንችል ይሆናል። ትራንስፖርት ስትጠቀሙ፣ ገበያ ስትወጡ ወይም ሥራ ስትሄዱ ለምን ትራክቱን ይዛችሁ አትሄዱም? በትራክቱ የመጨረሻ ገጽ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ስለተደረገው ዝግጅት በአጭሩ የሚጠቅስ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውንም መጽሐፍ ያስተዋውቃል።
4. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? የሚለውን ትራክት እንዴት መጠቀም እንችላለን?
4 ለምታነጋግሩት ሰው ትራክቱን ከሰጣችሁት በኋላ በመጀመሪያው ገጽ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች አሳዩት፤ ከዚያም “ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል የየትኛውን መልስ ማወቅ ትፈልጋለህ?” ብላችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። ከዚያም መልሱን ከትራክቱ ላይ ካሳያችሁት በኋላ በመጨረሻው ገጽ ላይ ያለውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ስለተደረገው ዝግጅት የሚገልጸውን ሐሳብ ማንበብ ወይም በቃላችሁ መናገር ትችላላችሁ። በተጨማሪም እሱ የመረጠው ርዕሰ ጉዳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ላይ የት ቦታ ይበልጥ እንደተብራራ አሳዩት፣ መጽሐፉን አበርክቱለትና ውይይቱን ለመቀጠል ቀጠሮ ያዙ።
5. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ንቁ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
5 በክልላችን ውስጥ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምን እንደሆነ ለማወቅ የሚጓጉ ሰዎች አሁንም ይገኛሉ። እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ንቁ በመሆን ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ እንዲጓዙ በመርዳት የሚገኘውን ደስታ ለማጣጣም የሚያስችለንን አጋጣሚ ከፍ ማድረግ እንችላለን።—ማቴ. 7:13, 14