ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ትኩረት አድርጉ
1. ሰዎች እንዲድኑ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
1 የ2014 ዓመታዊ የአገልግሎት ሪፖርት የአምላክ ሕዝቦች የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ያሳዩትን ቅንዓትና ቁርጠኝነት ያሳያል። (ማቴ. 24:14) ከቤት ወደ ቤት በመስበክ፣ ትራክቶችንና መጋበዣዎችን ለማሰራጨት ልዩ ዘመቻዎችን በማካሄድ እንዲሁም በአደባባይ ምሥክርነት አማካኝነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እንዲሰሙ ማድረግ ችለናል። ይሁን እንጂ ሰዎች እንዲድኑ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ይኖርብናል።—1 ጢሞ. 2:4
2. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመር ረገድ ንቁ እንድንሆን ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ አለብን?
2 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ንቁ ሁኑ፦ አንድ ሰው ፍላጎት ካሳየ አድራሻውን ለመቀበልና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር ግብ ይዘን ግለሰቡን ቶሎ ለማነጋገር ጥረት እናደርጋለን? አንድን ሰው ባነጋገራችሁበት የመጀመሪያ ዕለት መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ማጥናት እንደሚቻል ታሳዩታላችሁ? ይህን ለመጨረሻ ጊዜ ያደረጋችሁት መቼ ነው? የመጽሔት ደንበኞቻችሁ ጥናት እንዲጀምሩ ከጋበዛችሁ ምን ያህል ጊዜ ሆኗችኋል? መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው እንዴት ነው? የተባሉትን ቪዲዮዎች ለሥራ ባልደረቦቻችሁ፣ አብረዋችሁ ለሚማሩ፣ ለጎረቤቶቻችሁ፣ ለዘመዶቻችሁ ወይም ለሌሎች ሰዎች አሳይታችሁ ታውቃላችሁ? በጽሑፍ መደርደሪያ ተጠቅማችሁ ስታገለግሉ የማስጠኛ ጽሑፎችን ለሚወስዱ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንደምናስጠና ለመናገር ጥረት ታደርጋላችሁ?
3. እውነትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር ምን ያስፈልገናል?
3 ከይሖዋና ከኢየሱስ የምናገኘው እርዳታ፦ ኢየሱስ “ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን ትእዛዝ ከመስጠቱ በፊት “ሂዱ” የሚለውን ቃል መናገሩ ጥረት ማድረግ እንዳለብንና ተነሳሽነት ሊኖረን እንደሚገባ የሚጠቁም ነው። ይሁን እንጂ ይህን ሥራ ብቻችንን እንድንሠራ አልተወንም፤ ከዚህ ይልቅ አብሮን እንደሚሆን ቃል ገብቷል። (ማቴ. 28:19, 20) በተጨማሪም ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱንና እውነትን ለሰዎች ለማስተማር የሚያስፈልጉንን መሣሪያዎችም ሆነ ሥልጠናዎች ሰጥቶናል። (ዘካ. 4:6፤ 2 ቆሮ. 4:7) በጣም አስፈላጊ በሆነው በዚህ ሥራ ለመካፈል የሚያስችል ‘ፍላጎትና ኃይል’ እንዲሰጠንም መጸለይ እንችላለን።—ፊልጵ. 2:13
4. ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
4 ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልናል። አንድን ሰው እውነትን ስናስተምረውና ‘ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ’ ላይ አብሮን እንዲጓዝ ስንረዳው ደግሞ ደስታችን ይበልጥ ይጨምራል። (ማቴ. 7:14፤ 1 ተሰ. 2:19, 20) ከሁሉ በላይ ግን ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ትኩረት ማድረጋችን “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ” የማይፈልገውን ይሖዋን ያስደስተዋል።—2 ጴጥ. 3:9