በቅርብ አስቀምጡት
አኗኗራችሁ ይሖዋን የሚያስከብር ይሁን
ክፍል 1—በቤተሰብ ውስጥ
1, 2. አንዳንድ ማሳሰቢያዎች በድጋሚ መሰጠታቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
1 “የጠራችሁ ቅዱስ አምላክ፣ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም ራሳችሁ በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ምክንያቱም ‘እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ልትሆኑ ይገባል’ ተብሎ ተጽፏል።”—1 ጴጥ. 1:15, 16
2 ባለፉት ዓመታት ውስጥ ይሖዋ አእምሯችንን በማደስ እንድንለወጥ በድርጅቱ አማካኝነት በብዙ መንገዶች ሲረዳን ቆይቷል። ስለሆነም በዛሬው ጊዜ፣ አብዛኞቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ ስለምንችልበት መንገድ ግልጽ እውቀት አለን። ነገር ግን ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንዳንዶቹን እንደገና መለስ ብለን መመልከታችን ለሁላችንም በተለይ ደግሞ በቅርቡ ወደ እውነት ለመጡ በርካታ የእምነት ባልንጀሮቻችን ጠቃሚ ነው።—ሮም 12:2፤ 2 ጴጥ. 1:12፤ 3:1
ለጋብቻ ያለን አመለካከት
3. ይሖዋን በነጠላነት ያገለገሉ ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮችን ጥቀስ።
3 የጋብቻ መሥራች ይሖዋ ነው፤ ሆኖም ለደስታ ብቸኛው ቁልፍ ጋብቻ ነው? (መክ. 12:13፤ ማር. 12:30) ነጠላ ሆነው ይሖዋን በደስታ ያገለገሉ የብዙ ሰዎችን ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። የዮፍታሔ ልጅ፣ ለማግባትና ለመውለድ ትልቅ ቦታ በሚሰጥ ማኅበረሰብ ውስጥ ዕድሜዋን በሙሉ ነጠላ ሆና ኖራለች፤ ይህን ያደረገችው አባቷ ለይሖዋ የገባውን ስእለት መፈጸም እንዲችል ስትል ነበር። (መሳ. 11:34-40) ‘ትንቢት የሚናገሩት’ የፊልጶስ አራት ሴቶች ልጆች ያላገቡ ነበሩ፤ ሆኖም እነዚህ ሴቶች በዚህ መልኩ ይሖዋን ማወደሳቸው ከፍተኛ እርካታ እንዳስገኘላቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ‘ደስተኛ የሆነው አምላክ’ ነጸብራቅ የሆነው ኢየሱስም ቢሆን አላገባም። (ሥራ 21:8, 9፤ 1 ጢሞ. 1:11) በመሆኑም ነጠላ ሆነው ይሖዋን የሚያገለግሉ ክርስቲያኖችን ዝቅ አድርጎ መመልከት ተገቢ አይደለም።
4. አንዳንዶች ስለ ጋብቻ ያላቸው ባሕላዊ አመለካከት ስሕተት የሆነው ለምንድን ነው?
4 ሰዎች ለጋብቻ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው ካደረጉት ነገሮች መካከል የቀድሞ አባቶች አምልኮ የሚጠቀስ ነው። የቀድሞ አባቶችን የሚያመልኩ ሰዎች አንድ ሰው ዘር በመተካት ከቀድሞ አባቶቹ የተቀበለውን ሕይወት ማስተላለፍ እንዳለበት ያምናሉ፤ በመሆኑም አንዳንዶች የትኛውም መሥዋዕትነት ተከፍሎ ቢሆን ማግባትና ልጅ መውለድ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። እንዲያውም እንዲህ አለማድረግ የቀድሞ አባቶችን እንደሚያስቆጣ ያምናሉ። ክርስቲያኖች ግን ሙታን ‘ምንም እንደማያውቁ’ እንዲሁም አሁን በእንቅልፍ ላይ እንደሚገኙና ብቸኛው ተስፋቸው ትንሣኤ እንደሆነ እናውቃለን። (መክ. 9:5፤ ሥራ 24:15) ስለሆነም ሁሉም ክርስቲያኖች የተሳሳቱ ትምህርቶች ተጽዕኖ እንዳያሳድሩባቸው መጠንቀቅ አለባቸው፤ ማንም ቢሆን ነጠላ የሆኑ ክርስቲያኖችን ዝቅ አድርጎ መመልከት የለበትም።
5. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጋብቻ ምን ይላል? (ለ) አንዳንዶች ነጠላነታቸውን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማከናወን የተጠቀሙበት እንዴት ነው?
