አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ክብር ይገልጣሉ
ብዙ ሰዎች ተፈጥሮን ያደንቃሉ። ሆኖም ተፈጥሮ የታላቁ ፈጣሪ አስተሳሰብና ስሜት ነጸብራቅ እንደሆነ የሚረዱት በጣም ጥቂት ናቸው። (ሮም 1:20) ከረጅም ዘመናት በፊት የኖረው ዳዊት፣ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈውን ቃሉን በማንበብ ስለ ይሖዋ ማወቅ ችሎ ነበር። በተጨማሪም ዳዊት የፍጥረት ሥራዎችን ‘መመልከቱም’ ወደ አምላክ እንዲቀርብ ረድቶታል። (መዝ. 8:3, 4) በተመሳሳይም ዎንደርስ ኦቭ ክርኤሽን ሪቪል ጎድስ ግሎሪ (አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ክብር ይገልጣሉ) የተባለውን ቪዲዮ መመልከታችን እኛም ሆነ ልጆቻችን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ከይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች አንዳንዶቹን ጠለቅ ብለን እንድንመረምር ብሎም ታላቁ ፈጣሪያችን ያሉትን ባሕርያት እንድናስተውል ይረዳናል፤ ይህ ደግሞ ወደ እሱ ይበልጥ እንድንቀርብ ያስችለናል። ፊልሙን ከተመለከታችሁ በኋላ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሞክሩ።
(1) ግዑዙ አጽናፈ ዓለም ያለውን ስፋት እንዲሁም የተደራጀበት መንገድ ለይሖዋ ያለህ አድናቆት እንዲጨምር የሚያደርገው እንዴት ነው? (ኢሳ. 40:26) (2) ስለ ውኃ ጠለቅ ብለን ስንመረምር አምላክን በተመለከተ ምን እንማራለን? (ራእይ 14:7) (3) የምድራችን ስፋት እና ከፀሐይ ያላት ርቀት የይሖዋን ጥበብ የሚያሳየው እንዴት ነው? (4) ጨረቃ ምን ጥቅም አላት? (መዝ. 89:37) (5) ይሖዋ፣ የሰው ልጆችን በሕይወት እንዲደሰቱ አድርጎ የፈጠራቸው እንዴት ነው? (6) ዲ ኤን ኤ ምንድን ነው? (መዝ. 139:16) (7) በምድር ላይ ካሉት የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ሁሉ የሰው ልጆች የሚለዩት እንዴት ነው? (ዘፍ. 1:26) (8) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለማግኘት የምትጓጓው ነገር ምንድን ነው?
ተጨማሪ ክፍሎች፦ (9) አንድ ነገር ቀለም እንዲኖረው የሚያደርገው ምንድን ነው? (10) ውኃ የስበትን ኃይል ተቋቁሞ ወደ ዛፎች ጫፍ መድረስ የሚችለው እንዴት ነው? (11) ውኃ በሰውነታችን ውስጥ ምን ተግባር ያከናውናል? (12) ሕይወት ያላቸው ነገሮች እርስ በርስ እንደሚረዳዱ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ። (13) አንዳንድ ፍጥረታት ከሌሎች ፍጥረታት ጋር ዝምድና እንዲፈጥሩ የሚያደርጋቸው ነገር ምንድን ነው? (14) “ወርቃማ ማዕዘን” (ጎልደን አንግል) የሚባለው ነገር ምንድን ነው? ይህ ነገር በአንዳንድ ፍጥረታት ላይ የሚታየውስ እንዴት ነው?
የይሖዋን የእጅ ሥራዎች “ልብ ብላችሁ ተመልከቱ”፦ ኢየሱስ ‘የሰማይ ወፎችን’ እና ‘የሜዳ አበቦችን’ ልብ ብለን እንድንመለከት አበረታቶናል። (ማቴ. 6:26, 28) እንዲህ ማድረጋችን በይሖዋ ላይ ያለን እምነት እንዲጠናከር፣ በፈጣሪ እንድንተማመን እንዲሁም ለጥበቡ፣ ለማዳን ኃይሉና ለፍቅሩ ያለን አድናቆት ከፍ እንዲል ይረዳናል። በመሆኑም ሰዎች ለሚሠሯቸው ነገሮች የበለጠ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ አስደናቂ የሆኑትን የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች ለመመልከትና እነዚህ ፍጥረታት ስለ ታላቁ አምላካችን ስለሚናገሩት ነገር በጥሞና ለማሰብ ጊዜ መመደብ ይኖርብናል።—መዝ. 19:1