ብዙ ዓይነት ሰዎችን እንዲማርኩ ተደርገው የተዘጋጁት መጽሔቶቻችን
1. የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ የሚከተለው እንዴት ነው?
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች” ማራኪ አድርጎ ለማቅረብ ዘዴውን ይቀያይር እንደነበረ ሁሉ የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍልም መጽሔቶቻችን የተለያየ አስተዳደግና እምነት ላላቸው ሰዎች እንዲዳረሱ ጥረት ያደርጋል። (1 ቆሮ. 9:22, 23) በመሆኑም የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶቻችንን በጥሩ ሁኔታ መጠቀም እንድንችል መጽሔቶቹ የትኞቹን አንባቢዎች ታሳቢ በማድረግ እንደተዘጋጁ ግምት ውስጥ ማስገባታችን ተገቢ ነው።
2. ንቁ! መጽሔት የሚዘጋጀው እነማንን ታሳቢ በማድረግ ነው?
2 ንቁ!፦ ይህ መጽሔት፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ለአቴና ሰዎች’ ንግግር በሰጠበት ጊዜ የነበሩትን ዓይነት ሰዎች ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ነው። (ሥራ 17:22) እነዚያ ሰዎች ስለ ክርስትናም ሆነ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ብዙም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። በተመሳሳይም ንቁ! መጽሔት የሚዘጋጀው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ውስን እውቀት ላላቸው ወይም ምንም ግንዛቤ ለሌላቸው ሰዎች ነው። እነዚህ ሰዎች ስለ ክርስትና ትምህርቶች ምንም እውቀት የሌላቸው፣ ሃይማኖትን በጥርጣሬ ዓይን የሚመለከቱ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዳለው የማያውቁ ሊሆኑ ይችላሉ። የንቁ! መጽሔት ተቀዳሚ ዓላማ አንባቢዎች እውነተኛ አምላክ መኖሩን እንዲያምኑ መርዳት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች የተለዩ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ መርዳት ነው።
3. ሁለቱ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች የሚዘጋጁት ለየትኞቹ አንባቢዎች ነው?
3 መጠበቂያ ግንብ፦ ለሕዝብ የሚበረከተው የዚህ መጽሔት እትም የሚዘጋጀው ለአምላክና ለቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰነ አክብሮት ያላቸውን አንባቢዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። እነዚህ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰነ እውቀት ቢኖራቸውም ምን ብሎ እንደሚያስተምር ትክክለኛ እውቀት የላቸውም። እነዚህ አንባቢዎች ጳውሎስ “አምላክን የምትፈሩ” ሲል ከገለጻቸው አድማጮቹ ጋር ይመሳሰላሉ። (ሥራ 13:14-16) የሚጠናው የመጠበቂያ ግንብ እትም በዋነኝነት የሚጻፈው ለይሖዋ ምሥክሮች ነው። ጳውሎስ የላከላቸውን ደብዳቤ የሚያነቡት ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደሚያውቁና ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዳላቸው ያምን ነበር። (1 ቆሮ. 1:1, 2) በተመሳሳይም በሚጠናው እትም ላይ የሚወጡት ርዕሶች የሚጻፉት በስብሰባዎቻችን ላይ ለሚገኙ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙባቸውን ቃላትና ሐሳቦች ለሚያውቁ ሰዎች ነው።
4. መስክ አገልግሎት ላይ የምናበረክታቸውን መጽሔቶች በሙሉ ማንበብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
4 አብዛኛውን ጊዜ መጽሔቶቹን የምናበረክተው ሁለቱንም አንድ ላይ አድርገን ቢሆንም የምናስተዋውቀው ግን አንደኛውን መጽሔት ብቻ ነው። በመሆኑም እያንዳንዱን እትም ለማንበብ ግብ አውጡ። እንዲህ ካደረጋችሁ፣ የምታገኟቸውን ሰዎች በሚስብ መንገድ መጽሔቶቹን ለማስተዋወቅ በሚገባ የተዘጋጃችሁ ትሆናላችሁ።