አኗኗራችሁ ይሖዋን የሚያስከብር ይሁን
ክፍል 2—ክርስቲያናዊ ባልሆኑ ልማዶች እንዳትበከሉ ተጠንቀቁ
1, 2. ሁሉም ልማዶች መጥፎ ናቸው? አብራራ።
1 ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህን ነገሮች እየተጠባበቃችሁ ስለሆነ በመጨረሻ በእሱ ፊት ቆሻሻና እድፍ ሳይኖርባችሁ በሰላም እንድትገኙ የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ።” (2 ጴጥ. 3:14) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ምክር በመታዘዝ ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ልማዶችን ትተዋል። በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑ ያሉ ሰዎች አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተባለው ብሮሹር ትምህርት 11 ላይ ስለተጠቀሱት አምላካዊ ያልሆኑ አንዳንድ ልማዶች በቁም ነገር ሊያስቡ ይገባል።
2 ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይጋጩ ጥሩ ልማዶች እንደሚኖሩ አይካድም። ከእነዚህ መካከል እንግዳ ተቀባይነት፣ ለአዋቂዎች አክብሮት ማሳየት እንዲሁም የተቸገሩትን መርዳት ይገኙበታል። ከአለባበስ ወይም ከሰላምታ አሰጣጥ ጋር የሚያያዙ ሌሎች ልማዶችም ብዙውን ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር አይጋጩም። ይሁንና የእውነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን የሚያሳዝኑ ብዙ ልማዶች አሉ። እንዲህ ያሉት ልማዶች ጴጥሮስ “ከቀድሞ አባቶቻችሁ በወግና ልማድ [የወረሳችሁት] ፍሬ ቢስ አኗኗር” ብሎ ከጠራቸው ነገሮች ጋር ሊፈረጁ ይችላሉ፤ ሐዋርያው ክርስቲያኖችን ከእነዚህ ልማዶች እንዲርቁ አስጠንቅቋቸዋል። (1 ጴጥ. 1:18) በዚህ ረገድ ጳውሎስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ልብ ልንለው ይገባል፦ “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን . . . በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ . . . ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።” (ቆላ. 2:8) በአካባቢያችን የተለመዱ አንዳንድ ልማዶችን እስቲ እንመልከት።
ግርዘት
3, 4. (ሀ) የወንዶች ግርዘት በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ምን ቦታ ነበረው? (ለ) ይሖዋን የሚያሳዝን የግርዛት ዓይነቶችን ጥቀስ።
3 መጽሐፍ ቅዱስ የወንዶችን ግርዘት አይከለክልም። እንዲያውም ይሖዋ ለእስራኤላውያን በሰጣቸው ሕግ ውስጥ ግርዘት ተካትቶ የነበረ ሲሆን ኢየሱስ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ያልተገረዘ ወንድ እንደ ርኩስ ይታይ ነበር። ሆኖም “ሕጉ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ [ሞግዚት]” ከመሆን ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ አምላክ ለወንዶች ግርዘት የተለየ ቦታ የማይሰጥ ከመሆኑም ሌላ ግርዘት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ብቃት አይደለም።—ገላ. 3:24፤ 5:6
4 በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስገረዝ ቢመርጡ (ምናልባትም ለልጆቻቸው ጤንነት ሲሉ) ይህ የግል ውሳኔያቸው ነው። ይሁንና በአንዳንድ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች፣ በተመሳሳይ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዶች ልጆች አንድ ላይ የሚገረዙበት የተለየ ቀን ይመድባሉ። በዚህ ወቅት፣ እነዚህ ወንዶች ልጆች ወደ አንድ ማኅበራዊ ደረጃ መሸጋገራቸውን ለማሰብ ዘፈንና ጭፈራ ያለበት ድግስ ይዘጋጃል። እንዲህ ያሉት ሥነ ሥርዓቶች ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ስለሆኑ አንድ ክርስቲያን እንዲህ ባሉ አምላክን የሚያሳዝኑ ልማዶች ፈጽሞ መካፈል አይኖርበትም።
5. የሴቶች ግርዛት የሚያስከትላቸው የጤና እክሎች ምንድን ናቸው?
