ጥናት ለማግኘት የሚያስችሉ አምስት መንገዶች
1. በክልላችን ውስጥ ጥናት ማግኘት ተፈታታኝ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?
1 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማግኘት ተፈታታኝ ሆኖብህ ያውቃል? ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ይሖዋ የእሱን ፈቃድ ለማድረግ ተስፋ የማይቆርጡ ሰዎችን ይባርካል። (ገላ. 6:9) ጥናት ለማግኘት የሚያስችሉ አምስት መንገዶች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።
2. ጥናት ለማስጀመር ቀጥተኛ አቀራረብ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
2 ቀጥተኛ አቀራረብ፦ ብዙ ሰዎች መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እንደምናበረክት ቢያውቁም መጽሐፍ ቅዱስን ከእኛ ጋር እንዲያጠኑ ሰዎችን እንደምንጋብዝ ላያውቁ ይችላሉ። ከቤት ወደ ቤት ስታገለግሉ ቀጥተኛ አቀራረብ ለመጠቀም ለምን አትሞክሩም? የምታነጋግሯቸው ሰዎች ፍላጎት ካሳዩ፣ መጽሐፍ ቅዱስን መማር ይፈልጉ እንደሆነ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። ግብዣውን ካልተቀበሉ ግን ጽሑፎች ልትተዉላቸው እንዲሁም ፍላጎታቸውን ለማነሳሳት ጥረት ማድረጋችሁን ልትቀጥሉ ትችላላችሁ። አንድ ወንድም ለአንድ ባልና ሚስት ለዓመታት ጽሑፎችን ይወስድላቸው ነበር። አንድ ቀን አዲስ የወጡትን ጽሑፎች ከሰጣቸው በኋላ ለመሄድ ሲዘጋጅ አንድ ሐሳብ ወደ አእምሮው መጣ፤ በመሆኑም ወዲያውኑ “መጽሐፍ ቅዱስን መማር ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቃቸው። ፈቃደኛ መሆናቸውን ሲገልጹ ምን ያህል እንደተገረመ መገመት ትችላላችሁ። በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ባልና ሚስት ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክር ሆነዋል።
3. በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሰዎች በሙሉ አስጠኚ እንዳላቸው ማሰብ የሌለብን ለምንድን ነው?
3 ስብሰባ የሚመጡ ሰዎች፦ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየተመራላቸው ነው ብላችሁ አታስቡ። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ከግማሽ በላይ የሆኑትን ጥናቶቼን ያገኘሁት ስብሰባ ላይ የተገኙ ሰዎችን ቀርቤ በማናገሬ ነው።” አንዲት እህት የተጠመቁ ሴቶች ልጆች ያሏትን አንዲት ዓይናፋር ሴት ለማናገር ወሰነች። ይህች ሴት ለ15 ዓመታት ገደማ ስብሰባ ላይ የተገኘች ሲሆን ልክ ስብሰባው ሊጀምር ሲል ወደ መንግሥት አዳራሹ ትመጣና ስብሰባው እንዳለቀ ትወጣ ነበር። ይህች ሴት ለማጥናት የቀረበላትን ግብዣ በመቀበሏ ውሎ አድሮ ወደ እውነት መጣች። እህት “ይህችን ሴት ጥናት እንድትጀምር የጠየቅኳት ከ15 ዓመታት በኋላ በመሆኑ በጣም አዝኛለሁ” በማለት ጽፋለች።
4. በሌሎች አማካኝነት ጥናት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
4 በሌሎች አማካኝነት፦ አንዲት እህት ሌሎች ሰዎች ጥናት እንዲጋብዟት ጥረት ታደርጋለች። ጥናት የጋበዘቻት እህት የምትፈቅድላት ከሆነ ጥናቱ ሲደመደም ተማሪዋ መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚፈልግ ሌላ ሰው ታውቅ እንደሆነ ትጠይቃታለች። ተመላልሶ መጠየቅ ለምታደርጉለት ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ስታበረክቱ “ይሄን መጽሐፍ ሊፈልግ የሚችል ሌላ ሰው ታውቃለህ?” በማለት ልትጠይቁት ትችላላችሁ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ አስፋፊዎች ወይም አቅኚዎች በክልላቸው ውስጥ ያገኙትን ሰው ለማስጠናት ሁኔታቸው አይፈቅድ ይሆናል። በመሆኑም ጥናት ለመምራት ሁኔታችሁ እንደሚፈቅድላችሁ ለሌሎች ማሳወቁ ጠቃሚ ነው።
5. አንድ የማያምን የትዳር ጓደኛ ጥናት እንዲጀምር ግብዣ ማቅረብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
5 የማያምን የትዳር ጓደኛ፦ በጉባኤያችሁ ውስጥ የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው አስፋፊዎች አሉ? አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያን ከሆነው የትዳር ጓደኛቸው ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት ፈቃደኛ ባይሆኑም የቤተሰባቸው አባል ያልሆነ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ያቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል። ያም ቢሆን የማያምነውን የትዳር ጓደኛ እንዴት አድርጋችሁ ብትቀርቡት የተሻለ እንደሆነ ለማወቅ አማኝ የሆነውን የትዳር ጓደኛ አስቀድማችሁ ማማከራችሁ የተሻለ ነው።
6. ጥናት ለማግኘት መጸለያችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
6 ጸሎት፦ ጸሎት ያለውን ኃይል አቅልላችሁ አትመልከቱ። (ያዕ. 5:16) ይሖዋ ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ የቀረቡ ጸሎቶችን እንደሚሰማ ቃል ገብቷል። (1 ዮሐ. 5:14) የተጣበበ ጊዜ ያለው አንድ ወንድም ጥናት ለማግኘት ጸሎት አቀረበ። በዚህ ጊዜ ባለቤቱ፣ ጥናት ለመምራት ጊዜ ማግኘት እንደሚከብደው በተለይ ደግሞ ጥናቱ ብዙ ችግሮች ካሉበት ተፈታታኝ ሊሆንበት እንደሚችል ተሰማት። በመሆኑም ባለቤቷ ጥናት እንዲያገኝ ለይሖዋ ስትጸልይ እነዚህን ጉዳዮች በጸሎቷ ውስጥ አካተተች። ከሁለት ሳምንት በኋላ በጉባኤያቸው ያለች አንዲት አቅኚ እህት ያገኘችውን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የሚፈልግ ሰው ለዚህ ወንድም በሰጠችው ጊዜ ጸሎታቸው መልስ አገኘ። የወንድም ሚስት እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ጥናት መምራት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ የሚሰማቸው ሁሉ፣ ስላሉበት ሁኔታ ለይተው በመጥቀስ እንዲጸልዩና መጸለያቸውን እንዳያቋርጡ አበረታታለሁ። ካሰብኩት በላይ ደስታ አግኝተናል።” ተግታችሁ ከጸለያችሁ እናንተም ብትሆኑ ጥናት ልታገኙ እንዲሁም ጥናቶቻችሁን “ወደ ሕይወት [በሚያስገባው] በር” እንዲገቡ በመርዳት ደስታ ልታጭዱ ትችላላችሁ።—ማቴ. 7:13, 14