5 በ1 ቆሮንቶስ 7:8, 9, 28, 32-34, እና 38 ላይ ለጋብቻ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳ መመሪያ እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች እንዳያገቡ አይከለክልም። እንዲያውም ነጠላ በመሆናቸው ደስተኛ ያልሆኑ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና ለመፈጸም የሚፈተኑ ሰዎች ቢያገቡ የተሻለ ነው። ማግባት አንዳንድ ችግሮችን ቢፈታም ሌሎች ተጨማሪ ችግሮች ይፈጥራል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው ነጠላ የሆኑ ሰዎች ሳያገቡ ቢቀጥሉ ለመንፈሳዊነታቸው ‘የተሻለ ያደርጋሉ’። ብዙ ወንድሞችና እህቶች ሳያገቡ ለመኖር ወስነዋል፤ አንዳንዶች ይህን የሚያደርጉት ለተወሰነ ጊዜ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ሕይወታቸውን ሙሉ ነጠላ ሆነው ለመኖር መርጠዋል። ነጠላ የሆኑ በርካታ ወንድሞችና እህቶች የዘወትር እና ልዩ አቅኚዎች እንዲሁም ቤቴላውያን ሆነው ያገለግላሉ። ይሖዋ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ያሳዩትን ታማኝነት መቼም ቢሆን አይረሳም። (ዕብ. 6:10) ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ከማግባታቸው በፊት ለተወሰነ ጊዜ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ቢካፈሉ ደስ አይላችሁም?
ማንን ማግባት ይኖርብናል?
6, 7. (ሀ) ‘በጌታ’ ማግባት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ለማግባት የምታስቡት ሰው የትኞቹን ብቃቶች ሊያሟላ ይገባል?
6 ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ እንዳንጠመድ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቀናል። (2 ቆሮ. 6:14, 15) ይህን ምክር ችላ ማለት ጥበብ የጎደለው አካሄድ ነው። ከክርስቲያኖች ጋር ትዳር የሚመሠርቱት የማያምኑ ሰዎች ጨዋ እና እውነትን የማይቃወሙ ሊመስሉ ይችላሉ። አልፎ ተርፎም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኙ ይሆናል። ያም ቢሆን ይህ ባሕርያቸው ትዳር ውስጥ ከገቡ በኋላ ሊለወጥ ይችላል። በተጨማሪም ሆን ብለን የይሖዋን ሕግ ከጣስን በኋላ እሱ ትዳራችንን እንደሚባርከው ፈጽሞ መጠበቅ አይኖርብንም።—ኢዮብ 9:4ለ
7 የምናገባው “በጌታ” ቢሆንም እንኳ አስተዋይ መሆን ያስፈልገናል። (1 ቆሮ. 7:39) አንድን ሰው ለማግባት ከመወሰናችሁ በፊት ግለሰቡን በደንብ አጥኑት። በተቻለው መጠን ይሖዋን ለመታዘዝ፣ ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት ለማሳየት፣ ጥሩ የጥናት ልማድ ለማዳበር እንዲሁም ትሑት እና ደግ ለመሆን ጥረት የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጡ። ልታገቡት ያሰባችሁትን ሰው በደንብ የሚያውቁ የጎለመሱ ክርስቲያኖችን አማክሩ። ይህን ሁሉ ካደረጋችሁም በኋላ ምርጫችሁ ትክክል ስለመሆኑ ብትጠራጠሩስ? ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬ ካደረባችሁ ነገሩን በጥሞና ልታስቡበት ይገባል። ምንም ያህል ፍቅር ቢይዛችሁ ወይም ደግሞ ምንም ያህል የማግባት ጉጉት ቢያድርባችሁ ከባድ ለሆኑ ጉድለቶች ዓይናችሁን መጨፈን የለባችሁም። (ምሳሌ 22:3፤ መክብብ 2:14) አጥብቃችሁ የምትቃወሟቸውን ነገሮች ከምታዩበት ሰው ጋር ግንኙነት ፈጥራችሁ ከሆነ ግንኙነቱን ማቋረጥና ከዚያ ሰው ጋር ዘላቂ የሆነ ቃል ኪዳን ከመግባት መቆጠባችሁ ብልህነት ነው።” ጋብቻ ዘላቂ ጥምረት በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱ ቃል ኪዳን ውስጥ ከመግባታችን በፊት ውሳኔያችን ትክክል መሆኑን እርግጠኞች መሆን አለብን።—ማቴ. 19:5, 6
የባል ድርሻ