5 ስለ ሴቶች ግርዛትስ ምን ማለት ይቻላል? ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው ልማድ የሴቶችን የፆታ አካል መቁረጥ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በብዙ የአፍሪካ አገሮች የተለመደ ነው። የሴቶች ግርዛት በተለያየ መንገድ ይፈጸማል፤ በየትኛውም መንገድ ቢፈጸም ይህ ድርጊት ሴቶች ልጆች ሳያስፈልግ ለከፍተኛ ሥቃይ እንዲዳረጉ ያደርጋል። አንድ ጋዜጣ እንዲህ በማለት ዘግቧል፦ “የሴቶች ግርዛት እንደተከናወነ ሊከሰቱ ከሚችሉት የጤና እክሎች መካከል በጣም ከባድ ሥቃይ፣ ራስን መሳት፣ ከባድ የደም መፍሰስ፣ በአካባቢው ያሉ የአካል ክፍሎች ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ የቁስል ማመርቀዝ አልፎ ተርፎም ሞት ይገኙበታል።” ክርስቲያን ወላጆች፣ ሴት ልጆቻቸው እንዲህ ዓይነት ሥቃይ እንዲደርስባቸው እንደማይፈልጉ እሙን ነው! ይህ ልማድ ከአረማዊ አምልኮ ጋር የሚያያዝ መሆኑም ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
6. ከሴቶች ግርዛት ጋር በተያያዘ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊታሰብባቸው ይገባል?
6 ይሖዋ ሴቶችን የፈጠረው ከባሎቻቸው ጋር በፆታ ግንኙነት መደሰት እንዲችሉ አድርጎ ነው፤ የሴቶች ግርዛት ግን በፆታ ስሜታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። የሴቶች ግርዛት የሚፈጸመው ልጅቷ እስክታገባ ድረስ ድንግልናዋን ጠብቃ እንድትቆይ ለማድረግ እንደሆነ ይነገራል። ሆኖም ይህን ማድረግ የሚቻለው አካሏን በመቁረጥ ሳይሆን ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ እንድታደርግ በመርዳት ነው። የጥቅምት 1993 ንቁ! መጽሔት እንዲህ ይላል፦ “መጥፎ ድርጊቶች ሊወገዱ የሚችሉት የአካል ክፍልን በመቁረጥ ሳይሆን ትምህርት በመስጠት ነው። በምሳሌ ለማስረዳት፦ ሕጻናት ወደፊት ሌቦች እንዳይሆኑ ለማድረግ እጃቸውን መቁረጥ ይኖርብናልን? ወይም መጥፎ ነገሮች ፈጽሞ እንዳይናገሩ ምላሳቸውን መቁረጥ ይገባናልን?” የሴቶች ልጆችን የፆታ አካል መቁረጥ አደገኛ ከመሆኑም ሌላ በድርጊቱ የሚካፈሉት ሰዎች በደም ዕዳ ተጠያቂ እንዲሆኑ ሊያደርግ ይችላል። (1 ዜና 11:17-19፤ መዝ. 51:14) እንዲህ ያለው ጭካኔ የተሞላበት ልማድ እንዲፈጸም የሚፈቅድ ማንኛውም ሰው “የሕይወት ምንጭ” እና ‘የመልካም ስጦታ ሁሉ’ ሰጪ ለሆነው ለይሖዋ አክብሮት እንደሌለው ያሳያል። ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት እንዲህ ዓይነቱን ልማድ ባገደባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ክርስቲያን ወላጆች ሕጉን ማክበር ይኖርባቸዋል። (መዝ. 36:9፤ ያዕ. 1:17፤ ሮም 13:1) ሴት ልጆቻቸው እንዲገረዙ የሚፈቅዱ ክርስቲያን ወላጆች በጉባኤ ውስጥ ልዩ የአገልግሎት መብቶችን ለማግኘት ብቁ አይሆኑም። እንዲህ ዓይነቱ ልማድ እንዲፈጸምባት የምትፈቅድ ነጠላ እህትም ብትሆን መብቶችን ለማግኘት ብቁ አትሆንም።
ክታብ
7. ሰዎች ክታብ የሚያደርጉት ለምንድን ነው?
