የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
ክፍል 7፦ በጥናቱ ወቅት መጸለይ
1. (ሀ) ጥናቱን በጸሎት መክፈትና መደምደም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ወቅት ስለ ጸሎት እንዴት ልንነግራቸው እንችላለን?
1 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የይሖዋ እርዳታ የግድ አስፈላጊ ነው። (1 ቆሮ. 3:6) ስለዚህ ጥናቱን ከመክፈታችንና ከመደምደማችን በፊት መጸለያችን ተገቢ ነው። የምናስጠናው ሰው ስለ ጸሎት የሚያውቅ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ጥናቱን በጸሎት መክፈትና መደምደም እንችላለን። ለሌሎች ጥናቶቻችን ግን ስለ ጸሎት መቼ ብናወያያቸው የተሻለ እንደሚሆን ማስተዋል ያስፈልገን ይሆናል። ጸሎት የምናቀርብበትን ምክንያት ለማስረዳት መዝሙር 25:4, 5 እና 1 ዮሐንስ 5:14ን እንዲሁም ወደ ይሖዋ ስንጸልይ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መቅረባችን አስፈላጊ መሆኑን ለመግለጽ ዮሐንስ 15:16ን መጠቀም እንችላለን።
2. አንዲት እህት ከአንድ የተጠመቀ ወንድም ወይም ካልተጠመቀ የመንግሥቱ አስፋፊ ጋር ጥናት በምታስጠናበት ወቅት ጸሎት ማቅረብ ያለበት ማነው?
2 በጥናቱ ወቅት ጸሎት ማቅረብ ያለበት ማነው? አንዲት እህት ጥናት በምትመራበት ወቅት አንድ የተጠመቀ ወንድም የሚገኝ ከሆነ ጸሎቱን የሚያቀርበው እሱ ሲሆን እህት ራሷን ሸፍና ጥናቱን መምራት ትችላለች። (1 ቆሮ. 11:5, 10) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ያልተጠመቀ የመንግሥቱ አስፋፊ አብሯት ጥናቱ ላይ ከተገኘ እሷ መጸለይዋ ተገቢ ነው። በዚህ ወቅት እህት ጥናቱን ስትመራም ሆነ ስትጸልይ ራሷን መሸፈን አለባት።
3. በጥናታችን ወቅት በምናቀርበው ጸሎት ውስጥ የትኞቹን ነገሮች ማካተት ተገቢ ነው?
3 በጸሎቱ ውስጥ መካተት ያለባቸው ነገሮች:- በጥናቱ ወቅት የሚቀርበው ጸሎት አስፈላጊ የሆኑትን ነጥቦች ለይቶ ሊጠቅስ ይገባል እንጂ ከልክ በላይ ሊረዝም አይገባም። በጥናቱ ወቅት የአምላክን እርዳታ ከመጠየቅና ለሰጠን እውነት ከማመስገን በተጨማሪ ይሖዋ የትምህርቱ ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ሊወደስ ይገባዋል። (ኢሳ. 54:13) ከዚህም በላይ ለተማሪው ያለንን ልባዊ አሳቢነት እንዲሁም ይሖዋ እየተጠቀመበት ላለው ድርጅት አመስጋኝነታችንን በጸሎት መግለጽ እንችላለን። (1 ተሰ. 1:2, 3፤ 2: 7, 8) ጥናታችን እየተማረ ያለውን ነገር በሥራ ላይ ለማዋል የሚያደርገውን ጥረት ይሖዋ እንዲባርከው መጸለያችን ተማሪው ‘ቃሉ የሚናገረውን የማድረግን’ አስፈላጊነት እንዲገነዘብ ያደርገዋል።—ያዕ. 1:22
4. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን በጸሎት መክፈትና መዝጋታችን ምን ጥቅሞችን ያስገኛል?
4 በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት የሚደረገው ጸሎት ብዙ ጥቅሞች አሉት። የአምላክን በረከት ያስገኛል። (ሉቃስ 11:13) የአምላክን ቃል ማጥናት ምን ያህል ክብደት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ያጎላል። በምንጸልይበት ጊዜ ተማሪያችን እንዴት ብሎ መጸለይ እንዳለበትም ይማራል። (ሉቃስ 6:40) ከዚህም በላይ ለአምላክ ባለን ፍቅርና ወደር ለሌላቸው ባሕርያቱ ባለን አድናቆት ተገፋፍተን ከልብ በመነጨ ስሜት የምናቀርበው ጸሎት ጥናታችን ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና እንዲመሠርት ይረዳዋል።