8. አንድ ባል የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀምበት መንገድ ለይሖዋ የሚያቀርበውን አምልኮ የሚነካው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
8 አንድ ወንድ ማግባቱ በተወሰነ መጠን ነፃነቱን እንደሚገድብበትና ቀደም ሲል ያደርግ እንደነበረው እንዳሻው መሆን እንደማይችል የታወቀ ነው፤ ይህ ደግሞ ለአንዳንድ ወንዶች አይጥማቸውም። አንድ ክርስቲያን ባል ጋብቻ ቅዱስ እንደሆነ ይገነዘባል። ሚስቱን በሚገባ አለመያዝ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ይነካበታል። (1 ጢሞ. 5:8) አንድ ክርስቲያን ባል በሚስቱ ላይ አምባገነን አይሆንም፤ ከዚህ ይልቅ አካላዊና ስሜታዊ ሁኔታዋን ግምት ውስጥ በማስገባት በደግነት ይመራታል። (1 ጴጥ. 3:7) አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በማከናወን ያግዛታል። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የወጣ አንድ የንቁ! መጽሔት “በአንዳንድ ባሕሎች ላደጉ ባሎች የማይዋጥላቸው ቢሆንም በተለይ ሚስቲቱ ለሥራ ከቤት ውጭ የምትውል ከሆነ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል ይገባል” ይላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አንድ ባል በቤተሰብ ጥናት፣ በመስክ አገልግሎትና በሌሎች ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያውን ወስዶ ቤተሰቡን በመምራት ስለ ሚስቱ መንፈሳዊነት በጥልቅ እንደሚያስብ ያሳያል።
9. አንድ ባል የሚስቱን አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ፍላጎት ማሟላት የሚችለው እንዴት ነው?
9 አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ በመውደድ የኢየሱስን ምሳሌና መመሪያ ይከተላል። (ማቴ. 19:19፤ ኤፌ. 5:28) ይህ ደግሞ ሚስቱን በሚይዝበት መንገድ ሊታይ ይገባል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ባል እሱ ምርጥ ምርጡን እየበላ ሚስቱ የተራረፈውን እንድትበላ አያደርግም። ወይም ደግሞ ከደሞዙ ግማሹን ብቻ በመስጠት ሚስቱ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማሟላት ገንዘቡን እንዴት እንደምታብቃቃው እንድትጨነቅ አያደርግም። በተጨማሪም አንድ ባል ከሚስቱ ጋር የተለያዩ ነገሮችን ያከናውናል። ለምሳሌ ከቤት ወጣ ብለው ዞር ዞር በማለት ወይም ቁጭ ብለው በማውራት አብረው ጊዜ እንዲያሳልፉ ያደርጋል፤ ሚስቱ ስታዋራው በትኩረት ያዳምጣታል እንዲሁም በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል አብሯት እቅድ ያወጣል።
10. አንድ ክርስቲያን ባል ከራስነት ሥርዓት ጋር በተያያዘ ለሥጋ ዘመዶቹ ግልጽ ሊያደርግላቸው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
10 በአንዳንድ አካባቢዎች አንዲት ያገባች ሴት የምትታየው እንደ ቤተሰቡ ንብረት እንጂ እንደ ባሏ ረዳት ወይም ማሟያ ተደርጋ አይደለም። በመሆኑም የወንዱ ቤተሰቦች ሚስቱን እንደፈለጉ የማዘዝ ሥልጣን እንዳላቸው ይሰማቸው ይሆናል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሚስቶች መገዛት ያለባቸው “ለባሎቻቸው” እንደሆነ ይናገራል። (ኤፌ. 5:24) አንዲት ሚስት የባሏን ዘመዶች ብታከብርም መታዘዝ ያለባት ግን ባሏን ነው። በመሆኑም አንድ ክርስቲያን ባል ለዘመዶቹ በቤተሰቡ ውስጥ ስላለው የራስነት ሥርዓት በግልጽ በመንገር ሚስቱ ጫና እንዳይበዛባት ማድረግ ይኖርበታል።
የሚስት ድርሻ
11. አንዲት ሚስት ለባሏ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራት ይገባል? ይሖዋስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማዋል?