7 በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰዎች ራሳቸውን ከክፉ ነገር ለመጠበቅ ሲሉ ክታብ ያደርጉ ነበር። አንዳንድ ክታቦች የሚሠሩት ከእንስሳት ጸጉር፣ አጥንት፣ ጥርስ ወይም ጥፍር ነው። ሌሎቹ ደግሞ በብረት፣ በጨርቅ፣ በዶቃ ወይም ከዕፅዋት በሚገኙ ነገሮች ይሠራሉ። በጥንቷ ግብፅ፣ ሰዎች መናፍስትን ለማባረር ዶቃዎች ወይም ሌሎች ክታቦችን ያደርጉ ነበር።
8. ክታብ ማሰር ያሉትን አደጋዎች እንድናገናዝብ የሚረዱን ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
8 አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያሉ ዕቃዎች ካሉት ራሱን እንደሚከተለው ብሎ መጠየቁ የተገባ ነው፦ ‘ክታቡን ያስቀመጥኩት ለምንድን ነው? ከሕመም፣ ከአደጋ፣ ከቡዳ ወይም ከክፉ መናፍስት እንደሚጠብቀኝ አምናለሁ? ክታብ ማሰሬ በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? አንዳንድ ዘመዶቼ፣ ልጆቼ ክታብ አስረው ማየታቸው በሌሎች አረማዊ ልማዶችም እንድካፈል እንዲገፋፉኝ መንገድ ይከፍት ይሆን?’ አንድ ሰው፣ ክታብ ማሰሩ ጥበቃ አያስገኝለትም። እንዲያውም ለአጋንንት ጥቃት ሊያጋልጠው ወይም በመናፍስታዊ ድርጊቶች ይበልጥ እንድንጠላለፍ ሊያደርገው ይችላል። ክታብን እንደ ተራ ጌጥ ልንመለከተው አይገባም። ከመናፍስታዊ ሥራዎች ጋር የተያያዘ ሲሆን ይህ ልማድ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ያበላሽብናል።—ዘዳ. 18:10-12፤ ገላ. 5:19-21፤ ራእይ 21:8
ጥሎሽና የጋብቻ ሥነ ሥርዓት
9. (ሀ) ክርስቲያን ወላጆች ጥሎሽን በተመለከተ የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል? (ለ) ሴት ልጁን የሚድር አንድ ወንድም፣ አማኝ ያልሆኑ ዘመዶቹ ከጥሎሽም ሆነ ከሠርጉ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ጣልቃ እንዲገቡ መፍቀድ የሌለበት ለምንድን ነው?
