የጥያቄ ሣጥን
◼ በር ላይ እንደቆምን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ መጸለይ ይኖርብናል?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ ጥናቱን በጸሎት መክፈትና መደምደም የሚያስገኛቸው በርካታ ጥቅሞች አሉ። ለምናደርገው ውይይት ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ይሖዋን በጸሎት አማካኝነት ልንጠይቀው እንችላለን። (ሉቃስ 11:13) ጸሎት ማቅረባችን ጥናታችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን በቁም ነገር እንዲመለከተው የሚገፋፋው ከመሆኑም ሌላ እንዴት መጸለይ እንዳለበትም ያስተምረዋል። (ሉቃስ 6:40) በመሆኑም አዲስ ጥናት ስናገኝ ጥናቱን በጸሎት ለመጀመር ቶሎ ሐሳብ ማቅረባችን የተሻለ ነው። ሆኖም ሁኔታዎች ሊለያዩ ስለሚችሉ በር ላይ ጥናት የሚመሩ አስፋፊዎች ጸሎት ማቅረብ አለማቅረብን በተመለከተ ማስተዋል የታከለበት ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባው አንዱ ቁልፍ ነገር ጥናቱ የሚደረግበት ቦታ ነው። ጥናታችንን በቋሚነት የምናስጠናበት ቦታ የሰዎችን ትኩረት የማይስብ ከሆነ በጥናቱ መጀመሪያና መደምደሚያ ላይ አጭር ጸሎት ማቅረብ ይቻል ይሆናል። ይሁንና ጸሎት ማቅረብ የአላፊ አግዳሚውን ትኩረት የሚስብ አሊያም ጥናቱ እንዲያፍር የሚያደርገው ከሆነ ጥናቱን ከዚያ በተሻለ ቦታ መምራት የሚቻልበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ መቆየቱ ጥሩ ነው። ጥናቱ የሚከናወንበት ቦታ የትም ይሁን የት ጥናቱን በጸሎት መጀመር ያለብን መቼ እንደሆነ ለመወሰን የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀም ይገባናል።—የመጋቢት 2005 የመንግሥት አገልግሎታችንን ገጽ 4 ተመልከት።