11 አንድ ባል ካገባ በኋላ ነፃነቱ በተወሰነ መጠን እንደሚገደብ ሁሉ አንዲት ክርስቲያን ሚስትም ነጠላ በነበረችበት ወቅት ታደርግ እንደነበረው በራሷ መመራት አትችልም። አሁን ከባሏ ጋር አንድ አካል ከመሆኗም ሌላ የእሱ “ረዳት” ነች። (ዘፍ. 2:18) ልታፈራቸው ከሚገቡ ባሕርያት መካከል ‘ጭምትነትና ገር መንፈስ’ የሚገኙበት ሲሆን እነዚህም “በአምላክ ዓይን ከፍተኛ ዋጋ” አላቸው። (1 ጴጥ. 3:1-6) የባሏን ደግነት እንደ ድክመት በመቁጠር ቤተሰቡን በበላይነት ለመምራት አትሞክርም። ከዚህ ይልቅ ባሏ በመንፈሳዊ ነገሮች የሚሰጣትን አመራር ለመከተል ጥረት ታደርጋለች። አንዲት ሚስት እንዲህ ዓይነት የተገዢነት መንፈስ ማሳየቷ ይሖዋን ያስደስተዋል።
12. በምሳሌ 31:10-31 ላይ የተጠቀሰችውን አምላክን የምትፈራ ሴት እንዴት አድርገህ ትገልጻታለህ?
12 አምላክን የሚፈሩ ሴቶች ለሚያንጸባርቋቸው በርካታ ግሩም ባሕርያት ሊመሰገኑ ይገባል። ምሳሌ 31:10-31 ጠባየ መልካም ወይም ልባም ስለሆነች ሚስት የሚሰጠው ሐሳብ ልብ ልንለው የሚገባ ነው። እዚህ ላይ የተጠቀሰችው ሴት የቤት ውስጥ ሥራዎችን ከማከናወን በተጨማሪ ከመሬት ሽያጭ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ታስፈጽም፣ እርሻ ታሳርስ እንዲሁም ትነግድ ነበር። የምንኖረው “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ በመሆኑ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ሚስቶች ከቤት ውጭ ለመሥራት ተገድደዋል። (2 ጢሞ. 3:1) ይሁንና ከቤት ውጭ የምትሠራ ሚስትም ብትሆን “የቤተ ሰዎቿን ጕዳይ” በትጋት መከታተል አለባት። (ምሳሌ 31:27) ይህ የእሷ ኃላፊነት ነው፤ ዘመዶች ወይም የቤት ሠራተኞች ይህን ቦታ ሊተኩ አይችሉም። እንዲያውም ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ አንዲት ሚስት ውጭ የምትሠራውን ሥራ መቀነሷ ለአንድ ክርስቲያን ቤተሰብ ጠቃሚ ነው።
ለትዳር ጓደኛ የሚገባውን ማድረግ
13. አንድ ባል ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ አሳቢነት ማሳየት ያለበት ለምንድን ነው?
13 ዓለም ስለ ፆታ ግንኙነት ያለው አመለካከት ይሖዋ ካለው አመለካከት የተለየ ነው። አንድ ክርስቲያን ባል ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ ይሖዋ የሚሰጠውን ምክር በመከተል ለሚስቱ ከልብ የመነጨ ፍቅር ያሳያል። የሚስቱን አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባል እንዲሁም በዚህ ረገድ ሚስቱ የማትፈልገውን ነገር እንድታደርግ አያስገድዳትም። ከዚህ ጋር በተያያዘ መግ 11-110 [ሰኔ 1, 1989 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ)] ገጽ 14 አንቀጽ 18 እንዲህ ይላል፦ “በእስራኤል ውስጥ የተሰጡት ሕጎች በጋብቻ ማሰሪያም ውስጥ እንኳ ቢሆን ለጾታ ድርጊቶች ድንበር ያበጁ ነበር። አንድ ባል የወር አበባ በሚታያት ጊዜ ከሚስቱ ጋር የጾታ ግንኙነት ከማድረግ መራቅ ነበረበት። (ዘሌዋውያን 15:24፤ 18:19፤ 20:18) ይህም በእስራኤላውያን ወንዶች በኩል ፍቅራዊ አሳቢነትንና ራስን መግዛትን የሚጠይቅባቸው ነበር። ክርስቲያኖችስ ለሚስቶቻቸው ያላቸው አሳቢነት ከዚህ ያነሰ መሆን ይገባዋልን? ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያን ባሎች ከሚስቶቻቸው ጋር ‘በእውቀት’ መኖር አለባቸው ብሏል፤ ይህም ሲባል እንደ ‘ደካማ ዕቃ የሆነ የሴትነት’ አሠራር እንዳላቸው ማወቅ ማለት ነው።—1 ጴጥሮስ 3:7”
14. ባልም ሆነ ሚስት ‘አንዳቸው ለሌላው የሚገባውን ከመከልከል’ መቆጠብ የሚችሉት እንዴት ነው?