9 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሙሽሪት ወላጆች ስጦታ ስለመስጠት የሚናገር ዘገባ እናገኛለን። የአብርሃም አገልጋይ፣ ርብቃን ለይስሐቅ ሚስት አድርገው እንዲሰጡት ቤተሰቦቿን በጠየቀበት ወቅት “የወርቅና የብር ጌጣጌጥ፣ እንዲሁም ልብሶች” ሰጥቷቸዋል። (ዘፍ. 24:53) ይህን ስጦታ የሰጠው ለርብቃ፣ ለእናቷና ለወንድሟ በሌላ አባባል ለቅርብ የቤተሰቧ አባላት ነበር። ሌሎች ዘመዶች ጥሎሽ እንደተሰጣቸው የሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አናገኝም። ታዲያ ክርስቲያን ወላጆች፣ አማኝ ያልሆኑ ዘመዶች ጥሎሽን በተመለከተ እንዲደራደሩ መፍቀድ አለባቸው? አማኝ ያልሆኑ ዘመዶች በጣም ከፍተኛ ጥሎሽ የጠየቁባቸው ወይም ልጅቷን ከፍተኛ ጥሎሽ ላመጣው ሰው “ለመሸጥ” የሞከሩባቸው ሁኔታዎች አሉ። ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ግን እንዲህ ካለው ፍቅረ ነዋይ የሚንጸባረቅበት አመለካከት ይርቃሉ፤ ልጃቸው እንድታገባ የሚፈልጉት ይሖዋን የሚወድና በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች በቅንዓት የሚካፈል እንዲሁም እውነትን በአኗኗሩ የሚያንጸባርቅ ሰው ነው።
10. የአንድ ክርስቲያን የጋብቻ ሥነ ሥርዓትን ሊያጎድፉ የሚችሉ አንዳንድ ልማዶችን ጥቀስ።
10 የክርስቲያኖች ሠርግ፣ የጋብቻ መሥራች ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ውዳሴና ክብር የሚያመጣ መሆን አለበት። ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት መክሯል፦ “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ።” (1 ቆሮ. 10:31) ክርስቲያን ቤተሰቦች የሚያዘጋጁት የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በይሖዋም ሆነ በጉባኤው ላይ ነቀፋ እንዲያመጣ አይፈልጉም። የክርስቲያኖች ሠርግ ለፈንጠዝያና ለስካር ሰበብ መሆን የለበትም። በአፍሪካ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች፣ በሠርግ ላይ ሰዎች የመራባት አምልኮን የሚያወድሱ ዘፈኖችን እየዘፈኑ የሚጨፍሩ ከመሆኑም ሌላ እንደ ሩዝ መበተን ያሉ ሌሎች አረማዊ ልማዶችን ሲያከናውኑ ማየት የተለመደ ነው። እንደነዚህ ያሉት ልማዶች በክርስቲያኖች ሠርግ ላይ ሊታዩ አይገባም።
11. የጋብቻው ሥነ ሥርዓት የሚካሄደው በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከሆነ ምን ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል?
11 የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ የሚፈጸመው በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከሆነ ልዩ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ሽማግሌዎች፣ ከሠርጉ ጋር የተያያዙት ዝግጅቶች ከክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይጋጩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። መግ 4-105 ገጽ 12 አንቀጽ 17, 18 [ሚያዝያ 15, 1984 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 15 አንቀጽ 17, 18] የሚከተለውን ምክር ይሰጣል፦ “[በመንግሥት አዳራሹ] ውስጥ ማጫወት የሚቻለው በይሖዋ ምሥክሮች የመዝሙር መጽሐፍ ላይ እንደሚገኘው ያለ መንፈስን የሚያድስ ሙዚቃ ብቻ ነው። አበባ ወይም ሌላ ጌጥ ካለ መጠነኛና ልከኛ መሆን አለበት፤ ሠርገኞቹ ወደ አዳራሹ የሚገቡበትና ፎቶግራፍ የሚነሱበት ሁኔታም እንደዚሁ ሥርዓታማ መሆን አለበት።