14 በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የተጋቡ ሰዎችን እንዲህ በማለት ይመክራል፦ “አንዳችሁ ለሌላው የሚገባውን [ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ] አትከልክሉ።” (1 ቆሮ. 7:3, 5) ባልም ሆነ ሚስት ከትዳር ጓደኛቸው የሚፈልጉትን ለማግኘት ሲሉ የፆታ ግንኙነትን እንደ ማባበያ መጠቀም የለባቸውም። በተጨማሪም ባለትዳሮች በሰብዓዊ ሥራ ምክንያት ለረጅም ጊዜ ተለያይተው መቆየታቸው ጥበብ የጎደለው እርምጃ ነው። አንድ ባል፣ ከተማ ውስጥ ለመሥራት ሲል ቤተሰቡን ገጠር ትቶ መምጣቱ በዓለም ለሚገኙ ሰዎች የተለመደ ቢሆንም እንዲህ ዓይነቱ ጥበብ የጎደለው አካሄድ ባልም ሆነ ሚስት፣ ከሥነ ምግባር ብልግና ጋር በተያያዘ ሰይጣን ለሚያመጣቸው ፈተናዎች እንዲጋለጡ ያደርጋል።
ልጆች መውለድና ማሠልጠን
15. ለአምላክ መንግሥት ሲሉ ልጆች ላለመውለድ የወሰኑ ባለትዳሮች ምን በረከት ያገኛሉ?
15 ልጆች የይሖዋ ስጦታዎች ናቸው፤ በመሆኑም ለወላጆቻቸው ደስታ ያስገኛሉ። (መዝ. 36:9፤ 127:3) ባለትዳሮች ሁኔታቸውን በደንብ ከመረመሩ በኋላ ልጅ ለመውለድ ወይም ላለመውለድ ሊወስኑ ይችላሉ። ይሖዋ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማከናወን ሲሉ አሁን ልጆች ላለመውለድ የወሰኑ አገልጋዮቹን አብዝቶ ባርኳቸዋል። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ በአሁኑ ጊዜ የዘወትር እና ልዩ አቅኚዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እንዲሁም ቤቴላውያን ሆነው እያገለገሉ ነው።a በሌላ በኩል ግን ብዙ ባለትዳሮች ልጆች ለመውለድ ወስነዋል፤ ይህ ውሳኔም ቢሆን ስህተት አይደለም። ታዲያ እንዲህ ለማድረግ መወሰናቸው ምን ኃላፊነት ያስከትልባቸዋል?
16. (ሀ) የቤተሰብን ቁጥር መገደብ የጥበብ እርምጃ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ባለትዳሮች የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴ በሚመርጡበት ጊዜ ምን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው?
16 ይሖዋ፣ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን በአግባቡ እንዲያሳድጉ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል፤ ነገር ግን ትልቅ ቤተሰብ ያላቸው አንዳንድ ወላጆች ይህን ኃላፊነት መወጣት በጣም ከባድ ሆኖባቸዋል። በመሆኑም ወላጆች ምን ያህል ልጆች እንደሚወልዱ መነጋገራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ክርስቲያኖች የቤተሰባቸውን ቁጥር ለመወሰን ሲሉ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን መጠቀም አለባቸው? ይህ ባለትዳሮች ራሳቸው ሊያደርጉት የሚገባ ውሳኔ ነው። ያም ቢሆን የየካቲት 22, 1993 ንቁ! (እንግሊዝኛ) እንዲህ ይላል፦ “ክርስቲያን ባለትዳሮች የሚመርጡት የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ሕይወትን እንደ ቅዱስ አድርገው እንደሚመለከቱት የሚያሳይ ሊሆን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሕይወት የሚጀምረው ገና ፅንስ ሲፈጠር እንደሆነ ስለሚገልጽ ክርስቲያኖች የፅንሱ ሕይወት እንዲጠፋ የሚያደርግ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ አይመርጡም። . . . ባለትዳሮች ለእነሱ የሚስማማቸውን የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴ መምረጥ እንዲችሉ በዚህ ረገድ አስፈላጊውን መረጃ የሚሰጡ ሐኪሞችንና የቤተሰብ መምሪያ ክሊኒኮች ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎችን ማማከር ይችላሉ።” ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በዚህ ንቁ! መጽሔት ገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኘውን ሣጥን መመልከት ይቻላል።
17, 18. (ሀ) የቤተሰብ ጥናት ልጆችን በመቅረጽ ረገድ ምን ሚና ይጫወታል? (ለ) ወላጆች፣ ልጆቻቸው በማመዛዘን ችሎታቸው እንዲጠቀሙ በሚያሠለጥኑበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም የሚችሉት እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
17 የቤተሰብን ሥጋዊ ፍላጎት ከሟሟላት የበለጠ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነገር አለ። አባቶች ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ” እንዲያሳድጓቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያዛል። (ኤፌ. 6:4) ይህም ልጆችን የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጎ ማሳደግን ይጨምራል። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ደግሞ ወላጆች፣ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይኖርባችኋል። (ዮሐ. 5:19) በይሖዋ አምልኮ ረገድ ቅድሚያውን ወስዳችሁ ቤተሰባችሁን ለመምራት ሁኔታዎቻችሁን አስተካክሉ። እያንዳንዱን ልጅ ለማሠልጠን ብዙ ጊዜ፣ ከፍተኛ ትኩረትና ጥልቅ ፍቅር እንደሚጠይቅ አስታውሱ። ወላጆች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከልጆቻቸው ጋር ከማሳለፍ ይልቅ ከቤት ውጭ ከጓደኞቻቸው ጋር የሚያሳልፉ ከሆነ ልጆቹ መጎዳታቸው አይቀርም።
18 ልጆቻችሁ በማመዛዘን ችሎታቸው መጠቀም የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ይህን እንዲያደርጉ አሠልጥኗቸው። እንዲሁ በደፈናው “ይሄ ትክክል አይደለም፣” “እንዲህ ማድረግ የለብንም” ወይም “እንዲህ ማድረግ ክልክል ነው” ብሎ ከመናገር ይልቅ አንዳንድ ነገሮች ስህተት የሆኑበትን ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስተምሯቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ለእንስሳት ሕይወት ያለውን አመለካከት ለልጆቻችሁ ስታስተምሩ በዮናስ 4:11 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ መጠቀም ትችላላችሁ፤ ጥቅሱ ይሖዋ በነነዌ ለሚገኙት ሰዎች ብቻ ሳይሆን በከተማዋ ለሚገኙ “አያሌ እንስሶች” ጭምር ምሕረት እንዳሳየ ይገልጻል። በተመሳሳይም አመስጋኝ፣ ሐቀኛና ንጹሕ መሆን ጠቃሚ የሆነው ለምን እንደሆነ ንገሯቸው። ከታላቁ አስተማሪ ተማር የተባለው መጽሐፍ የተዘጋጀው ለትንንሽ ልጆቻችሁ እንዲህ ዓይነቶቹን አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች በማስተማር ረገድ እንዲረዳችሁ ታስቦ ነው።
19. ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ስለ የትኞቹ መንፈሳዊ ግቦች መወያየት ይኖርባቸዋል?