—ፊልጵስዩስ 4:5” አጃቢ እንዲሆኑ ስለሚመረጡት ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ይኸው መጽሔት አክሎ እንዲህ ይላል፦ “[የአጃቢዎቹን] ቁጥር፣ አለባበሳቸውንና የሚያደርጓቸውን ነገሮች በተመለከተም ምክንያታዊ መሆን ያስፈልጋል። የተወገዱ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ አስነዋሪ አኗኗር ያላቸውን ሰዎች ወደ ሠርጉ መጋበዝም ተገቢ አይደለም። (2 ቆሮንቶስ 6:14-16) ብዙ ክርስቲያን ሙሽሮች (እንዲሁም ተናጋሪዎች) ታዋቂ የሆኑ ወይም ውድ ስጦታ መስጠት የሚችሉ ሰዎች ከሚጠሩ ይልቅ አብረዋቸው ይሖዋን የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች በሠርጉ ላይ ቢኖሩ ይመርጣሉ።”
12. ክርስቲያኖች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በሚያዘጋጁበት ወቅት ምክንያታዊና ሚዛናዊ መሆን ያለባቸው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
12 ተጋቢዎቹ ከሠርጉ ጋር በተያያዘ ብዙ ውሳኔዎችን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ከእነዚህም መካከል የሚለብሱት ልብስ ዓይነትና ቀለም፣ የጋብቻ ቀለበት እንዲሁም የተጋባዦች ቁጥር ይገኙበታል። ተጋቢዎቹ እንደነዚህ ያሉ ውሳኔዎችን ሲያደርጉ ምክንያታዊና ሚዛናዊ መሆን እንዳለባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ አጃቢዎች የመኪናዎቻቸውን ጥሩንባ እያስጮኹ ሙሽሮቹን አጅበው መሄዳቸው በዓለም የተለመደ ነው። አንድ ክርስቲያን ስለዚህ ጉዳይ ምን አመለካከት ሊኖረው ይገባል? የሚያዝያ 15, 1997 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ሠርግ ላይ የተገኘ ቢሆንም እንኳን ዛሬ ቢኖር ኖሮ የአካባቢውን ልማድ በመከተል ሙሽሮችን አጅበው ከፍተኛ ድምፅ እያሰሙ ከተማ በመኪና ከሚዞሩና በሚያሰሙት የጥሩንባ ድምፅ የተነሳ ትራፊክ ከሚቀጣቸው ሹፌሮች ጋር አብሮ ይጓዝ ነበር ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው። (ማቴዎስ 22:21ን ተመልከት።) በአጠቃላይ ክርስቲያኖች አሕዛብ የሚያሳዩትን የይታይልኝ መንፈስና አድራጎታቸውን ከመቅዳት ይልቅ በትሑታን ዘንድ ያለውን ጥበብ ያንጸባርቃሉ።”
አስከሬን መጠበቅና የቀብር ሥነ ሥርዓት
13. (ሀ) የምንወደው ሰው ሲሞት ማዘን አልፎ ተርፎም ማልቀስ ስህተት ነው? (ለ) የትንሣኤ ተስፋ ያለው ሰው ሊከተላቸው የማይገቡ ከሐዘን ጋር የተያያዙ ባሕሎች የትኞቹ ናቸው?
13 ሁላችንም የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ በከፍተኛ የሐዘን ስሜት እንዋጣለን። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ አንድ ክርስቲያን ሊያለቅስ ይችላል፤ ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ እንኳ በወዳጁ በአልዓዛር ሞት ምክንያት የሚያለቅሱትን ሰዎች ሲያይ ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐ. 11:35) ክርስቲያኖች ሐዘን ላይ በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በስፋት የሚታየውን ባሕላዊ የሐዘን ሥርዓት አይከተሉም። ከእነዚህ ባሕሎች መካከል ፀጉርን መንጨት ወይም እስከ ጭራሹ መላጨት፣ የለበሱትን ልብስ አለመቀየርና ያደፈ ልብስ መልበስ እንዲሁም እየተነሱ መሬት ላይ መፍረጥ፣ ደረት መድቃትና ሙሾ ማውረድ ይገኙበታል። እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እንዲህ ዓይነቶቹን ከመጠን ያለፉና ለታይታ የሚደረጉ የሐዘን ልማዶች ከመከተል መራቃችን የምንወዳቸው ሰዎች ከሞት የሚነሱበትን ጊዜ በእርግጠኝነት በእርግጠኝነት እንደምንጠባበቅ ያሳያል።—ኢዮብ 14:14, 15፤ ዮሐ. 5:28, 29፤ ሥራ 24:15
14. አስከሬንን የመጠበቅ ልማድ በሐዘን በተጎዳው ቤተሰብ ላይ ምን ተጽዕኖ ይሳድራል?