19 ለልጆቻችሁ መንፈሳዊ ግቦች አውጡላቸው። የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆን ስለሚያስገኘው ጥቅም ተወያዩ። አቅኚዎችን ቤታችሁ ጋብዙ። ከተቻለም ልጆቻችሁ ቤቴልን እንዲጎበኙ ይዛችኋቸው ሂዱ። የተጠመቁ ልጆች ካሏችሁ ትምህርት ቤት በሚዘጋበት ወቅት ረዳት አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ አበረታቷቸው። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና ልጆችን በተመለከተ ከተለመደው አመለካከት እንደሚለይ የታወቀ ነው። ያም ሆኖ እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ ማድረጋችሁ ቤተሰባችሁ ጠንካራና ደስተኛ እንዲሆን መሠረት ይጥላል።
20. ወላጆች በዘዳግም 6:6, 7 ላይ የሚገኘውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
20 በአፍሪካ ውስጥ በሚገኙ በአብዛኞቹ አካባቢዎች፣ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያዩአቸው ለእርጅና ዘመናቸው መጦሪያ እንደሚሆኗቸው አድርገው ነው። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ወላጆች፣ ልጆቻቸው በጉባኤ ውስጥ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ከማበረታታት ይልቅ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ ሊገፋፏቸው ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ ጥራት ያለው ትምህርት እንደሚሰጡ ወደሚነገርላቸው አዳሪ ትምህርት ቤቶች ልጆቻቸውን ይልካሉ፤ ልጆቹ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይሖዋን ለማገልገል የሚኖራቸው አጋጣሚ በጣም ጠባብ ሊሆን ወይም ጨርሶ አጋጣሚ ላይኖራቸው ይችላል። አንዳንድ ልጆች በዚህ ሁኔታ በመንፈሳዊ በጣም ከመድከማቸው የተነሳ የትምህርት ቤቱ ባለሥልጣኖች ያዘዟቸውን ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ ያላቸው ድርጊቶች ፈጽመዋል። እንዲህ ዓይነት ልጆች ያሏቸው ወላጆች የልጆቻቸውን መንፈሳዊ ደህንነት መጠበቅ እንዳልቻሉ ግልጽ ነው።—ዘዳ. 6:6, 7
21. ለትምህርት ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
21 ለትምህርት ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ አስፈላጊ ነው። የነሐሴ 1999 የመንግሥት አገልግሎታችን (እንግሊዝኛ) እንዲህ ይላል፦ “በልጅነት ጥሩ መሠረታዊ ትምህርት ማግኘት የማንበብና የመጻፍ ችሎታን ለማዳበር ይረዳል። . . . እንዲህ ዓይነት ትምህርት በምትቀስምበት ጊዜ ነገሮችን የማገናዘብ፣ ነጥቦችን የመገምገም፣ ችግሮችን የመፍታት እና ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን የማመንጨት ችሎታህ እያደገ ይሄዳል።” በመሆኑም ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ ሁሉም ልጆች መሠረታዊ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ እጅግ ጠቃሚ ነው። ይሁንና ለትምህርት ሲባል ከቤታቸው ርቀው የሄዱ ወይም ከፍተኛ ትምህርት የተከታተሉ አብዛኞቹ ልጆች ከእውነት ቤት ወጥተዋል። አቅኚ ለመሆን አቅደው የነበሩ ሌሎች ደግሞ የኮሌጅ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ትኩረታቸው ቁሳዊ ነገሮችን ወደ ማሳደድ ዞሯል። እንዲህ ዓይነቱን ትምህርት መከታተል በመንፈሳዊነት ላይ የሚያስከትለው ኪሳራ በጣም ከፍተኛ ነው! አንድ ልጅ በዋነኝነት የሚያስፈልገው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚሰጠው ትምህርት ነው። ይሖዋን ስለማወደስ መማር ይኖርበታል። ይሖዋን በሙሉ ጊዜያቸው እንዲያገለግሉት ልጆቻቸውን ለእሱ አደራ የሚሰጡ ወላጆች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ይሖዋ እንደማይጥላቸው ሊተማመኑበት ይችላሉ።—መዝ. 37:25
22. ልጆችን አምላክን እንዲፈሩ አድርጎ ማሳደግ ምን በረከቶች ያስገኛል?
22 ልጆችን አምላክን እንዲፈሩ አድርጎ ማሳደግ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። የወላጅነት ኃላፊነታችሁን በቁም ነገር የምትመለከቱ ከሆነ ብዙ በረከቶች ታገኛላችሁ። ሁሉም የቤተሰብ አባላት ደስተኛ ይሆናሉ፤ እንዲሁም ‘በሚደክሙበት ሁሉ ርካታን’ ያገኛሉ።—መክ. 2:24፤ 3:12, 13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ለምሳሌ የነሐሴ 1, 2000 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 20-23 ተመልከት።