14 በብዙ ቦታዎች ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ በፊት አስከሬኑን ቁጭ ብሎ መጠበቅ የተለመደ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች በርከት ያሉ ሰዎች ሌሊቱን ሙሉ እየዘፈኑ፣ እያለቀሱ ወይም የአልኮል መጠጥ እየጠጡ ቁጭ ብለው ያድራሉ። እንዲህ ያሉት ልማዶች ከፍተኛ ወጪ ያስወጣሉ። ብዙውን ጊዜ ምግብ መግዛት፣ ከብት ማረድ እንዲሁም ድንኳንና መጓጓዣ መከራየት ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነቶቹ ዝግጅቶች በሐዘን የተጎዳውን ቤተሰብ ዕዳ ውስጥ የሚከቱ ከመሆኑም በላይ ክርስቲያናዊ ባልሆኑ ልማዶች እንዲካፈሉ ያደርጓቸዋል። እነዚህ ምንም እርባና የሌላቸው ነገሮች ናቸው። እንደነዚህ ያሉትን ሥር የሰደዱ ባሕሎች ከመከተል መቆጠብ ከሰዎች ስደት ሊያስከትል ቢችልም ከአምላክ ዘንድ ወሮታ ያስገኛል።—2 ጢሞ. 1:7
15, 16. አስከሬኑ የሚቀበርበትን ቦታ ለመወሰን የሚረዱን ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?
15 ስለ ቀብር ቦታስ ምን ማለት ይቻላል? አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመልከት። አብርሃም፣ ለቤተሰቡ መቀበሪያ ቦታ የሚሆን መሬት የገዛው በራሱ ወጪ ነበር። (ዘፍ. 23:3-20፤ 25:9፤ 49:29-32) ዮሴፍ የአባቱን አስከሬን ወደ ከነዓን ምድር ወስዶ በመቅበር የአባቱን ፍላጎት አክብሯል። ዮሴፍ ይህን ማድረግ እንዲችል ፈርዖን ከመንግሥት መዝገብ ቤት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ሳይሰጠው አልቀረም።—ዘፍ. 47:29, 30፤ 50:6-13
16 በዘመናችን የቀብር ሥነ ሥርዓቱን የማዘጋጀትም ሆነ የአገሩን ሕግ ግምት ውስጥ በማስገባት የቀብሩን ቦታ መወሰን በዋነኝነት የሟቹ የቅርብ የቤተሰብ አባላት ኃላፊነት ነው። አንዳንዶች አስከሬኑን፣ አያት ቅድመ አያቶቹ ወደተቀበሩበት ቦታ ወስዶ የመቅበር ልማድ አላቸው። እያንዳንዱ ቤተሰብ ወጪውን በማስላት በዚህ ረገድ የግሉን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። (ሉቃስ 14:28) አንዳንዶች በአካባቢያቸው ሕጋዊ የሆነ የመቃብር ቦታ ቢኖርም አስከሬኑን ወደ አንድ ቦታ (ብዙውን ጊዜ ዘመዶቹ ወደተቀበሩበት ቦታ) ለማጓጓዝ ሲሉ ብዙ ችግር ውስጥ የሚገቡ ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ ወጪ ያወጣሉ፤ ይህ ጥበብ የጎደለው እርምጃ ነው። እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? የግለሰቡ አስከሬን፣ አያት ቅድመ አያቶቹ የተቀበሩበት መሬት ላይ ማረፉ ከእነሱ መንፈስ ጋር ለመገናኘት እንደሚያስችለው ስለሚታመን ነው። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እንዲህ ባሉት እምነቶች የተመሠረቱ ውሳኔዎችን አናደርግም።—መክ. 9:5, 10
17. ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከሚጋጨው ከየትኛው የሐዘን ልማድ መራቅ ይኖርባቸዋል?
17 በአንዳንድ ባሕሎች የሟቹ ሚስት በሐዘኑ ወቅት ለባልየው ወንድ ዘመዶች “እንድትተላለፍ” የማድረግ ልማድ አለ፤ አንዲት ባሏ የሞተባት ክርስቲያን እንዲህ ዓይነቱን ልማድ አጥብቃ ልትቃወመው ይገባል። ይህ ልማድ፣ ላቅ ካሉት የይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር በግልጽ የሚጋጭ ከመሆኑም ሌላ የሚስትየዋን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው። አንዲት ክርስቲያን ሚስት እንዲህ ያለውን ልማድ ለመፈጸም በጭራሽ አትስማማም።
18. (ሀ) አንድ ክርስቲያን የቀብር ንግግር እንዲያቀርብ ቢጠየቅ ምን ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል? (ለ) ሌሎች ክርስቲያኖች በሐዘን ለተጎዳው ቤተሰብ አሳቢነት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
18 ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የቀብር ንግግር እንዲቀርብ ዝግጅት ያደርጋሉ። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ንግግር እንዲያቀርብ በሚጠየቅበት ጊዜ ለዚህ ወቅት የተዘጋጀውን የንግግር አስተዋጽኦ መከተል ይኖርበታል፤ ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ልማዶችን የሚከተሉ ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ መሠረተ ትምህርቶች የሚያስተምሩ ሌሎች ተናጋሪዎች በሚያካሂዱት ፕሮግራም ውስጥ አይካፈልም። የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ቀላል፣ ክብር ያለውና ሐዘንተኞቹን የሚያጽናና መሆን አለበት። አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ወቅት የሚቀርበው የቀብር ንግግር ሐዘንተኞቹንም ሆነ በቦታው የተገኙ ወዳጆቻቸውን በመንፈሳዊ ለማበረታታት ያስችላል። ሐዘንተኞቹን አልፎ አልፎ እየሄዱ ማጽናናት ፍቅር የሚንጸባረቅበት ድርጊት ቢሆንም በርካታ ወንድሞችና እህቶች አንድ ላይ ተሰባስበው መዝሙር የሚዘምሩባቸው ዝግጅቶችን በማድረግ ሐዘንተኞቹ ቤት ረዘም ያለ ጊዜ ማሳለፍ አስፈላጊ አይደለም። ከሐዘን ጋር የተያያዙ ዝግጅቶች ቀለል ያሉ እንዲሆኑ በማድረግ አላስፈላጊ ወጪን ማስቀረት ይቻላል፤ ብዙውን ጊዜ ደግሞ ወንድሞች በዚያ ወቅት የሚያደርጉት እርዳታ ከሐዘኑ ጋር የተያያዘውን አነስተኛ ወጪ ለመሸፈን በቂ ይሆናል። ጉባኤዎች ቋሚ የሆነ ‘የቀብር ወጪ መሸፈኛ’ ማዘጋጀት አያስፈልጋቸውም።
ከአምላክ ፍቅር አትውጡ
19. (ሀ) በብዙዎች ዘንድ የተለመዱ ባሕሎችንና ልማዶችን በተመለከተ ትክክለኛ አቋም ለመያዝ ምን ሊረዳን ይችላል? (ለ) አምላክን ከማያውቀው ዓለም ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ ያደረግኸው ለምንድን ነው?
19 ይሖዋን የምናመልከው እሱን በማያውቅ ዓለም ውስጥ እንደመሆኑ መጠን አንዳንድ ችግሮች መፈጠራቸው የማይቀር ነው። ይሁንና እያንዳንዱን ሁኔታ የሚመለከት ሕግ ማውጣት አይቻልም። በመሆኑም ውሳኔዎች ለማድረግና አንዳንድ ሁኔታዎችን ለመወጣት የሚያስችለን ጥበብና ማስተዋል እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ መጸለያችን አስፈላጊ ነው። (ያዕ. 1:5) የጉባኤ ሽማግሌዎች ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንድንችል እኛን ለማበርታት ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊያሳዩን ፈቃደኞች ናቸው። አኗኗራችን ይሖዋን የሚያስከብር እንዲሆን በማድረግ ‘ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ የዘላለም ሕይወትን እየተጠባበቅን መኖር’ እንችላለን።—ይሁዳ 21፤ 2 ጴጥ. 3:13